በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፓናማ ያሉትን እንቅፋቶች መወጣት

በፓናማ ያሉትን እንቅፋቶች መወጣት

በፓናማ ያሉትን እንቅፋቶች መወጣት

“ፓናማ፣ ዓለምን የምታገናኝ ድልድይ።” በመካከለኛው አሜሪካ በምትገኘው በፓናማ አንድ ታዋቂ የሬዲዮ ፕሮግራም፣ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ይህን አባባል በተደጋጋሚ ሲናገር መሰማቱ የተለመደ ነበር። ዛሬ ይህ አባባል ብዙ ሰዎች ለዚህች አገር ያላቸውን ስሜት የሚያንጸባርቅ ሆኗል።

ፓናማ ሰሜን አሜሪካና ደቡብ አሜሪካ የሚገናኙባት ድልድይ በመሆን ታገለግላለች። ከዚህ በተጨማሪ ብሪጅ ኦቭ ዚ አሜሪካስ በመባል የሚጠራው ድልድይ ታዋቂ በሆነው የፓናማ ካናል ላይ ተዘርግቷል። አስደናቂ የምህንድስና ውጤት የሆነው የፓናማ ካናል አገሪቱን አቋርጦ የሚያልፍ ሲሆን አትላንቲክና ፓስፊክ ውቅያኖሶችንም ያገናኛል። የፓናማ ካናል፣ ከተለያየ የዓለም ክፍል የሚመጡ መርከቦች ብዙ ቀናት አሊያም ሳምንታት የሚፈጅባቸውን መንገድ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለመሸፈን አስችሏቸዋል። አዎን፣ ፓናማ አብዛኛውን የዓለም ክፍል የምታገናኝ ጠቃሚ ድልድይ በመሆን ታገለግላለች።

ድልድይ ሆና የምታገለግል ጉራማይሌ ባሕል ያላት አገር

ፓናማ ከበርካታ የዓለም ክፍሎች የመጡ የተለያየ ብሔር፣ ጎሳና ባሕል ያላቸው ሰዎች መኖሪያ ሆናለች። እነዚህን ሰዎች ጨምሮ በርካታ ዝርያ ያላቸው የአገሬው ተወላጆች ማራኪ በሆነችው በዚህች ምድር ላይ ተሰበጣጥሮ የሚገኝ ጉራማይሌ ባሕል ያለው ሕዝብ ፈጥረዋል። ይሁንና ይህን የማኅበራዊ ሕይወት፣ የባሕል፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነት አሸንፎ እጅግ ውድ በሆነው የአምላክ ቃል እውነት ላይ የተመሠረተ የአስተሳሰብና የዓላማ አንድነት መፍጠር ይቻል ይሆን?

አዎን፣ ይቻላል። በኤፌሶን 2:17, 18 ላይ የሚገኙት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት እንደሚጠቁሙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከአይሁድና ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ አንድነት ማስገኘት ችለው ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[ኢየሱስ] መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተ፣ ቀርበው ለነበሩትም ለእነርሱ ሰላምን ሰበከ [“ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፣” የ1954 ትርጉም]፤ ሁላችንም በእርሱ አማካይነት በአንዱ መንፈስ ወደ አብ መቅረብ እንችላለንና።”

በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የተለያየ ሃይማኖት ላላቸውም ይሁን ቃል በቃል ከሩቅ ቦታዎች ለመጡ በፓናማ ለሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች ‘የሰላምን ምስራች’ በማወጅ ላይ ይገኛሉ። ወደ ይሖዋ ‘በቀረቡት’ ሰዎች መካከልም አስደሳች አንድነት ተመሥርቷል። በዚህም ሳቢያ በፓናማ በስድስት ቋንቋዎች ማለትም በስፓንኛ፣ በካንቶኒዝ፣ በፓናማ የምልክት ቋንቋ፣ በእንግሊዝኛ እንዲሁም የአገሬው ተወላጆች ቋንቋ በሆኑት በኩና እና በንጎብሬ (ጉዋሚ) የሚመሩ ጉባኤዎች ተቋቁመዋል። የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩት እነዚህ ሰዎች በይሖዋ አምልኮ እንዴት አንድ መሆን እንደቻሉ ማወቁ እጅግ ያበረታታል።

