በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እጃችሁን አበርቱ

እጃችሁን አበርቱ

እጃችሁን አበርቱ

“ነቢያት የተናገሩትን ቃል አሁን የምትሰሙ ሁሉ . . . እጃችሁን አበርቱ።” —ዘካርያስ 8:9

1, 2. ለሐጌና ለዘካርያስ መጻሕፍት ትኩረት መስጠት የሚገባን ለምንድን ነው?

 የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች የተጻፉት ከ2,500 ዓመታት በፊት ቢሆንም ለሕይወትህ የሚጠቅም ትምህርት ይዘዋል። በእነዚህ ሁለት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ታሪክ ብቻ አይደሉም። ‘ለትምህርታችን ቀደም ብለው የተጻፉት’ መጻሕፍት ክፍል ናቸው። (ሮሜ 15:4) በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የሰፈረው አብዛኛው ዘገባ በ1914 የአምላክ መንግሥት በሰማይ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በመከናወን ላይ ያሉትን ሁኔታዎች እንድናስብ ያደርገናል።

2 ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንት ዘመን የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች የገጠሟቸውን ሁኔታዎች በመጥቀስ “ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) በመሆኑም ‘የሐጌና የዘካርያስ መጻሕፍት ለዚህ ዘመን ምን ጥቅም አላቸው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

3. ሐጌና ዘካርያስ ትኩረት ያደረጉት በምን ላይ ነበር?

3 ከዚህ በፊት የነበረው የጥናት ርዕስ እንዳመለከተው የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ወጥተው አምላክ ወደሰጣቸው ምድር ከተመለሱበት ወቅት ጋር የተያያዙ ናቸው። ሁለቱም ነቢያት ትኩረት ያደረጉት ቤተ መቅደሱ ዳግመኛ በመገንባቱ ላይ ነበር። አይሁዳውያን በ536 ከክርስቶስ ልደት በፊት የቤተ መቅደሱን መሠረት ጣሉ። አንዳንድ በዕድሜ የገፉ አይሁዳውያን ትኩረት ያደረጉት በቀድሞዎቹ ዘመናት ላይ ቢሆንም ሕዝቡ በአጠቃላይ ግን “የደስታ ጩኸት” አሰምተው ነበር። በዘመናችን ከዚያ እጅግ የላቀ ነገር ተከናውኗል። እንዴት?—ዕዝራ 3:3-13

4. አንደኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ምን ተከናወነ?

4 አንደኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ ወጥተዋል። ይህም ይሖዋ እንደሚደግፋቸው የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነበር። ከዚያ ቀደም የሃይማኖት መሪዎችና የፖለቲካ አጋሮቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያካሂዱትን የስብከትና የማስተማር ሥራ ማስቆም የቻሉ መስሎ ነበር። (ዕዝራ 4:8, 13, 21-24) ሆኖም ይሖዋ አምላክ የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ እንዲስተጓጎል ያደረጉትን እንቅፋቶች አስወግዷቸዋል። ከ1919 ወዲህ ባለፉት በርካታ አሥርተ ዓመታት የመንግሥቱ ሥራ በእጅጉ የተስፋፋ ከመሆኑም በላይ እድገቱን ምንም ነገር ሊገታው አልቻለም።

5, 6. ዘካርያስ 4:7 የትኛውን ታላቅ ክንውን ያመለክታል?

5 በጊዜያችን ታዛዥ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች የሚያከናውኑት የስብከትና የማስተማር ሥራም በአምላክ ድጋፍ እንደሚቀጥል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ዘካርያስ 4:7 “ሰዎች፣ ‘ሞገስ ይሁንለት! ሞገስ ይሁንለት!’ ብለው እየጮኹ፣ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል” ይላል። ይህ በዘመናችን የትኛውን ታላቅ ክንውን ያመለክታል?

