በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመጠመቅ የሚያስችለውን ብቃት ማሟላት

ለመጠመቅ የሚያስችለውን ብቃት ማሟላት

ለመጠመቅ የሚያስችለውን ብቃት ማሟላት

“እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?”—የሐዋርያት ሥራ 8:36

1, 2. ፊልጶስ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን ጋር ውይይት የጀመረው እንዴት ነው? ይህ ሰው መንፈሳዊ ዝንባሌ እንደነበረው የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?

 ኢየሱስ ከሞተ አንድ ወይም ሁለት ዓመት ገደማ በኋላ አንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣን፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እየተጓዘ ነበር። ከፊቱ ወደ 1,500 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርቀት ያለው አድካሚ የሰረገላ ጉዞ ይጠብቀዋል። ይህ መንፈሳዊ ሰው ከኢትዮጵያ ተነስቶ ኢየሩሳሌም ድረስ የሄደው ለይሖዋ አምልኮ ለማቅረብ ነበር። በረጅሙ የመልስ ጉዞው ወቅት ጊዜውን በጥበብ ለመጠቀም አስቦ የአምላክን ቃል እያነበበ ነበር፤ ይህ ሁኔታ፣ ኢትዮጵያዊው የእምነት ሰው እንደነበረ ይጠቁማል። ይሖዋ ይህንን ልበ ቀና ሰው በመመልከት ፊልጶስ ሄዶ እንዲሰብክለት አንድ መልአክ ልኮ ነገረው።—የሐዋርያት ሥራ 8:26-28

2 ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን በዚያን ዘመን ልማድ መሠረት ድምፁን ከፍ አድርጎ ያነብብ ስለነበር ፊልጶስ ውይይት ለመጀመር አልከበደውም። እንዲሁም ባለ ሥልጣኑ እያነበበ ያለው ከኢሳይያስ ጥቅልል ላይ እንደነበረ መስማት ችሏል። “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” በማለት ፊልጶስ ያቀረበው ቀላል ጥያቄ የሰውየውን ፍላጎት ቀሰቀሰ። በዚህ መልኩ በኢሳይያስ 53:7, 8 ላይ ተመርኩዘው ውይይት ጀመሩ። በመጨረሻም ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው “ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሰበከለት።”—የሐዋርያት ሥራ 8:29-35

3, 4. (ሀ) ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ወዲያው ያጠመቀው ለምንድን ነው? (ለ) አሁን የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ኢትዮጵያዊው፣ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ምን ሚና እንደሚጫወትና የተጠመቀ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆንን አስፈላጊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገነዘበ። ባለ ሥልጣኑ በአቅራቢያቸው ውኃ በተመለከተ ጊዜ “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” ሲል ፊልጶስን ጠየቀው። በእርግጥ የዚህ ሰው ሁኔታ ለየት ይላል። ይህ ኢትዮጵያዊ ቀደሞውንም ቢሆን ወደ ይሁዲነት በመለወጥ በታማኝነት አምላክን ያመልክ የነበረ የእምነት ሰው ነው። እንዲሁም ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ቶሎ ለመጠመቅ አጋጣሚ ላያገኝ ይችላል። ከሁሉም በላይ አምላክ ምን እንደሚጠብቅበት ስለተገነዘበ በሙሉ ልቡ ምላሽ መስጠት ፈልጎ ነበር። ፊልጶስም በጥያቄው በደስታ ተስማማ፤ ኢትዮጵያዊው ከተጠመቀ በኋላ ‘ደስ እያለው ጉዞውን ቀጠለ።’ አገሩ ከገባ በኋላም በቅንዓት ምሥራቹን ይሰብክ እንደነበረ አያጠራጥርም።—የሐዋርያት ሥራ 8:36-39

4 በእርግጥ ራስን መወሰንና መጠመቅ በችኮላ ወይም በሚገባ ሳይታሰብባቸው የሚወሰዱ እርምጃዎች ባይሆኑም፣ ግለሰቦች የአምላክን ቃል እውነት ከሰሙ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ የተጠመቁባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ የኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን ምሳሌ ያሳያል። a ስለዚህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመሩ ተገቢ ነው:- አንድ ሰው ለመጠመቅ ምን ዝግጅት ማድረግ አለበት? ጥምቀት የዕድሜ ገደብ አለው? አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት ምን ዓይነት መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አለበት? ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ ይህንን እርምጃ እንዲወስዱ የሚጠብቅባቸው ለምንድን ነው?

