በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሐሰት አምልኮ ራቁ!

ከሐሰት አምልኮ ራቁ!

ከሐሰት አምልኮ ራቁ!

“ከመካከላቸው ውጡ፤ ለእኔም የተለያችሁ ሁኑ፤ ይላል ጌታ። ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ።”—2 ቆሮንቶስ 6:17

1. ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?

 ልበ ቅን የሆኑ በርካታ ሰዎች ስለ አምላክም ሆነ ስለ ሰው ዘር የወደፊት ሁኔታ ትክክለኛ እውቀት የላቸውም። በጥልቅ ለሚያሳስቧቸው መንፈሳዊ ጉዳዮች መልስ ማግኘት ባለመቻላቸው ግራ ተጋብተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጣሪያችንን በሚያሳዝኑ አጉል እምነቶች፣ የአምልኮ ሥርዓቶችና ክብረ በዓሎች ተጠላልፈዋል። አንተም ብትሆን በእሳታማ ሲኦል፣ በሥላሴ፣ በነፍስ አለመሞት ወይም በሌሎች የሐሰት ትምህርቶች የሚያምኑ ጎረቤቶችና ዘመዶች ይኖሩህ ይሆናል።

2. የሃይማኖት መሪዎች ምን አድርገዋል? ይህስ ምን ዓይነት ሁኔታ አስከትሏል?

2 በዓለም ላይ ለተስፋፋው እንዲህ ላለው መንፈሳዊ ጨለማ ተጠያቂው ማነው? ነገሩ የሚያስገርም ቢሆንም ለዚህ ሁኔታ በኃላፊነት የሚጠየቀው ሃይማኖት ነው፤ በተለይ ደግሞ ከአምላክ ሐሳብ ጋር የሚጋጩ ትምህርቶችን የሚያስተምሩት ሃይማኖታዊ ድርጅቶችና መሪዎች ተጠያቂ ናቸው። (ማርቆስ 7:7, 8) በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ እንደሚያመልኩ ቢያምኑም ሳያውቁት እርሱን የሚያሳዝን ነገር ያደርጋሉ። ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆነው የሐሰት ሃይማኖት ነው።

3. የሐሰት ሃይማኖትን በማስፋፋት ረገድ ዋነኛው ተዋናይ ማን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥስ እንዴት ተደርጎ ተገልጿል?

3 ከሐሰት ሃይማኖት በስተ ጀርባ አንድ የማይታይ አካል አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ አካል ሲናገር “የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ፣ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሮአል” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) “የዚህ ዓለም አምላክ” የተባለው ከሰይጣን ዲያብሎስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ሰይጣን የሐሰት አምልኮን በማስፋፋት ረገድ ዋና ተዋናይ ነው። ጳውሎስ “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል” ሲል ጽፏል። አክሎም “እንግዲህ የእርሱ አገልጋዮች፣ የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ የሚያስገርም አይደለም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 11:14, 15) ሰይጣን መጥፎ ነገሮች መልካም መስለው እንዲታዩ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሰዎች ውሸቶቹን እንዲያምኑ በማድረግ ያታልላቸዋል።

4. አምላክ ለጥንት እስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ሐሰተኛ ነቢያትን አስመልክቶ ምን ይላል?

4 መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ሃይማኖትን አጥብቆ የሚያወግዝ መሆኑ ምንም አያስገርምም! ለአብነት ያህል፣ የሙሴ ሕግ የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ሐሰተኛ ነቢያትን እንዳይሰሙ በግልጽ አስጠንቅቋቸዋል። እውነት ያልሆኑ ትምህርቶችንና የሐሰት አማልክት አምልኮን የሚያስፋፋ ማንኛውም ሰው ‘በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምፁ ስለተናገረ ይገደል’ ነበር። እስራኤላውያን ‘ክፉውን ከመካከላቸው እንዲያስወግዱ’ ታዝዘው ነበር። (ዘዳግም 13:1-5) በእርግጥም ይሖዋ የሐሰት ሃይማኖትን ይጠላል።—ሕዝቅኤል 13:3

5. በዛሬው ጊዜ የትኞቹን ማስጠንቀቂያዎች ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል?

5 ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱም ቢሆኑ የሐሰት ሃይማኖትን በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አንጸባርቀዋል። ኢየሱስ “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵሎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 7:15፤ ማርቆስ 13:22, 23) ጳውሎስ “በክፋታቸው እውነትን ዐፍነው በሚይዙ፣ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 1:18) እውነተኛ ክርስቲያኖች እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ተግባራዊ በማድረግ፣ የአምላክ ቃል እውነት እንዳይታወቅ ከሚያደርግ ወይም የሐሰት ትምህርቶችን ከሚያሰራጭ ከማንኛውም ሰው መራቃቸው በጣም አስፈላጊ ነው!—1 ዮሐንስ 4:1

‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ሽሹ

6. “ታላቂቱ ባቢሎን” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸችው በምን መንገድ ነው?

6 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ የሐሰት ሃይማኖትን እንዴት እንደሚገልጸው ተመልከት። የሐሰት ሃይማኖት በብዙ መንግሥታትና በሕዝቦቻቸው ላይ ተጽዕኖ በምታሳድር የሰከረች ጋለሞታ ተመስሏል። ይህቺ ምሳሌያዊት ሴት ከበርካታ ነገሥታት ጋር ከማመንዘሯም በላይ በአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች ደም ሰክራለች። (ራእይ 17:1, 2, 6, 18) አስጸያፊና አስነዋሪ ከሆነው ድርጊቷ ጋር የሚስማማ “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰቶች እናት” የሚል ስም በግንባሯ ላይ ተጽፏል።—ራእይ 17:5

7, 8. የሐሰት ሃይማኖቶች አመንዝራ የሆኑት እንዴት ነው? ይህስ ምን አስከትሏል?

7 መጽሐፍ ቅዱስ ታላቂቱ ባቢሎንን አስመልክቶ የሚሰጠው መግለጫ በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩት ሃይማኖቶች ተዋህደው አንድ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ባይመሠርቱም በዓላማና በድርጊት ተጣምረዋል። በራእይ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸችው ሥነ ምግባር የጎደላት ሴት ሁሉ የሐሰት ሃይማኖቶችም በመንግሥታት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ለጋብቻ ቃል ኪዳኗ ታማኝ ካልሆነች ሴት ጋር በሚመሳሰል መንገድ፣ የሐሰት ሃይማኖቶች ከተለያዩ ፖለቲካዊ መንግሥታት ጋር የኅብረት ስምምነት በመፍጠር መንፈሳዊ ምንዝር ፈጽመዋል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” ሲል ጽፏል።—ያዕቆብ 4:4

8 የሐሰት ሃይማኖት ከመንግሥታት ጋር የመሠረተው ይህ ጥምረት በሰው ዘሮች ላይ ከፍተኛ ሥቃይ አስከትሏል። ዶክተር ኦኔና ሜንጎ የተባሉ አፍሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ “የዓለም ታሪክ፣ ሃይማኖት ከፖለቲካ ጋር በመቀላቀሉ ምክንያት በተከሰቱ በርካታ የጅምላ ጭፍጨፋዎች የተሞላ ነው” ብለዋል። በቅርቡ የወጣ አንድ ጋዜጣ ደግሞ “በዛሬው ጊዜ ብዙ ደም የፈሰሰባቸውና በጣም አደገኛ የሆኑት ግጭቶች . . . ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ናቸው” ብሏል። ሃይማኖቶች በሚደግፏቸው ጦርነቶች ሳቢያ የብዙዎች ሕይወት ተቀጥፏል። ታላቂቱ ባቢሎን የአምላክን እውነተኛ አገልጋዮች እንኳ በማሳደድና በመግደል በምሳሌያዊ አባባል በደማቸው ሰክራለች።—ራእይ 18:24

9. ይሖዋ ለሐሰት አምልኮ ያለው ጥላቻ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው እንዴት ነው?

9 በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይሖዋ የሐሰት አምልኮን እንደሚጠላ በግልጽ ያሳያል። ራእይ 17:16 እንዲህ ይላል:- “አውሬውና ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች አመንዝራዪቱን ይጠሏታል፤ ባዶዋንና ዕራቊቷን ያስቀሯታል። ሥጋዋን ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል።” በመጀመሪያ አንድ ግዙፍ አውሬ ለሞት የሚያደርስ ጥቃት ከሰነዘረባት በኋላ ሥጋዋን ይበላል። ከዚያም የቀረው አካሏ ሙሉ በሙሉ በእሳት ይቃጠላል። ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ በቅርቡ የዓለም መንግሥታት በሐሰት ሃይማኖት ላይ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ ይወስዳሉ። አምላክ እንዲህ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። (ራእይ 17:17) የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ተወስኖባታል። “ተመልሳም አትገኝም።”—ራእይ 18:21

10. ከሐሰት ሃይማኖት ጋር በተያያዘ አቋማችን ምን ሊሆን ይገባል?

10 የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር በተያያዘ ምን አቋም ሊኖራቸው ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ “ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ ከመቅሠፍቷም እንድትካፈሉ፣ ከእርሷ ውጡ” በማለት ግልጽ መመሪያ ይሰጣል። (ራእይ 18:4) ለመዳን የሚፈልጉ ሁሉ ጊዜው ከማለፉ በፊት ከሐሰት ሃይማኖት መውጣት ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ እያለ፣ በመጨረሻው ዘመን ብዙዎች እርሱን የሚከተሉት ለይስሙላ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:3-5) እንደነዚህ ያሉትን ግለሰቦች “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ!” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 7:23) አሁን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።

ከሐሰት አምልኮ መራቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

11. ከሐሰት አምልኮ ለመራቅ ምን ማድረግ አለብን?

11 እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሐሰት አምልኮም ሆነ ከተሳሳቱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ይርቃሉ። ይህም ሲባል በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን አንከታተልም እንዲሁም ስለ አምላክና ስለ ቃሉ የሐሰት ትምህርቶችን የሚያሰራጩ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን አናነብም ማለት ነው። (መዝሙር 119:37) ከዚህም በላይ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር የተያያዘ ማንኛውም ድርጅት ባዘጋጃቸው ማኀበራዊ ግብዣዎችም ሆነ መዝናኛዎች ላይ አንገኝም። እንዲሁም የሐሰት አምልኮን በምንም መልኩ አንደግፍም። (1 ቆሮንቶስ 10:21) እንደዚህ ያሉ እርምጃዎችን መውሰዳችን “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ” እንዳይወስደን ይጠብቀናል።—ቈላስይስ 2:8

12. አንድ ሰው ከሐሰት ሃይማኖታዊ ድርጅት ጋር ያለውን ግንኙነት ማቋረጥ የሚችለው እንዴት ነው?

12 የይሖዋ ምሥክር መሆን የሚፈልግ ግለሰብ በአንድ የሐሰት ሃይማኖታዊ ድርጅት ውስጥ በአባልነት የተመዘገበ ከሆነስ? አብዛኛውን ጊዜ ግለሰቡ ከድርጅቱ መውጣቱን የሚገልጽ ደብዳቤ መላኩ የሐሰት ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል ሆኖ መቆጠር እንደማይፈልግ የሚያሳይ ማስረጃ ይሆናል። ግለሰቡ በምንም ዓይነት መልኩ በሐሰት አምልኮ ላለመበከል ወሳኝ እርምጃ መውሰዱ በጣም አስፈላጊ ነው። የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የሚፈልገው ሰው ቀድሞ ከነበረበት ሃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ለድርጅቱም ሆነ ለሌሎች ሰዎች በድርጊቱ ግልጽ ማድረግ አለበት።

13. መጽሐፍ ቅዱስ ከሐሰት አምልኮ የመራቅን አስፈላጊነት አስመልክቶ ምን ምክር ሰጥቷል?

13 ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ኀብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን ስምምነት አለው? የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ኀብረት አለው? የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋር ምን ስምምነት አለው? . . . ‘ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡ፤ ለእኔም የተለያችሁ ሁኑ፤ ይላል ጌታ። ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ።’” (2 ቆሮንቶስ 6:14-17) ከሐሰት አምልኮ በመራቅ ይህንን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን። ጳውሎስ የሰጠው ምክር የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ከሆኑ ሰዎችም መራቅ እንዳለብን የሚያሳይ ነው?

“በጥበብ ተመላለሱ”

14. በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ፈጽሞ ልንርቃቸው ይገባል? አብራራ።

14 እውነተኛ አምላኪዎች የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ከሆኑ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው አይገባም ማለት ነው? ከእኛ የተለየ እምነት ካላቸው ሰዎች ፈጽመን መራቅ ይኖርብናል? በጭራሽ። ከታላላቆቹ ትእዛዛት ሁለተኛው “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” ይላል። (ማቴዎስ 22:39) ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የምሥራች ስንነግራቸው እንደምንወዳቸው እያሳየን ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናትና ከሐሰት አምልኮ የመራቅን አስፈላጊነት በማስገንዘብ ፍቅር እናሳያቸዋለን።

15. ‘ከዓለም አይደለንም’ ሲባል ምን ማለት ነው?

15 ምሥራቹን ለሰዎች ብንሰብክም የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ‘ከዓለም አይደለንም።’ (ዮሐንስ 15:19) እዚህ ላይ የተሠራበት “ዓለም” የሚለው ቃል ከአምላክ የራቀውን የሰው ዘር ኅብረተሰብ ያመለክታል። (ኤፌሶን 4:17-19፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ይሖዋን ከሚያሳዝን ዝንባሌ፣ አነጋገርና አኗኗር ስለምንርቅ ከዓለም የተለየን ነን። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ከዚህም በላይ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” የሚለውን መመሪያ በመከተል ከክርስትና የአቋም መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ከማይኖሩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት አንመሠርትም። (1 ቆሮንቶስ 15:33) የዓለም ክፍል አለመሆን “ከዓለም ርኲሰት ራስን መጠበቅ” ማለት ነው። (ያዕቆብ 1:27) ስለዚህ የዓለም ክፍል አይደለንም ሲባል ከሌሎች ሰዎች እንርቃለን ማለት አይደለም።—ዮሐንስ 17:15, 16፤ 1 ቆሮንቶስ 5:9, 10

16, 17. ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የማያውቁ ሰዎችን እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?

16 እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች የማያውቁ ሰዎችን እንዴት ልንይዛቸው ይገባል? ጳውሎስ በቈላስይስ ለነበረው ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በውጭ ካሉት ሰዎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ ተመላለሱ፤ በተገኘውም ዕድል ሁሉ ተጠቀሙ። ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን።” (ቈላስይስ 4:5, 6) ሐዋርያው ጴጥሮስም “ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:15) ጳውሎስ “በማንም ላይ ክፉ እንዳይናገሩ፣ ሰላማውያን እንዲሆኑ፣ ለሰዎችም ሁሉ ከልብ የመነጨ ትሕትና እንዲያሳዩ” ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል።—ቲቶ 3:2

17 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ሌሎችን አናንጓጥጥም ወይም ክፉ ቃል አንናገርም። ስለ ሌላ ሃይማኖት አባላት ስንናገር የሚያንቋሽሹ ቃላትን አንጠቀምም። ከዚህ ይልቅ ጎረቤታችን፣ የሥራ ባልደረባችን ወይም በአገልግሎት ላይ ያነጋገርነው ሰው ደግነት የጎደለው ወይም የስድብ ቃል ቢሰነዝርም እንኳ ዘዴኞች እንሆናለን።—ቈላስይስ 4:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24

‘የጤናማውን ትምህርት ምሳሌ ያዙ’

18. ወደ ሐሰት አምልኮ የሚመለሱ ሰዎች ምን አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ ይገጥማቸዋል?

18 አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከተማረ በኋላ ወደ ሐሰት አምልኮ ቢመለስ እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን አሳዛኝ ውጤት ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ እንደ ገና ተጠላልፈው ቢሸነፉ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ ይሆንባቸዋል። . . . ‘ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል’ እንዲሁም ‘ዐሣማ ቢታጠብም ተመልሶ በጭቃ ላይ ይንከባለላል’ የሚለው ምሳሌ እውን ይሆንባቸዋል።”—2 ጴጥሮስ 2:20-22

19. መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ማንኛውንም ነገር በንቃት መከታተል የሚኖርብን ለምንድን ነው?

19 መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ ሊጥል ከሚችል ከማንኛውም ነገር መራቅ ይኖርብናል። ምንጊዜም ቢሆን አደጋ ሊያጋጥመን ስለሚችል ንቁ መሆን አለብን! ሐዋርያው ጳውሎስ “በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች እምነትን ክደው አታላይ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት እንደሚከተሉ መንፈስ በግልጥ ይናገራል” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) የምንኖረው “በኋለኞች ዘመናት” ነው። ከሐሰት አምልኮ የማይርቁ ሰዎች ‘በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዱ፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ ይንገዋለላሉ።’—ኤፌሶን 4:13, 14

20. የሐሰት ሃይማኖት ከሚያስከትለው ጎጂ ተጽዕኖ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

20 የሐሰት ሃይማኖት ከሚያስከትለው ጎጂ ተጽዕኖ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሰጠንን ነገሮች እንመልከት። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በተጨማሪም ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብም ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) በእውነት ውስጥ እያደግን ስንሄድ ‘ለበሰሉ ሰዎች የሚሆነውን ጠንካራ ምግብ’ መልመድ እንዲሁም መንፈሳዊ እውነቶችን ወደምንማርባቸው ስብሰባዎች መምጣት አይኖርብንም? (ዕብራውያን 5:13, 14፤ መዝሙር 26:8) የሰማነውን ‘የጤናማውን ትምህርት ምሳሌ መያዝ እንድንችል’ ይሖዋ ባቀረበልን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) እንዲህ ካደረግን ከሐሰት አምልኮ መራቅ እንችላለን።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• “ታላቂቱ ባቢሎን” ማን ናት?

• ከሐሰት ሃይማኖት ለመራቅ ምን ማድረግ አለብን?

• በመንፈሳዊነታችን ላይ አደጋ ሊያስከትሉ ከሚችሉት ከየትኞቹ ሁኔታዎች መራቅ አለብን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ታላቂቱ ባቢሎን” ሥነ ምግባር በጎደላት ሴት የተመሰለችው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ታላቂቱ ባቢሎን” ጥፋት ተበይኖባታል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከእኛ የተለየ እምነት ላላቸው ሰዎች ‘ትሕትናና አክብሮት’ እናሳያለን