በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሂዱና እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’

‘ሂዱና እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’

‘ሂዱና እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’

“ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።”—ማቴዎስ 28:19, 20

1. እስራኤላውያን በሲና ተራራ ግርጌ ምን ውሳኔ አድርገው ነበር?

 ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት እያንዳንዱ የብሔሩ አባል ለአምላክ ቃል ገባ። በሲና ተራራ ግርጌ የተሰበሰቡት እስራኤላውያን “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው በይፋ ተናገሩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለአምላክ የተወሰኑና በእርሱ ‘የተወደዱ ርስቱ’ ሆኑ። (ዘፀአት 19:5, 8፤ 24:3) በመሆኑም ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸውና እነርሱም ሆኑ ዘሮቻቸው “ማርና ወተት የምታፈሰውን” አገር እንደሚወርሱ ተስፋ ማድረግ ጀመሩ።—ዘሌዋውያን 20:24

2. በዛሬው ጊዜ ሰዎች ከአምላክ ጋር ምን ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ?

2 ይሁን እንጂ መዝሙራዊው አሳፍ እንደገለጸው እስራኤላውያን “የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፤ በሕጉም መሠረት ለመሄድ እንቢ አሉ።” (መዝሙር 78:10) አባቶቻቸው ለይሖዋ የገቡትን ቃል ከመፈጸም ወደኋላ አሉ። ውሎ አድሮም ብሔሩ ከአምላክ ጋር የመሠረተውን ልዩ ወዳጅነት አጣ። (መክብብ 5:4፤ ማቴዎስ 23:37, 38) በዚህ ምክንያት አምላክ “ለእርሱ የሚሆነውን ሕዝብ” ለመውሰድ ትኩረቱን ወደ አሕዛብ አደረገ። (የሐዋርያት ሥራ 15:14) እንዲሁም በዚህ የመጨረሻ ዘመን፣ “ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ” እየሰበሰበ ነው፤ እነዚህ ሰዎች “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣ የአምላካችንና የበጉ” እንደሆነ በደስታ እየገለጹ ነው።—ራእይ 7:9, 10

3. አንድ ሰው ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና ለመመሥረት ከፈለገ ምን እርምጃዎች መውሰድ አለበት?

3 አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ውድ ዝምድና ከመሠረቱት ሰዎች መሃል መሆን ከፈለገ፣ ራሱን ለይሖዋ መወሰን ብሎም ይህን አቋሙን በውኃ በመጠመቅ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይገባዋል። አንድ ሰው ራሱን ሲወስንና ሲጠመቅ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን የሚከተለውን ትእዛዝ እንዳከበረ ያሳያል:- “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) እስራኤላውያን ‘የኪዳኑ መጽሐፍ’ ሲነበብ ያዳምጡ ነበር። (ዘፀአት 24:3, 7, 8) በመሆኑም ይሖዋ ምን እንደሚፈልግባቸው አውቀዋል። ዛሬም በተመሳሳይ አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት፣ በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው የይሖዋ ዓላማ ትክክለኛ እውቀት ማግኘቱ በጣም አስፈላጊ ነው።

4. አንድ ሰው ለጥምቀት ብቁ እንዲሆን ምን ማድረግ አለበት? (ከላይ ያለውን ሣጥን ጨምረህ መልስ።)

4 በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ከመጠመቃቸው በፊት ጠንካራ መሠረት ያለው እምነት እንዲኖራቸው ፈልጎ ነበር። ተከታዮቹ ሄደው ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ብቻ ሳይሆን ‘ያዘዘውንም ሁሉ እንዲጠብቁ’ እንዲያስተምሯቸው ጭምር መመሪያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 7:24, 25፤ ኤፌሶን 3:17-19) ብዙውን ጊዜ ለመጠመቅ ብቁ የሚሆኑት ለበርካታ ወራት አልፎ ተርፎም ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ ሰዎች ናቸው፤ ይህም ውሳኔያቸው የችኮላ ወይም በበቂ እውቀት ያልተደገፈ እንዳይሆን ይረዳል። የጥምቀት እጩዎች በሚጠመቁበት ዕለትም እንኳን ለሁለት ቁልፍ ጥያቄዎች ‘አዎን’ የሚል መልስ ይሰጣሉ። ኢየሱስ ‘ቃላችን አዎን ከሆነ አዎን፣ አይደለም ከሆነ አይደለም’ መሆን እንዳለበት አጥብቆ ስላሳሰበን ሁላችንም ሁለቱ የጥምቀት ጥያቄዎች የያዙትን ቁም ነገር እንደገና በጥንቃቄ ማጤናችን ጠቃሚ ነው።—ማቴዎስ 5:37

ንስሐ መግባትና ራስን መወሰን

5. የመጀመሪያው የጥምቀት ጥያቄ የትኞቹን ሁለት ወሳኝ እርምጃዎች ያጎላል?

