በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ምን ያስፈልግሃል?

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ምን ያስፈልግሃል?

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ምን ያስፈልግሃል?

“ይህን ሁሉ ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት . . . [ገለጥህላቸው]።” (ሉቃስ 10:21) ኢየሱስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ትክክለኛ ዝንባሌ ሊኖረን እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ይሖዋ፣ ትሑትና ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ብቻ ሊረዱት የሚችሉት መጽሐፍ በማጻፉ ጥበቡ ታይቷል።

አብዛኞቻችን ትሕትናን ማሳየት ይከብደናል። ሁላችንም የኩራት ዝንባሌን ወርሰናል። በተጨማሪም የምንኖረው “ራሳቸውን የሚወዱ . . . ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ” ሰዎች በበዙበት “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) እንዲህ ዓይነቶቹ ዝንባሌዎች ደግሞ የአምላክን ቃል እንዳንረዳ እንቅፋት ይሆኑብናል። የሚያሳዝነው፣ በዙሪያችን ያለው ዓለም በተወሰነ መልኩም ቢሆን በሁላችንም ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችል ዝንባሌ እንዴት ማዳበር ትችላለህ?

ልብንና አእምሮን ማዘጋጀት

ጥንት የአምላክ ሕዝብ መሪ የነበረው ዕዝራ ‘የእግዚአብሔርን ሕግ ለመፈለግ ልቡን አዘጋጅቶ’ ነበር። (ዕዝራ 7:10 የ1954 ትርጉም) ልባችንን ማዘጋጀት የምንችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎን አለ። ለቅዱሳን ጽሑፎች ተገቢ አመለካከት ለማዳበር በመጣር ልንጀምር እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት አጋሮቹ “ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ . . . እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ [አልተቀበላችሁትም]” ሲል ጽፎላቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጻፍ ሰዎችን ቢጠቀምም መልእክቱ የመጣው ከእርሱ ነው። ይህን መሠረታዊ እውነታ መገንዘባችን ያነበብናቸውን ነገሮች አምነን ለመቀበል ይበልጥ ቀላል ያደርግልናል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ልባችንን ማዘጋጀት የምንችልበት ሌላው መንገድ ጸሎት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈ እንደመሆኑ መጠን መልእክቱን ለመረዳትም ቢሆን ይኸው መንፈስ ያግዘናል። ይህን እርዳታ ለማግኘት ደግሞ መጸለይ ይኖርብናል። መዝሙራዊው ምን እንዳለ ልብ በል:- “ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ።” (መዝሙር 119:34) መጸለይ ያለብን የተጻፈውን ለመገንዘብ የሚያስችል የአእምሮ ችሎታ እንድናገኝ ብቻ ሳይሆን ያነበብነውን አምነን ለመቀበል የሚያስችል የልብ ዝንባሌ እንዲኖረንም ጭምር መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ከፈለግን እውነት የሆነውን ነገር የመቀበል ፍላጎት ሊኖረን ይገባል።

ትክክለኛ ዝንባሌ ማዳበር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስታሰላስል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችልም አስብ። የአምላክን ቃል ለማንበብ የሚያነሳሱን በርከት ያሉ ጠንካራ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኛው ግን ይበልጥ ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚያስችለን መሆኑ ነው። (ያዕቆብ 4:8) ይሖዋ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ምን እርምጃ እንደወሰደ፣ እርሱን የሚወድዱትን የቱን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸውና ከእርሱ የራቁትን ደግሞ በምን መልኩ እንደያዛቸው ማንበባችን ስለ ማንነቱ ይበልጥ ለማወቅ ያስችለናል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የምንነሳሳበት ዋናው ዓላማ ስለ አምላክ ይበልጥ ለማወቅና ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር መሆን ይኖርበታል።

ትክክለኛ ዝንባሌ እንዳይኖረን እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች

የአምላክን ቃል እንዳንረዳ ምን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል? አንዱ ተገቢ ያልሆነ ታማኝነት ማሳየት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የአንዳንድ ሰዎችን አመለካከትና እምነት ከፍ አድርገህ ትመለከት ይሆናል። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ከአምላክ ቃል ለሚገኘው እውነት አክብሮት የሌላቸው ቢሆኑስ? እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ትምህርት መረዳት ፈታኝ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም፣ መጽሐፍ ቅዱስ የምንማራቸውን ነገሮች በጥንቃቄ እንድንመረምር ያበረታታናል።—1 ተሰሎንቄ 5:21

የኢየሱስ እናት ማርያም እንዲህ ዓይነቱ ፈታኝ ሁኔታ ገጥሟት ነበር። ያደገችው ለአይሁድ ልማድ ከፍተኛ አክብሮት እንዲኖራት ተደርጋ ነው። የሙሴን ሕግ በጥንቃቄ ትጠብቅና ወደ ምኩራብ ትሄድ እንደነበረ እሙን ነው። የኋላ ኋላ ግን ወላጆቿ ያስተማሯት አምልኮ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ተገነዘበች። በዚህ ምክንያት የኢየሱስን ትምህርቶች ተቀብላ ከክርስቲያን ጉባኤ የመጀመሪያ አባላት መካከል ለመሆን በቃች። (የሐዋርያት ሥራ 1:13, 14) ይህ ለወላጆቿም ሆነ ይከተሉት ለነበረው ልማድ አክብሮት እንደሌላት የሚያሳይ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ያላትን ፍቅር የሚገልጽ ነው። እኛም ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመጠቀም ከፈለግን ልክ እንደ ማርያም ለሰው ሳይሆን ለአምላክ ታማኝ መሆን ይኖርብናል።

የሚያሳዝነው ግን ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እምብዛም አክብደው አይመለከቱም። አንዳንዶች በውሸት ላይ የተመሠረቱ ሃይማኖታዊ ልማዶችን በመከተል ብቻ ረክተው ይኖራሉ። ሌሎች ደግሞ ለእውነት አክብሮት እንደሌላቸው በአነጋገራቸውና በአኗኗራቸው ያሳያሉ። ከዚህም የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበል መሥዋዕትነት ይጠይቃል፤ ምናልባትም ከወዳጆችህ፣ ከጎረቤቶችህ፣ ከሥራ ባልደረቦችህና ከቤተሰቦችህ ጋር እንኳ ሳይቀር ልትቃቃር ትችላለህ። (ዮሐንስ 17:14) ይሁንና ጠቢቡ ሰሎሞን “እውነትን ግዛት እንጂ አትሽጣት” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 23:23) እውነትን ከፍ አድርገህ የምትመለከት ከሆነ ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን እንድትረዳ ያግዝሃል።

የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንዳንረዳ እንቅፋት የሚሆንብን ሌላው ነገር ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆን ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። የሕዝቡ ልብ ደንድኖአልና፤ ጆሮአቸውም አይሰማም።” (ማቴዎስ 13:11, 15) ኢየሱስ ከመሰከረላቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ የተማሩትን በተግባር ለማዋልና ለመለወጥ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ በምሳሌው ላይ ከጠቀሰው ነጋዴ ምንኛ ይለያሉ! ነጋዴው ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ገዝቶታል። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መረዳትን የዚህን ያህል እንደ ውድ ነገር ልንመለከተው ይገባል።—ማቴዎስ 13:45, 46

ለመማር ፈቃደኛ አለመሆን

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ስንጥር ከሚያጋጥሙን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ዋነኛው ለመማር ፈቃደኛ አለመሆን ነው። አንድ ግለሰብ ተራ የሆነ ሰው የሚያቀርብለትን አዲስ ሐሳብ መቀበል ይቸግረው ይሆናል። ሆኖም የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 4:13) ጳውሎስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ወንድሞች ሆይ፤ በተጠራችሁ ጊዜ ምን እንደ ነበራችሁ እስቲ አስቡ። በሰው መስፈርት ከእናንተ ብዙዎቻችሁ ዐዋቂዎች አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ኀያላን አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ከትልቅ ቤተሰብ አልተወለዳችሁም።” (1 ቆሮንቶስ 1:26, 27) ተራ ነው ብለህ ከምትገምተው ሰው ትምህርት ስትቀስም ትሕትና ማሳየት ከከበደህ እርሱ ወይም እርሷ አምላክ አንተን ለማስተማር የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ብቻ መሆናቸውን አስታውስ። ‘በታላቁ አስተማሪ’ በይሖዋ ከመማር የበለጠ ታላቅ መብት ከየት ሊገኝ ይችላል?—ኢሳይያስ 30:20 NW፤ 54:13

የሶርያ ጦር አዛዥ የነበረው ንዕማን አንድ ተራ አገልጋይ የሰጠውን መመሪያ መቀበል ከብዶት ነበር። ንዕማን ከለምጹ ለመፈወስ ኤልሳዕ የተባለ የይሖዋ ነቢይ ዘንድ ሄዶ ነበር። ሆኖም ከበሽታው ለመፈወስ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚገልጸው የአምላክ መመሪያ የተነገረው በአንድ አገልጋይ በኩል ነበር። የመልእክቱ ይዘትና የቀረበበት መንገድ ንዕማን መመሪያውን በትሕትና ለመቀበል እንዲከብደው አደረገው፤ በመሆኑም መጀመሪያ ላይ የአምላክ ነቢይ የሰጠውን መመሪያ ለመከተል አሻፈረኝ አለ። በኋላ ላይ ግን አስተሳሰቡን የለወጠ ከመሆኑም በላይ ከበሽታውም ተፈወሰ። (2 ነገሥት 5:9-14) መጽሐፍ ቅዱስንም በተመለከተ ተመሳሳይ የሆነ ፈታኝ ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል። መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ፈውስ ለማግኘት አዲስ የሆነ አኗኗር መከተል እንደሚያስፈልገን ተምረን ሊሆን ይችላል። ሆኖም ትሑት በመሆን አንድ ሰው ማድረግ ያለብንን እንዲያስተምረን እንፈቅዳለን? መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት የሚችሉት ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው።

ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ከፍተኛ ባለሟል የነበረ አንድ ሰው በዚህ ረገድ ግሩም ዝንባሌ አሳይቷል። ይህ ሰው ወደ አፍሪካ እየተመለሰ ሳለ ደቀ መዝሙሩ ፊልጶስ ወደ ሠረገላው ቀርቦ አነጋገረውና የሚያነበውን ያስተውለው አንደሆነ ጠየቀው። ባለ ሥልጣኑም “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” ሲል በትሕትና መለሰለት። ይህ ሰው የአምላክን ቃል እውቀት ከቀሰመ በኋላ ተጠመቀ። “ደስ እያለውም ጒዞውን ቀጠለ።”—የሐዋርያት ሥራ 8:27-39

በጥቅሉ ሲታይ የይሖዋ ምሥክሮች ተራ ሰዎች ናቸው። ይሁንና በየሳምንቱ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የተሻለው የሕይወት ጎዳና ምን እንደሆነ ያስተምራል፣ የሰው ልጆች ያላቸው እውን የሆነ ብቸኛ ተስፋ ምን መሆኑን ይገልጻል፤ እንዲሁም ስለ አምላክ እንዴት ማወቅ እንደምንችል ይጠቁመናል። በመሆኑም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸውና መልእክቱን በመገንዘባቸው ይህ ነው የማይባል ደስታ አግኝተዋል። አንተም እንዲህ ያለውን ደስታ ማግኘት ትችላለህ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንዕማን ከአንድ ተራ አገልጋይ የተሰጠውን መመሪያ ለመቀበል ተቸግሮ ነበር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መረዳታችን ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል