በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ክርስቶስን ምሰሉ

በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ክርስቶስን ምሰሉ

በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ክርስቶስን ምሰሉ

ከጥቂት ዓመታት በፊት የሰውን ልጅ ባሕርይ አስመልክቶ የተደረገ አንድ ምርምር አስገራሚ ውጤት አስገኝቶ ነበር። ምርምሩ የተካሄደባቸው ሰዎች በሁለት ቡድን ከተከፈሉ በኋላ፣ በአንዱ ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች በሌላኛው ቡድን በሚገኙትና እንደ እስረኛ በተቆጠሩት ሰዎች ላይ ጠባቂ ሆነው ተመደቡ። ውጤቱ ምን ነበር?

ሪፖርቱ እንደሚከተለው ይላል:- “ከጥቂት ቀናት በኋላ ጠባቂ ተደርገው ከተሾሙት መካከል ብዙዎቹ ተሳዳቢዎችና ጉልበተኞች ከመሆናቸውም ባሻገር በሥራቸው ያሉትን ሰዎች በተደጋጋሚ መቅጣት ጀመሩ፤ እንደ እስረኛ የሆኑት ደግሞ ሽቁጥቁጦችና ያለምንም ማንገራገር የሚገዙ ሆኑ።” ታዲያ ተመራማሪዎቹ የደረሱበት መደምደሚያ ምን ነበር? ማንኛውም ሰው ለማለት ይቻላል ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም ወጥመድ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል።

ሥልጣንን በአግባቡ ወይም አላግባብ መጠቀም ምን ያስከትላል?

ሥልጣን በአግባቡ ከተጠቀሙበት በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። መልካም መመሪያዎችን ለመስጠት ከማገልገሉም በላይ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጥቅሞች ያስገኛል። (ምሳሌ 1:5፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) ሆኖም ከላይ የተጠቀሰው የምርምር ውጤት እንዳመለከተው ሥልጣንን አላግባብ የመጠቀም አደጋ ምንጊዜም ሊያጋጥም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን አደጋ አስመልክቶ “ክፉዎች ሲገዙ . . . ሕዝብ ያቃስታል” ይላል።—ምሳሌ 29:2፤ መክብብ 8:9

አንድ ሰው ለበጎ ዓላማ ቢሆንም እንኳ ሥልጣኑን አላግባብ ከተጠቀመበት ውጤቱ ጎጂ ይሆናል። ለአብነት ያህል፣ በአየርላንድ በሚገኝ በቤተ ክርስቲያን የሚተዳደር አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የተከሰተውን ሁኔታ ተመልከት። አንዳንድ መምህራን በተማሪዎቻቸው ላይ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀማቸው ትምህርት ቤቱ በቅርቡ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል። ከእነዚህ መምህራን አብዛኞቹ ዓላማቸው በጎ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ይሁንና አንዳንዶቹ የተጠቀሙባቸው ዘዴዎች በጣም ጎጂ ነበሩ። አንድ ጋዜጣ “[አስተማሪዎቹ] ልጆቹን በኃይል ይደበድቧቸውና ያመናጭቋቸው ስለነበር ብዙዎቹ ለስሜት ጠባሳ ተዳርገዋል” ሲል ዘግቧል። (ዚ አይሪሽ ታይምስ) ታዲያ ሌሎችን በቃልም ሆነ በድርጊት ሳታሳዝናቸው ወይም ሳትጎዳቸው የቻሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው በሚችል መልኩ ሥልጣንህን መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?—ምሳሌ 12:18

“ሥልጣን ሁሉ” ለኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቶታል

የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ተመልከት። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ሲል ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:18) ኢየሱስ ይህን ማለቱ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የፍርሃት ስሜት ጭሮባቸው ነበር? ኢየሱስ፣ ሥልጣናቸውን የሚጋፋ ማንኛውንም ተቃውሞ ወይም ዓመጽ በኃይል እርምጃ ጸጥ እንደሚያሰኙ ከሚታወቁት የሮም ቄሣሮች ጋር ተመሳሳይ የሆነ መንፈስ እንደሚያንጸባርቅ ተሰምቷቸው ይሆን?

ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳልነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በማያሻማ መንገድ ያሳያሉ! ክርስቶስ ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ልክ እንደ አባቱ ነው። ምንም እንኳ ይሖዋ ኃያልና የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ቢሆንም ተገዢዎቹ ከልባቸው ተነሳስተው እንዲያገለግሉት እንጂ በጭፍን እንዲገዙለት አሊያም ደግሞ ፈርተው ወይም በአድር ባይነት እንዲታዘዙት አይፈልግም። (ማቴዎስ 22:37) ይሖዋ መቼም ቢሆን ሥልጣኑን አላግባብ አይጠቀምበትም። ሕዝቅኤል ያየው አስደናቂ ራእይ ይህን ያሳያል።