6 ዘካርያስ 4:7 የሉዓላዊው ጌታ እውነተኛ አምልኮ በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ምድራዊ አደባባይ ላይ ወደ ፍጽምና ደረጃ የሚደርስበትን ጊዜ የሚያመለክት ነው። ይህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ኃጢአትን በሚያስተሰርየው የክርስቶስ ኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት በአምልኮ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚቻልበት የአምላክ ዝግጅት ነው። ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንስቶ እንደነበረ አይካድም። ሆኖም እውነተኛው አምልኮ በምድራዊው አደባባይ ወደ ፍጽምና ደረጃ መድረስ ይኖርበታል። በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ አምላኪዎች በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ያገለግላሉ። እነዚህና ከሞት የሚነሱት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። ይህ ሺህ ዓመት ሲያበቃ በጸዳችው ምድር ላይ የሚቀሩት እውነተኛዎቹ የይሖዋ አምላኪዎች ብቻ ይሆናሉ።

7. በዘመናችን እውነተኛውን አምልኮ ወደ ፍጽምና ደረጃ በማምጣት ረገድ ኢየሱስ ምን ሚና ይጫወታል?

7 ገዥው ዘሩባቤልና ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ በ515 ከክርስቶስ ልደት በፊት የቤተ መቅደሱ ግንባታ ሲጠናቀቅ መመልከት ችለዋል። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ኢየሱስ እውነተኛውን አምልኮ ወደ ፍጽምና ደረጃ በማምጣት ረገድ ስለሚጫወተው ሚና በዘካርያስ 6:12, 13 [የ1954 ትርጉም] ላይ ተተንብዮአል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነሆ፤ ስሙ ቁጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፣ የእግዚአብሔርንም መቅደስ ይሠራል። እርሱ . . . ክብርንም ይሸከማል፣ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል።” በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ የሚካሄደውን የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ የሚደግፈው በሰማይ ያለውና የዳዊት የነገሥታት የዘር ሐረግ እንዲያቆጠቁጥ የሚያደርገው ኢየሱስ በመሆኑ ሥራውን ሊገታው የሚችል ሰው የሚኖር ይመስልሃል? በፍጹም አይኖርም! ይህ ሁኔታ በዕለት ተዕለት የኑሮ ጭንቀቶች ሳንዘናጋ አገልግሎታችንን እንድናከናውን ሊያበረታታን አይገባም?

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች

8. በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ለሚከናወነው ሥራ በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ልንሰጠው የሚገባን ለምንድን ነው?

8 የይሖዋን ድጋፍና በረከት ማግኘት እንድንችል በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ለሚከናወነው ሥራ በሕይወታችን ውስጥ ምንጊዜም ቀዳሚውን ቦታ ልንሰጠው ይገባል። ‘ጊዜው ገና ነው’ ይሉ ከነበሩት አይሁዶች በተለየ መልኩ ዛሬ የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (ሐጌ 1:2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) ኢየሱስ፣ ታማኝ ተከታዮቹ የመንግሥቱን ምሥራች እንደሚሰብኩና ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርጉ አስቀድሞ ተናግሯል። ይህን የአገልግሎት መብታችንን ቸል እንዳንል መጠንቀቅ ይኖርብናል። ዓለም ባስነሳው ተቃውሞ ሳቢያ ለተወሰነ ጊዜ የተስተጓጎለው የስብከትና የማስተማር ሥራ በ1919 እንደገና ቢጀመርም ገና አልተጠናቀቀም። ሆኖም ይህ ሥራ መጠናቀቁ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ!