በኮማርካ እንቅፋቶችን መወጣት

በፓናማ የአገሬው ተወላጆች ከሆኑት ስምንት ጎሳዎች መካከል የንጎቤ ጎሳ ትልቁ ነው። ይህ ጎሳ 170,000 ገደማ የሚሆን የሕዝብ ብዛት ሲኖረው ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የሚኖሩት በቅርቡ ለመኖሪያነት በተከለለው ኮማርካ ወይም የተወሰነ ክልል ውስጥ ነው። የዚህ ሠፊ ክልል አብዛኛው ክፍል በእግር ብቻ የሚያስኬዱ ወጣ ገባ የሆኑና በደን የተሸፈኑ ተራራማ ቦታዎችን እንዲሁም ውብ በሆኑ የባሕር ዳርቻዎች አካባቢ የሚገኙ ክልሎችን ያካተተ ነው። ብዙዎቹ መንደሮች በባሕር ዳርቻዎችና በወንዞች አቅራቢያ የሚገኙ ሲሆን ወንዞቹም መገናኛ መሥመር ሆነው ያገለግላሉ። አብዛኞቹ የኮማርካ ነዋሪዎች በተራራዎቹ ላይ ቡና በመትከል፣ ዓሣ በማስገር ወይም በእርሻ ሥራ በመሰማራት የዕለት ጉርሳቸውን ያገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ በርካታዎቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባላት ናቸው። ይሁንና ማማ ታታ የተሰኘውን የአካባቢውን ሃይማኖት የሚከተሉም አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሲታመሙ አሊያም ክፉ መንፈስ እያስቸገራቸው እንዳለ ሆኖ ሲሰማቸው በአካባቢያቸው ወዳለው ሱኪያስ (ቃልቻ) ዘንድ ይሄዳሉ። ከነዋሪዎቹ መካከል አብዛኞቹ ስፓንኛ ቢናገሩም ይበልጥ የሚገባቸው ግን የንጎብሬ ቋንቋ ነው።

የሰዎችን ልብ ለመንካት መጣር

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ከመርዳትም አልፈው ወደ ልባቸው ጠልቆ እንዲገባ በሚያደርግ መልኩ ማስተማራቸው አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘባሉ። እውነት በሰዎች ልብ ጠልቆ ሲገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ራሳቸውን ለማስማማት በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊ ለውጦችን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። በመሆኑም፣ በክልሉ በሚገኙ ስምንት መንደሮች የተመደቡት ልዩ አቅኚዎች በአካባቢው ወንድሞች እርዳታ የንጎብሬ ቋንቋ ተምረዋል።

በአካባቢው የተቋቋሙት 14 ጉባኤዎች ከፍተኛ እድገት ሊያደርጉ እንደሚችሉ እየታየ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ዲማስና ሂዜላ የተባሉ ልዩ አቅኚ ባልና ሚስት በባሕር ዳርቻ አካባቢ ባለው በቶቦቢ በሚገኝ 40 ያህል አስፋፊዎች ያሉት አንድ አነስተኛ ጉባኤ ውስጥ ተመድበው ነበር። በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ለሚኖሩ ትሑት ሰዎች ለመመስከር በተደጋጋሚ በታንኳ መጓዝ ለእነዚህ አቅኚዎች ቀላል አልነበረም። ዲማስና ሂዜላ ጸጥ ያለው ውቅያኖስ ከመቅጽበት ተለውጦ አደገኛ የሆነ ማዕበል ሊነሳ እንደሚችል መገንዘብ ችለዋል። ከአንዱ መንደር ወደ ሌላው ሲቀዝፉ ከቆዩ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ክንዳቸውንና ወገባቸውን ያምማቸዋል። ሌላው ፈታኝ ሁኔታ ደግሞ የአካባቢውን ቋንቋ መማር ነበር። ይሁንና የከፈሉት መሥዋዕትነትና ያሳዩት ጽናት ክሷቸዋል፤ በ2001 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 552 ያህል ሰዎች ተገኝተዋል።