ትልቅ ትርጉም ያለው ስምምነት

5, 6. (ሀ) ባለፉት ዘመናት የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ለይሖዋ ፍቅር ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው? (ለ) ከተጠመቅን በኋላ ከአምላክ ጋር ምን ዓይነት የቅርብ ወዳጅነት ሊኖረን ይችላል?

5 ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ነጻ ካወጣቸው በኋላ ‘የተወደደ ርስቱ’ አድርጎ ሊቀበላቸው፣ ሊወዳቸው፣ ሊጠብቃቸው፣ ሊንከባከባቸውና “የተቀደሰ ሕዝብ” ሊያደርጋቸው ፈቃደኛ ሆኖ ነበር። ነገር ግን እንዲህ ያለውን በረከት ለማግኘት ለይሖዋ ፍቅር ተጨባጭ ምላሽ መስጠት ነበረባቸው። እንዲህ ያደረጉት ‘ይሖዋ ያለውን ሁሉ’ ለመተግበር በመስማማትና ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመጋባት ነው። (ዘፀአት 19:4-9) ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ተከታዮቹ ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ አዝዟቸው ነበር፤ ትምህርቱን የተቀበሉትም ተጠምቀዋል። ሰዎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረታቸው የተመካው በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በመጠመቃቸው ላይ ነበር።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ የሐዋርያት ሥራ 2:38, 41

6 ይሖዋ እርሱን ለማገልገል ትልቅ ትርጉም ያለው ቃል የሚገቡትንና ቃላቸውን የሚጠብቁትን ሰዎች እንደሚባርክ እነዚህ የቅዱሳን ጽሑፎች ዘገባዎች ያሳያሉ። ራስን መወሰንና መጠመቅ ክርስቲያኖች የይሖዋን በረከት ለማግኘት የሚያስችሏቸው ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው። እኛም የእርሱን መንገዶች ለመከተልና መመሪያውን ለማግኘት ቆርጠናል። (መዝሙር 48:14) ይሖዋም በምላሹ በምሳሌያዊ አነጋገር እጃችንን ይዞ ልንጓዝበት በሚገባን መንገድ ይመራናል።—መዝሙር 73:23፤ ኢሳይያስ 30:21፤ 41:10, 13

7. ራስን መወሰንና መጠመቅ የግል ውሳኔ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

7 እነዚህን እርምጃዎች እንድንወስድ የሚገፋፋን ለይሖዋ ያለን ፍቅርና እርሱን ለማገልገል ያለን ምኞት መሆን ይኖርበታል። ማንም ቢሆን ለረጅም ጊዜ አጥንተሃል ስለተባለ ወይም ጓደኞቹ ስለተጠመቁ ብቻ መጠመቅ የለበትም። አንድ ሰው ራስን ስለመወሰንና ስለመጠመቅ እንዲያስብ ቤተሰቦቹና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሊያበረታቱት ይችላሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት ሲያዳምጡት የነበሩትን ሰዎች “ተጠመቁ” በማለት አሳስቧቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:38) ሆኖም ራስን መወሰን የግል ጉዳይ በመሆኑ ማንም እንዲህ ሊያደርግልን አይችልም። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ መወሰን ያለብን እኛው ራሳችን ነን።—መዝሙር 40:8

ለጥምቀት በሚገባ መዘጋጀት

8, 9. (ሀ) የሕፃናት ጥምቀት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለው ለምንድን ነው? (ለ) ልጆች ከመጠመቃቸው በፊት ምን መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አለባቸው?

