በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል

በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል

በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል

ሐዋርያው ዮሐንስ “ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር” በማለት ጽፏል። (ራእይ 14:6) በዚህ ትንቢታዊ ራእይ ፍጻሜ መሠረት የአምላክ መንግሥት ወንጌል ወይም ምሥራች በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተሰበከ ነው። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል አብዛኞቹ የሚነገሩት ከትውልድ አገራቸው ርቀው በሚገኙ ስደተኞች ነው። እነዚህ ግለሰቦችም ሌላ ቋንቋ በተማሩ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች አማካኝነት ምሥራቹን እየሰሙ ነው።

አንተስ በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ከሚያገለግሉ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ነህ? ወይስ እንዲህ ለማድረግ እያሰብክ ነው? ይህ ጥረትህ እንዲሳካልህ የምትፈልግ ከሆነ የተነሳሳህበት ምክንያት ከራስ ወዳድነት የራቀ መሆን ይኖርበታል፤ እንዲሁም ትክክለኛ አመለካከት ሊኖርህ ይገባል። ዓላማህ ሌሎች በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት እንዲማሩ መርዳት እንደመሆኑ መጠን የተነሳሳኸው ጥሩ የውስጥ ግፊት ኖሮህ ይኸውም አምላክንና ሰዎችን ስለምትወድ ነው። (ማቴዎስ 22:37-39፤ 1 ቆሮንቶስ 13:1) የሌላ አገር ሕዝቦችን ቋንቋ ለመማር የምትነሳሳው ከሰዎቹ ጋር መወዳጀት ስለሚያስደስትህና ምግባቸውን አሊያም ባሕላቸውን ስለምትወድ ብቻ ሳይሆን ስለ አምላክ እንዲያውቁ ለመርዳት ስለምትፈልግ መሆኑ ይበልጥ ጠንካራ ግፊት ይሆንልሃል። አዲስ ቋንቋ መልመድ ከባድ እንደሆነ ይሰማሃል? ከሆነ ተገቢ የሆነ አመለካከት መያዝ ይረዳሃል። ጃፓንኛ ቋንቋ የተማረው ጄምስ “ቋንቋ መማር ሊያስፈራህ አይገባም” በማለት ይናገራል። ከአንተ በፊት ብዙዎች ሞክረው እንደተሳካላቸው ማሰብህ ሳትሰለች እንድትጥርና አዎንታዊ አመለካከት እንድታዳብር ይረዳሃል። ታዲያ አዲስ ቋንቋ እንዴት መማር ትችላለህ? እየተማርክ ባለኸው ቋንቋ የሚመራውን ጉባኤ እንድትለምድ ምን ሊረዳህ ይችላል? እንዲሁም በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነህ እንድትቀጥል ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ቋንቋ መማር ያለውን መሰናክል መወጣት

አንድን ቋንቋ በተለያዩ መንገዶች መማር ይቻላል። አስተማሪዎችና ተማሪዎች ለመማርም ሆነ ለማስተማር የተለያየ ዘዴ ይመርጡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙ ተማሪዎች በአንድ ጎበዝ አስተማሪ አማካኝነት ጥቂት ጊዜ መማር የትምህርቱን ሂደት ይበልጥ ቀላልና ቀልጣፋ እንደሚያደርገው ይሰማቸዋል። እየተለማመድህ ባለው ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማንበብህ እንዲሁም ማንኛውንም በቋንቋው የሚገኝ ካሴት ማዳመጥህ ብዙ ቃላትን እንድታውቅ የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ ቲኦክራሲያዊ በሆኑ ቃላት ረገድ ያለህ እውቀትም ይሰፋል። ጥሩ ይዘት ያላቸውን የሬዲዮ፣ የቲሌቪዥንና የቪዲዮ ፕሮግራሞች መከታተልህ ከቋንቋውና ከባሕሉ ጋር ይበልጥ እንድትተዋወቅ ይረዳሃል። ከስንት አንዴ እየተገናኙ ረጅምና አድካሚ ጥናት ከማድረግ ይልቅ በየቀኑ ትንሽ ትንሽ መወያየቱ ይበልጥ ውጤታማ ነው።

አዲስ ቋንቋ መማር፣ ዋና ከመለማመድ ጋር ተመሳሳይ ነው። የውኃ ዋናን መጽሐፍ በማንበብ መማር አትችልም። ውኃ ውስጥ ገብተህ እየተንቦጫረቅህ መለማመድ ይኖርብሃል። ቋንቋ መማርም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። እንዲሁ ዝም ብሎ ስለተጠና ብቻ የሚሆን ነገር አይደለም። አጋጣሚውን ካገኘህ ቋንቋውን ከሚናገሩ ሰዎች ጋር ተቀላቅለህ ሲነጋገሩ ማዳመጥ፣ ከእነርሱ ጋር መጫወት ወይም የምትችለውን ያህል ማውራት ይኖርብሃል! ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ይህን ለማድረግ የሚያስችል ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራሉ። ብዙውን ጊዜ የምትማራቸውን ነገሮች በመስክ አገልግሎት ላይ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። ቻይንኛ እየተማረች ያለችው ሚዶሪ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ይህን ማድረግ የሚያስፈራ ይመስላል፤ ነገር ግን የምናነጋግራቸው ሰዎች እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ያህል እንደምንጥር ይመለከታሉ። ይህ ደግሞ ልባቸውን ይነካል። ከእኛ የሚጠበቀው በቋንቋቸው ‘እቤትህ ስላገኘሁ ደስ ብሎኛል’ ማለት ብቻ ነው። በዚህ ወቅት ሊያነጋግሩህ ፈቃደኛ መሆናቸውን በደስታ ከተሞላው ፊታቸው ማየት ትችላለህ!”

ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ትልቅ እርዳታ ያበረክታሉ። በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሐሳብ ለመስጠት ሞክር። ይህ መጀመሪያ አካባቢ ሊያስፈራህ ቢችልም አትጨነቅ። ጉባኤው አንተ ተሳክቶልህ ማየት ይፈልጋል! የኮሪያ ቋንቋ እየተማረች ያለችው ሞኒፋ “በስብሰባዎች ላይ ከጎኔ ተቀምጣ የአንዳንድ ቃላትን ትርጉም የምትጽፍልኝን እህት ላመሰግናት እወዳለሁ። የእርሷ ወዳጃዊ አቀራረብ እንዲሁም በትዕግሥት ያደረገችልኝ እርዳታ በእርግጥም ትልቅ እገዛ አድርጎልኛል” በማለት ትናገራለች። የምታውቃቸው ቃላት ብዛት እየጨመረ ሲሄድ በአዲሱ ቋንቋ ማሰብ ትጀምራለህ፤ ይህም ማለት እያንዳንዱን ቃል በአእምሮህ ውስጥ ከመተርጎም ይልቅ ቃላቱ ከሚወክሉት ነገር ጋር ታዛምዳቸዋለህ።

የመጀመሪያ ግብህ ‘ከአንደበትህ ትርጒም ያለው ቃል እንዲወጣ’ መጣር ሊሆን ይገባል። (1 ቆሮንቶስ 14:8-11) ምንም እንኳ ሰዎች ጥረትህን ቢያደንቁም በተደጋጋሚ የምትሳሳት ወይም ቃላትን በተለየ መንገድ የምትጠራ ከሆነ በምትናገረው መልእክት ላይ ላያተኩሩ ይችላሉ። ከለመደብህ ለማስተካከል ስለሚከብድህ የቃላትን ትክክለኛ አጠራርና የሰዋሰው ሕግ ገና ከመጀመሪያው ትኩረት ሰጥተህ መማር ይኖርብሃል። ስዋሂሊ የተማረው ማርክ እንዲህ በማለት ሐሳብ ይሰጣል:- “ከበድ ያለ ስህተት ስትሠራ እንዲያርሙህ ቋንቋውን በደንብ የሚናገሩ ሰዎችን ጠይቅ፤ ከዚያም ለሰጡህ ሐሳብ አመስግናቸው!” እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ለማድረግ ጊዜና ጉልበት እንደሚጠይቅባቸው ማሰብ ይኖርብሃል። ያዘጋጀኸውን ማስታወሻ ሌላ ሰው አይቶ እንዲያርምልህ ማድረግ የምትችል ቢሆንም እንኳ በምታውቃቸው ወይም ከመዝገበ ቃላት ፈልገህ ባገኘሃቸው ቃላት ተጠቅመህ ንግግር ለማቅረብ ወይም ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርግ። ይህም የመማር ሂደቱን የሚያፋጥነው ከመሆኑም ሌላ በድፍረት እንድትናገር ይረዳሃል።

እድገት ማድረግህን ቀጥል

ሞኒፋ “እስከ ዛሬ ከሠራኋቸው ሥራዎች ሁሉ ሌላ ቋንቋ የመማርን ያህል የከበደኝ የለም” በማለት ትናገራለች። አክላም እንዲህ ብላለች:- “ለማቋረጥ ያሰብኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ ባወቅኳቸው ጥቂት የኮሪያ ቋንቋ ቃላት ተጠቅሜ የምነግራቸውን ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶች ምን ያህል እንደሚወዱት እንዲሁም ወንድሞች የማደርገው ትንሽ እድገት ምን ያህል እንደሚያስደስታቸው አስታወስሁ።” ነጥቡ ግልጽ ነው፤ በቀላሉ ተስፋ አትቁረጥ። ዋናው ግብህ ሕይወት አድን የሆነውን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ለሌሎች ማስተማር ነው። (1 ቆሮንቶስ 2:10) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በሌላ ቋንቋ ማስተማር ከፍተኛ ትኩረት መስጠትና የረጅም ጊዜ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። እድገት ባደረግህ መጠን ራስህን ከሌሎች ጋር ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከማወዳደር ተቆጠብ። አዲስ ቋንቋ የሚማሩ ሰዎች እድገት የሚያደርጉበት ፍጥነትም ሆነ አቅጣጫ ይለያያል። ይሁን እንጂ የራስህን እድገት በንቃት መከታተል ይኖርብሃል። (ገላትያ 6:4) ቻይንኛ መማር የጀመረው ጁን “ቋንቋ መማር ደረጃ ከመውጣት ጋር ይመሳሰላል። ምንም ነገር እንዳላሻሻልክ በተሰማህ ጊዜ፣ እድገት ማድረግህን በድንገት ታስተውላለህ።”

አዲስ ልሳን መማር የዕድሜ ልክ ጉዞ ነው። ስለዚህ በጉዞው ተደሰት፤ እንዲሁም ከራስህ ፍጽምናን አትጠብቅ። (መዝሙር 100:2) በመማር ሂደት ውስጥ መሳሳት የማይቀር ነገር ነው። አንድ ክርስቲያን በጣሊያንኛ መስበክ በጀመረ ሰሞን የሚያነጋግረውን ሰው “የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ያውቃሉ” ብሎ ለመጠየቅ ፈልጎ “የሕይወት መጥረጊያ ምን እንደሆነ ያውቃሉ?” ብሎት ነበር። የፖሊሽ ቋንቋ እየተማረ የነበረ አንድ ሌላ የይሖዋ ምሥክር ደግሞ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ወንድሞችን ‘መዝሙር እንዘምር’ ለማለት ‘ውሻ እንዘምር’ ብሏቸዋል። ቻይንኛ እየተማረ ያለ አንድ ሰው ቃላቱን የጠራበት መንገድ ትንሽ ለየት በማለቱ ለአድማጮቹ ‘በኢየሱስ ቤዛ እመኑ’ ለማለት ፈልጎ ‘በኢየሱስ የመጽሐፍ መደርደሪያ’ ላይ እምነት አሳድሩ አላቸው። የስህተት መልካም ጎን አንዴ የተሳሳትነው ቃል ትክክለኛ አጠራር ለሁለተኛ ጊዜ እንዳንረሳው ማድረጉ ነው።

ከጉባኤው ጋር ተባብሮ መሥራት

ሰዎችን የሚለያያቸው የቋንቋ አንድ አለመሆን ብቻ አይደለም። ከባሕል፣ ከዘርና ከአገር ጋር የተያያዙ ልዩነቶች ብዙውን ጊዜ ሕዝቦች ይበልጥ እንዲራራቁ ያደርጋቸዋል። እነዚህ መሰናክሎች ግን ለማለፍ የሚከብዱ አይደሉም። በአውሮፓ በሚገኙና ቻይንኛ ተናጋሪ በሆኑ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ላይ ጥናት የሚያደርጉ አንድ ምሑር የይሖዋ ምሥክሮች “ብሔራዊ ድንበር” እንደማይገድባቸው ተናግረዋል። እኚህ ሰው በምሥክሮቹ መካከል “የዘር ልዩነት ምንም ቦታ የለውም። ቋንቋም ቢሆን የአምላክን ቃል ለመረዳት የሚጠቀሙበት መሣሪያ ነው” ብለዋል። እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል እውነተኛ ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት እንዲያሸንፉ ረድቷቸዋል። ‘አዲሱን ሰው’ የለበሱ ሁሉ ግሪካዊ ወይም አይሁዳዊ አሊያም መጻተኛ ብለው ልዩነት አያደርጉም።—ቈላስይስ 3:10, 11

በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉም ወንድሞች ለጉባኤው አንድነት ተባብረው መሥራት ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ አንድ ሰው አዳዲስ አስተሳሰቦችንና ስሜቶችን እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ነገሮችን የሚያከናውኑበትን መንገድ ለመቀበል አእምሮውንና ልቡን ማዘጋጀት ይጠይቅበታል። የግል ምርጫህን ወደኋላ ገሸሽ በማድረግ የዘርና የመሳሰሉት ልዩነቶች ወደ መከፋፈል እንዳያመሩ ማድረግ ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 1:10፤ 9:19-23) ሁሉም ባሕሎች ያላቸውን ጥሩ ጎን ለመልመድ ጥረት አድርግ። ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ከሌሎች ጋር ለሚኖርህ ግንኙነትና ለአንድነት ቁልፍ ነገር እንደሆነ አትዘንጋ።

አብዛኛውን ጊዜ በውጭ አገር ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች የሚቋቋሙት ከትንሽ ቡድን በመነሳት ነው። እነዚህ ቡድኖች አዲሱን ቋንቋ በመማር ላይ ያሉ በርከት ያሉ አስፋፊዎችንና በቅርቡ መጽሐፍ ቅዱስን መማር የጀመሩ ጥቂት ሰዎችን የሚያቅፉ ናቸው። ከዚህም የተነሳ አብዛኛውን ጊዜ አለመግባባቶች የሚፈጠሩት በቆዩ ጉባኤዎች ውስጥ ሳይሆን እንደነዚህ ባሉ ቡድኖች ውስጥ ነው። ጎልማሳ የሆኑ ክርስቲያኖች ጉባኤው የተረጋጋ እንዲሆን መጣር ይኖርባቸዋል። በቃላትም ይሁን በድርጊት ፍቅርና ደግነት ማሳየታቸው አዲሶች በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የሚያስችል ጥሩ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።

በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ወንድሞችም ቢሆኑ ከሌሎች በሚጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ይኖርባቸዋል። እንዲህ ባለው ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ሪክ እንዲህ በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል:- “በዚህ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አዳዲስ የይሖዋ ምሥክሮች በቆዩ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉትን ያህል በድርጅታዊ አሠራር በደንብ አልሠለጠኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ የጎደላቸውን ችሎታ በፍቅራቸውና በቅንዓታቸው ያካክሱታል። እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩ ብዙ ሰዎች ወደ እውነት እየመጡ ነው።” ቋንቋ እየተማርክ ቢሆንም እንኳ በሁሉም የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ላይ በመካፈልና በምትችለው ሁሉ ለመርዳት ራስህን በማቅረብ ለጉባኤው በረከት መሆን ትችላለህ። አንድ ላይ ተባብሮ መሥራት ለጉባኤው መንፈሳዊ እድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል።

መንፈሳዊ ጥንካሬን ጠብቆ መኖር

በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በውጭ አገር ቋንቋ ለሚመራ ጉባኤ አዲስ የሆነ አንድ ወንድም አንዲት እናት ልጅዋ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ሐሳብ እንዲሰጥ ስታዘጋጀው የሚባባሉት ነገር ጆሮው ውስጥ ጥልቅ አለ። ልጁ እናቱን “እማማ፣ ምናለበት አጭር የሆነውን መልስ ብመልስ?” ይላታል። እናትም መልሳ “አይሆንም የኔ ልጅ፤ አጫጭሮቹን መልሶች ገና ቋንቋውን እየለመዱ ላሉት እንተውላቸው” አለችው።

አንድ አዋቂ ሰው ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት ከሌሎች ጋር በሚገባ መነጋገር አለመቻሉ አእምሯዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትልበት ይችላል። በአሁኑ ወቅት ስፓንኛ አቀላጥፋ የምትናገረው ጃኔት “እንደፈለግሁ መናገር ባለመቻሌ ጭንቀት ይዞኝ ነበር” በማለት ትናገራለች። እንግሊዝኛ የተማረችው ሂሮኮ ደግሞ ‘በአካባቢው የሚገኙት ውሾችና ድመቶች እንኳ እንግሊዝኛን ከኔ በተሻለ ይረዳሉ’ ብላ ታስብ እንደነበረ ተናግራለች። ካቲ ደግሞ “ወደ ስፓንኛ ተናጋሪ ጉባኤ ከመዛወሬ በፊት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሩኝ፤ ማስታወሻ ደብተሬም ተመላልሶ መጠየቅ ላደርግላቸው በቀጠርኳቸው ሰዎች ስም የተሞላ ነበር፤ በኋላ ግን ባዶ እጄን ቀረሁ። አንድም የረባ ነገር እንዳልሠራሁ ተሰምቶኝ ነበር” ብላለች።

አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር የሚገባው በዚህ ወቅት ነው። ሂሮኮ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማት “ሌሎች ይህን ማድረግ ከቻሉ እኔ የማልችልበት ምክንያት የለም” ብላ ራሷን ታሳምን ነበር። ካቲ ደግሞ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “በዚህ ረገድ ጥሩ እድገት ያደረገውንና በጉባኤ ውስጥ ብዙ ሥራ እየሠራ ያለውን ባለቤቴን አሰብኩ። ይህም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዳሸንፍ ረዳኝ። አሁንም ቢሆን ብዙ መሥራት ይጠበቅብኛል፤ ሆኖም ቀስ በቀስ መስበክና ማስተማር ችያለሁ፣ እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጌም ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል።” ባለቤቷ ጄፍ ደግሞ “ማስታወቂያ ሲነገርም ሆነ በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ሁሉንም ነገር መረዳት አለመቻል በጣም የሚያሳዝን ነው። እኔም ሐቀኛና ትሑት ሆኜ በደንብ እንዲያስረዱኝ መጠየቅ አለብኝ። ደስ የሚለው ወንድሞች እኔን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው” በማለት ተናግሯል።

በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ በምታገለግልበት ጊዜ በመንፈሳዊ እንዳትዳከም ለራስህ መንፈሳዊ ጤንነት ቅድሚያ መስጠት ይኖርብሃል። (ማቴዎስ 5:3) በፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ ክልል ውስጥ ለዓመታት ያገለገለው ካዙዩኪ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በቂ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘታችን በጣም አስፈላጊ ነው። በቤተሰብ ደረጃ በራሳችን ቋንቋ እንዲሁም በፖርቹጋልኛ የምናጠናውና ለጉባኤ ስብሰባዎች የምንዘጋጀው በዚህ ምክንያት ነው።” አንዳንዶች በገዛ ቋንቋቸው በሚደረጉ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አልፎ አልፎ ይገኛሉ። ከዚህም በላይ በቂ እረፍት ማድረግም አስፈላጊ ነው።—ማርቆስ 6:31

ዋጋውን ማስላት

በሌላ ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ለመዛወር አስበህ ከሆነ እንዲህ ማድረግ የሚያስከፍለውን ዋጋ ማስላት ይኖርብሃል። (ሉቃስ 14:28) በዚህ ረገድ ትልቅ ትኩረት መስጠት የሚኖርብህ ለመንፈሳዊነትህና ከይሖዋ ጋር ላለህ ዝምድና ነው። ያለህበትን ሁኔታ አስመልክተህ ጸልይ። የትዳር ጓደኛህንና ልጆችህን ከግምት አስገባ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህን የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ለመጀመር የተመቻቸ ሁኔታ እንዲሁም መንፈሳዊና ስሜታዊ ጥንካሬ አለኝ?’ ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ መንፈሳዊነት የሚጠቅም እርምጃ መውሰድህ የጥበብ መንገድ ነው። የአምላክ መንግሥት ምሥራች ሰባኪ ሆነህ የትም ብታገለግል ልትሠራውና ደስታ ልታገኝበት የሚያስችል ብዙ ሥራ አለ።

በውጭ አገር ቋንቋ በሚናገሩ ጉባኤዎች ውስጥ እያገለገሉ ያሉ አስፋፊዎች የሚያገኙት ብዙ በረከት አለ። ከባሏ ጋር ወደ ስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ ሄዳ የምታገለግለው ባርባራ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ይህ እስካሁን ካጋጠሙኝ አስደሳች ተሞክሮዎች አንዱ ነው። ልክ እውነትን ዳግመኛ የሰማሁ ያህል ሆኖ ነበር የተሰማኝ። ሌላ አገር ሚስዮናዊ ሆነን መሄድ ስለማንችል እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በማግኘታችን በጣም አመስጋኝ ነኝ።”

በዓለም ዙሪያ በሺህ የሚቆጠሩ በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ተራ ሰዎች ምሥራቹን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማዳረስ ሲሉ ሌላ ቋንቋ መማር የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛሉ። ከእነርሱ አንዱ ከሆንክ የተነሳህበትን ዓላማ አጥብቀህ ያዝ፤ እንዲሁም ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥረትህን እንዲባረክልህ በይሖዋ ታመን።—2 ቆሮንቶስ 4:7

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩ ችሎታ ባለው አስተማሪ አማካኝነት የቋንቋ ትምህርት መከታተል የትምህርቱን ሂደት ይበልጥ ቀላልና ቀልጣፋ ያደርገዋል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የውጪ አገር ቋንቋ ለመማር ብለህ መንፈሳዊ ደኅንነትህን አደጋ ላይ መጣል አይገባህም