ከቶቦቢ የባሕር ዳርቻ ባሻገር የፑንታ ኢስኮንዲዳ መንደር ትገኛለች። በዚህች መንደር የሚኖሩት ጥቂት አስፋፊዎች አየሩ ደህና በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ወደ ቶቦቢ በጀልባ በመጓዝ ስብሰባዎችን ሲካፈሉ የቆዩ ሲሆን በአካባቢው ጉባኤ ሊቋቋም እንደሚችል የሚጠቁሙ ሪፖርቶችም ነበሩ። በዚህም የተነሳ ዲማስና ሂዜላ ወደ መንደሪቱ እንዲዛወሩ ጥያቄ ቀረበላቸው። በፑንታ ኢስኮንዲዳ ያለው ቡድን ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 28 አስፋፊዎችን ያቀፈ ጉባኤ ከመሆኑም በላይ በየሳምንቱ የሕዝብ ንግግር ለማዳመጥ የሚመጡ ተሰብሳቢዎች ቁጥርም በአማካይ 114 ደረሰ። በ2004 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 458 ተሰብሳቢዎች መገኘታቸው በአዲሱ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችን በእጅጉ አስደስቷቸዋል።

መሃይምነት የሚያስከትለውን ችግር መቅረፍ

በርካታ ቅን ሰዎች ከመሃይምነት መላቀቃቸው ከይሖዋ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ አስችሏቸዋል። ይህ ሁኔታ በኮማርካ ተራራማ አካባቢ በምትኖረው ፈርሚና በተባለች አንዲት ወጣት ላይ ታይቷል። ሚስዮናውያን የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በምትኖርበት ገለልተኛ መንደር ውስጥ በማገልገል ላይ ሳሉ ያገኟት ይህቺ ወጣት ለመንግሥቱ መልእክት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ሲጠይቋትም ይበልጥ ለማወቅ ፈቃደኛ መሆኗን ገለጸችላቸው። ይሁንና አንድ ችግር ነበር። ስፓንኛና የንጎብሬ ቋንቋ ብትናገርም ከእነዚህ ቋንቋዎች በአንዱም ቢሆን መጻፍም ሆነ ማንበብ አትችልም ነበር። ከሚስዮናውያኑ አንዷ ማንበብና መጻፍ መማር (እንግሊዝኛ) a በተባለው ብሮሹር አማካኝነት ልታስተምራት ፈቃደኛ መሆኗን ገለጸችላት።

ፈርሚና ትምህርቱን በጉጉት የምትዘጋጅ፣ የቤት ሥራዋን በሙሉ በአግባቡ የምትሠራና ፊደላቱን ለመጻፍ በትጋት የምትለማመድ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። ስለሆነም በአንድ ዓመት ውስጥ እድገት አድርጋ የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ!* የተባለውን ብሮሹር ማጥናት ቻለች። በአካባቢው ስብሰባዎች ለማካሄድ ዝግጅት ሲደረግ በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት ጀመረች። ይሁንና ቤተሰቧ ድሃ በመሆኑ ሁሉንም ልጆቿን ይዛ ወደ ስብሰባ ለመሄድ ለመጓጓዣ የምትከፍለው ገንዘብ አልነበራትም። የፈርሚናን ችግር ያስተዋለች አንዲት አቅኚ የንጎቤ ሴቶች የሚለብሱትን የአገር ባሕል ልብስ እየሠራች እንድትሸጥ ሐሳብ አቀረበችላት። ፈሪሚናም ልክ እንዳለቻት አደረገች፤ ምንም እንኳ ልታሟላቸው የሚገቡ ሌሎች ቁሳዊ ፍላጎቶች ቢኖሩም ከሽያጩ የምታገኘውን ገንዘብ የምታውለው ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመሄድ ብቻ ነበር። አሁን ከቤተሰቧ ጋር ወደ ሌላ አካባቢ የተዘዋወረች ቢሆንም መንፈሳዊ እድገት ማድረጓን ቀጥላለች። እነዚህ ሰዎች ከመሃይምነት በመላቀቃቸው ብቻ ሳይሆን ይሖዋን በማወቃቸውም እጅግ ተደስተዋል።