ሕዝቅኤል በዚህ ራእይ ላይ የአምላክን ሉዓላዊነት በታማኝነት የደገፉ አራት መላእክታዊ ፍጥረታትን ተመልክቶ ነበር። እያንዳንዳቸውም አራት ፊት ነበራቸው። ሕዝቅኤል እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ፊታቸውም እንዲህ ነበር፤ አራቱም እያንዳንዳቸው የሰው ፊት ነበራቸው፤ በቀኝ በኩል የአንበሳ ፊት፣ በግራ በኩልም የበሬ ፊት ነበራቸው፤ እያንዳንዳቸውም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።” (ሕዝቅኤል 1:10) አራቱ ፊቶች ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀምባቸውን አራቱን የአምላክ ዋና ዋና ባሕርያት ያመለክታሉ። የአምላክ ቃል፣ በሰው ፊት የተመሰለው ፍቅር፣ በአንበሳ ፊት የተመሰለው ፍትሕ እንዲሁም በንስር ፊት የተመሰለው ጥበብ እንደሆነ ይገልጻል። እነዚህ ባሕርያት ደግሞ ከአራተኛውና በበሬ ፊት ከተመሰለው ከኃይል ጋር ተቀናጅተው ይሠራሉ። ይህ ሁሉ ምን ትርጉም አለው? ይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይሉንም ሆነ ሥልጣኑን የሚጠቀመው ከሌሎቹ ዋና ዋና ባሕርያቱ ጋር በሚስማማ መልኩ መሆኑን ራእዩ ያሳያል።

ኢየሱስ ክርስቶስም የአባቱን አርዓያ በመከተል ምንጊዜም ቢሆን ሥልጣኑን በፍቅር፣ በጥበብና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። ደቀ መዛሙርቱ በኢየሱስ ሥልጣን ሥር ሆነው ማገልገላቸው ታላቅ እረፍት አስገኝቶላቸዋል። (ማቴዎስ 11:28-30) ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ተለይተው የሚታወቁት በፍቅራቸው እንጂ ባላቸው ኃይል ወይም ሥልጣን አይደለም!—1 ቆሮንቶስ 13:13፤ 1 ዮሐንስ 4:8

በሥልጣንህ የምትጠቀመው እንዴት ነው?

አንተስ በሥልጣን አጠቃቀምህ እንዴት ነህ? ለምሳሌ ያህል፣ በቤተሰብ ውስጥ ሥልጣን ስላለህ ብቻ እኔ ያልኩት ካልሆነ ትላለህ? የቤተሰብህ አባላት ውሳኔህን የሚያከብሩት ስለሚፈሩህ ነው ወይስ ስለሚወዱህ? የሚታዘዙልህ በኃይል ስለምትጠቀም ነው? የቤተሰብ ራሶች በቤተሰባቸው ውስጥ ቲኦክራሲያዊ ሥርዓትን የማስፈን ግብ ይዘው እነዚህን ጥያቄዎች ሊያስቡባቸው ይገባል።—1 ቆሮንቶስ 11:3

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተወሰነ ሥልጣን የተሰጠህ ብትሆንስ? ኃላፊነትህን በተገቢው መንገድ እየተወጣህ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉትና በኢየሱስ ሕይወት ከተንጸባረቁት ከሚከተሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር ራስህን ገምግም።

“የጌታም አገልጋይ . . . ለሰው ሁሉ ገር፣ . . . ትዕግሥተኛም መሆን ይገባዋል፤ . . . የሚቃወሙትን በየዋህነት የሚያቃና መሆን ይኖርበታል።”—2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25

በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው። ለአብነት ያህል፣ ጢሞቴዎስ ‘አንዳንድ ሰዎች የሐሰት ትምህርት እንዳያስተምሩ የማዘዝ’ ሥልጣን ሳይቀር ነበረው። (1 ጢሞቴዎስ 1:3) ያም ሆኖ ጢሞቴዎስ በተግባሩ ሁሉ አምላካዊ ባሕርያትን ያንጸባርቅ እንደነበረ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ጢሞቴዎስ የክርስቲያን ጉባኤን በሚመራበት ወቅት ሌሎችን “በየዋህነት” እንዲያቀናና “ለሰው ሁሉ ገር” እንዲሆን ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ያደርግ እንደነበረ አያጠራጥርም። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ እርሱ ራሱ ገና ወጣት ስለነበር አረጋውያንን እንደ ልጃቸው በመሆን በአክብሮት መያዝ፣ የዕድሜ እኩዮቹን ደግሞ እንደ አሳቢ ወንድም መንከባከብ ነበረበት። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) ሽማግሌዎች እንዲህ ዓይነቱን ፍቅራዊ አሳቢነት ሲያሳዩ የክርስቲያን ጉባኤ፣ መተሳሰብና መተዛዘን ከማይታይበት የንግድ ማኅበር በተለየ መልኩ ሞቅ ያለና ቤተሰባዊ ፍቅር የሚንጸባረቅበት ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 4:14፤ 1 ተሰሎንቄ 2:7, 8

“የአሕዛብ ገዢዎች በሕዝባቸው ላይ ጌቶች እንደሚሆኑ፣ ባለ ሥልጣኖቻቸውም በኀይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ፤ በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም። ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን።”—ማቴዎስ 20:25, 26

