‘ለመንጋው ምሳሌ’ የሚሆኑ እረኞች
‘ለመንጋው ምሳሌ’ የሚሆኑ እረኞች
‘በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ በፈቃደኝነትና በጽኑ ፍላጎት ጠብቁ፤ እንዲሁም ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ።’—1 ጴጥሮስ 5:2, 3
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ምን አደራ ሰጥቶታል? ኢየሱስ በጴጥሮስ ላይ እምነት መጣሉ ምንም ስህተት አልነበረውም ማለት የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለተሾሙ እረኞች ምን ስሜት አለው?
በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ጥቂት ቀደም ብሎ ጴጥሮስና ሌሎች ስድስት ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ ያዘጋጀላቸውን ቁርስ እየተመገቡ ነበር። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን ከሞት ከተነሳ በኋላ ሲያየው ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አልነበረም፤ ኢየሱስ በሕይወት መኖሩን ማወቁ እንዳስደሰተው ምንም አያጠራጥርም። ነገር ግን ሳይጨነቅም አልቀረም፤ ምክንያቱም ከጥቂት ቀናት በፊት ኢየሱስን በጭራሽ እንደማያውቀው በመናገር ክዶት ነበር። (ሉቃስ 22:55-60፤ 24:34፤ ዮሐንስ 18:25-27፤ 21:1-14) ኢየሱስ፣ ንስሐ የገባው ጴጥሮስ እምነት ስላነሰው ወቅሶታል? በጭራሽ። እንዲያውም የእርሱን ‘በጎች’ የመመገብና የመጠበቅ ሥራ በአደራ ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 21:15-17) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ የሚናገረው ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ኢየሱስ በጴጥሮስ ላይ እምነት መጣሉ ምንም ስህተት አልነበረውም። ጴጥሮስ ከሌሎች ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም ከነበሩ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ከባድ ስደትም ይሁን ፈጣን እድገት በነበረበት ጊዜ ሁሉ የክርስቲያን ጉባኤ እረኛ ሆኖ ሠርቷል።—የሐዋርያት ሥራ 1:15-26፤ 2:14፤ 15:6-9
2 ከታሪክ ዘመናት ሁሉ በጣም አስጨናቂ በሆነው በዛሬው ጊዜ ይሖዋ፣ በጎቹን እንዲመሩ መንፈሳዊ እረኞች ሆነው ለማገልገል ብቃት ያላቸውን ወንዶች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሾሟል። (ኤፌሶን 4:11, 12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሖዋ እንዲህ ባሉ ሰዎች ላይ እምነት መጣሉ ስህተት ነው? ዓለም አቀፍ የሆነው ሰላማዊው የክርስቲያን ወንድማማቾች ኅብረት፣ ይሖዋ በእነርሱ ላይ እምነት መጣሉ ስህተት እንዳልሆነ ያረጋግጣል። እውነት ነው፣ እነዚህ እረኞች ልክ እንደ ጴጥሮስ ሊሳሳቱ የሚችሉ ሰዎች ናቸው። (ገላትያ 2:11-14፤ ያዕቆብ 3:2) ቢሆንም ይሖዋ ‘በገዛ ልጁ ደም የዋጃቸውን’ በጎች እንደሚንከባከቡ ይተማመንባቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28 NW) ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ጥልቅ ፍቅር አለው፤ እንዲሁም ‘ዕጥፍ ክብር እንደሚገባቸው’ ያምናል።—1 ጢሞቴዎስ 5:17
3. መንፈሳዊ እረኞች የፈቃደኝነት መንፈስና ጽኑ ፍላጎት ማዳበር የሚችሉት እንዴት ነው?
3 መንፈሳዊ እረኞች ለመንጋው ምሳሌ ለመሆን የፈቃደኝነት መንፈስና ጽኑ ፍላጎት ማዳበር የሚችሉት እንዴት ነው? ልክ እንደ ጴጥሮስና እንደ ሌሎች የመጀመሪያው መቶ ዘመን እረኞች፣ የኃላፊነት ሸክማቸውን እንዲሸከሙ የሚረዳቸውን ጥንካሬ ለማግኘት በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ይተማመናሉ። (2 ቆሮንቶስ 4:7) በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት ወይም ደግነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት ያሉትን የመንፈስ ፍሬዎች እንዲያፈሩ ያደርጋቸዋል። (ገላትያ 5:22, 23 የ1954 ትርጉም) እረኞች በእነርሱ ሥር ያለውን የአምላክ መንጋ ሲንከባከቡ ይህንን ፍሬ በማፍራት አርዓያ መሆን የሚችሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።
ለመንጋውም ሆነ ለእያንዳንዱ በግ ፍቅር ይኑራችሁ
4, 5. (ሀ) ይሖዋና ኢየሱስ ለመንጋው ፍቅር የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) መንፈሳዊ እረኞች ለመንጋው ፍቅር የሚያሳዩባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
4 የአምላክ መንፈስ የሚያፈራው ከሁሉ የላቀ ባሕርይ ፍቅር ነው። ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ማቅረቡ መንጋውን በጠቅላላ እንደሚያፈቅር ያሳያል። (ኢሳይያስ 65:13, 14፤ ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) ሆኖም መንጋውን ከመመገብ የበለጠ ነገርም ያደርጋል። ለእያንዳንዱ በግ ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳያል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ኢየሱስም ለመንጋው ፍቅር አለው። ለመንጋው ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠቱም በላይ በጎቹን በግለሰብ ደረጃ “በየስማቸው” ያውቃቸዋል።—ዮሐንስ 10:3, 14-16
5 መንፈሳዊ እረኞች ይሖዋንና ኢየሱስን ይኮርጃሉ። እነዚህ እረኞች ጉባኤውን ‘ለማስተማር በመትጋት’ በቡድን ደረጃ ለአምላክ መንጋ ፍቅር ያሳያሉ። የሚያቀርቡት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር መንጋውን ለመመገብና ለመጠበቅ ይረዳል፤ በትጋት የሚያከናውኑት ይህ ሥራ ከማንም የተሰወረ አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 4:13, 16) ሆኖም የጉባኤ መዝገቦችን በመያዝ፣ ደብዳቤዎችን በመጻጻፍ፣ ፕሮግራም በማዘጋጀት እንዲሁም የጉባኤ ስብሰባዎችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች “በአግባብና በሥርዐት” እንዲከናወኑ የሚያስችሉ በርካታ ነገሮችን በመፈጸም የሚያሳልፉት ጊዜ ብዙም የሚስተዋል አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 14:40) ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ አብዛኞቹ የሚከናወኑት ሌሎች እያዩ ስላልሆነ ብዙም ላይታወቁ ይችላሉ። ይህ በእርግጥም በፍቅር የሚከናወን ተግባር ነው።—ገላትያ 5:13
6, 7. (ሀ) እረኞች ከበጎች ጋር በተሻለ ሁኔታ መተዋወቅ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው? (ለ) ስሜታችንን ለሽማግሌዎች መንገር አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
6 አፍቃሪ ክርስቲያን እረኞች የጉባኤው አባል ለሆነ ለእያንዳንዱ በግ ልባዊ አሳቢነት ለማሳየት ይጣጣራሉ። (ፊልጵስዩስ 2:4) የክርስቲያን ጉባኤ እረኞች ከእያንዳንዱ በግ ጋር በተሻለ ሁኔታ መተዋወቅ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ ለሕዝብ በመስበኩ ሥራ አብሮ መካፈል ነው። ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ከተከታዮቹ ጋር በስብከቱ ሥራ ይካፈል የነበረ ሲሆን እንዲህ ያሉትን አጋጣሚዎች እነርሱን ለማበረታታት ተጠቅሞባቸዋል። (ሉቃስ 8:1) አንድ ተሞክሮ ያካበተ ክርስቲያን እረኛ “አንድን ወንድም ወይም አንዲትን እህት ለማወቅና ለማበረታታት በጣም ጥሩ ከሆኑት መንገዶች አንዱ ከእርሱ ወይም ከእርሷ ጋር በመስክ አብሮ ማገልገል እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ” ብሏል። በቅርቡ ከአንድ ሽማግሌ ጋር የማገልገል አጋጣሚ ካላገኘህ ለምን አብረኸው ወደ መስክ አገልግሎት ለመሄድ ዝግጅት አታደርግም?