8 ልጆች ማስተዋል ኖሯቸው ራሳቸውን መወሰን ይችላሉ? ቅዱሳን ጽሑፎች ከጥምቀት ጋር በተያያዘ ስለ ዕድሜ የሚገልጹት ነገር የለም። ሆኖም ጨቅላ ሕፃናት አማኝ ሊሆኑ፣ በእምነት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ሊያደርጉ ወይም ራሳቸውን ለአምላክ ሊወስኑ እንደማይችሉ የተረጋገጠ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 8:12) ኦግስተስ ኔአንደር የተባሉ የታሪክ ተመራማሪ ጀነራል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክሪስቺያን ሪሊጅን ኤንድ ቸርች በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “መጀመሪያ ላይ፣ እንዲጠመቁ የሚፈቀድላቸው አዋቂዎች ብቻ ነበሩ፤ ምክንያቱም የጥምቀትን ትርጉምና ከዚህ ጋር የቅርብ ተያያዥነት ያለውን እምነት የሚረዱት ትልልቆች ናቸው።”

9 አንዳንድ ወጣቶች በአንጻራዊ ሁኔታ ገና በልጅነታቸው መንፈሳዊ ቁም ነገሮችን ሲያስተውሉ ሌሎች ደግሞ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ነገር ግን ልጆች ከመጠመቃቸው በፊት እንደ አዋቂዎች ሁሉ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት፣ የቅዱሳን ጽሑፎችን መሠረተ ትምህርቶች በትክክል መረዳትና ራስን መወሰን የሚጨምራቸውን ነገሮች በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።

10. ራስን ከመወሰንና ከመጠመቅ መቅደም ያለባቸው እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?

10 ኢየሱስ፣ ያዘዛቸውን ነገሮች ሁሉ ለአዳዲስ ሰዎች እንዲያስተምሩ ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:20) ስለዚህ አዳዲሶች በመጀመሪያ ትክክለኛውን የእውነት እውቀት ማግኘት አለባቸው፤ ይህም በይሖዋና በቃሉ ላይ እምነት እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። (ሮሜ 10:17፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:4፤ ዕብራውያን 11:6) ከዚያ የሰውየው ልብ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሲነካ ንስሐ ለመግባትና የቀድሞ አኗኗሩን እርግፍ አድርጎ ለመተው ይነሳሳል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) በመጨረሻም ግለሰቡ የሚፈልገው ደረጃ ላይ ይደርሳል፤ ማለትም ኢየሱስ እንዳዘዘው ራሱን ለይሖዋ መወሰንና መጠመቅ ይችላል።

11. ከመጠመቃችን በፊት አዘውትረን በስብከቱ ሥራ መካፈል ያለብን ለምንድን ነው?

11 ወደ ጥምቀት የሚያደርስ እድገት ለማድረግ የሚያስፈልገው ሌላው ነገር ደግሞ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ መካፈል ነው። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ ሕዝቡ በዋነኝነት እንዲሠራው ያዘዘው ይህንን ሥራ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ስለዚህ ያልተጠመቁ የምሥራቹ አስፋፊዎች ለሌሎች ስለ እምነታቸው በመናገር ደስታ ማግኘት ይችላሉ። እንዲሁም ከወዲሁ በዚህ ሥራ መካፈላቸው ከተጠመቁ በኋላ ዘወትር በመስክ አገልግሎት በቅንዓት እንዲሳተፉ ያስታጥቃቸዋል።—ሮሜ 10:9, 10, 14, 15

እንዳትጠመቅ የሚከለክልህ ነገር አለ?

12. አንዳንዶች ከመጠመቅ ወደኋላ የሚሉት ለምን ሊሆን ይችላል?

