በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ”

“እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ”

“እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ”

“የእግዚአብሔር መልእክተኛ . . . እንዲህ ሲል ተናገረ፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ይላል እግዚአብሔር።” —ሐጌ 1:13

1. ኢየሱስ የትኞቹ ታሪኮች በዘመናችን ትንቢታዊ አምሳያ እንደሚኖራቸው ተናግሯል?

 የምንኖረው በጣም ወሳኝ በሆነ የታሪክ ዘመን ላይ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንደሚያሳየው በ1914 ‘የጌታ ቀን’ ጀምሯል። (ራእይ 1:10) ስለ ጌታ ቀን ጥሩ ግንዛቤ ካለህ ኢየሱስ፣ ‘የሰው ልጅ’ በመንግሥቱ ላይ ሥልጣን የሚይዝበትን ጊዜ ‘ከኖኅ ዘመን’ እና ‘ከሎጥ ዘመን’ ጋር እንዳመሳሰለው ሳታውቅ አትቀርም። (ሉቃስ 17:26, 28) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ታሪኮች ትንቢታዊ አምሳያዎች እንደሆኑ ያመለክታል። ይሁንና በጥሞና ልንመረምረው የሚገባ ሌላም ትንቢታዊ አምሳያ አለ።

2. ይሖዋ ለሐጌና ለዘካርያስ ምን ተልእኮ ሰጣቸው?

2 እስቲ ሐጌና ዘካርያስ የተባሉት ዕብራውያን ነቢያት በኖሩበት ዘመን የነበረውን ሁኔታ መለስ ብለን እንመልከት። እነዚህ ሁለት ታማኝ ነቢያት በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚችሉት ምን መልእክት አስተላልፈዋል? ሐጌና ዘካርያስ፣ አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ ወደ ሕዝቡ የተላኩ ‘የእግዚአብሔር መልእክተኞች’ ነበሩ። እነዚህ ነቢያት ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ግንባታ ረገድ እስራኤላውያንን እንደሚደግፋቸው እንዲናገሩ ተልከው ነበር። (ሐጌ 1:13፤ ዘካርያስ 4:8, 9) ሐጌና ዘካርያስ የጻፏቸው መጻሕፍት አጫጭር ቢሆኑም ‘ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናትና በጽድቅ መንገድ ለመምከር የሚጠቅሙት የአምላክ መንፈስ ያለባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት’ ክፍል ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ለሐጌና ለዘካርያስ ትንቢቶች ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል

3, 4. ለሐጌና ለዘካርያስ ትንቢቶች ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

3 የሐጌና የዘካርያስ መልእክቶች በዘመኑ ለነበሩት አይሁዶች ጠቃሚ እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም፤ የተናገሯቸው ትንቢቶችም በወቅቱ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ይሁንና በዛሬው ጊዜ የምንኖረው ክርስቲያኖች ለእነዚህ ሁለት መጻሕፍት ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል የምንለው ለምንድን ነው? ዕብራውያን 12:26-29 መልሱን ይጠቁመናል። እዚያ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ ‘ሰማያትንና ምድርን እንደሚያናውጥ’ የሚገልጸውን ሐጌ 2:6ን ጠቅሷል። ይህ ነውጥ በመጨረሻ ‘የመንግሥታትን ዙፋን ይገለብጣል፤ የአሕዛብ መንግሥታትንም ኃይል ያጠፋል።’—ሐጌ 2:22 የ1954 ትርጉም

4 ሐዋርያው ጳውሎስ የሐጌን ትንቢት በመጥቀስ ‘የአሕዛብ መንግሥታት’ ምን እንደሚደርስባቸው ያመለከተ ከመሆኑም በላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚቀበሉት የማይናወጥ መንግሥት ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጿል። (ዕብራውያን 12:28) እንግዲያው የሐጌና የዘካርያስ መጻሕፍት የዕብራውያን መጽሐፍ ከተጻፈበት ከአንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ብዙ ቆይቶ የሚፈጸም ትንቢት እንደያዙ ከጳውሎስ ንግግር መረዳት ትችላለህ። በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ከኢየሱስ ጋር የመሲሐዊው መንግሥት ወራሾች የሆኑ የተቀቡ ክርስቲያኖች በምድር ላይ ይገኛሉ። ስለዚህ የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች በእኛም ዘመን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው።

5, 6. ሐጌና ዘካርያስ አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው በፊት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል?