7 ፍቅር፣ ኢየሱስ የተከታዮቹ ደስታም ሆነ ሐዘን ተካፋይ እንዲሆን አድርጎታል። ለምሳሌ ያህል፣ 70 ደቀ መዛሙርቱ ተደስተው ከስብከት ሥራቸው ሲመለሱ “ሐሤት” አድርጎ ነበር። (ሉቃስ 10:17-21 የ1954 ትርጉም) ነገር ግን ማርያም፣ ቤተሰቦቿና ወዳጆቿ በአልዓዛር መሞት ምን ያህል እንደተጎዱ በተመለከተ ጊዜ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:33-35) ዛሬም በተመሳሳይ አሳቢ እረኞች ለበጎቻቸው ስሜት ግዴለሾች አይደሉም። ፍቅር፣ ‘ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ እንዲላቸው፣ ከሚያዝኑም ጋር እንዲያዝኑ’ ያነሳሳቸዋል። (ሮሜ 12:15) አንተም በሕይወትህ ውስጥ ደስታ ወይም ሐዘን ቢያጋጥምህ ምንም ሳትፈራ ስሜትህን አውጥተህ ለክርስቲያን እረኞች ንገራቸው። ደስታህን መስማታቸው ያበረታታቸዋል። (ሮሜ 1:11, 12) ችግር እንዳለብህ ማወቃቸው ደግሞ ማበረታቻና ማጽናኛ እንዲሰጡህ ያስችላቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 1:6፤ 3:1-3
8, 9. (ሀ) አንድ ሽማግሌ ሚስቱን እንደሚወዳት ያሳይ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) አንድ እረኛ ለቤተሰቡ ፍቅር ማሳየቱ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
8 አንድ እረኛ ለበጎቹ ፍቅር እንዳለው በይበልጥ የሚረጋገጠው የራሱን ቤተሰብ ከሚይዝበት መንገድ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 4) ባለትዳር ከሆነ ሚስቱን በመውደድና በማክበር ለሌሎች ባሎች አርዓያ ይሆናል። (ኤፌሶን 5:25፤ 1 ጴጥሮስ 3:7) ሊንዳ የተባለች ክርስቲያን የሰጠችውን አስተያየት ተመልከት። ባለቤቷ ከመሞቱ በፊት ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። እንዲህ ብላለች:- “ባለቤቴ ጉባኤውን በመንከባከቡ ሥራ የተጠመደ ነበር። ሆኖም በዚህ ሥራ አጋሩ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርግ ነበር። ለማደርገው ድጋፍ በተደጋጋሚ ያመሰግነኝ ነበር፤ እንዲሁም ትርፍ ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው ከእኔ ጋር ነው። ይህም እንደምወደድ እንዲሰማኝ ስለሚያደርግ ጉባኤውን በማገልገል ጊዜ የሚያጠፋ መሆኑ የቅናት ስሜት አልፈጠረብኝም።”
9 አንድ ክርስቲያን እረኛ ልጆች ካሉት ለልጆቹ ፍቅራዊ ተግሣጽ መስጠቱና አዘውትሮ የሚያመሰግናቸው መሆኑ ለሌሎች ወላጆች ጥሩ ምሳሌ እንዲሆን ያደርገዋል። (ኤፌሶን 6:4) እንዲያውም ለቤተሰቡ የሚያሳየው ፍቅር፣ በመንፈስ ቅዱስ በተሾመ ጊዜ የተጣለበትን አደራ እየተወጣ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5
የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ ደስታና ሰላምን አስፍኑ
10. (ሀ) በጉባኤው ደስታና ሰላም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ምንድን ነው? (ለ) የመጀመሪያውን መቶ ዘመን ጉባኤ ሰላም ስጋት ላይ ጥሎ የነበረው ጉዳይ ምንድን ነው? መፍትሔ ያገኘውስ እንዴት ነበር?
10 መንፈስ ቅዱስ በአንድ ክርስቲያን ልብ ውስጥ፣ በሽማግሌዎች መካከልና በጠቅላላው ጉባኤ ውስጥ ደስታና ሰላም መፍጠር ይችላል። ነገር ግን ግልጽ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት አለመኖሩ በዚህ ደስታና ሰላም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በጥንት ዘመን የኖረው ሰሎሞን “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 15:22) በሌላ በኩል ደግሞ አክብሮት የሚንጸባረቅበትና ግልጽ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት ደስታና ሰላም ያሰፍናል። ለአብነት ያህል፣ የግርዘት ጉዳይ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤን ሰላም ስጋት ላይ በጣለ ጊዜ በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረው የበላይ አካል የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለማግኘት ጥረት አድርጓል። እንዲሁም አባላቱ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን የተለያየ አመለካከት ገልጸዋል። ሞቅ ያለ ውይይት ካደረጉ በኋላ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። በአንድ ድምፅ የወሰኑትን ውሳኔ ለጉባኤዎች ባስተላለፉ ጊዜ ወንድሞች ‘አበረታች በሆነው ቃል ደስ ተሰኙ።’ (የሐዋርያት ሥራ 15:6-23, 25, 31፤ 16:4, 5) በመካከላቸው ደስታና ሰላም ሰፍኖ ነበር።
11. ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ደስታና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
11 ዛሬም በተመሳሳይ ክርስቲያን እረኞች ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ በጉባኤው ውስጥ ደስታና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ይችላሉ። የጉባኤውን ሰላም ስጋት ላይ የሚጥል ችግር ቢከሰት ተሰብስበው ስሜታቸውን በግልጽ ይነጋገራሉ። ሌሎች እረኞች የሚሰጡትን አስተያየት በአክብሮት ያዳምጣሉ። (ምሳሌ 13:10፤ 18:13) መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት ከጸለዩ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና “ታማኝና ልባም ባሪያ” ባወጣቸው መመሪያዎች ላይ ተመሥርተው ውሳኔ ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም፤ 1 ቆሮንቶስ 4:6) የሽማግሌዎች አካል በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ካደረገ በኋላ፣ እያንዳንዱ ሽማግሌ ሐሳቡ በአብዛኞቹ ሽማግሌዎች ዘንድ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳን ውሳኔውን በመደገፍ ለመንፈስ ቅዱስ አመራር እንደሚታዘዝ ያሳያል። በዚህ መልክ ትሕትናን ማንጸባረቅ ደስታና ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በጎቹ እንዴት ከአምላክ ጋር መጓዝ እንደሚችሉ በምሳሌ ለማሳየትም ያስችላል። (ሚክያስ 6:8) የጉባኤ ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ሲያደርጉ በትሕትና ትስማማለህ?
ታጋሽና ደግ ሁኑ
12. ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ታጋሽና ደግ መሆን ያስፈለገው ለምን ነበር?
12 ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ በተደጋጋሚ ስህተት ይፈጽሙ የነበረ ቢሆንም ከእነርሱ ጋር በነበረው ግንኙነት ረገድ ታጋሽና ደግ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ትሕትና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ብዙ ጊዜ ሞክሮ ነበር። (ማቴዎስ 18:1-4፤ 20:25-27) ይሁንና በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ላይ እግራቸውን በማጠብ ስለ ትሕትና ትምህርት ከሰጣቸው በኋላም እንኳን “ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ።” (ሉቃስ 22:24፤ ዮሐንስ 13:1-5) በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ገሠጻቸው? በፍጹም፤ ከዚህ ይልቅ እንዲህ በማለት በደግነት አስረዳቸው:- “ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው።” (ሉቃስ 22:27) ውሎ አድሮም የሐዋርያቱ ልብ በኢየሱስ ትዕግሥት፣ ደግነትና መልካም ምሳሌነት ተነክቷል።
13, 14. እረኞች ደግ መሆን ያለባቸው በተለይ መቼ ነው?