መስማት ለተሳናቸው ሰዎች መመስከር

በፓናማ አብዛኞቹ ሰዎች ከቤተሰባቸው አባላት መካከል መስማት የተሳነው ካለ እፍረት ይሰማቸዋል። መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከትምህርት የሚገለሉበት ጊዜም አለ። እንዲህ ዓይነት ችግር ካለባቸው ሰዎች ጋር መግባባት አዳጋች ስለሚሆን ብዙዎቹ እንደተገለሉ ሆኖ ይሰማቸዋል።

በመሆኑም መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ምሥራቹን ለማድረስ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ግልጽ ነበር። በአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች አነሳሽነት የተሰባሰቡ ፍላጎት ያላቸው አቅኚዎችና ሌሎች አስፋፊዎች የፓናማን የምልክት ቋንቋ ለመማር ወሰኑ። ይህ ጥረታቸውም ወሮታ አስገኝቶላቸዋል።

በ2001 መገባደጃ አካባቢ በፓናማ ሲቲ የምልክት ቋንቋ ቡድን ተቋቋመ። የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር 20 ይደርስ ነበር። ወንድሞችና እህቶች በቋንቋው ይበልጥ እየተካኑ ሲሄዱ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ በቋንቋቸው “እንዲሰሙ” ለማድረግ ችለዋል። መስማት የተሳናቸው ልጆች ያሏቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክር ወላጆችም በምልክት ቋንቋ በሚካሄዱት ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመሩ ሲሆን ልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በቀላሉ መረዳት መቻላቸውንና እውነትን የማወቅ ጉጉታቸው መጨመሩን ተገንዝበዋል። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆቹ በምልክት ቋንቋ መናገር የተማሩ ሲሆን ከልጆቻቸውም ጋር በተሻለ ሁኔታ ይግባባሉ። እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን በመንፈሳዊ መርዳትና ጠንካራ ቤተሰብ መገንባት ችለዋል። የኤልሳና የሴት ልጇ የኢራይዳ ተሞክሮ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆናል።

በምልክት ቋንቋው ቡድን ውስጥ የምትገኝ አንዲት እህት ስለ ኢራይዳ ሁኔታ ስትሰማ ሄዳ ካነጋገረቻት በኋላ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! b የተባለውን ብሮሹር አበረከተችላት። ኢራይዳ ሥዕላዊ መግለጫዎቹን በመመልከት ስለ መጪው አዲስ ዓለም ያወቀችው ነገር እጅግ አስደሰታት። ከዚያም ብሮሹሩን ከይሖዋ ምሥክሯ ጋር ማጥናት ጀመረች። ብሮሹሩን አጥንተው ሲጨርሱ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?* በተባለው ሌላ ብሮሹር ጥናታቸውን ቀጠሉ። በዚህ ጊዜ ኢራይዳ ለጥናቷ ስትዘጋጅ እንድትረዳትና አንዳንድ ሐሳቦችን እንድታብራራላት እናቷን መጠየቅ ጀመረች።