5 የዕዝራ መጽሐፍ የሐጌና የዘካርያስ መጻሕፍት ከተጻፉበት ዘመን በፊት የነበረውን ታሪካዊ ሁኔታ ይገልጻል። አይሁዳውያን በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ፣ በገዥው በዘሩባቤልና በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ የበላይ ተቆጣጣሪነት በ536 ከክርስቶስ ልደት በፊት የአዲሱ ቤተ መቅደስ መሠረት ተጣለ። (ዕዝራ 3:8-13፤ 5:1) ይህ በጣም የሚያስደስት ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ አይሁዳውያን በፍርሃት ተዋጡ። ዕዝራ 4:4 እንደሚገልጸው ጠላቶቻቸው የሆኑት “የምድሪቱ ነዋሪዎች የይሁዳን ሕዝብ ተስፋ ማስቈረጥና ሥራውንም እንዳይቀጥሉ ማስፈራራት ጀመሩ።” እነዚህ ተቃዋሚዎች በተለይ ደግሞ ሳምራውያን በአይሁዶች ላይ የሐሰት ክሶች በመሰንዘር የፋርሱ ንጉሥ የቤተ መቅደሱን ግንባታ የሚያስቆም ትእዛዝ እንዲያወጣ አደረጉ።—ዕዝራ 4:10-21

6 አይሁዳውያን መጀመሪያ ላይ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የነበራቸው የጋለ ስሜት እየቀዘቀዘ ሄደ። ሕዝቡ በግል ጉዳዮቻቸው ተጠመዱ። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ የቤተ መቅደሱ መሠረት ከተጣለ ከ16 ዓመታት በኋላ ማለትም በ520 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሕዝቡ የቤተ መቅደሱን ሥራ ዳግመኛ እንዲጀምር ለማነቃቃት ሐጌንና ዘካርያስን አስነሳ። (ሐጌ 1:1፤ ዘካርያስ 1:1) አይሁዳውያን፣ የአምላክ መልእክተኞች ስላበረታቷቸውና ይሖዋ እንደሚደግፋቸው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ስለሰጧቸው የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደገና በመጀመር በ515 ከክርስቶስ ልደት በፊት ግንባታውን አጠናቀቁ።—ዕዝራ 6:14, 15

7. በሐጌና በዘካርያስ ዘመን የነበረው ሁኔታ በዘመናችን ካለው ከየትኛው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል?

7 ይህ ሁሉ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው ታውቃለህ? በዛሬው ጊዜ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ከመስበክ ጋር በተያያዘ የምናከናውነው ሥራ አለ። (ማቴዎስ 24:14) ለዚህ ሥራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነበር። የጥንት አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ቃል በቃል ነፃ እንደወጡ ሁሉ በዚህ ዘመን ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ ወጥተዋል። በመንፈስ የተቀቡት የአምላክ አገልጋዮች በስብከቱ፣ በማስተማሩና ሰዎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ በመምራቱ ሥራ መካፈል ጀመሩ። ይህ ሥራ በዛሬው ጊዜ በስፋት እየተከናወነ ሲሆን አንተም በሥራው ትካፈል ይሆናል። የዚህ ክፉ ሥርዓት መደምደሚያ በጣም ስለተቃረበ ሥራው ሊከናወን የሚገባው አሁን ነው! ከአምላክ የተሰጠን ይህ ሥራ ይሖዋ በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት “ታላቅ መከራ” እስኪደርስ ድረስ መቀጠል ይኖርበታል። (ማቴዎስ 24:21) በዚያ ወቅት ክፋት በሙሉ ተወግዶ እውነተኛው አምልኮ በምድር ሁሉ ላይ ይስፋፋል።

8. አምላክ ሥራችንን እንደሚደግፈው እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

8 የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች እንደሚያሳዩት በስብከቱ ሥራ በሙሉ ልባችን ስንሳተፍ የይሖዋን ድጋፍና በረከት እንደምናገኝ ልንተማመን እንችላለን። አንዳንዶች የአምላክን አገልጋዮች ለማገድ ወይም ከአምላክ የተሰጣቸውን ሥራ ለማስቆም ጥረት ቢያደርጉም የወንጌላዊነቱ ሥራ እንዳይስፋፋ ማድረግ የቻለ መንግሥት ግን የለም። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እስከ ዘመናችን ድረስ ባለፉት በርካታ አሥርተ ዓመታት ውስጥ ይሖዋ የመንግሥቱ ሥራ እያደገ እንዲሄድ በማድረግ እንዴት እንደባረከው አስብ። ይሁንና አሁንም ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ።

9. በጥንት ዘመን በነበረው በየትኛው ሁኔታ ላይ ትኩረት እናደርጋለን? ለምንስ?

9 ከሐጌና ከዘካርያስ መጻሕፍት የምናገኘው ትምህርት እንድንሰብክና እንድናስተምር የተሰጠንን መለኮታዊ ትእዛዝ ለመፈጸም ይበልጥ የሚያነሳሳን እንዴት ነው? እስቲ ከእነዚህ ሁለት መጻሕፍት የምናገኛቸውን ትምህርቶች እንመልከት። ለአብነት ያህል፣ ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ካከናወኑት የቤተ መቅደስ ግንባታ ጋር የተያያዙ ጥቂት ዝርዝር ጉዳዮችን እንመርምር። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን የቤተ መቅደሱን ግንባታ አልቀጠሉበትም። መሠረቱን ከጣሉ በኋላ ሥራው ተጓተተ። ሕዝቡ ምን የተሳሳተ አመለካከት አድሮባቸው ነበር? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ለቁሳዊ ነገሮች ተገቢ አመለካከት መያዝ

10. አይሁዳውያን ምን የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው? ይህስ ምን አስከተለ?

10 ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት አይሁዶች ‘ጊዜው ገና ነው’ ይሉ ነበር። (ሐጌ 1:2) በ536 ከክርስቶስ ልደት በፊት መሠረቱን በመጣል የቤተ መቅደሱን ግንባታ በጀመሩበት ወቅት ‘ጊዜው ገና ነው’ የሚል አመለካከት አልነበራቸውም። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በአካባቢያቸው የሚኖሩ ሰዎች ተቃውሞና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ተጽዕኖ አሳደረባቸው። አይሁዳውያኑ ስለ ራሳቸው ቤቶችና ስለ ምቾታቸው ይበልጥ ማሰብ ጀመሩ። ይሖዋ፣ ምርጥ በሆነ እንጨት በተዋበው የግል ቤታቸውና ግንባታው ባልተጠናቀቀው ቤተ መቅደስ መካከል ያለውን ልዩነት በማነጻጸር “ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ፣ እናንተ ራሳችሁ በተዋቡ ቤቶቻችሁ ውስጥ ለመኖር ጊዜው ነውን?” ሲል ጠይቋቸዋል።—ሐጌ 1:4

11. ይሖዋ በሐጌ ዘመን ለነበሩት አይሁዳውያን ምክር መስጠት ያስፈለገው ለምን ነበር?

11 አዎን፣ አይሁዶች ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ነገር ቅድሚያ አልሰጡም። የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋ ቤተ መቅደሱ እንዲገነባ ያለውን ዓላማ ከማስቀደም ይልቅ ለራሳቸው ምቾትና ለግል ቤቶቻቸው የበለጠ ትኩረት ከመስጠታቸውም በላይ የይሖዋን የአምልኮ ቤት ግንባታ ቸል ብለውት ነበር። በሐጌ 1:5 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የይሖዋ ቃል አይሁዳውያኑ ‘መንገዳቸውን ልብ እንዲሉ’ አሳስቧቸዋል። ይሖዋ እያደረጉ ያሉትን ነገር ቆም ብለው እንዲያስቡና በሕይወታቸው ውስጥ ለቤተ መቅደሱ የግንባታ ሥራ ቅድሚያ ባለመስጠታቸው ምን እንደደረሰባቸው እንዲያስተውሉ ማሳሰቡ ነበር።

12, 13. ሐጌ 1:6 የአይሁዳውያኑን ሁኔታ የሚገልጸው እንዴት ነው? ይህ ጥቅስ ምን ትርጉም አለው?

12 ከሁኔታው መገመት እንደምትችለው አይሁዳውያን ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ነገር ቅድሚያ አለመስጠታቸው በግለሰብ ደረጃ ጎድቷቸው ነበር። አምላክ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ በሐጌ 1:6 ላይ እንዲህ ብሏል:- “ብዙ ዘራችሁ፤ ነገር ግን ያጨዳችሁት ጥቂት ነው፤ በላችሁ ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዝን ተቀበላችሁ፤ ግን በቀዳዳ ኰረጆ የማስቀመጥ ያህል ነው።”

13 አይሁዳውያን አምላክ በሰጣቸው ምድር ላይ የነበሩ ቢሆንም ምድሪቱ የፈለጉትን ያህል ምርት አልሰጠቻቸውም። ይሖዋ አስቀድሞ ባስጠነቀቃቸው መሠረት በረከቱን ነፍጓቸው ነበር። (ዘዳግም 28:38-48) ዘር ቢዘሩም እንኳ የይሖዋ ድጋፍ ስላልነበራቸው ያጨዱት ጥቂት ነው፤ ፍላጎታቸውን የሚያረካ በቂ እህል አላገኙም። የይሖዋን በረከት ስላጡ የሚሞቁ ልብሶች መልበስ አልቻሉም። ሌላው ቀርቶ ደሞዛቸው እንኳ ለደሞዝተኞቹ ምንም ጥቅም ሊሰጥ ባለመቻሉ በቀዳዳ ኮረጆ የተቀመጠ ያህል ሆኖ ነበር። “ጠጣችሁ ግን አልረካችሁም” የሚለው አገላለጽስ ምን ትርጉም አለው? ይህም ቢሆን አይሁዳውያን የይሖዋ በረከት እንደራቃቸው የሚያመለክት ነው። የሚያመርቱት ወይን በጣም ትንሽ ስለሚሆን ጠጥተው ሊረኩ አይችሉም።

14, 15. ከሐጌ 1:6 ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 ከእነዚህ ጥቅሶች የምናገኘው ትምህርት፣ ቤት ስለ መገንባት ወይም ስለ ማሳመር አይደለም። አይሁዳውያን ወደ ግዞት ከመሄዳቸው ከረጅም ዓመታት በፊት ነቢዩ አሞጽ፣ በእስራኤል ውስጥ የነበሩ ሀብታሞች ‘በዝሆን ጥርስ ባጌጡ ቤቶች’ ውስጥ በመኖራቸውና ‘በዝሆን ጥርስ ባጌጠ ዐልጋ ላይ በመተኛታቸው’ ወቅሷቸው ነበር። (አሞጽ 3:15፤ 6:4) ሆኖም ያማሩ ቤቶቻቸውና ያጌጡ ዕቃዎቻቸው ብዙም አልቆዩም። ጠላቶቻቸው ንብረታቸውን ዘርፈውባቸው ነበር። ያም ሆኖ ግን፣ የአምላክ ሕዝቦች ለ70 ዓመታት በግዞት ከኖሩ በኋላም እንኳ አብዛኞቹ ከዚህ ሁኔታ ትምህርት አላገኙም። እኛስ? እያንዳንዳችን እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን በሐቀኝነት ብንጠይቅ ተገቢ ይሆናል:- ‘ቤቴን ስለ ማሳመር ምን ያህል እጨነቃለሁ? ለበርካታ ዓመታት ሊዘልቅና አስፈላጊ ለሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ ሊያሳጣኝ ቢችልም በሥራዬ እድገት ለማግኘት ስል ተጨማሪ ትምህርት ስለመከታተልስ ምን ይሰማኛል?’—ሉቃስ 12:20, 21፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:17-19

15 በሐጌ 1:6 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በሕይወታችን ውስጥ የአምላክ በረከት እንደሚያስፈልገን ሊያስገነዝበን ይገባል። የጥንቶቹ አይሁዳውያን የአምላክን በረከት ማጣታቸው ጎድቷቸዋል። እኛም በቁሳዊ ነገሮች ሀብታሞች ብንሆንም ባንሆንም የይሖዋን በረከት ካላገኘን ከአምላክ ጋር ያለን ግንኙነት እንደሚበላሽ ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 25:34-40፤ 2 ቆሮንቶስ 9:8-12) ይሁን እንጂ የአምላክን በረከት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ይረዳናል

16-18. ዘካርያስ 4:6 ለጥንቶቹ አይሁዳውያን ምን ትርጉም ነበረው?