13 በተመሳሳይም አንድ መንፈሳዊ እረኛ አንድ ዓይነት ድክመት ላለበት ሰው ተደጋጋሚ ምክር መስጠት ያስፈልገው ይሆናል። ምናልባትም እረኛው በግለሰቡ ይበሳጭ ይሆናል። ይሁን እንጂ ራሱ የሚፈጽማቸውን ስህተቶች የሚያስታውስ ከሆነ፣ ‘ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን በሚገሥጽበት’ ጊዜ ለወንድሞቹ ትዕግሥትና ደግነት ማሳየት አይከብደውም። በዚህ መንገድ እረኞችን ጨምሮ ለሁሉም ክርስቲያኖች እነዚህን ባሕርያት የሚያሳዩትን ይሖዋንና ኢየሱስን ይመስላል።—1 ተሰሎንቄ 5:14 የ1954 ትርጉም፤ ያዕቆብ 2:13
14 አንዳንድ ጊዜ እረኞች ከባድ ኃጢአት ለፈጸሙ ሰዎች ጠንከር ያለ ምክር መስጠት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ኃጢአት የሠራው ግለሰብ ንስሐ ካልገባ ደግሞ ከጉባኤ ሊያስወግዱት ይገባል። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) ሆኖም እንዲህ ያለውን ሰው በሚያነጋግሩበት ጊዜ የሚያሳዩት ጠባይ ግለሰቡን ሳይሆን የሠራውን ኃጢአት እንደሚጠሉ የሚያሳይ ነው። (ይሁዳ 23) እረኞች የሚያሳዩት ደግነት የባዘነው በግ ወደ መንጋው መመለስ እንዲቀለው ሊያደርግ ይችላል።—ሉቃስ 15:11-24
ለበጎ ሥራ የሚያነሳሳው እምነት ነው
15. እረኞች የይሖዋን በጎነት የሚያንጸባርቁበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸውስ ምንድን ነው?
15 ‘ይሖዋ ለሁሉም’ ሰዎች ሌላው ቀርቶ ያደረገላቸውን ለማያደንቁ ጭምር “ቸር” ወይም በጎ አምላክ ነው። (መዝሙር 145:9፤ ማቴዎስ 5:45) በተለይ የይሖዋን በጎነት የሚያረጋግጠው ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ እንዲሰብኩ ሕዝቡን መላኩ ነው። (ማቴዎስ 24:14) እረኞች ይህንን የስብከት ሥራ በግንባር ቀደምትነት በማከናወን የአምላክን በጎነት ያንጸባርቃሉ። ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? በይሖዋና በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያላቸው ጠንካራ እምነት ነው።—ሮሜ 10:10, 13, 14
16. እረኞች ለበጎች ‘መልካም ማድረግ’ ወይም በጎነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
16 መንፈሳዊ እረኞች፣ በስብከት ሥራቸው ‘ለሰው ሁሉ መልካም’ ከማድረግ በተጨማሪ “በተለይም ለእምነት [ቤተሰቦቻቸው]” በጎነት የማሳየት ኃላፊነት አለባቸው። (ገላትያ 6:10) ይህን ኃላፊነት ከሚወጡባቸው መንገዶች አንዱ የሚያንጽ እረኝነት ማድረግ ነው። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “እረኝነት ማድረግ ያስደስተኛል” በማለት ተናግሯል። አክሎም “እነዚህ ወቅቶች ወንድሞችና እህቶችን ላደረጉት ጥረት ለማመስገንና የሚያከናውኑት ትጋት የተሞላበት ሥራ ትልቅ ዋጋ እንዳለው እንዲገነዘቡ ለመርዳት አጋጣሚ ይሰጡኛል” ብሏል። አንዳንድ ጊዜ እረኞች አንድ ግለሰብ ለአምላክ የሚያቀርበውን አገልግሎት ሊያሻሽል የሚችልባቸውን መንገዶች በተመለከተ ሐሳብ ሊሰጡት ይችላሉ። ጥበበኛ እረኞች እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ይከተላሉ። ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚገኙ ክርስቲያኖችን “እኛ ያዘዝናችሁን አሁን አደረጋችሁ፤ ወደ ፊትም እንደምታደርጉ በጌታ እንታመናለን” ባለ ጊዜ ምን ዓይነት አነጋገር እንደተጠቀመ ልብ በል። (2 ተሰሎንቄ 3:4) እንዲህ በእርግጠኝነት የተነገረ ሐሳብ በጎች በጎ ዝንባሌ እንዲኖራቸውና ‘ለመሪዎቻቸው መታዘዝ’ እንዲቀላቸው ያደርጋል። (ዕብራውያን 13:17) ሽማግሌዎች የሚያበረታታ እረኝነት ሲያደርጉልህ ለምን ምስጋና አታቀርብላቸውም?