5 የመጀመሪያው የጥምቀት ጥያቄ፣ እጩ ተጠማቂው ስለ ቀድሞው አኗኗሩ ንስሐ ገብቶና የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ወስኖ እንደሆነ ይጠይቃል። ይህ ጥያቄ ከጥምቀት በፊት በቅደም ተከተል ሊወሰዱ የሚገባቸውን ሁለት ወሳኝ እርምጃዎች ያጎላል፤ እነርሱም ንስሐ መግባትና ራስን መወሰን ናቸው።

6, 7. (ሀ) የጥምቀት እጩዎች ሁሉ ንስሐ መግባት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው ንስሐ ከገባ በኋላ ምን ዓይነት ለውጦች ማድረግ ይገባዋል?

6 አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት ንስሐ መግባት ያለበት ለምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን . . . እንኖር ነበር” በማለት ገልጿል። (ኤፌሶን 2:3) የአምላክን ፈቃድ በትክክል ከማወቃችን በፊት ከዓለም ጋር ተስማምተን ማለትም በዓለም መመሪያዎችና የአቋም ደረጃዎች መሠረት እንኖር ነበር። አኗኗራችን የዚህ ዓለም አምላክ በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:4) የአምላክን ፈቃድ ካወቅን በኋላ ግን “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት” ላለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።—1 ጴጥሮስ 4:2

7 እንዲህ ያለው አዲስ አኗኗር በርካታ ጥቅሞች ያስገኛል። ከሁሉም በላይ ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችል መንገድ ይከፍታል። ዳዊት ይህንን ሁኔታ በአምላክ “ድንኳን” እና ‘በተቀደሰ ኮረብታው’ ለማደር ከመጋበዝ ጋር አመሳስሎታል፤ ይህ በእርግጥም ታላቅ መብት ነው። (መዝሙር 15:1) ይሖዋ የሚጋብዘው እንዲያው ማንንም ሰው ሳይሆን ‘አካሄዳቸው ንጹሕ የሆነውን፣ ጽድቅን የሚያደርጉትንና ከልባቸው እውነትን የሚናገሩትን’ ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው። (መዝሙር 15:2) በዚህ ጥቅስ ላይ ያለውን ብቃት ማሟላት ሲባል እውነትን ከመማራችን በፊት እንደነበርንበት ሁኔታ በምግባርም ሆነ በባሕርይ ረገድ የተለያዩ ለውጦችን ማድረግ ማለት ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ቈላስይስ 3:5-10) እንዲህ ያለውን ለውጥ ለማድረግ የሚገፋፋን ንስሐ መግባታችን ማለትም ስለ በፊቱ አኗኗራችን ከልብ መጸጸታችንና ይሖዋን ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን ነው። ይህም ራስ ወዳድነትና ዓለማዊ አኗኗር ከሚንጸባረቅበት አካሄድ ሙሉ በሙሉ ተመልሰን አምላክን የሚያስደስት ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል።—የሐዋርያት ሥራ 3:19

8. ራሳችንን የምንወስነው እንዴት ነው? ራስን መወሰን ከጥምቀት ጋር ምን ግንኙነት አለው?

8 ለጥምቀት እጩዎች የሚቀርበው የመጀመሪያው ጥያቄ ሁለተኛ ክፍል፣ እጩዎቹ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሳቸውን ወስነው እንደሆነ የሚጠይቅ ነው። ራስን መወሰን ከጥምቀት በፊት መወሰድ ያለበት በጣም አስፈላጊ እርምጃ ነው። ራሳችንን የምንወስነው፣ ሕይወታችንን በክርስቶስ በኩል ለይሖዋ የመስጠት ልባዊ ፍላጎት እንዳለን በጸሎት በመግለጽ ነው። (ሮሜ 14:7, 8፤ 2 ቆሮንቶስ 5:15) በዚህ ጊዜ ይሖዋ ጌታችን ይሆናል፣ እኛም ንብረቱ እንሆናለን፤ እንደ ኢየሱስም ፈቃዱን በመፈጸም እንደሰታለን። (መዝሙር 40:8፤ ኤፌሶን 6:6) ለይሖዋ እንዲህ ያለውን ትልቅ ትርጉም ያዘለ ቃል መግባት የምንችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ራስን መወሰን ማንም ሳያውቅ በግላችን ለይሖዋ የምንገባው ቃል ነው፤ በመሆኑም በምንጠመቅበት ቀን በሕዝብ ፊት የምንገባው ቃል፣ በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ራሳችንን በመወሰን ትልቅ ትርጉም ያለው እርምጃ መውሰዳችንን ይፋ የሚያደርግ ነው።—ሮሜ 10:10

9, 10. (ሀ) የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ምንን ይጨምራል? (ለ) የናዚ ባለ ሥልጣኖች እንኳን ራሳችንን ስለ መወሰናችን ምን የተረዱት ነገር ነበር?