በዓለም ያሉ አምባገነን መሪዎች ፈቃዳቸው እንዲፈጸምና ሁሉ ነገር እነርሱ ባሰቡት መንገድ ብቻ እንዲከናወን በማስገደድ እንዲሁም ለመታዘዝ አሻፈረኝ ያሉትን ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በማስፈራራት በተገዥዎቻቸው ላይ “ጌቶች” ይሆናሉ። ይሁንና ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎችን ከመጫን ይልቅ ማገልገል እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 20:27, 28) ደቀ መዛሙርቱን ዘወትር በፍቅርና በአሳቢነት ይይዛቸው ነበር። የኢየሱስን ምሳሌ ስትከተል ሌሎች ከአንተ ጋር ተባብሮ መሥራት ቀላል ይሆንላቸዋል። (ዕብራውያን 13:7, 17) ከዚህም በላይ አቅማቸው በፈቀደ መጠን “ዕጥፉን መንገድ” ለመጓዝ ይነሳሳሉ፤ ይህንንም በግዴታ ሳይሆን በውዴታ ያደርጉታል።—ማቴዎስ 5:41

“በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም . . . ምሳሌ በመሆን እንጂ በላያቸው በመሠልጠን አይሁን።”—1 ጴጥሮስ 5:2, 3

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የበላይ ተመልካቾች የጉባኤውን መንፈሳዊ ደኅንነት በተመለከተ አደራ እንደተጣለባቸው ይገነዘባሉ። ይህን ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር ይመለከቱታል። የአምላክን መንጋ የሚንከባከቡትም በፈቃደኝነት፣ በሙሉ ፍላጎትና በፍቅር ነው። ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚንከባከቧቸውን ወንድሞች እምነት ለማጎልበት ጠንክረው ይሠራሉ እንጂ በእምነታቸው ላይ መሠልጠን አይፈልጉም።—2 ቆሮንቶስ 1:24

ሽማግሌዎች አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ኃጢአት ውስጥ የገባን ሰው ለመመለስ ወይም የእምነት ባልንጀራቸውን መንፈሳዊነት ለማሳደግ በገርነት ተገቢውን ምክር ይሰጣሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል የሰጣቸውን ማሳሰቢያ በአእምሯቸው ይይዛሉ:- “ወንድሞች ሆይ፤ አንድ ሰው በኀጢአት ውስጥ ገብቶ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ በገርነት ልትመልሱት ይገባል። ነገር ግን አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።”—ገላትያ 6:1፤ ዕብራውያን 6:1, 9-12

“እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ . . . በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።”—ቈላስይስ 3:13, 14

ለክርስቲያኖች የተሰጡትን መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ መፈጸም ያቃታቸው ቢኖሩስ? ይሖዋና ኢየሱስ እንደሚያደርጉት አንተም አለፍጽምና የሚያሳድርባቸውን ተጽዕኖ ግምት ውስጥ ታስገባለህ? (ኢሳይያስ 42:2-4) ወይስ በእያንዳንዱ ሁኔታ ላይ ሕጉ ካልተፈጸመ በማለት ከልክ በላይ ጥብቅ ትሆናለህ? (መዝሙር 130:3) በማንኛውም ጊዜ ደግነት ማሳየት እንደሚገባህና ጥብቅ መሆን ያለብህ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ መሆኑን አትዘንጋ። ፍቅር ማሳየትህ በአንተና በሥርህ ባሉት ሰዎች መካከል የመተማመን መንፈስ ያለበት ጠንካራ ትስስር እንዲኖር ያደርጋል።

ማንኛውም ዓይነት ሥልጣን ቢኖርህ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣንን በመጠቀም ረገድ ያሳዩትን ምሳሌ ለመኮረጅ ብርቱ ጥረት አድርግ። ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር በተያያዘ ሥልጣኑን ስለሚጠቀምበት መንገድ መዝሙራዊው የሰጠውን ግሩም መግለጫ አስታውስ። ዳዊት እንደሚከተለው ሲል ዘምሯል:- “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል።” ስለ ኢየሱስም ተመሳሳይ ነገር እናነባለን:- “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ።” ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ሥልጣንን በመጠቀም ረገድ ከይሖዋና ከኢየሱስ የተሻለ ምሳሌ ከየት ልናገኝ እንችላለን?—መዝሙር 23:1-3፤ ዮሐንስ 10:14, 15

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ ሁልጊዜ ኃይሉን የሚጠቀመው በፍቅር፣ በጥበብና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች ኃጢአት ውስጥ ለወደቁ ሰዎች ፍቅራዊ ምክር መለገስ ይገባቸዋል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጢሞቴዎስ አረጋውያንን እንደ ልጃቸው በመሆን በአክብሮት እንዲይዝና የዕድሜ እኩዮቹን ደግሞ እንደ አሳቢ ወንድም እንዲንከባከብ ጳውሎስ መክሮታል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣኑን በፍቅር፣ በጥበብና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል