በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ምሳሌያዊው ድራማ’ ለእኛ ያለው ጥቅም

‘ምሳሌያዊው ድራማ’ ለእኛ ያለው ጥቅም

‘ምሳሌያዊው ድራማ’ ለእኛ ያለው ጥቅም

አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባዎችን ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ግልጽ ባያደርጉልን ኖሮ ሙሉ ትርጉማቸውን መረዳት እንዴት ከባድ ይሆን ነበር! በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ታሪካዊ ክስተቶችን እንዳለ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ታሪኮች ለመረዳት የሚያስቸግር ጥልቅ ትርጉም አላቸው። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በአብርሃም ቤት ስለ ነበሩት ሁለት ሴቶች የሚናገረው ታሪክ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ታሪክ “ምሳሌያዊ ድራማ” በማለት ጠርቶታል።—ገላትያ 4:24 NW

ይህ ድራማ በውስጡ የያዘው እውነት የይሖዋ አምላክን በረከት ማግኘት ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው በጣም ጠቃሚ ስለሆነ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል። እንዲህ ያልንበትን ምክንያት ከመመርመራችን በፊት ጳውሎስ የዚህን ድራማ ትርጉም ለመግለጽ የተገፋፋው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

በአንደኛው መቶ ዘመን በገላትያ በሚኖሩ ክርስቲያኖች ዘንድ ችግር ተከስቶ ነበር። አንዳንዶቹ በሙሴ ሕግ መሠረት “ቀኖችን፣ ወሮችን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን” በጥንቃቄ ያከብሩ ነበር። እነዚህ ግለሰቦች፣ አማኞች የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለጉ በዓላትን ማክበር እንዳለባቸው ይናገሩ ነበር። (ገላትያ 4:10፤ 5:2, 3) ይሁን እንጂ ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በዓላትን ማክበር እንደማያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። በመሆኑም ይህን ጉዳይ ለማስረዳት ሁሉም አይሁዳውያን የሚያውቁትን አንድ ታሪክ ጠቀሰ።

ጳውሎስ የአይሁድ ብሔር አባት የሆነው አብርሃም እስማኤልንና ይስሐቅን መውለዱን በገላትያ ለሚገኙ ክርስቲያኖች አስታወሳቸው። የመጀመሪያውን ልጅ የወለደው አጋር ከተባለችው አገልጋይ ሲሆን ሁለተኛውን ደግሞ ነጻ ከሆነችው ከሣራ ነበር። የሙሴን ሕግ መጠበቅ አለብን ብለው የሚከራከሩት እነዚህ በገላትያ የሚኖሩት ክርስቲያኖች ሣራ መጀመሪያ ላይ መካን እንደነበረችና ልጅ እንዲወልድላት ስለፈለገች አብርሃም ወደ አገልጋይዋ ወደ አጋር እንዲገባ እንደፈቀደች የሚናገረውን ታሪክ ጠንቅቀው ያውቁ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲሁም አጋር እስማኤልን ባረገዘች ጊዜ እመቤቷን መናቅ እንደ ጀመረች ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ሣራ አምላክ በሰጠው ተስፋ መሠረት ከጊዜ በኋላ ወንድ ልጅ ወለደች። በመጨረሻም አብርሃም፣ እስማኤል ለይስሐቅ ጥሩ አመለካከት እንዳልነበረው ሲያውቅ አጋርንና ልጅዋን ከቤቱ አስወጣቸው።—ዘፍጥረት 16:1-4፤ 17:15-17፤ 21:1-14፤ ገላትያ 4:22, 23

ሁለቱ ሴቶችና ሁለት ቃል ኪዳኖች

ጳውሎስ የዚህን “ምሳሌያዊ ድራማ” ገጽታዎች ማብራራት ጀመረ። “እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች” እንደሚያመለክቱ ከገለጸ በኋላ አክሎ እንዲህ አለ:- “አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት . . . አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌም ትመስላለች፤ ከልጇ ጋር በባርነት ናትና።” (ገላትያ 4:24, 25) አጋር ዋና ከተማዋን ኢየሩሳሌም ያደረገችውን እስራኤልን ትወክላለች። የአይሁድ ብሔር በሲና ተራራ ላይ በተሰጠው በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት የይሖዋን ሕግ ለመታዘዝ ግዴታ ውስጥ ገብቶ ነበር። ይህ የሕግ ቃል ኪዳን እስራኤላውያን በኃጢአት ባርነት ሥር እንዳሉና ነፃ አውጪ እንደሚያስፈልጋቸው ዘወትር ያስታውሳቸው ነበር።—ኤርምያስ 31:31, 32፤ ሮሜ 7:14-24

“ነጻዪቱ ሴት” ሣራና ልጇ ይስሐቅስ የሚወክሉት ማንን ነው? ጳውሎስ “መካን” የነበረችው ሣራ፣ የይሖዋን ሚስት ማለትም የይሖዋን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል የምትወክል መሆኗን ገለጸ። ይህች ሰማያዊ ሴት መካን የተባለችው ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ በመንፈስ የተቀቡ “ልጆች” ስላልነበሯት ነው። (ገላትያ 4:27፤ ኢሳይያስ 54:1-6) ይሁን እንጂ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጰንጠቆስጤ በዓል በተከበረበት ዕለት ተሰብስበው በነበሩ ወንዶችና ሴቶች ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። ይህም የዚህች ሰማያዊ ሴት ልጆች በመሆን ዳግም እንዲወለዱ አደረጋቸው። ይህች ሰማያዊ ድርጅት የወለደቻቸው ልጆች የአምላክ ልጅ የመሆን መብት ከማግኘታቸውም በላይ በአዲሱ ቃል ኪዳን መሠረት ከክርስቶስ ጋር ወራሾች ይሆናሉ። (ሮሜ 8:15-17) ከእነዚህ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ “ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት” በማለት ጽፏል።—ገላትያ 4:26