9 የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ የኢየሱስን ፈለግ መከተል ምንን ይጨምራል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 16:24) ኢየሱስ ልናደርጋቸው የሚገቡንን ሦስት ነገሮች እዚህ ጥቅስ ላይ አመልክቷል። በመጀመሪያ ራሳችንን ‘እንክዳለን።’ በሌላ አነጋገር ራስ ወዳድና ኃጢአተኛ ለሆነው ዝንባሌያችን ፊት አንሰጥም፤ በተቃራኒው የአምላክን ምክርና መመሪያ እንታዘዛለን። ሁለተኛ፣ ‘መስቀላችንን’ ወይም የመከራችንን እንጨት እንሸከማለን። በኢየሱስ ዘመን የመከራ እንጨት የውርደትና የሥቃይ ምልክት ነበር። ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ለምሥራቹ ስንል አንዳንድ ጊዜ ችግር ሊደርስብን እንደሚችል አምነን እንቀበላለን። (2 ጢሞቴዎስ 1:8) ዓለም ቢያፌዝብንና ቢነቅፈን እንኳን፣ አምላክን እያስደሰትን እንዳለን በማወቃችን ምክንያት የምናገኘው ደስታ ልክ እንደ ክርስቶስ የሚደርስብንን ‘ውርደት ንቀን’ እንድናልፍ ያስችለናል። (ዕብራውያን 12:2) በመጨረሻም፣ ኢየሱስን ሁልጊዜ እንከተላለን።—መዝሙር 73:26፤ 119:44፤ 145:2

10 ደስ የሚለው ነገር አንዳንድ ተቃዋሚዎች ሳይቀሩ የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑት እርሱን ሙሉ በሙሉ ለማገልገል እንደሆነ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ ያህል ቡከንዋልድ በሚባለው የናዚ ጀርመኖች ማጎሪያ ካምፕ ታስረው የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን ለመካድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት የሚከተለውን ሐሳብ በያዘ ወረቀት ላይ እንዲፈርሙ ይጠየቁ ነበር:- “አሁንም ቢሆን ራሴን የወሰንኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ነኝ፤ ለይሖዋ የገባሁትን ቃል በፍጹም አላጥፍም።” ይህ ጽሑፍ የሁሉንም ራሳቸውን የወሰኑ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አስተሳሰብ በሚገባ ይገልጻል!—የሐዋርያት ሥራ 5:32

እንደ አንድ የይሖዋ ምሥክር መቆጠር

11. የተጠመቀ ሰው ምን መብት ያገኛል?

11 ለእጩ ተጠማቂው የሚቀርብለት ሁለተኛ ጥያቄ፣ ግለሰቡ መጠመቁ እንደ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንደሚያስቆጥረው የተገነዘበ መሆኑን ይጠይቃል። ከጥምቀቱ በኋላ የይሖዋን ስም የሚሸከም የተሾመ አገልጋይ ይሆናል። ይህ ታላቅ መብት ቢሆንም ከባድ ኃላፊነትም ያስከትላል። እንዲሁም የተጠመቀው ሰው ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ከቀጠለ ለዘላለም የመዳን ተስፋ ይኖረዋል።—ማቴዎስ 24:13

12. የይሖዋን ስም የመሸከም መብት ምን ግዴታ ያስከትላል?

12 ሁሉን ቻይ የሆነውን የይሖዋ አምላክን ስም መሸከም ልዩ መብት እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። ነቢዩ ሚክያስ እንዲህ ብሏል:- “አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።” (ሚክያስ 4:5) ሆኖም ይህ መብት ግዴታም ያስከትላል። ለተሸከምነው ስም ክብር በሚያመጣ መንገድ ሕይወታችንን ለመምራት ጥረት ማድረግ አለብን። ጳውሎስ በሮም የነበሩ ክርስቲያኖችን እንዳሳሰበው፣ አንድ ሰው የሚሰብከውን ነገር በሥራ ካላዋለ የአምላክ ስም “ይሰደባል” ወይም በመልካም አይነሳም።—ሮሜ 2:21-24

13. ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ስለ አምላካቸው የመመሥከር ኃላፊነት ያለባቸው ለምንድን ነው?