9, 10. አንድ ሰው የይሖዋን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት? ይህስ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

9 ሥራውን በትጋት ማከናወናችንን ከቀጠልን በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የዚያኑ ያህል እንባረካለን። ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆነንን ይሖዋ የገባውን ቃል ልብ በል። አይሁዳውያን ይሖዋን በሙሉ ልባቸው ማምለክና የቤተ መቅደሱን መሠረት በደንብ መሥራት በጀመሩ ጊዜ ይሖዋ “ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ” ሲል ቃል ገብቶላቸዋል። (ሐጌ 2:19) የእርሱን ሞገስ ሙሉ በሙሉ ያገኛሉ። አሁን ደግሞ አምላክ እንደሚባርካቸው የገባውን ተስፋ ተመልከት:- “ሰላምን እዘራለሁ፤ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፣ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፣ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ ለዚህም ሕዝብ ቅሬታ ይህን ነገር ሁሉ አወርሳለሁ።”—ዘካርያስ 8:9-13 የ1954 ትርጉም

10 ይሖዋ አይሁዳውያንን በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ እንደባረካቸው ሁሉ እኛም የሰጠንን ሥራ በትጋትና በደስታ የምናከናውን ከሆነ ይባርከናል። እነዚህ በረከቶች በመካከላችን ያለውን ሰላም፣ ደኅንነት፣ ብልጽግናና መንፈሳዊ እድገት ያጠቃልላሉ። ይሁንና አምላክ እኛን መባረኩን የሚቀጥለው በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ እርሱ በሚፈልገው መንገድ የምንሠራ ከሆነ ብቻ ነው።

11. በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ረገድ ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?

11 አሁን ‘መንገዳችንን ልብ የምንልበት’ ጊዜ ነው። (ሐጌ 1:5, 7) ሁላችንም ጊዜ ወስደን በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ስለምንሰጣቸው ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ የሚባርከን ስሙን የምናወድስና በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ የምንሠራውን ሥራ በሚገባ የምናከናውን ከሆነ ነው። ራስህን እንደሚከተለው እያልክ መጠየቅ ትችላለህ:- ‘በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጣቸው ነገሮች ተቀይረዋል? ለይሖዋ፣ ለእውነትና እርሱ ለሰጠን ሥራ ያለኝ ቅንዓት ስጠመቅ እንደነበረው ነው? የተደላደለ ሕይወት ለመምራት ያለኝ ፍላጎት በይሖዋና በመንግሥቱ ላይ ትኩረት እንዳላደርግ ተጽዕኖ እያሳደረብኝ ነው? የሰው ፍርሃት ማለትም ሌሎች ምን ይሉኛል ብሎ መጨነቅ ይሖዋን እንዳላወድስና በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ በሚከናወነው ሥራ እንዳልቀጥል እንቅፋት እየሆነብኝ ነው?’—ራእይ 2:2-4

12. ሐጌ 1:6, 9 እንደሚገልጸው አይሁዳውያን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነበሩ?

12 የአምላክን ስም የማወደሱን ሥራ ችላ በማለታችን የተነሳ የይሖዋ የተትረፈረፈ በረከት እንዲቀርብን አንፈልግም። ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን የቤተ መቅደሱን ግንባታ በቅንዓት ማከናወን ከጀመሩ በኋላ ሥራውን ትተው ‘ሁሉም የራሳቸውን ቤት ለመሥራት መሯሯጥ’ እንደቀጠሉ የሚገልጸውን የሐጌ 1:9ን ዘገባ አስታውስ። ሕዝቡ በዕለታዊ ፍላጎቶቻቸውና ኑሯቸው ተጠምደው ነበር። በዚህም ምክንያት ‘ያጨዱት ጥቂት ነው፤’ የምግብና የመጠጥ እጥረት ያጋጠማቸው ከመሆኑም ሌላ ሙቀት የሚሰጥ ልብስ ማግኘት አልቻሉም። (ሐጌ 1:6) ይሖዋ በረከቱን ነፍጓቸው ነበር። እኛስ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ይኖር ይሆን?

