ሞት አስከፊው እውነታ!
ሞት አስከፊው እውነታ!
አርኖልድ ቶይንቢ የተባሉ እንግሊዛዊ ታሪክ ጸሐፊ “የሰው ልጅ ከተወለደበት ቅጽበት አንስቶ በማንኛውም ጊዜ ሊሞት ይችላል፤ አንድ ቀን ይህ ሐቅ እውን መሆኑ አይቀርም” በማለት ጽፈዋል። ሞት የምንወደውን የቤተሰባችንን አባል ወይም የቅርብ ወዳጃችንን ሲነጥቀን ከፍተኛ ሐዘን ይደርስብናል!
ለብዙ ሺህ ዓመታት ይህ አስከፊ እውነታ የሰው ልጆችን ሲያሰቅቅ ኖሯል። የምንወደው ሰው ሲሞትብን የከንቱነት ስሜት ይሰማናል። እገሌ ከገሌ ሳይል ሁሉም ሰው የዚህ ዓይነት ሐዘን ያጋጥመዋል። ከሞት ሊያመልጥ የሚችል ሰው የለም። አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ጸሐፊ “ምንም ያህል የትምህርት ደረጃ ቢኖረን [ስለ ሞት ለሚፈጠሩብን ጥያቄዎች] መልስ ስለማይኖረን ሐዘን ሁላችንንም እንደ ልጆች ያደርገናል። አዋቂ የተባለው ሰው እንኳ ምንም አያውቅም” በማለት ጽፈዋል። ልክ እንደ ሕፃናት ሁኔታዎችን ልንቀይር የማንችል አቅመ ቢስ እንሆናለን። ሀብትም ሆነ ሥልጣን ያጣነውን ሰው ሊመልስልን አይችልም። አዋቂዎችም ሆኑ ምሑራን መልስ የላቸውም። ብርቱውም እንደ ደካማው እንባውን ያፈሳል።
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ልጁ አቤሴሎም በሞተበት ጊዜ ይህን የመሰለ መሪር ሐዘን ደርሶበታል። ንጉሡ የአቤሴሎምን ሞት በሰማበት ጊዜ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም ሆይ፣ ልጄን፣ ወየው ልጄን!” ብሎ አልቅሷል። (2 ሳሙኤል 18:33) ኃያላን የሆኑት ጠላቶቹን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገው ብርቱ ንጉሥ እንኳ ምንም ነገር ለማድረግ ስላልቻለ በልጁ ምትክ ‘የመጨረሻ ጠላት ለሆነው ሞት’ ራሱን ለመስጠት ተመኝቷል።—1 ቆሮንቶስ 15:26
ታዲያ ሞት መፍትሔ ይኖረው ይሆን? ካለው የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው? የምንወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ እናያቸው ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ ይሰጠናል።