13 አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ሲሆን ስለ አምላኩ የመመሥከር ኃላፊነትንም ይቀበላል። ይሖዋ ለእርሱ የተወሰነው የእስራኤል ብሔር ስለ ዘላለማዊ አምላክነቱ የሚናገርለት ምሥክር እንዲሆን ጋብዞት ነበር። (ኢሳይያስ 43:10-12, 21) ብሔሩ ግን ይህንን ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ የኋላ ኋላ የይሖዋን ሞገስ ሙሉ በሙሉ አጣ። በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ ይሖዋ የመመሥከር መብት ማግኘታቸውን እንደ ትልቅ ክብር ያዩታል። ስለ ስሙ የምንመሠክረው እርሱን ስለምንወደውና ስሙ እንዲቀደስ ስለምንፈልግ ነው። በሰማይ ስላለው አባታችን እውነቱን ካወቅንና የእርሱን ዓላማ ከተማርን በኋላ እንዴት ዝም ማለት እንችላለን? እኛም “የምሰብከው ግዴታዬ ስለሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ” እንዳለው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት አለን።—1 ቆሮንቶስ 9:16

14, 15. (ሀ) የይሖዋ ድርጅት እኛ መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ምን ሚና ይጫወታል? (ለ) እኛን በመንፈሳዊ ለመርዳት ምን ዝግጅቶች ተደርገዋል?

14 ለጥምቀት እጩዎች የሚቀርበው ሁለተኛ ጥያቄ፣ ተጠማቂው ይሖዋ በመንፈሱ ከሚመራው ድርጅት ጋር ተባብሮ የመሥራት ኃላፊነት እንዳለበት ጭምር ያሳስባል። ይሖዋን ብቻችንን ሆነን ማገልገል ስለማንችል ‘የመላው የወንድማማቾች ማኅበር’ እርዳታ፣ ድጋፍና ማበረታቻ ያስፈልገናል። (1 ጴጥሮስ 2:17 NW፤ 1 ቆሮንቶስ 12:12, 13) የአምላክ ድርጅት መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህ ድርጅት ትክክለኛ እውቀት እያዳበርን እንድንሄድ፣ ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ጥበብ ያለበት እርምጃ እንድንወስድና ከአምላክ ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ የሚረዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በገፍ ያቀርብልናል። አንዲት እናት ልጅዋን በሚገባ ለመመገብና ለመንከባከብ ጥረት እንደምታደርግ ሁሉ “ታማኝና ልባም ባሪያ” መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ አትረፍርፎ ያቀርብልናል።—ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም፤ 1 ተሰሎንቄ 2:7, 8

15 በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ፣ የይሖዋ ሕዝቦች የእርሱ ታማኝ ምሥክሮች እንዲሆኑ የሚረዳቸውን ማሠልጠኛና ማበረታቻ ያገኛሉ። (ዕብራውያን 10:24, 25) በሕዝብ ፊት እንዴት ንግግር ማቅረብ እንደሚቻል በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንማራለን፤ በአገልግሎት ስብሰባ ደግሞ መልእክታችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የሚረዳ ሥልጠና እናገኛለን። በስብሰባዎች ወቅትም ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በግል በምናጠናበት ጊዜ የይሖዋ መንፈስ እየሠራና ድርጅቱን እየመራ እንዳለ ማስተዋል እንችላለን። እንዲህ ባሉት ቋሚ ዝግጅቶች አማካኝነት አምላክ ከአደጋዎች እንድንጠበቅ ያስጠነቅቀናል፣ ውጤታማ ምሥክርነት መስጠት እንድንችል ያሠለጥነናል እንዲሁም በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንኖር ይረዳናል።—መዝሙር 19:7, 8, 11፤ 1 ተሰሎንቄ 5:6, 11፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:13

ለመጠመቅ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

16. ራሳችንን ለይሖዋ እንድንወስን የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

16 ሁለቱ የጥምቀት ጥያቄዎች፣ የውኃ ጥምቀት ትልቅ ትርጉም እንዳለውና ኃላፊነት እንደሚያስከትል እጩዎቹን ያስታውሷቸዋል። ታዲያ ለመጠመቅ እንዲወስኑ የሚያነሳሳቸው ምን መሆን አለበት? የተጠመቅን ደቀ መዛሙርት የምንሆነው ሌላ ሰው ግድ ስላለን ሳይሆን ይሖዋ ‘ስለሳበን’ ነው። (ዮሐንስ 6:44) ‘እግዚአብሔር ፍቅር በመሆኑ’ ጽንፈ ዓለምን የሚገዛው በግድ ሳይሆን በፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) የይሖዋ ግሩም ባሕርያትና እኛን የሚይዝበት መንገድ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይገፋፋናል። አንድያ ልጁን ለእኛ ከመስጠቱም በላይ በጣም ጥሩ የወደፊት ተስፋ ዘርግቶልናል። (ዮሐንስ 3:16) እኛም በአጸፋው ራሳችንን ለእርሱ በመወሰን ሕይወታችንን ሰጥተነዋል።—ምሳሌ 3:9፤ 2 ቆሮንቶስ 5:14, 15

17. ራሳችንን የወሰንነው ለምን ነገር አይደለም?