የዋህ ለመሆን ራስን መግዛት ያስፈልጋል
17. ጴጥሮስ ከኢየሱስ ምን ትምህርት አግኝቷል?
17 ኢየሱስ የሚያበሳጭ ነገር በሚያጋጥመው ጊዜም እንኳ የዋህነትን ያሳይ ነበር። (ማቴዎስ 11:29) አልፎ በተሰጠበትና በታሰረበት ዕለት የዋህነትና ከፍተኛ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቷል። ጴጥሮስ በችኮላ ሰይፉን መዝዞ የአጸፋ እርምጃ ወስዶ ነበር። ኢየሱስ ግን “ካስፈለገ አባቴን ብጠይቀው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድልኝ ይመስልሃል?” አለው። (ማቴዎስ 26:51-53፤ ዮሐንስ 18:10) ጴጥሮስ ከክስተቱ ትምህርት አግኝቶ ስለነበር ከጊዜ በኋላ ክርስቲያኖችን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው። . . . ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም።”—1 ጴጥሮስ 2:21-23
18, 19. (ሀ) እረኞች የዋህነትና ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት ያለባቸው በተለይ መቼ ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
18 በተመሳሳይም እረኞች ውጤታማ ለመሆን ከፈለጉ አግባብ ያልሆነ ነገር ቢደርስባቸው እንኳን የዋህ መሆን አለባቸው። ለምሳሌ፣ ሊረዷቸው የሞከሩ አንዳንድ የጉባኤ አባላት በጎ ምላሽ ላይሰጡ ይችላሉ። እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው በመንፈሳዊ ደክሞ ወይም ታምሞ ከሆነ ምክር ሲሰጠው ‘እንደ ሰይፍ በሚወጋ ግድ የለሽ ቃል’ መልስ ሊሰጥ ይችላል። (ምሳሌ 12:18) የሆነ ሆኖ እረኞች ሻካራ ቃላትን በመናገር ወይም የብቀላ እርምጃ በመውሰድ አጸፋውን ከመመለስ በመታቀብ ኢየሱስን ይመስላሉ። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን በመግታት የአሳቢነት መንፈስ ያሳያሉ፤ ይህም እርዳታ ለሚያስፈልገው ሰው በረከት ያስገኝለታል። (1 ጴጥሮስ 3:8, 9) ምክር ሲሰጥህ የዋህነትና ራስን የመግዛት ባሕርይ በማሳየት የሽማግሌዎችን ምሳሌ ትከተላለህ?
19 ይሖዋና ኢየሱስ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እረኞች በዓለም ዙሪያ የሚገኘውን መንጋ ለመንከባከብ በፈቃደኝነትና በትጋት የሚያከናውኑትን ሥራ እንደሚያደንቁ ምንም አያጠራጥርም። እንዲሁም ሽማግሌዎችን በመደገፍ ‘ቅዱሳንን ለሚረዱ’ በሺዎች የሚቆጠሩ የጉባኤ አገልጋዮች ጥልቅ ፍቅር አላቸው። (ዕብራውያን 6:10) ታዲያ አንዳንድ የተጠመቁ ወንድሞች ይህንን “መልካም ሥራ” የመሥራት መብት ለማግኘት ከመጣጣር ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው? (1 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሖዋ፣ እረኛ አድርጎ የሾማቸውን ወንድሞች የሚያሠለጥናቸው እንዴት ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።
ታስታውሳለህ?
• እረኞች ለመንጋው ፍቅር የሚያሳዩባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
• ሁሉም የጉባኤው አባላት ለጉባኤው ደስታና ሰላም አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
• እረኞች ምክር ሲሰጡ ታጋሽና ደግ የሚሆኑት ለምንድን ነው?
• የጉባኤ ሽማግሌዎች በጎነትና እምነት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች በፍቅር ተነሳስተው ጉባኤውን ያገለግላሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በተጨማሪም ከቤተሰባቸው ጋር በመዝናናት . . .
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
. . . እንዲሁም በማገልገል አብረዋቸው ጊዜ ያሳልፋሉ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረጋቸው ለጉባኤው ደስታና ሰላም አስተዋጽኦ ያደርጋል