የኢዮብ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የኢዮብ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
ኢዮብ የኖረው አሁን አረቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በዖፅ ምድር ነው። በዚያ ዘመን ብዙ ቁጥር ያላቸው እስራኤላውያን በግብጽ ይኖሩ ነበር። ኢዮብ ምንም እንኳ እስራኤላዊ ባይሆንም ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ነበር። እርሱን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔር የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም” በማለት ይናገራል። (ኢዮብ 1:8) ኢዮብ የኖረው ሁለቱ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ማለትም የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍና ነቢዩ ሙሴ በኖሩበት ዘመን መካከል መሆን አለበት።
የኢዮብን መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ እንደሆነ ይገመታል፤ ሙሴ የኢዮብን ታሪክ የሰማው ለዖፅ ምድር ቅርብ በነበረችው በምድያም ለ40 ዓመታት ያህል በተቀመጠበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። በተጨማሪም ሙሴ፣ ኢዮብ በመጨረሻዎቹ ዓመታት ስላጋጠመው ሁኔታ የሰማው እስራኤላውያን የ40 ዓመቱ የምድረ በዳ ቆይታቸው ሊጠናቀቅ አካባቢ ዖፅ አቅራቢያ በነበሩበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። a የኢዮብ ተሞክሮ ግሩም በሆነ ሁኔታ በጽሑፍ ስለሰፈረ ምርጥ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ተደርጎ ይታያል። ከዚህም በላይ መጽሐፉ ጥሩ ሰዎች ለምን መከራ ይደርስባቸዋል? ይሖዋ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ? ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት ሳያላሉ መኖር ይችላሉ? እንደሚሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። የኢዮብ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ከተጻፉ ጽሑፎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ዛሬም ቢሆን ሕያውና የሚሠራ ነው።—ዕብራውያን 4:12
“የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ”
አንድ ቀን ሰይጣን፣ ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ መሆኑን በተመለከተ ጥያቄ አነሳ። ይሖዋም፣ ሰይጣን ያነሳቸውን ጥያቄዎች በመቀበል በኢዮብ ላይ የተለያዩ መከራዎች እንዲያደርስበት ፈቀደለት። ያም ሆኖ ግን ኢዮብ ‘እግዚአብሔርን አልረገመም።’—ኢዮብ 2:9
የኢዮብ ሦስት ወዳጆች “ሊያስተዛዝኑት” ወደ እርሱ መጡ። (ኢዮብ 2:11) ኢዮብ “የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ” ብሎ ዝምታውን እስከ ሰበረበት ጊዜ ድረስ አንድም ቃል ሳይተነፍሱ አብረውት ቁጭ አሉ። (ኢዮብ 3:3) ኢዮብ “ብርሃንን እንዳለየ ሕፃን” ማለትም ሞቶ እንደተወለደ ሕፃን ለመሆን ተመኝቶ ነበር።—ኢዮብ 3:11, 16
