በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሐዋርያው ጳውሎስ ሴቶች “በጉባኤ ዝም ይበሉ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው፣ ሴቶች በጉባኤ ዝም ይበሉ፤ ሕግም እንደሚለው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም።” (1 ቆሮንቶስ 14:33, 34) ይህ ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ለመረዳት አንድንችል ጳውሎስ ምክሩን በሰጠበት ጊዜ የነበሩትን አንዳንድ ሁኔታዎች እንመልከት።

ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14 ላይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚደረጉ ስብሰባዎች ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን ጽፏል። የስብሰባዎቹ ይዘት ምን ሊመስል እንደሚገባና እንዴት መካሄድ እንዳለባቸው ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 14:1-6, 26-34) ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚደረጉበት ዋነኛ ዓላማ ‘ቤተ ክርስቲያንን ማነጽ’ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።—1 ቆሮንቶስ 14:4, 5, 12, 26

ጳውሎስ ‘ዝም እንዲሉ’ የሰጠው መመሪያ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14 ላይ ሦስት ጊዜ ይገኛል። በሦስቱም ጊዜያት ‘ዝም እንዲሉ’ ምክር የተሰጣቸው የተለያዩ የጉባኤው አባላት ቢሆኑም ምክሩ መሰጠት ያስፈለገበት ምክንያት ግን ተመሳሳይ ነው። ይኸውም “ሁሉም በአግባብና በሥርዐት” እንዲከናወን ለማድረግ ነው።—1 ቆሮንቶስ 14:40

በመጀመሪያ ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “በልሳን የሚናገር ቢኖር፣ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ ሌላው ደግሞ ይተርጒም፤ የሚተረጒም ሰው ከሌለ ግን በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና፤ ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር።” (1 ቆሮንቶስ 14:27, 28) ይህ ሲባል ግን ይህ ሰው መቼም ቢሆን በጉባኤ መካከል መናገር የለበትም ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ከመናገር መቆጠብ የሚያስፈልግበት ጊዜ እንዳለ መጠቆሙ ነው። ደግሞም፣ ማንም ሰው ሊረዳው በማይችል ባዕድ ቋንቋ የሚናገር ከሆነ በስብሰባው ዋነኛ ዓላማ መሠረት እርስ በርስ መተናነጽ አይቻልም።

ቀጥሎም፣ ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሏል:- “ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ይመዝኑ። ከተቀመጡትም መካከል አንድ ሰው አንድ ነገር ቢገለጥለት፣ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል።” ይህም ቢሆን መጀመሪያ ላይ የተናገረው ነቢይ በጉባኤ ውስጥ ከመናገር መቆጠብ አለበት ማለት ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ ዝም ማለት እንደሚኖርበት የሚያሳይ ነው። ይህ ከሆነ ተአምራዊው ራእይ የተገለጠለት ሰው ያየውን ለጉባኤው ተናግሮ ‘እያንዳንዳቸው እንዲበረታቱ’ በማድረግ የስብሰባውን ዓላማ ዳር ሊያደርስ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 14:26, 29-31

በመጨረሻም፣ ጳውሎስ ክርስቲያን ሴቶችን አስመልክቶ “ሴቶች በጉባኤ ዝም ይበሉ፤ ሕግም እንደሚለው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 14:34) ጳውሎስ ይህን መመሪያ ለእህቶች መስጠት ያስፈለገው ለምን ነበር? በጉባኤ ውስጥ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ነው። “ሴቶች ለማወቅ የሚፈልጉት አንዳንድ ነገር ካለ፣ ባሎቻቸውን በቤት ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በጉባኤ መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 14:35

አንዳንድ እህቶች በጉባኤ ውስጥ የሚሠጠውን ትምህርት መቃወም ሳይጀምሩ አልቀሩም። የጳውሎስ ምክር እህቶች እንዲህ ከመሰለው የተቃዋሚነት መንፈስ እንዲርቁ ከማስቻሉም ባሻገር ይሖዋ ባዘጋጀው የራስነት ሥርዓት ውስጥ የተሰጣቸውን ቦታ እንዲያከብሩ በተለይም ደግሞ ከባሎቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ በትሕትና ቦታቸውን ጠብቀው እንዲመላለሱ ረድቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በተጨማሪም እህቶች ዝም በማለት፣ በጉባኤ ውስጥ አስተማሪ ለመሆን እንደማይመኙ ማሳየት ይችላሉ። ጳውሎስ ሴቶች በጉባኤ ውስጥ የማስተማር ኃላፊነት ሊኖራቸው እንደማይገባ በመግለጽ እንደሚከተለው ሲል ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል:- “ሴት ዝም እንድትል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም።”—1 ጢሞቴዎስ 2:12

ይህ ማለት ግን አንዲት ክርስቲያን ሴት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አንዳችም ነገር መናገር የለባትም ማለት ነው? በጭራሽ። በጳውሎስ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያን ሴቶች በጉባኤ መካከል ይጸልዩ አሊያም ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ይህንንም ያደረጉት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ተገፋፍተው ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ይህን ሲያደርጉም ቢሆን ቦታቸውን እንደሚያውቁ ለማሳየት ራሳቸውን ይሸፍናሉ። a (1 ቆሮንቶስ 11:5) ከዚህም በላይ በጳውሎስ ዘመንም ይሁን በዛሬው ጊዜ ያሉ እህቶች ከወንድሞች ጎን ተሰልፈው ስለ ተስፋቸው ለሌሎች እንዲናገሩ ተበረታተዋል። (ዕብራውያን 10:23-25) እህቶች በመስክ አገልግሎት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የታሰበበት ሐሳብ በመስጠት፣ ሠርቶ ማሳያዎችን አሊያም የተማሪ ክፍሎችን በማቅረብ ተስፋቸውን በመናገር ሌሎችን ያበረታታሉ።

በመሆኑም ክርስቲያን ሴቶች በጉባኤ ውስጥ የወንዶችን ቦታ ለመያዝ ከመሞከርና ጉባኤውን ከማስተማር በመቆጠብ ‘ዝም ይላሉ።’ አከራካሪ ጥያቄዎችን በማንሳት ጉባኤውን እንዲያስተምሩ ኃላፊነት የተጣለባቸውን ወንድሞች ሥልጣን ለመጋፋት አይሞክሩም። ክርስቲያን እህቶች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ተገቢ ቦታ ጠብቀው በመመላለስ ጉባኤው ሰላማዊና ሁሉም ‘የሚታነጽበት’ እንዲሆን ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ።—1 ቆሮንቶስ 14:26, 33

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዛሬው ጊዜ ያሉ በመንፈሳዊ የበሰሉ እህቶች የተጠመቁ ወንድሞች ሊያከናውኑት የሚገባውን ሥራ ለመሥራት የሚያስገድድ ሁኔታ ሲገጥማቸው ይህን ምሳሌ ይከተላሉ።—የሐምሌ 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26⁠ን ተመልከት።