ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ ሰው 25,000 የአሜሪካ ዶላር ባንክ ለማስገባት ይሄዳል። ገንዘቡን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለማውጣት በሚያስችለው የባንክ ሒሳብ ለማስቀመጥ አስቦ ነበር። ሆኖም የባንኩ ሠራተኛ ገንዘቡን እንዲሁ ከሚያስቀምጠው አክሲዮን ቢገዛበት የተሻለ እንደሆነና እንዲህ በማድረጉ መቼም እንደማይከስር መከረው። ሰውዬውም በባንክ ቤቱ ሠራተኛ ሐሳብ ተስማማ። ሆኖም መዋዕለ ነዋዩን ያፈሰሰበት አክሲዮን ብዙም ሳይቆይ ዋጋውን አጣ።
ይህ ገጠመኝ፣ ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ማድረግ ቀላል አለመሆኑን ያሳያል። በሕይወታችን ውስጥ ስለምናደርጋቸው የተለያዩ ውሳኔዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ያሰብነው ነገር መሳካት አለመሳካቱ የተመካው በምናደርጋቸው በርካታ ውሳኔዎች ላይ ሊሆን ይችላል፤ እነዚህ ውሳኔዎች ውሎ አድሮ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ሊሆኑም ይችላሉ። ታዲያ ትክክለኛ ውሳኔ ስለማድረጋችን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
“መንገዱ ይህ ነው”
በየዕለቱ የምንመገበውን፣ የምንለብሰውን፣ የምንሄድበትን ወይም እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔ እናደርጋለን። አንዳንዶቹ ነገሮች እምብዛም ከባድ ባይሆኑም ውጤታቸው ግን አስከፊ ሊሆን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጋራን ለማጨስ መወሰን ለዕድሜ ልክ የማጨስ ልማድ ሊዳርግ ይችላል። ስለሆነም ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ሳይቀር የምናደርገውን ውሳኔ አቅልለን መመልከት የለብንም።
ጥቃቅን የሆኑ ጉዳዮችን ጨምሮ ውሳኔዎችን ስናደርግ መመሪያ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው? ከባድ ውሳኔዎች ከፊታችን ሲደቀኑብን ምክር ሊሰጠን የሚችል እምነት የምንጥልበት ሰው ማግኘት እጅግ ያስደስታል! አንተም እንዲህ ዓይነቱን አማካሪ ማግኘት ትችላለህ። በዛሬው ጊዜ ለምንኖር ሰዎች ጠቃሚ መልእክቶችን የያዘ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ “ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ ‘መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ’ የሚል ድምፅ ይሰማል” ሲል ይናገራል። (ኢሳይያስ 30:21) ይህን የተናገረው ማን ነው? ምክሩ እምነት የሚጣልበት መሆኑን ማወቅ የምትችለውስ እንዴት ነው?
ከላይ የተሰጠው ማረጋገጫ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት መጽሐፉ ፈጣሪ በሆነው በይሖዋ አምላክ መንፈስ አነሳሽነት መጻፉን ለመገንዘብ ችለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይሖዋ አፈጣጠራችንን ስለሚያውቅ ከሁሉ የላቁ ጠቃሚ ምክሮችን ሊለግሰን ይችላል። ከዚህም በላይ እርሱ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ፤ ‘ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም አደርጋለሁ’ እላለሁ” በማለት ስለተናገረ የወደፊቱን ያውቃል። (ኢሳይያስ 46:10) በመሆኑም መዝሙራዊው በይሖዋ ቃል ላይ ያለውን እምነት “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” በማለት ገልጿል። (መዝሙር 119:105) ያም ሆኖ ይሖዋ እንደሚናወጥ ባሕር በሆነው ዓለም ላይ አቅጣጫችንን ሳንስት ደኅንነታችን ተጠብቆ እንድንጓዝ የሚረዳን እንዴት ነው? ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ውሳኔ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ አድርግ
ይሖዋ አምላክ ለክርስቲያኖች ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚያስችሏቸውን መለኮታዊ መመሪያዎች ሰጥቷቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መማርና ተግባራዊ ማድረግ አንድን ቋንቋ ከመማርና በቋንቋው ከመጠቀም ጋር ይመሳሰላል። አንድ ጊዜ ቋንቋውን በደንብ ከቻልከው ሌላ ሰው ቋንቋውን ሲናገር ስህተት ቢሠራ ስህተቱን በቀላሉ መለየት ትችላለህ። ለምን ቢባል አንድ የሆነ ችግር እንዳለበት ስለሚሰማህ ነው። ምናልባት የሠራውን ስህተት ከሰዋስው አንጻር ለይተህ መጥቀስ ባትችልም እንኳ ትክክል አለመሆኑ ግን ይታወቅሃል። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ስታውቅና በሕይወትህ ውስጥ እንዴት በተግባር ማዋል እንደምትችል ስትገነዘብ የምታደርገው ውሳኔ ከመለኮታዊ መመሪያ ጋር የሚጋጭ መሆን አለመሆኑን መናገር ትችላለህ።
ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወጣት የፀጉር አበጣጠሩን በተመለከተ ሊያደርገው የሚገባውን ውሳኔ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ የትኛውንም የፀጉር አበጣጠር ለይቶ በመጥቀስ አያወግዝም። ይሁንና እስቲ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ሴቶች በጨዋነትና ራስን በመግዛት ተገቢ የሆነ ልብስ ይልበሱ እንጂ በሹሩባ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋቸው ውድ በሆኑ ልብሶች አይሽቀርቀሩ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉ እንደሚገባ በመልካም ተግባር ይዋቡ።” (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) ጳውሎስ ይህንን የጻፈው ሴቶችን አስመልክቶ ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለሁለቱም ጾታዎች ማለትም ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ይሠራል። መሠረታዊ ሥርዓቱ ምንድን ነው? አለባበሳችንና የፀጉር አበጣጠራችን ጨዋነትና ራስን መግዛት የሚታይበት መሆን ይገባዋል። በመሆኑም ይህ ወጣት ‘የፀጉር አቆራረጤ ልከኛና ለአንድ ክርስቲያን ተስማሚ ነው?’ በማለት ራሱን ሊጠይቅ ይችላል።
አንድ ወጣት፣ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ከጻፈው መሠረታዊ ሥርዓት ምን የሚማረው ነገር ይኖራል? ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ያዕቆብ 4:4) ክርስቲያኖች ከዓለም ጋር መወዳጀትን አጥብቀው ይጠላሉ፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ወዳጅነት የአምላክ ጠላቶች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። አንድ ወጣት በጓደኞቹ ዘንድ የተወደደለት የፀጉር አቆራረጥ የአምላክ ወዳጅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ወይስ የዓለም? የፀጉር አቆራረጡን በተመለከተ በጥንቃቄ የሚያስብ ወጣት እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተጠቅሞ ጥበብ ያለበት ውሳኔ ማድረግ ይችላል። አዎን፣ መለኮታዊ መመሪያዎች ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዱናል። በመለኮታዊ መመሪያዎች ላይ የተመረኮዙ ውሳኔዎችን ማድረግ ስንለምድ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውና አስከፊ ውጤቶች የማያስከትሉ ውሳኔዎች ማድረግ ቀላል ይሆንልናል።
በአምላክ ቃል ውስጥ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ዘፍጥረት 4:6, 7, 13-16፤ ዘዳግም 30:15-20፤ 1 ቆሮንቶስ 10:11) እነዚህን ዘገባዎች ማንበባችንና ውጤታቸውን ማገናዘባችን አምላክ የሚደሰትበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ መለኮታዊ መመሪያዎች ለማግኘት ያስችለናል።
እናገኛለን። እርግጥ ነው፣ ስላጋጠመን ሁኔታ በቀጥታ የሚናገር ጥቅስ ላናገኝ እንችል ይሆናል። ያም ሆኖ አንዳንድ ሰዎች መለኮታዊውን መመሪያ እንዴት እንዳከበሩና ሌሎች ደግሞ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ እንዴት ችላ እንዳሉ እናነብባለን። (ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር ያደረገውን አጠር ያለ ውይይት ተመልከት። በጊዜው የነበሩት ግብር ሰብሳቢዎች ጴጥሮስን “መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር የቤተ መቅደስ ግብር አይከፍልምን?” በማለት ሲጠይቁት “ይከፍላል እንጂ” ሲል መለሰላቸው። ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ “ስምዖን፤ የምድር ነገሥታት ግብር ወይም ቀረጥ የሚቀበሉት ከራሳቸው ልጆች ወይስ ከሌሎች ይመስልሃል?” በማለት ጴጥሮስን ጠየቀው። ጴጥሮስም “ከሌሎች ነው የሚቀበሉት” ሲል መለሰ። ኢየሱስም “እንግዲያውስ ልጆች ነጻ ናቸው፤ ሆኖም እንዳናስቀይማቸው ሄደህ መንጠቆህን ወደ ባሕር ጣል፤ መጀመሪያ የምትይዘውን ዓሣ አፉን ስትከፍት የምታገኘውን አንድ እስታቴር በእኔና በአንተ ስም ክፈል” አለው። (ማቴዎስ 17:24-27) ከዚህ ዘገባ ምን ዓይነት መለኮታዊ መመሪያ እናገኛለን?