16 ነቢዩ ዘካርያስም ይሖዋ በዚያ ዘመን ለእርሱ ያደሩ ሰዎችን ለሥራ ለማንቀሳቀስና ለመባረክ የሚጠቀምበትን መንገድ እንዲናገር ተልኮ ነበር። ይህ መልእክት ይሖዋ አንተንም የሚባርክህ እንዴት እንደሆነ ያሳያል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “‘በመንፈሴ እንጂ በኀይልና በብርታት አይደለም’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።” (ዘካርያስ 4:6) ይህ ጥቅስ ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ ሰምተህ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ጥቅሱ በሐጌና በዘካርያስ ዘመን ለነበሩት አይሁዶች ምን ትርጉም ነበረው? ለአንተስ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

17 በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩት የሐጌና የዘካርያስ ቃላት በዚያ ወቅት ግሩም ውጤት እንዳስገኙ ማስታወስ ያስፈልገናል። እነዚህ ሁለት ነቢያት የተናገሩት መልእክት ታማኝ የነበሩትን አይሁዳውያን መንፈስ አነቃቅቷል። ሐጌ ትንቢት መናገር የጀመረው በ520 ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው ወር ላይ ነው። ዘካርያስ ደግሞ መተንበይ የጀመረው በዚያው ዓመት በስምንተኛው ወር ላይ ነው። (ዘካርያስ 1:1) ሐጌ 2:18 እንደሚገልጸው የቤተ መቅደሱ መሠረት ግንባታ በተጠናከረ ሁኔታ እንደገና የተጀመረው በዘጠነኛው ወር ነው። ስለዚህ አይሁዳውያን ለሥራ የተነሳሱ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ እንደሚደግፋቸው ሙሉ በሙሉ በመተማመን ቃሉን ታዘዋል። ዘካርያስ 4:6 አምላክ እንደሚደግፋቸው ያሳያል።

18 አይሁዳውያን በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ኃይል አልነበራቸውም። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ ከባቢሎን ወደ አገራቸው ሲጓዙ የመራቸው ከመሆኑም በላይ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የቤተ መቅደሱ ግንባታ ሲጀመር በመንፈሱ ይመራቸው ነበር። በሙሉ ልባቸው እንደገና መሥራት ከጀመሩ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይደግፋቸዋል።

19. የአምላክ መንፈስ የትኛውን ከባድ ተጽዕኖ አሸንፏል?

19 ዘካርያስ ተከታታይ በሆኑ ስምንት መለኮታዊ ራእዮች አማካኝነት፣ ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ሥራ እስከ ፍጻሜው ድረስ በታማኝነት ከሚካፈሉ ሕዝቦቹ ጎን እንደሚሆን ማረጋገጫ ተሰጥቶት ነበር። ምዕራፍ 3 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው አራተኛው ራእይ ሰይጣን፣ አይሁዳውያን የቤተ መቅደሱን ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያደርጉትን ጥረት ይቃወም እንደነበረ ያሳያል። (ዘካርያስ 3:1) ሰይጣን፣ ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ በአዲሱ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሕዝቡን ወክሎ የክህነት አገልግሎት ሲያከናውን ማየት እንደማያስደስተው የተረጋገጠ ነው። ዲያብሎስ አይሁዳውያን የሚያከናውኑትን የቤተ መቅደስ ግንባታ ለማደናቀፍ ይጥር የነበረ ቢሆንም የይሖዋ መንፈስ እንቅፋቶችን በማስወገድና የቤተ መቅደሱ ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ወደኋላ እንዳይሉ አይሁዳውያንን በማበርታት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

20. መንፈስ ቅዱስ አይሁዳውያን የአምላክን ፈቃድ እንዲፈጽሙ የረዳቸው እንዴት ነበር?

20 የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በቤተ መቅደሱ ግንባታ ሥራ ላይ እገዳ እንዲጣል በማድረጋቸው አይሁዳውያን መወጣት የማይችሉት መሰናክል የተደቀነባቸው ይመስል ነበር። ሆኖም ይሖዋ ይህ “ተራራ” የሚመስል እንቅፋት እንደሚወገድና “ደልዳላ ሜዳ” እንደሚሆን ቃል ገብቶ ነበር። (ዘካርያስ 4:7) የተፈጸመውም ይኸው ነው! ቀዳማዊ ዳርዮስ ምርመራ እንዲካሄድ ሲያደርግ አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን ዳግመኛ እንዲገነቡ ቂሮስ ያወጣውን አዋጅ አገኘ። በዚህም ምክንያት የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ከማድረጉም በተጨማሪ አይሁዳውያን የግንባታውን ወጪ መሸፈን የሚችሉበት ገንዘብ ከመንግሥት ግምጃ ቤት እንዲሰጣቸው አዝዟል። ሁኔታዎቹ እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ ተለዋወጡ! የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በዚህ ረገድ የተጫወተው ሚና ነበር? ምንም ጥርጥር የለውም። የቤተ መቅደሱ ግንባታ በ515 ከክርስቶስ ልደት በፊት በቀዳማዊ ዳርዮስ ስድስተኛ የግዛት ዘመን ተጠናቀቀ።—ዕዝራ 6:1, 15

21. (ሀ) በጥንት ጊዜ አምላክ ‘ሕዝቦችን ሁሉ ያናወጠው’ እንዴት ነበር? ይህ ሁኔታ ‘የሕዝቦች ሀብት’ በተባሉት ላይ ምን ውጤት አስከትሏል? (ለ) ይህ ትንቢት በዘመናችን የተፈጸመው እንዴት ነው?