ኤልሳ ሁለት ችግሮች ነበሩባት፤ የይሖዋ ምሥክር ባለመሆኗ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ካለማወቋም ሌላ የምልክት ቋንቋ አትችልም። ከዚህ ቀደም ልጇ መናገር እንድትችል ሲባል በምልክት ቋንቋ እንዳታነጋግራት ተመክራ ነበር። በመሆኑም በእናትና በልጅ መካከል ያለው ግንኙነት የተገደበ ነበር። በኋላም ኤልሳ፣ ኢራይዳን ለመርዳት ስትል፣ በምልክት ቋንቋ ቡድን ውስጥ ያለች አንዲት እህት እንድታስጠናት ጠየቀች። ኤልሳ እንዲህ ትላለች:- “ጥያቄውን ያቀረብኩት ለልጄ ስል ነው፤ ምክንያቱም ኢራይዳ ለምንም ነገር እንደዚያ ስትጓጓ አይቼያት አላውቅም።” እርሷም እንደ ልጇ ማጥናት የጀመረች ሲሆን የምልክት ቋንቋም ተማረች። ከልጇ ጋር ብዙ ጊዜ ባሳለፈች መጠን ቤታቸው ውስጥ ያለው የሐሳብ ግንኙነትም የዚያኑ ያህል ተሻሻለ። ኢራይዳ በጓደኛ አመራረጧም ረገድ ጠንቃቃ ከመሆኗም በላይ ጉባኤ መሄድ ጀመረች። አሁን እናትና ልጅ የጉባኤው አዘውታሪ ተሰብሳቢዎች ናቸው። ኤልሳ በቅርቡ ተጠምቃለች፤ ኢራይዳም ብትሆን እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ እድገት እያደረገች ነው። ኤልሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ልጇን ማወቅ እንደቻለችና አሁን ለሁለቱም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እያነሱ እንደሚጨዋወቱ ትናገራለች።

ይህ የምልክት ቋንቋ ቡድን በሚያዝያ 2003 ጉባኤ ሆኗል፤ አሁን 50 የሚሆኑ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ሲኖሩት የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር ግን ከዚህ ይበልጣል። ከእነዚህ ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሆኑት መስማት የተሳናቸው ናቸው። በአሁኑ ወቅት ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ ከሚታይባት ከፓናማ ሲቲ ውጪ በሚገኙ ሦስት ከተሞች ሌሎች የምልክት ቋንቋ ቡድኖች ተቋቁመዋል። በዚህ መስክ ገና ብዙ የሚሠራ ነገር ቢኖርም ይህ እርምጃ መስማት በተሳናቸው ልበ ቅን ሰዎችና በአፍቃሪ ፈጣሪያቸው በይሖዋ አምላክ መካከል የነበረውን “ዝምታ” ለማስቀረት የሚያስችል መሸጋገሪያ ድልድይ መሆኑ አያጠራጥርም።

እስካሁን የተመለከትናቸው ተሞክሮዎች በፓናማ ምን እየተከናወነ እንዳለ የሚያሳዩ ናቸው። ብዙዎች ከተለያየ ባሕል፣ ቋንቋና አስተዳደግ ቢመጡም እንኳ እውነተኛውን አምላክ በማምለክ አንድ ሆነዋል። በብዙዎች ዘንድ “ዓለምን የምታገናኝ ድልድይ” እንደሆነች ተደርጋ በምትቆጠረው በዚህች አገር ከሰዎች ጋር ለመነጋገር እንቅፋቶች የነበሩ ቢሆንም የይሖዋን ቃል እውነት ማስተላለፍ ተችሏል።—ኤፌሶን 4:4

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

[በገጽ  8 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ካሪቢያን ባሕር

ፓናማ

ቶቦቢ

ፓስፊክ ውቅያኖስ

ፓናማ ካናል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ካርታ]

ጥልፍ የያዙ የኩና ሴቶች

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት ሚስዮናዊ ለንጎቤ ሴት ስትመሰክር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በንጎቤ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ልዩ ስብሰባ ለመሄድ ታንኳ ሲሳፈሩ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፓናማ ያለው የባሕልና የቋንቋ ልዩነት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዳይሰራጭ አላደረገውም

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምልክት ቋንቋ “መጠበቂያ ግንብ” ሲጠና

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልሳና ልጇ ኢራይዳ ትርጉም ያለው ውይይት ያደርጋሉ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

መርከብና የኩና ሴቶች:- © William Floyd Holdman/Index Stock Imagery; መንደር:- © Timothy O’Keefe/Index Stock Imagery