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:4 NW—የኢዮብ ልጆች የልደት በዓልን ያከብሩ ነበር? አያከብሩም። “ቀን” እና “የልደት ቀን” ለማለት የሚሠራባቸው የዕብራይስጥ ቃላት ትርጉማቸው የተለያየ ነው። (ዘፍጥረት 40:20) በኢዮብ 1:4 [NW] ላይ የሚገኘው “ቀን” የሚለው ቃል ከጠዋት እስከ ማታ ያለውን ጊዜ የሚያመለክት ነው። ሰባቱ የኢዮብ ወንዶች ልጆች በዓመት አንድ ጊዜ ለሰባት ቀናት የሚቆይ የቤተሰብ ግብዣ ያደርጉ የነበረ ይመስላል። ሁሉም በዙር ይደርሳቸው ስለነበር እያንዳንዱ ልጅ ‘የእርሱ ቀን’ ሲደርስ ቤቱ ድግስ በማዘጋጀት ሌሎቹን ያስተናግዳል።
1:6፤ 2:1—በይሖዋ ፊት እንዲቆሙ የተፈቀደላቸው እነማን ናቸው? በይሖዋ ፊት ከቆሙት መካከል ቃል የተባለው የአምላክ አንድያ ልጅና ታማኝ መላእክት እንዲሁም ሰይጣን ዲያብሎስን ጨምሮ ዓመጸኛ የሆኑት መላእክታዊ ‘የአምላክ ልጆች’ ይገኙበታል። (ዮሐንስ 1:1, 18) ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ የተጣሉት በ1914 የአምላክ መንግሥት ከተቋቋመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው። (ራእይ 12:1-12) ይሖዋ ሁሉም በእርሱ ፊት እንዲቆሙ በመፍቀድ ሰይጣን ያነሳውን ግድድርና ጥያቄ በሁሉም መንፈሳዊ ፍጡራን ፊት እንዲያቀርብ አደረገው።
1:7፤ 2:2—ይሖዋ ሰይጣንን በቀጥታ አነጋግሮታል? ይሖዋ ከመንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር እንዴት ግንኙነት እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም። ይሁን እንጂ ነቢዩ ሚክያስ መላእክት በቀጥታ ከይሖዋ ጋር ሲነጋገሩ በራእይ ተመልክቷል። (1 ነገሥት 22:14, 19-23) ከዚህ በመነሳት ይሖዋ ሰይጣንን በቀጥታ አነጋግሮታል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይመስላል።
1:21—ኢዮብ ወደ ‘እናቱ ማሕፀን’ (የ1954 ትርጉም) ሊመለስ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ሰውን “ከምድር ዐፈር” ስላበጀው እዚህ ላይ “እናት” የሚለው ቃል የገባው ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ምድርን ለማመልከት ነው።—ዘፍጥረት 2:7
2:9—የኢዮብ ሚስት ባሏን “እግዚአብሔርን ርገምና ሙት” ባለችው ጊዜ በምን ዓይነት ስሜት ውስጥ ነበረች? የኢዮብ ሚስት ባሏ ያጣቸውን ነገሮች በሙሉ አጥታለች። በአንድ ወቅት ጠንካራ የነበረው ባሏ በጣም አስከፊ በሆነ በሽታ ተይዞ ሲማቅቅ ማየቷ በእርሷም ላይ የስሜት ሥቃይ አስከትሎባት መሆን አለበት። ከዚህም በተጨማሪ የምትወዳቸውን ልጆቿን በሞት ተነጥቃለች። ይህ ሁሉ ሲደርስባት እጅግ ከመጨነቋ የተነሳ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ጉዳይ ማለትም ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ዘንግታ ሊሆን ይችላል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:8-11፤ 2:3-5:- ከኢዮብ ሁኔታ እንደታየው አንድ ሰው ታማኝነቱን እንዲጠብቅ ተገቢ የሆነ አነጋገርና ድርጊት ብቻ ሳይሆን ይሖዋን ለማገልገል ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያስፈልገዋል።
1:21, 22:- በአስቸጋሪ ጊዜም ሆነ በደህና ወቅት ለይሖዋ ታማኝ ሆነን በመቀጠል ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማረጋገጥ እንችላለን።—ምሳሌ 27:11
2:9, 10:- ቤተሰቦቻችን መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችንን ባይወዱት አሊያም እምነታችንን እንድንክድ ወይም እንድንተው ቢጫኑን ልክ እንደ ኢዮብ በእምነት ጸንተን መቆም ይገባናል።
2:13:- የኢዮብ ጓደኞች መንፈሳዊነት ስለሚጎድላቸው ስለ አምላክና እርሱ ስለሰጣቸው ተስፋዎች በመግለጽ ሊያጽናናው የሚችል ነገር መናገር አልቻሉም።
“ጨዋነቴን [“ታማኝነቴን፣” NW] እስክሞት ድረስ አልጥልም”
የኢዮብ ሦስት ጓደኞች አነጋገር ኢዮብ አንድ ከባድ የሆነ ኃጢአት በመሥራቱ አምላክ እየቀጣው ነው ብለው እንደሚያስቡ ያሳያል። በመጀመሪያ የተናገረው ኤልፋዝ ሲሆን ቀጥሎ በልዳዶስ አጥንት የሚሰብሩ ቃላትን ይናገር ጀመር። የሶፋር ንግግር ግን ከሁሉም የከፋ ነበር።
ኢዮብ የእነዚህን ሰዎች የተሳሳተ አስተሳሰብ አልተቀበለም። አምላክ መከራ እንዲደርስበት ለምን እንደፈቀደ ባለማወቁ ራሱን ንጹሕ ለማድረግ ይጥር ነበር። ያም ሆኖ ግን ኢዮብ አምላክን ይወድ ስለነበር “ጨዋነቴን [“ታማኝነቴን፣” NW] እስክሞት ድረስ አልጥልም” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 27:5
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
7:1፤ 14:14—ኢዮብ “ብርቱ ተጋድሎ [“የግዳጅ ሥራ፣” NW]” ወይም “ተጋድሎ [“የግዳጅ አገልግሎት፣” NW]” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ኢዮብ ሥቃዩ በጣም የበዛበት ከመሆኑ የተነሳ ሕይወት ከባድና አድካሚ የግዳጅ ሥራ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። (ኢዮብ 10:17 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ትንሣኤ እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ በሲኦል የሚቆየው ወዶ ሳይሆን ግድ ሆኖበት ስለሆነ ኢዮብ ይህን ወቅት ከግዳጅ አገልግሎት ጋር አመሳስሎታል።
7:9, 10፤ 10:21፤ 16:22—እነዚህ ጥቅሶች ኢዮብ በትንሣኤ እንደማያምን ያሳያሉ? እነዚህ ጥቅሶች ኢዮብ በቅርብ የሚያጋጥመውን ሁኔታ አስመልክቶ የተናገራቸው ሐሳቦች ናቸው። ታዲያ ምን ማለቱ ነበር? እንደዚህ ያለው ቢሞት በዘመኑ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳቸውም እንደማያዩት ለማመልከት ሊሆን ይችላል። በእነርሱ አስተሳሰብ እርሱ ወደ ቤቱ በፍጹም አይመለስም አሊያም አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪመጣ ድረስ የሚያውቀው አይኖርም። ወይም ደግሞ ኢዮብ ይህን ሲናገር በራሱ ጥረት ከሲኦል መውጣት የሚችል ሰው የለም ማለቱ ይሆናል። ኢዮብ ወደ ፊት ትንሣኤ እንደሚኖር ያምን እንደነበር ኢዮብ 14:13-15 በግልጽ ያሳያል።
10:10—ይሖዋ ኢዮብን ‘እንደ ወተት ያፈሰሰው እንዲሁም እንደ እርጎ ያረጋው’ እንዴት ነው? ይህ አባባል ኢዮብ በእናቱ ማኅፀን እንዴት እንደተሠራ የሚያሳይ ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
19:20 NW—ኢዮብ “የጥርሴ ቆዳ ብቻ ቀርቶ አመለጥሁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ኢዮብ ቆዳ የሌለውን ነገር ጠቅሶ በዚያ ማምለጡን ሲገልጽ ምናልባትም ምንም ሳይዝ እንዳመለጠ መናገሩ ሊሆን ይችላል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
4:7, 8፤ 8:5, 6፤ 11:13-15:- አንድ ሰው መከራ ቢፈራረቅበት የዘራውን እያጨደ ነው እንዲሁም የአምላክን ሞገስ ቢያጣ ነው ብለን ለመደምደም መቸኮል የለብንም።
4:18, 19፤ 22:2, 3:- የምንሰጠው ምክር በራሳችን አመለካከት ላይ ሳይሆን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