21 በሐጌ 2:5 ላይ ነቢዩ፣ አይሁዳውያን በሲና ተራራ ግርጌ ከአምላክ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አስታውሷቸዋል፤ በዚያን ጊዜ ‘ተራራው በሙሉ በኀይል ተናውጦ’ ነበር። (ዘፀአት 19:18) በቁጥር 6 እና 7 ላይ ምሳሌያዊ በሆነ አነጋገር በተገለጸው መሠረት ይሖዋ በሐጌና በዘካርያስ ዘመን ሌላ ነውጥ ለማካሄድ ተዘጋጅቶ ነበር። በፋርስ ግዛት ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ ባይኖርም የቤተ መቅደሱ ግንባታ ግን በተሳካ ሁኔታ ይጠናቀቃል። “የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ” የተባሉት አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች በዚያ የአምልኮ ሥፍራ ከአይሁዳውያን ጋር ሆነው አምላክን ያወድሳሉ። በዘመናችን አምላክ በክርስቲናያዊው የስብከት ሥራችን አማካኝነት በታላቅ ሁኔታ ‘ሕዝቦችን በማናወጡ’፣ “የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ” የተባሉት ሰዎች ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ሆነው እርሱን ማምለክ ጀምረዋል። በእውነትም ቅቡዓኑና ሌሎች በጎች በአንድነት ሆነው የይሖዋን ቤት በክብር እየሞሉት ነው። እነዚህ እውነተኛ አምላኪዎች ይሖዋ “ሰማያትንና ምድርን” ለየት ባለ መንገድ ‘የሚያናውጥበትን’ ጊዜ በእምነት ይጠባበቃሉ። ይሖዋ በዚያን ጊዜ የአሕዛብን መንግሥታት ኃይል በመገልበጥ ያጠፋቸዋል።—ሐጌ 2:22

22. አሕዛብ ‘የተናወጡት’ እንዴት ነው? ይህ ምን ውጤት አስከትሏል? ወደፊትስ ምን ይፈጸማል?

22 የሐጌ ትንቢት ‘በሰማያትና በምድር እንዲሁም በባሕርና በየብስ’ በተመሰሉት የተለያዩ ነገሮች ላይ የተከሰተውን ነውጥ እንድናስታውስ ያደርገናል። በመጀመሪያ ደረጃ ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ወደ ምድር ተወርውረዋል። (ራእይ 12:7-12) ከዚህም በላይ በአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች ግንባር ቀደምትነት የሚካሄደው የስብከቱ ሥራ የዚህን ሥርዓት ምድራዊ ኃይሎች አናውጧል። (ራእይ 11:18) ያም ሆኖ የሕዝቦች ሁሉ ሀብት የሆነው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ይሖዋን በማገልገል ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር ተባብሯል። (ራእይ 7:9, 10) እጅግ ብዙ ሰዎች አምላክ በቅርቡ አሕዛብን በአርማጌዶን እንደሚያናውጣቸው የሚገልጸውን ወንጌል ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጎን ተሰልፈው እየሰበኩ ነው። ይህ ክንውን እውነተኛው አምልኮ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ፍጹም ወደሆነ ደረጃ እንዲደርስ መንገድ ይጠርጋል።

ታስታውሳለህ?

• ሐጌና ዘካርያስ ያገለገሉት መቼና በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነበር?

• ሐጌና ዘካርያስ ያስተላለፉትን መልእክት ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

በዘካርያስ 4:6 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የሚያበረታታ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች ይሖዋ እንደሚደግፈን ያረጋግጡልናል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ፣ እናንተ ራሳችሁ በተዋቡ ቤቶቻችሁ ውስጥ ለመኖር ጊዜው ነውን?”

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ አገልጋዮች ‘የሕዝቦች ሀብት’ የተባሉትን በማምጣቱ ሥራ ይካፈላሉ