17 ራሳችንን የወሰንነው ለአንድ ጽንሰ ሐሳብ ወይም ለአንድ ሥራ ሳይሆን ለይሖዋ ለራሱ ነው። አምላክ ለሕዝቡ የሚሰጠው ሥራ የተለያየ ሊሆን ቢችልም ሕዝቡ ራሱን ለይሖዋ የወሰነ መሆኑ መቼም ቢሆን አይቀየርም። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃምና ኤርምያስ እንዲያደርጉ የታዘዟቸው ነገሮች በጣም የተለያዩ ናቸው። (ዘፍጥረት 13:17, 18፤ ኤርምያስ 1:6, 7) ሆኖም ሁለቱም ይሖዋን ይወዱና ፈቃዱንም በታማኝነት ለመፈጸም ይፈልጉ ስለነበር አምላክ የሰጣቸውን ሥራ አከናውነዋል። በዚህ የመጨረሻ ዘመን የሚገኙ የተጠመቁ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ፣ ክርስቶስ የመንግሥቱን ምሥራች ስለመስበክና ደቀ መዛሙርት ስለማድረግ የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም ጥረት ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ይህንን ሥራ በሙሉ ልብ መፈጸማችን በሰማይ ላለው አባታችን ያለንን ፍቅርና ከልብ ራሳችንን ለእርሱ መወሰናችንን ማሳየት የምንችልበት ጥሩ መንገድ ነው።—1 ዮሐንስ 5:3

18, 19. (ሀ) ስንጠመቅ በሕዝብ ፊት ምን ብለን የተናገርን ያህል ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን ይብራራል?

18 ጥምቀት ብዙ በረከቶች የምናገኝበትን መንገድ እንደሚከፍትልን ምንም አያጠራጥርም፤ ሆኖም አቅልለን የምንመለከተው እርምጃ አይደለም። (ሉቃስ 14:26-33) ከሌላ ከማንኛውም ኃላፊነት የበለጠ ቦታ ሊሰጠው ለሚገባው ነገር ቆራጥ አቋም መያዝን ያሳያል። (ሉቃስ 9:62) በምንጠመቅበት ጊዜ “ይህ አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችን ነውና፤ እስከ መጨረሻው የሚመራንም እርሱ ነው” ብለን በሕዝብ ፊት የተናገርን ያህል ነው።—መዝሙር 48:14

19 የሚቀጥለው ርዕስ ከውኃ ጥምቀት ጋር በተያያዘ ሊነሱ የሚችሉ ሌሎች ጥያቄዎችን ያብራራል። አንድ ሰው ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲል የሚያደርጉት በቂ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ? ዕድሜስ የሚያመጣው ለውጥ አለ? የጥምቀት ሥርዓቱ ክብር እንዲኖረው በዚያ የተገኙ ሁሉ አስተዋጽዖ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

ልታብራራ ትችላለህ?

• እያንዳንዱ ክርስቲያን ከመጠመቁ በፊት ንስሐ መግባት ያለበት ለምንድን ነው?

• ራስን ለአምላክ መወሰን ምንን ይጨምራል?

• የይሖዋን ስም የመሸከም መብት ማግኘት ምን ኃላፊነቶች ያስከትላል?

• ለመጠመቅ እንድንወስን የሚያነሳሳን ምን መሆን አለበት?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ለጥምቀት ዕጩዎች የሚቀርቡት ሁለቱ ጥያቄዎች

በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት በማመን ከኃጢአታችሁ ንስሐ ገብታችሁ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችሁን ወስናችኋል?

ራሳችሁን ለአምላክ መወሰናችሁና መጠመቃችሁ በአምላክ መንፈስ በሚመራው ድርጅት ውስጥ ከታቀፉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ እንደሚያስቆጥራችሁ ተገንዝባችኋል?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስን መወሰን በጸሎት አማካኝነት ለይሖዋ የሚገባ ከባድ ቃለ መሐላ ነው

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስብከቱ ሥራችን ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን ያሳያል