ኢየሱስ የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ የአምላክ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ከቀረጥ ነጻ መሆኑን እንዲያስተውል ጴጥሮስን ረድቶታል። ጴጥሮስ መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ ከቀረጥ ነጻ መሆኑን ያልተረዳ ቢሆንም ኢየሱስ ነገሩን እንዲገነዘብ በደግነት ረድቶታል። እኛም ሌሎች ሲሳሳቱ ስንመለከት ስህተታቸውን አጉልተን በመጥቀስ ክፉ ቃል ከመናገር አሊያም ከመኮነን ይልቅ ልክ እንደ ኢየሱስ በርኅራኄ ልንይዛቸው ይገባል።
ጴጥሮስ ቀረጡ መከፈል ያስፈለገው ሌሎችን ላለማስቀየም ወይም ላለማሰናከል እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ይህ ደግሞ ከዘገባው የምንማረው ሌላም መሠረታዊ ሥርዓት መኖሩን ይጠቁማል። የራሳችንን መብት ለማስከበር ከመታገል ይልቅ የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ማስገባት ጠቃሚ መሆኑን ያስገነዝበናል።
ውሳኔያችን የሌሎችን ሕሊና እንደምናከብር የሚያሳይ እንዲሆን የሚያነሳሳን ምንድን ነው? ለባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ባልንጀሮቻችንን እንደራሳችን መውደድ አምላክን በሙሉ ነፍሳችን ከመውደድ ቀጥሎ የሚመጣ ታላቅ ትእዛዝ መሆኑን አስተምሯል። (ማቴዎስ 22:39) ሆኖም የምንኖረው ራስ ወዳድ በሆነ ዓለም ውስጥ ሲሆን ኃጢአተኞች በመሆናችን የራስ ወዳድነት ዝንባሌም ያጠቃናል። በመሆኑም አንድ ሰው ባልንጀራውን እንደ ራሱ ለመውደድ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ይኖርበታል።—ሮሜ 12:2
ብዙዎች እንዲህ ዓይነቱን የአስተሳሰብ ለውጥ አድርገዋል፤ በተጨማሪም ቀላልም ሆነ ከባድ ውሳኔ ሲያደርጉ የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ያስገባሉ። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል።” (ገላትያ 5:13) ይህን እንዴት ማድረግ እንችላለን? የአምላክን ቃል ሌሎች እንዲያውቁ ለመርዳት ስትል ወደ ገጠራማ አካባቢ የሄደችን የአንዲት ወጣት ሁኔታ ተመልከት። ይህች እህት አገልግሎቷን ስትጀምር ምንም እንኳ የለበሰችው ልብስ በከተማው አካባቢ ልከኛ የሚባል ዓይነት ቢሆንም አለባበሷ የመንደሩ መነጋገሪያ ርዕስ መሆኑን አስተዋለች። አለባበሷም ይሁን የፀጉር አሠራሯ ጨዋነትን የተላበሰ ቢሆንም “የእግዚአብሔር ቃል በማንም ዘንድ እንዳይሰደብ” ስትል ደማቅ ቀለም ያላቸውን ልብሶች ላለመልበስ ወሰነች።—ቲቶ 2:5
አንተም የፀጉር አበጣጠርህንም ሆነ ሌሎች የግል ምርጫዎችህን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ቢያስፈልግህ ምን ታደርጋለህ? ውሳኔዎችህ የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ያስገቡ መሆናቸው አምላክን እንደሚያስደስተው አትጠራጠር።
አርቀህ አስብ
ውሳኔ ስናደርግ ሁኔታውን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ከማገናዘብና የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ከማስገባት በተጨማሪ ምን ነገሮችን ልናስብ ይገባል? የክርስትና መንገድ አስቸጋሪና ጠባብ ቢሆንም አምላክ ያወጣቸው ገደቦች የማያፈናፍኑ አይደሉም። (ማቴዎስ 7:13, 14) የምናደርገው ውሳኔ በመንፈሳዊነታችን፣ በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችንና በጤንነታችን ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ማሰብ ይኖርብናል።
በአንድ ሥራ ላይ ለመቀጠር አስበሃል እንበል። ሥራው ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ አሊያም አግባብነት የሌለው አይደለም። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ይሁን በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት አያግድህም። ክፍያውም ቢሆን ከጠበቅከው በላይ ነው። ቀጣሪህ ብቃትህን በጣም ስለሚያደንቅ ባለህ ችሎታ ሁሉ እንድታገለግለው የሚፈልግ ሲሆን ሥራውም ቢሆን የምትወደው ዓይነት ነው። የቀረበልህን ግብዣ እንዳትቀበል የሚያግድህ ነገር ይኖራል? ወደፊት በሥራው ሙሉ ለሙሉ የመጠመድ አደጋ እንዳለ ብትመለከት ምን ታደርጋለህ? ከሥራ ሰዓት ውጪ ለመሥራት እንደማትገደድ ተነግሮህ ሊሆን ይችላል። ይሁንና የጀመርከውን ሥራ ለመጨረስ ስትል መሥራት ካለብህ በላይ ለመቆየት ፈቃደኛ ትሆናለህ? እንዲህ ያለው የሥራ ጫና በተደጋጋሚ ጊዜ ያጋጥምህ ይሆን? ይህ ሁኔታ ከቤተሰቦችህ ጋር የምታሳልፈውንና በምንም ዓይነት ሊያመልጡህ ለማይገቡ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህ የምታውለውን ጊዜ ቀስ በቀስ ይሻማብህ ይሆን?