13, 14. በሐጌ 1:6, 9 ላይ የሚገኘውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

13 የይሖዋን በረከት ማግኘታችንን እንቀጥል ዘንድ የእርሱን አምልኮ ቸል ብለን የራሳችንን ፍላጎቶች ከማሳደድ መቆጠብ ይኖርብናል ቢባል አትስማማም? ሀብት፣ በአጭር ጊዜ ለመክበር ያስችላሉ የሚባሉ ውጥኖች፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ቦታ ለማግኘት ሲባል አድካሚ የሆነ ከፍተኛ ትምህርት የመከታተል ዕቅድ ወይም የግል ፍላጎቶችን ለማርካት ያስችላሉ የሚባሉ ፕሮግራሞች ትኩረታችንን ሊስቡት ይችላሉ፤ ያም ሆነ ይህ ግን የይሖዋን አምልኮ ችላ ብለን የራሳችንን ፍላጎቶች ከማሳደድ መቆጠብ ይኖርብናል።

14 እንዲህ ያሉት ነገሮች በራሳቸው ኃጢአት ላይሆኑ ቢችሉም እንኳ የዘላለም ሕይወት ከማግኘት አንጻር ስንመለከታቸው ‘የሞቱ ሥራዎች’ እንደሆኑ አይሰማህም? (ዕብራውያን 9:14) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመንፈሳዊ የሞቱ፣ ከንቱና ዋጋ ቢስ ነገሮች ናቸው። አንድ ሰው እነዚህን ነገሮች ማሳደዱን ከቀጠለ ለመንፈሳዊ ሞት ይዳርጉታል። በሐዋርያት ዘመን የነበሩ አንዳንድ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ይህ ዓይነቱ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። (ፊልጵስዩስ 3:17-19) በዘመናችንም አንዳንዶች ተመሳሳይ ሁኔታ ደርሶባቸዋል። ቀስ በቀስ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎችንና በጉባኤ መገኘትን ያቆሙ ክርስቲያኖች እንዳሉ ታውቅ ይሆናል፤ እነዚህ ሰዎች ወደ ይሖዋ አገልግሎት የመመለስ ምንም አዝማሚያ የላቸውም። እነዚህ ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ እንደሚመለሱ ተስፋ ብናደርግም ‘የሞቱ ሥራዎችን’ መከታተል የይሖዋን ሞገስና በረከት ሊያሳጣን እንደሚችል ልብ ማለት ይኖርብናል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ምን ያህል አሳዛኝ እንደሚሆን መገንዘብ አያዳግትህም። የአምላክ መንፈስ የሚያስገኘውን ደስታና ሰላም እንድናጣ ያደርገናል። ከዚህም በላይ ፍቅር ከሰፈነበት የወንድማማች ማኅበር ውስጥ መውጣት የሚያስከትለውን ኪሳራም አስበው።—ገላትያ 1:6፤ 5:7, 13, 22-24

15. ሐጌ 2:14 ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ በቁም ነገር ልንመለከተው እንደሚገባ የሚያሳየው እንዴት ነው?

15 ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ይሖዋ ቃል በቃልም ይሁን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ቤታቸውን በማስጌጥ የአምልኮ ቤቱን ችላ ብለው ለነበሩት አይሁዳውያን ምን አመለካከት እንደነበረው የሚገልጸውን ሐጌ 2:14 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ልብ እንበል። “‘ይህ ሕዝብና ይህ ወገንም በፊቴ እንደዚሁ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የእጃቸው ሥራና የሚያቀርቡት ሁሉ የረከሰ ነው።’” ይሖዋን በሙሉ ልባቸው የማያገለግሉት አይሁዳውያን እውነተኛውን አምልኮ ችላ እስካሉ ድረስ ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው ጊዜያዊ መሠዊያ ላይ የሚያቀርቡት ማንኛውም የይስሙላ መሥዋዕት ተቀባይነት አይኖረውም።—ዕዝራ 3:3

አምላክ ታዛዥ አገልጋዮቹን እንደሚደግፍ ማረጋገጫ ሰጠ

16. ዘካርያስ በተመለከታቸው ራእዮች መሠረት አይሁዳውያን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?