10:1:- ኢዮብን ምሬት ስላሳወረው እየደረሰበት ላለው መከራ ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል ብሎ እንዳያስብ አድርጎታል። ከኢዮብ በተለየ መልኩ መከራ እየደረሰብን ያለው ለምን እንደሆነ ስለምናውቅ ችግር ሲደርስብን ልንመረር አይገባም።
14:7, 13-15፤ 19:25፤ 33:24:- የትንሣኤ ተስፋ ሰይጣን የሚያመጣብንን ማንኛውንም ፈተና በጽናት እንድንወጣው ያስችለናል።
16:5፤ 19:2:- ከአንደበታችን የሚወጡ ቃላት ሌሎችን የሚያበረታቱና የሚያጠናክሩ እንጂ የሚያናድዱ መሆን የለባቸውም።—ምሳሌ 18:21
22:5-7:- ተጨባጭ ማስረጃ በሌለው ውንጀላ ላይ ተመሥርቶ የሚሰጥ ምክር እርባና ቢስ ከመሆኑም በላይ ጎጂ ነው።
27:2፤ 30:20, 21:- ታማኝነትን ለመጠበቅ የግድ ፍጹም መሆን አያስፈልግም። ኢዮብ አምላክን የወቀሰው በስህተት ነው።
27:5:- ታማኝነት አንድ ሰው ለአምላክ ባለው ፍቅር ላይ የተመካ ስለሆነ ኢዮብ እራሱ ታማኝነቱን ካላጓደለ በስተቀር ታማኝ ከመሆን ምንም ሊያግደው አይችልም። እኛም ለይሖዋ እንዲህ ያለ ጠንካራ ፍቅር እንዲኖረን ጥረት እናድርግ።
28:1-28:- የሰው ልጅ ምድር የያዘቻቸው ውድ ሀብቶች የት እንደሚገኙ ያውቃል። ሰው እነዚህን ሀብቶች ለማግኘት ፍለጋ በሚያደርግበት ጊዜ ጥበቡ ከርቀት ማየት የሚችሉ አሞራዎች ማየት ወደማይችሏቸው ከመሬት በታች ወዳሉ ቦታዎች ዘልቆ እንዲገባ ያስችለዋል። አምላካዊ ጥበብ ግን የሚገኘው ይሖዋን ከመፍራት ነው።
29:12-15:- ችግረኛ ለሆኑ ሰዎች ፍቅራዊ ደግነት ልናሳያቸው ይገባናል።
31:1, 9-28:- ኢዮብ ከማሽኮርመምና ከምንዝር፣ ሌሎችን ከመበደልና ከማንገላታት እንዲሁም ከፍቅረ ንዋይና ከጣዖት አምልኮ በመራቅ ረገድ ምሳሌ ትቶልናል።
“በትቢያና በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ”
ኤሊሁ የተባለ ወጣት ኢዮብና ጓደኞቹ ሲከራከሩ አጠገባቸው ሆኖ በትዕግሥት ያዳምጣቸው ነበር። በኋላ ላይ ግን ሐሳቡን በድፍረት መናገር ጀመረ። ኢዮብም ሆነ ኢዮብን በነገር ያቆሰሉት ሦስት ሰዎች ትክክል እንዳልሆኑ ነገራቸው።
ኤሊሁ ሐሳቡን ተናግሮ እንደጨረሰ ይሖዋ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ መልስ ሰጠ። ይሁን እንጂ ኢዮብ ስለደረሰበት ችግር ምንም ዓይነት ማብራሪያ አልሰጠም። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ተከታታይ ጥያቄዎችን በማንሳት ኢዮብ ስለ አስፈሪ ኃይሉና ስለ ታላቅ ጥበቡ እንዲያስተውል አደረገው። ኢዮብም ሳያስተውል እንደተናገረ በማመን እንዲህ አለ:- “ራሴን እንቃለሁ፤ በትቢያና በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ።” (ኢዮብ 42:6) ኢዮብ የሚፈተንበት ጊዜ ሲያበቃ ላሳየው ጽናት ተክሷል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
32:1-3—ኤሊሁ እዚያ ቦታ የደረሰው መቼ ነበር? ኤሊሁ ሁሉንም ንግግሮች መስማት ችሎ ስለነበር ኢዮብ ንግግሩን ጀምሮ ለሰባት ቀን የቆየውን የሦስት ጓደኞቹን ዝምታ ከመስበሩ በፊት የሚሉትን ለመስማት በሚያስችል ቦታ ላይ ተቀምጦ ነበር ማለት ይቻላል።—ኢዮብ 3:1, 2
34:7—ኢዮብ ‘ፌዝን እንደ ውሃ የጠጣን’ ሰው የመሰለው እንዴት ነው? ኢዮብ ተጨንቆ በነበረበት ወቅት ሦስቱ ጓደኞቹ የሚሰነዝሩት ነቀፋ በአምላክ ላይ ሳይሆን በእርሱ ላይ እንዳነጣጠረ ተሰምቶት ነበር። (ኢዮብ 42:7) ስለዚህ ኢዮብ ውኃን ደስ እያለው እንደሚጨልጥ ሰው ፌዝን ይጠጣት ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