ጂም ሥራውን አስመልክቶ ያደረገውን ከባድ ውሳኔ ተመልከት። ጂም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ይሠራ ስለነበር እድገት አገኘ። በመሆኑም የሚሠራበት ኩባንያ በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ውስጥ የሚያከናውነውን እንቅስቃሴ በኃላፊነት መቆጣጠር ጀመረ፤ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ወንድማማች ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ኩባንያው በአውሮፓ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የዲሬክተር ቦርድ አባል ለመሆን ቻለ። ይሁንና በጃፓን የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል በተከሰተ ጊዜ ገንዘብና ሥልጣንን ማሳደድ ምን ያህል ከንቱ እንደሆነ ተገነዘበ። ጥሮ ግሮ ያጠራቀመው ገንዘብ ወዲያውኑ አለቀ። ሕይወት ትርጉም አልባ ሆነበት። ‘የዛሬ አሥር ዓመት ምን እሆን ይሆን?’ ሲል ራሱን ጠየቀ። ሆኖም ለዓመታት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲሰበሰቡ የቆዩት ባለቤቱና ልጆቹ ዓላማ ያለው ሕይወት እየመሩ እንዳለ መገንዘብ አልተሳነውም። ጂምም እነርሱ እያገኙ ያሉትን ደስታና እርካታ ለመቅመስ ስለፈለገ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ።
ብዙም ሳይቆይ ጂም፣ የሚከተለው የአኗኗር ዘይቤ እንደ አንድ ክርስቲያን ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት እንዳላስቻለው አስተዋለ። ከእስያ ወደ ዩናይትድ ስቴትስና ወደ አውሮፓ በተደጋጋሚ ይመላለስ ስለነበር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲሁም ከእምነት አጋሮቹ ጋር ለመሰብሰብ ጊዜ አልነበረውም። በመሆኑም ‘ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ስመላለስ በቆየሁበት የአኗኗር ዘይቤ ልቀጥል ወይስ አዲስ የሕይወት ጎዳና ልከተል?’ የሚል ጥያቄ ፊቱ ተደቀነ። ውሳኔው የሚያስከትለውን ውጤት አርቆ በመመልከት ነገሩን በጸሎት ካሰበበት በኋላ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ለመከታተል የሚያስችል በቂ ጊዜ ለማግኘት ሲል ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹን ሥራዎች በሙሉ ለቀቀ። (1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) ይህን ውሳኔ ማድረጉም በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጠመድና ይበልጥ ደስተኛ እንዲሆን አስችሎታል።
የምታደርጋቸው ውሳኔዎች ከባድም ሆኑ ቀላል በሕይወትህ ውስጥ ለውጥ ያመጣሉ። ዛሬ የምታደርገው ውሳኔ የወደፊቱ ሕይወትህ ስኬታማ መሆን አለመሆኑ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር አልፎ ተርፎም የሞትና የሕይወት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የምታገናዝብ፣ የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ የምታስገባ እንዲሁም ውሳኔህ የሚያስከትለውን ውጤት አርቀህ የምትመለከት ከሆነ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ። ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ውሳኔ አድርግ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀላል የሚመስሉ ውሳኔዎች አስከፊ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድታደርግ የሚረዳት እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ጴጥሮስን በርኅራኄ አነጋግሮታል