16 ዘካርያስ በተከታታይ የተመለከታቸው ስምንት ራእዮች የአምላክን ቤተ መቅደስ ዳግመኛ በመገንባቱ ሥራ ላይ የሚካፈሉት ታዛዥ አይሁዳውያን መለኮታዊ ድጋፍ እንዳላቸው ማረጋገጫ ሆነውላቸዋል። የመጀመሪያው ራእይ አይሁዳውያን ሥራቸውን በታዛዥነት እስካከናወኑ ድረስ የቤተ መቅደሱ ግንባታ እንደሚጠናቀቅና ኢየሩሳሌምና ይሁዳ እንደሚበለጽጉ ዋስትና ሰጥቷቸዋል። (ዘካርያስ 1:8-17) ሁለተኛው ራእይ እውነተኛውን አምልኮ የሚቃወሙ መንግሥታት በሙሉ እንደሚጠፉ የሚያረጋግጥ ነበር። (ዘካርያስ 1:18-21) ሌሎቹ ራእዮች ደግሞ አይሁዳውያን የቤተ መቅደሱን ግንባታ በሚያካሂዱበት ጊዜ አምላክ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው፣ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት እንደሚሰጣቸው፣ አምላክ ያዘዛቸውን ሥራ የሚያስተጓጉሉ ከባድ እንቅፋቶች እንደሚወገዱላቸው፣ መላእክታዊ አመራርና ጥበቃ እንደሚያገኙ እንዲሁም ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ከተለያዩ ብሔራት በርካታ ሰዎች ወደ ይሖዋ አምልኮ ቤት እንደሚጎርፉና ክፋት እንደሚቀር አረጋግጠውላቸዋል። (ዘካርያስ 2:5, 11፤ 3:10፤ 4:7፤ 5:6-11፤ 6:1-8) ታዛዥ የሆኑ አይሁዳውያን መለኮታዊ ድጋፍ እንዳላቸው የሚያረጋግጡ እንዲህ ያሉ ዋስትናዎች ስለተሰጧቸው አኗኗራቸውን አስተካክለው ትኩረታቸውን አምላክ ባዘዛቸው ሥራ ላይ ያደረጉት ለምን እንደሆነ መገንዘብ ትችላለህ። ይሖዋም ከባቢሎን ነፃ ያወጣቸው ይህን ሥራ እንዲያከናውኑ ነበር።

17. አስተማማኝ ከሆነው ተስፋችን አንጻር ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

17 በተመሳሳይም እውነተኛው አምልኮ ድል እንደሚቀዳጅ የተሰጠን አስተማማኝ ዋስትና ለሥራ ሊያነሳሳንና ስለ ይሖዋ የአምልኮ ቤት በቁም ነገር እንድናስብ ሊገፋፋን ይገባል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ሊሠራ የሚገባው አሁን እንደሆነ የማምን ከሆነ ግቦቼም ሆኑ አኗኗሬ ከዚህ ጋር ይስማማሉ? በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ ተገቢ ትኩረት በማድረግ ቃሉን ለማጥናት እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቼም ሆነ ከማገኛቸው ሰዎች ጋር በቃሉ ላይ ለመወያየት በቂ ጊዜ እመድባለሁ?’

18. በዘካርያስ ምዕራፍ 14 መሠረት ወደፊት ምን ይጠብቀናል?

18 ዘካርያስ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት እንዲሁም ከዚያ በኋላ ስለሚመጣው የአርማጌዶን ጦርነት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።” የይሖዋ ቀን በምድር ላይ ላሉ ጠላቶቹ የጨለማና የጭጋግ ቀን ይሆናል! የይሖዋ ታማኝ አምላኪዎች ግን የማያቋርጥ ብርሃንና ሞገስ የሚያገኙበት ጊዜ ይሆናል። ከዚህም በላይ ዘካርያስ፣ በአዲሲቱ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሁሉ የይሖዋን ቅድስና እንደሚያውጅ ገልጿል። በምድር ላይ የሚኖረው አምልኮ፣ በታላቁ የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚከናወነው እውነተኛ አምልኮ ብቻ ይሆናል። (ዘካርያስ 14:7, 16-19) ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ትንቢት ነው! አስቀድሞ የተነገረው ትንቢት ሲፈጸምና የይሖዋ ሉዓላዊነት ሲረጋገጥ እንመለከታለን። ያ ቀን ለይሖዋ የተወሰነ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቀን ይሆናል!

ዘላቂ በረከቶች

19, 20. ዘካርያስ 14:8, 9 የሚያበረታታ የሆነው እንዴት ነው?

19 ከዚህ አስደናቂ ክንውን በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ በጥልቁ ውስጥ ታስረው ከእንቅስቃሴ ውጭ ይሆናሉ። (ራእይ 20:1-3, 7) ከዚያም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን የሰው ልጆች በእጅጉ ይባረካሉ። ዘካርያስ 14:8, 9 እንዲህ ይላል:- “በዚያን ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይፈሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል። እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር አንድ፣ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል።”

20 ይሖዋ ሕይወት እንድናገኝ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች የሚወክለው “የሕይወት ውሃ” ወይም “የሕይወት ውሃ ወንዝ” ከመሲሐዊው መንግሥት ዙፋን ያለማቋረጥ ይፈስሳል። (ራእይ 22:1, 2) ከአርማጌዶን የተረፉ ይሖዋን የሚያመልኩ እጅግ ብዙ ሰዎች ከአዳም ከወረሱት የሞት እርግማን ነፃ በመሆን ከዚህ ዝግጅት ይጠቀማሉ። የሞቱ ሰዎችም እንኳ ሳይቀሩ በትንሣኤ አማካኝነት ከበረከቱ ተካፋይ ይሆናሉ። በዚህ መንገድ በምድር ላይ ይሖዋ የሚገዛበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል። በምድር ላይ ያሉ የሰው ዘሮች በሙሉ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ መሆኑንና ሊመለክ የሚገባው እሱ ብቻ እንደሆነ አምነው ይቀበላሉ።

21. ቁርጥ አቋማችን ምን መሆን አለበት?

21 ሐጌና ዘካርያስ ከተነበዩአቸው ትንቢቶችና ከተፈጸሙት ነገሮች አንጻር ይሖዋ በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ምድራዊ አደባባይ ላይ እንድንሠራው የሰጠንን ሥራ በትጋት እንድናከናውን የሚገፋፋ ጠንካራ ምክንያት አለን። እውነተኛው አምልኮ ወደ ፍጽምና ደረጃ እስከሚደርስበት ጊዜ ድረስ ሁላችንም ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ ለመስጠት ጥረት እናድርግ። ዘካርያስ 8:9 “ነቢያት የተናገሩትን ቃል አሁን የምትሰሙ ሁሉ . . . እጃችሁን አበርቱ” በማለት ያሳስበናል።

ታስታውሳለህ?

• የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ ጠቃሚ የሆኑት ከየትኛው ታሪክ ጋር በመመሳሰላቸው ነው?

• የሐጌና የዘካርያስ ትንቢቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች ምን ትምህርት ይሰጡናል?

• የሐጌንና የዘካርያስን መጻሕፍት መመርመራችን ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንድንተማመን የሚያደርገን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐጌና ዘካርያስ፣ አይሁዳውያኑ በሙሉ ነፍሳቸው እንዲሠሩና በረከት እንዲያገኙ አበረታተዋቸዋል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘የራስህን ቤት ለመሥራት እየተሯሯጥህ ነው?’

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ሕዝቦቹን እንደሚባርካቸው የገባውን ቃል ፈጽሟል