32:8, 9:- ጥበብ የሚገኘው በዕድሜ ብቻ አይደለም። የአምላክን ቃል መረዳትና የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልጋል።
34:36:- የአንድ ሰው ታማኝነት የሚረጋገጠው በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ‘እስከ መጨረሻው ከተፈተነ’ ነው።
35:2:- ኤሊሁ መናገር ከመጀመሩ በፊት በጥሞና አዳምጦ ዋናው ጉዳይ ምን እንደሆነ ተረድቷል። (ኢዮብ 10:7፤ 16:7፤ 34:5) የጉባኤ ሽማግሌዎችም ምክር መስጠት ከመጀመራቸው በፊት እውነታውን ለማወቅና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች ለመረዳት በጥሞና ማዳመጥ ይኖርባቸዋል።—ምሳሌ 18:13
37:14፤ 38:1 እስከ 39:30:- የይሖዋ ኃይልና ጥበብ መግለጫ በሆኑት ድንቅ ሥራዎቹ ላይ ማሰላሰል ትሑት እንድንሆን ከማድረጉም ሌላ የእርሱ ሉዓላዊነት ተረጋግጦ ማየት ከእኛ የግል ጥቅም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ እንድናስተውል ይረዳናል።—ማቴዎስ 6:9, 10
40:1-4:- ሁሉን በሚችለው አምላክ ላይ እንድናጉረመርም የሚገፋፋ ስሜት ሲያድርብን ‘እጃችንን በአፋችን ላይ መጫን’ ይኖርብናል።
40:15 እስከ 41:34:- ብሄሞትና (ጉማሬ) ሌዋታን (አዞ) ያላቸው ኃይል እንዴት ታላቅ ነው! እኛም በአምላክ አገልግሎት መጽናት ከፈለግን እነዚህን ኃይለኛ እንስሳት ከፈጠረውና ኃይልን ሊሰጠን ከሚችለው ብርታት ማግኘት እንችላለን።—ፊልጵስዩስ 4:13
42:1-6:- ኢዮብ የይሖዋን ቃል መስማቱና የኃይሉ መግለጫ የሆኑ ነገሮችን እንዲያስታውስ መደረጉ ‘እግዚአብሔርን እንዲያይ’ ወይም ስለ እርሱ እውነቱን እንዲያስተውል አድርጎታል። (ኢዮብ 19:26) ይህም አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ረድቶታል። እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጠን ስሕተታችንን በፍጥነት መቀበልና ማስተካከያዎችን ማድረግ ይኖርብናል።
እንደ ‘ኢዮብ ጽና’
የኢዮብ መጽሐፍ በሰው ልጅ ላይ እየደረሰ ላለው መከራ ተጠያቂው አምላክ ሳይሆን ሰይጣን መሆኑን በግልጽ ያሳያል። አምላክ በምድር ላይ መከራ እንዲኖር መፍቀዱ ከይሖዋ ሉዓላዊነትና ከእኛ ታማኝ መሆን አለመሆን ጋር በተያያዘ በተነሱት ጥያቄዎች ረገድ ምን አቋም እንዳለን ለማሳየት አጋጣሚ ከፍቶልናል።
ልክ እንደ ኢዮብ ይሖዋን የሚወዱ ሁሉ ይፈተናሉ። ስለ ኢዮብ የሚናገረው ይህ ዘገባ መጽናት እንደምንችል ማረጋገጫ ይሰጠናል። ችግሮቻችን ለዘላለም እንደማይቀጥሉ ያስታውሰናል። ያዕቆብ 5:11 “ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል” በማለት ይናገራል። አቋሙን ሳያጎድፍ በመጽናቱ ይሖዋ ባርኮታል። (ኢዮብ 42:10-17) በምድር ላይ በገነት ለዘላለም ለመኖር የሚያስችል እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ከፊት ለፊታችን ተዘርግቶልናል! እኛም እንደ ኢዮብ ፍጹም አቋማችንን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ዕብራውያን 11:6
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የኢዮብ መጽሐፍ ከ1657 እስከ 1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት ያሉትን ከ140 የሚበልጡ ዓመታት ታሪክ ይሸፍናል።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ከኢዮብ ጽናት’ ምን ትምህርት እናገኛለን?