የሁለቱ ሴቶች ልጆች

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እስማኤል ይስሐቅን አሳዶታል። በተመሳሳይም በአንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በባርነት ሥር ያለችው የኢየሩሳሌም ልጆች በላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ልጆች ላይ አፊዘውባቸዋል እንዲሁም አሳደዋቸዋል። ይህን ሁኔታ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “በዚያን ጊዜ እንደ ሥጋ ልማድ የተወለደው፣ ልጅ [እስማኤል] በመንፈስ ኀይል የተወለደውን [ይስሐቅን] አሳደደው፤ አሁንም እንደዚያው ነው።” (ገላትያ 4:29) ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ ሲጀምር የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የአጋር ልጅ እስማኤል የአብርሃም እውነተኛ ወራሽ በሆነው በይስሐቅ ላይ የወሰደው ዓይነት እርምጃ ወስደዋል። ራሳቸውን የአብርሃም ሕጋዊ ወራሽ፣ ኢየሱስን ደግሞ መብቱ ያልሆነውን ነገር ለማግኘት እንደሚሞክር አድርገው በመቁጠር በእርሱ ላይ አፊዘዋል እንዲሁም አሳድደውታል።

ኢየሱስ በእስራኤላውያን ገዥዎች ከመገደሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር:- “አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ አንቺ ኢየሩሳሌም! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን ፈቃደኛ አልሆናችሁም፤ እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል!”—ማቴዎስ 23:37, 38

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለተፈጸሙ አንዳንድ ክስተቶች የሚናገሩ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በአጋር የተመሰለው የሥጋዊ እስራኤል ብሔር ከክርስቶስ ጋር ወራሽ የሚሆኑ ልጆችን በቀጥታ ማስገኘት አልቻለም። አይሁዳውያን እስራኤላዊ ሆነው ስለተወለዱ ብቻ ይህ ቦታ እንደሚገባቸው በማሰብ ይኩራሩ የነበረ ቢሆንም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ በትውልድ እስራኤላዊ የሆኑ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ወራሽ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ይህን መብት ያገኙት ሥጋዊ እስራኤላውያን በመሆናቸው ሳይሆን በክርስቶስ ላይ እምነት በማሳደራቸው ነበር።

ከክርስቶስ ጋር ወራሽ ከሚሆኑት ሰዎች መካከል የአንዳንዶቹ ማንነት በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ግልጽ ሆኗል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ሌሎች ሰዎችንም የላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ልጆች እንዲሆኑ ቀብቷቸዋል።

ጳውሎስ ይህን “ምሳሌያዊ ድራማ” ያብራራው አዲሱ ቃል ኪዳን ሙሴ መካከለኛ ከሆነለት የሕግ ቃል ኪዳን የሚበልጥ መሆኑን ለማሳየት ነው። የሰው ዘር ፍጽምና ስለሚጎድለውና ሕጉም ሰዎች የኃጢአት ባርያ መሆናቸውን ስለሚያጎላ ማንም ቢሆን የሙሴን ሕግ በመፈጸም የአምላክን ሞገስ ማግኘት አይችልም። ያም ሆኖ ግን ጳውሎስ እንደገለጸው ኢየሱስ የመጣበት ምክንያት “ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው።” (ገላትያ 4:4, 5) ከዚህም የተነሣ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ባለው ዋጋ ላይ እምነት ማሳደር ከሕግ ኩነኔ ነፃ ያወጣል።—ገላትያ 5:1-6

ከድራማው የምናገኘው ጥቅም

ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ላብራራው ለዚህ ድራማ ትኩረት መስጠት የሚገባን ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት እንዲህ ያለ ማብራሪያ ባናገኝ ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥልቀት መረዳት ስለማንችል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ማብራሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ባለው አንድነትና ስምምነት ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።—1 ተሰሎንቄ 2:13

በተጨማሪም በዚህ ምሳሌያዊ ድራማ ላይ የተወከሉት ሰዎች ወደፊት በምናገኘው ደስታ ላይ ወሳኝ ቦታ አላቸው። የላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ልጆች ባይገለጡ ኖሮ ለሞትና ለኃጢአት ባሮች ሆነን እንቀር ነበር። ይሁን እንጂ በክርስቶስ እንዲሁም አምላክ ለአብርሃም በሰጠው ተስፋ መሠረት አብረው ወራሽ በሚሆኑት ሰዎች ፍቅራዊ አመራር አማካኝነት ‘በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች . . . ይባረካሉ።’ (ዘፍጥረት 22:18) ይህም ቃል የሚፈጸመው የሰው ልጆች ከኃጢአት፣ ከአለፍጽምና፣ ከሐዘንና ከሞት ለዘላለም ነፃ ሲሆኑ ነው። (ኢሳይያስ 25:8, 9) ይህ ወቅት እንዴት ያለ ክብራማ ጊዜ ይሆናል!

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሕጉ ቃል ኪዳን የተሰጠው በሲና ተራራ ላይ ነው

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሰው “ምሳሌያዊ ድራማ” ትርጉም ምንድን ነው?