12 አንዳንዶች ጥምቀት የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ከመጠመቅ ወደኋላ ይሉ ይሆናል። ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር ለመስማማት በሕይወታቸው ላይ ከባድ ለውጥ ማድረግ እንደሚገባቸው ይገነዘባሉ። ወይም ደግሞ ከተጠመቁ በኋላ አምላክ የሚፈልግባቸውን ብቃቶች እያሟሉ መኖር ሊከብዳቸው እንደሚችል ይሰማቸው ይሆናል። አልፎ ተርፎም “ምናልባት አንድ ቀን መጥፎ ነገር ልፈጽምና ከጉባኤ ልወገድ እችላለሁ” የሚል ሰበብ የሚያቀርቡም አሉ።

13. በኢየሱስ ዘመን አንዳንዶች የእርሱ ተከታዮች ከመሆን ወደኋላ እንዲሉ ያደረጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

13 በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የግል ፍላጎቶቻቸውና ከቤተሰባቸው ጋር የነበራቸው የጠበቀ ትስስር የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንዳይሆኑ አግደዋቸው ነበር። አንድ ጸሐፊ ለኢየሱስ፣ እርሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እንደሚከተለው ተናገረ። ኢየሱስ ግን ብዙውን ጊዜ የሚያድርበት ቦታ እንኳን እንደሌለው ገልጸለት። ኢየሱስ ሌላውን አድማጩን ደግሞ እንዲከተለው ሲጋብዘው መጀመሪያ አባቱን ‘መቅበር’ እንደሚፈልግ ገለጸ። ይህ ሰው ኢየሱስን ከመከተልና አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ቤተሰቡን ከመርዳት ይልቅ አባቱ እስኪሞት ድረስ ቤቱ መቆየት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። የመጨረሻውና ሦስተኛው ሰው ደግሞ ኢየሱስን ከመከተሉ በፊት ቤተሰቡን ‘መሰናበት’ እንደሚፈልግ ተናገረ። ኢየሱስ በእንዲህ ዓይነት ሰበቦች እርምጃ ከመውሰድ መዘግየትን ‘ወደ ኋላ ከመመልከት’ ጋር አመሳስሎታል። እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ የሚሉ ሰዎች ክርስቲያናዊ ኃላፊነታቸውን ላለመወጣት ሁልጊዜም ሰበብ የማያጡ ይመስላል።—ሉቃስ 9:57-62

14. (ሀ) ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ሰዎችን አጥማጆች እንዲሆኑ ኢየሱስ በጋበዛቸው ጊዜ መልስ የሰጡት እንዴት ነበር? (ለ) የኢየሱስን ቀንበር ከመሸከም ማመንታት የሌለብን ለምንድን ነው?

14 የጴጥሮስ፣ የእንድርያስ፣ የያዕቆብና የዮሐንስ አቋም ግን ፈጽሞ የተለየ ነበር። ኢየሱስ እንዲከተሉትና ሰዎችን እንዲያጠምዱ በጋበዛቸው ጊዜ ምን እንደተከሰተ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት” ይላል። (ማቴዎስ 4:19-22) ፈጣን ምላሽ በመስጠታቸው ኢየሱስ በኋላ ላይ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ በራሳቸው ላይ ሲፈጸም ማየት ችለዋል:- “ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።” (ማቴዎስ 11:29, 30) እርግጥ ነው፣ ጥምቀት የኃላፊነት ቀንበር መሸከምን ይጠይቃል፤ ቢሆንም ኢየሱስ እንዳረጋገጠው ይህ ቀንበር ልዝብና ቀላል በመሆኑ ትልቅ እረፍት ይሰጣል።

15. የሙሴና የኤርምያስ ምሳሌ አምላክ እንደሚረዳን መተማመን እንደምንችል የሚያሳዩት እንዴት ነው?

15 ብቃት የለኝም የሚል ስሜት ቢሰማን እንግዳ ነገር አይደለም። ሙሴና ኤርምያስ ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ ለመፈጸም መጀመሪያ ላይ ችሎታ እንደሌላቸው ተሰምቷቸው ነበር። (ዘፀአት 3:11፤ ኤርምያስ 1:6) ይሖዋ ያበረታታቸው እንዴት ነው? ሙሴን “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” ያለው ሲሆን ኤርምያስን ደግሞ “እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝ” በማለት ቃል ገብቶለታል። (ዘፀአት 3:12፤ ኤርምያስ 1:8) እኛም መለኮታዊ ድጋፍ እንደምናገኝ መተማመን እንችላለን። ለይሖዋ ያለን ፍቅርና በእርሱ ላይ መተማመናችን፣ ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር በሚስማማ ሁኔታ መኖር ሊያቅተን ይችላል እያልን ከማመንታት እንድንቆጠብ ይረዳናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:18) አንድ ትንሽ ልጅ ብቻውን መራመድ ያስፈራው ይሆናል፤ የአባቱን እጅ ከያዘ ግን ተማምኖ ይጓዛል። እኛም በተመሳሳይ በሙሉ ልባችን በይሖዋ ተማምነን ከጎኑ የምንሄድ ከሆነ ‘ጐዳናችንን ቀና እንደሚያደርግልን’ ቃል ገብቶልናል።—ምሳሌ 3:5, 6

በአክብሮት ሊታይ የሚገባው ሥነ ሥርዓት

16. ጥምቀት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ የሚከናወነው ለምንድን ነው?

16 ከጥምቀት ሥነ ሥርዓት አስቀድሞ ክርስቲያናዊ ጥምቀት ያለውን ትልቅ ትርጉም የሚያብራራ ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግር ይቀርባል። በዚህ ንግግር መደምደሚያ ላይ እጩ ተጠማቂዎች ለሁለቱ የጥምቀት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት በሕዝብ ፊት ስለ እምነታቸው እንዲመሠክሩ ይጠየቃሉ። (ሮሜ 10:10፤ በገጽ 22 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ከዚያም ልክ እንደ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ጠልቀው ይጠመቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ‘ከውሃ እንደወጣ’ ይናገራል። (ማቴዎስ 3:16፤ ማርቆስ 1:10) በመሆኑም መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ አጥልቆት እንደነበር ከዚህ በግልጽ መረዳት ይቻላል። b ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅ በሕይወታችን ላይ ላደረግነው አስገራሚ ለውጥ ተስማሚ ምሳሌ ነው፤ በምሳሌያዊ አነጋገር ለበፊቱ አኗኗራችን ሞተን በአምላክ አገልግሎት አዲስ ሕይወት መምራት መጀመራችንን ያሳያል።

17. የጥምቀት እጩዎችና ሌሎች ተሰብሳቢዎች ሥርዓቱ ክብር እንዲላበስ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

17 የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በቁም ነገር መታየት የሚገባው ቢሆንም የደስታም ወቅት ነው። ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ዮሐንስ ሲያጠምቀው ይጸልይ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሉቃስ 3:21, 22) ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ በተወው ምሳሌ መሠረት እጩ ተጠማቂዎች ሥርዓታማ ምግባር ሊያሳዩ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ በተገቢ ሁኔታ መልበስ እንዳለብን የሚገልጽ በመሆኑ በጥምቀታችን ዕለትም ይህንን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባን ምንም አያጠራጥርም! (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ሌሎችም የጥምቀት ንግግሩን በጥሞና በማዳመጥና ጥምቀት ሲከናወን በሥርዓት በመመልከት ተገቢውን አክብሮት ማሳየት ይችላሉ።—1 ቆሮንቶስ 14:40

የተጠመቁ ደቀ መዛሙርት የሚያገኟቸው በረከቶች

18, 19. ጥምቀት ምን መብቶችንና በረከቶችን ያስገኛል?

18 ራሳችንን ለአምላክ ከወሰንንና ከተጠመቅን በኋላ የአንድ ልዩ ቤተሰብ አባል እንሆናለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ አባታችንና ወዳጃችን ይሆናል። ከመጠመቃችን በፊት ከአምላክ ርቀን ነበር፤ ከተጠመቅን በኋላ ግን ከእርሱ ጋር ታርቀናል። (2 ቆሮንቶስ 5:19፤ ቈላስይስ 1:20) በክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ወደ አምላክ ቀርበናል፤ እርሱም ወደ እኛ ቀርቧል። (ያዕቆብ 4:8) ነቢዩ ሚልክያስ ይሖዋ በስሙ የሚጠቀሙና ስሙን የሚሸከሙ ሰዎችን በትኩረት እንደሚመለከት እንዲሁም የሚናገሩትን እንደሚያዳምጥ ገልጿል፤ አክሎም ስማቸውን በመታሰቢያ መጽሐፉ ላይ እንደሚያሰፍር ተናግሯል። አምላክ “እነርሱ የገዛ ገንዘቤ ይሆናሉ . . . አባት የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚታደግ ሁሉ እኔም እታደጋቸዋለሁ” በማለት ተናግሯል።—ሚልክያስ 3:16-18

19 በተጨማሪም ጥምቀት የአንድ ዓለም አቀፍ ወንድማማች ማኅበር አባል ለመሆን ያስችለናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለከፈሉት መሥዋዕት ምን ወሮታ እንደሚያገኙ ኢየሱስን በጠየቀው ጊዜ እንዲህ የሚል ቃል ገብቶለት ነበር:- “ስለ ስሜ ብሎ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን፣ ልጆችን ወይም ዕርሻን የሚተው ሁሉ መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።” (ማቴዎስ 19:29) ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ከተናገረ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ጴጥሮስ “በዓለም ዙሪያ” ስለተስፋፋው “መላው የወንድማማቾች ማኅበር” ጽፎ ነበር። ጴጥሮስ ራሱ አፍቃሪው የወንድማማች ማኅበር የሚሰጠውን ድጋፍ አግኝቷል፣ የሚያስገኛቸውንም በረከቶች ቀምሷል፤ እኛም ተመሳሳይ ነገር ማግኘት እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 2:17 NW፤ 5:9

20. ጥምቀት ምን ዓይነት አስደናቂ ተስፋ ያስገኝልናል?

20 ከዚህም በላይ ኢየሱስ እርሱን የሚከተሉ ሰዎች ‘የዘላለም ሕይወት እንደሚወርሱ’ ተናግሯል። አዎን፣ ራስን መወሰንና መጠመቅ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” የማግኘት ማለትም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን ለወደፊቱ መሠረት የሚሆን ምን ከዚህ የተሻለ ነገር ይገኛል? ይህ ድንቅ ተስፋ ‘በአምላካችን በይሖዋ ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም እንድንሄድ’ ያስችለናል።—ሚክያስ 4:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በጰንጠቆስጤ ዕለት የጴጥሮስን ንግግር ሲያዳምጡ የነበሩ ሦስት ሺህ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎችም እንዲሁ ወዲያውኑ ተጠምቀዋል። እነዚህ ሰዎች እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሁሉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ትምህርቶችና መመሪያዎች ያውቁ እንደነበር የተረጋገጠ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 2:37-41

b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ጥምቀትን’ ለማመልከት የተሠራበት ግሪክኛ ቃል “ውኃ ውስጥ ጠልቆ ወይም ሙሉ በሙሉ ገብቶ የመውጣትን ሂደት” እንደሚያመለክት በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ ገልጿል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ለይሖዋ ፍቅር ምላሽ መስጠት ያለብን ለምንና እንዴት ነው?

• ከጥምቀት በፊት ምን መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ያስፈልጋል?

• አይሳካልን ይሆናል የሚለው ፍራቻ ወይም ኃላፊነት ለመሸከም ፈቃደኛ አለመሆን ከመጠመቅ ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን የማይገባው ለምንድን ነው?

• የተጠመቁ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ልዩ በረከቶች ማግኘት ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በቁም ነገር መታየት የሚገባው ቢሆንም የደስታም ወቅት ነው