ንጉሡን ክርስቶስን በታማኝነት ማገልገል
ንጉሡን ክርስቶስን በታማኝነት ማገልገል
“ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት።”—ዳንኤል 7:14
1, 2. ክርስቶስ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ እንዳልያዘ እንዴት እናውቃለን?
ለተገዢዎቹ ሕይወቱን አሳልፎ ሊሰጥና እንደገና ሕይወት አግኝቶ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚችል ገዢ አለ? በምድር ላይ በመኖር ተገዢዎቹ እምነት እንዲጥሉበትና ለእርሱ ታማኝ እንዲሆኑ ካደረገ በኋላ ከሰማይ ሆኖ መግዛት የሚችል ንጉሥ የትኛው ነው? ይህንና ከዚህም የበለጡ ነገሮችን መፈጸም የቻለው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። (ሉቃስ 1:32, 33) ኢየሱስ ከሞተ፣ ትንሣኤ ካገኘና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ማለትም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት አምላክ “በቤተ ክርስቲያንም፣ በማንኛውም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾመው።” (ኤፌሶን 1:20-22፤ የሐዋርያት ሥራ 2:32-36) ክርስቶስ በዚህ ጊዜ በተወሰነ መጠን መግዛት ጀምሮ ነበር። የመጀመሪያ ተገዢዎቹ ‘የአምላክ እስራኤል’ የተባሉትን መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ያዋቀሩት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ናቸው።—ገላትያ 6:16፤ ቈላስይስ 1:13
2 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጰንጠቆስጤ በዓል ከተከበረ ወደ 30 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቶስ “በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል” በማለት ኢየሱስ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ እንዳልተረከበ አረጋግጧል። (ዕብራውያን 10:12, 13) ቆይቶም አረጋዊ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዢ ይሖዋ በሰማይ በተቋቋመው አዲስ መንግሥት ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ ሲሾመው በራእይ ተመልክቷል። (ራእይ 11:15፤ 12:1-5) ካለንበት የታሪክ ዘመን አንጻር ክርስቶስ በ1914 በሰማይ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት መጀመሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን መመርመር እንችላለን። a
3. (ሀ) የመንግሥቱ ምሥራች ከ1914 ወዲህ ምን አዲስ ገጽታ ይዟል? (ለ) ራሳችንን ምን እያልን መጠየቅ እንችላለን?
3 አዎን፣ የመንግሥቱ ምሥራች ከ1914 ጀምሮ አስደናቂ የሆነ አዲስ ገጽታ ይዟል። ኢየሱስ ‘በጠላቶቹ መካከል’ ቢሆንም እንኳን በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ከመሆኑም ባሻገር በምድር ያሉት ተገዢዎቹ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመምራት ሥልጣኑን እየተጠቀመበት ነው። (መዝሙር 110:1, 2፤ ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 12:7-12) በተጨማሪም በመላው ምድር የሚገኙ ታማኝ ተገዢዎቹ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ወደር በማይገኝለትና ዓለም አቀፍ ይዘት ባለው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ በመካፈል ለሥልጣኑ በደስታ እየተገዙ ነው። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 28:18) ‘የአምላክ መንግሥት ልጆች’ የሆኑት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች “የክርስቶስ እንደራሴዎች” ሆነው ያገለግላሉ። የአምላክ መንግሥት መልእክተኞች ሆነው የሚያገለግሉት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው “ሌሎች በጎች” እነዚህን ክርስቲያኖች በታማኝነት እየደገፏቸው ነው። (ማቴዎስ 13:38፤ 2 ቆሮንቶስ 5:20፤ ዮሐንስ 10:16) ሆኖም የክርስቶስን ሥልጣን በእርግጥ መቀበላችንን ለማረጋገጥ በግለሰብ ደረጃ ራሳችንን መመርመር አለብን። ለእርሱ የጸና የታማኝነት አቋም አለን? ሰማይ ሆኖ እየገዛ ላለው ንጉሥ ታማኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ በመጀመሪያ ለክርስቶስ ታማኝ መሆን ያለብን ለምን እንደሆነ እንመልከት።
ታማኝ እንድንሆንለት የሚያነሳሱ ባሕርያት ያሉት ንጉሥ
4. ኢየሱስ እጩ ንጉሥ ሆኖ በምድር ባገለገለበት ወቅት ምን አከናውኗል?
4 ለክርስቶስ ታማኝ እንድንሆን የሚያነሳሳን ላደረጋቸው ነገሮችና ወደር ለሌላቸው ባሕርያቱ ያለን አድናቆት ነው። (1 ጴጥሮስ 1:8) ለንግሥና የታጨው ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አምላክ በወሰነው ጊዜ ዓለምን በሙሉ ሲገዛ የሚያከናውነውን ነገር በጥቂቱ አሳይቷል። የተራቡትን መግቧል። የታመሙትን፣ የአካል ጉዳት ያለባቸውን እንዲሁም ማየት፣ መስማትና መናገር የተሳናቸውን ፈውሷል። ሌላው ቀርቶ ሙታንን እንኳ አስነስቷል። (ማቴዎስ 15:30, 31፤ ሉቃስ 7:11-16፤ ዮሐንስ 6:5-13) በተጨማሪም ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወት ማወቃችን፣ የወደፊቱ የምድራችን ንጉሥ ስላሉት ባሕርያት በተለይ ደግሞ የራስን ጥቅም እስከ መሠዋት ስለሚያደርሰው ፍቅሩ ግንዛቤ እንድናገኝ ያስችለናል። (ማርቆስ 1:40-45) ከዚህ ጋር በተያያዘ ናፖሊዮን ቦናፓርት እንዲህ እንዳለ ይነገራል:- “እስክንድር፣ ቄሣር፣ ሻርለማኝና እኔ ሰፋፊ ግዛቶች መመሥረት ችለናል፤ ነገር ግን እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ውጤት ያገኘነው እንዴት ነው? በኃይል ነው። መንግሥቱን በፍቅር ላይ የመሠረተው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በአሁኑ ጊዜም እንኳን ለእርሱ ሲሉ ለመሞት ፈቃደኛ የሚሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ።”
5. የኢየሱስ ባሕርይ ሰዎችን ይማርክ የነበረው ለምንድን ነው?
5 ኢየሱስ የዋህና ትሑት ስለነበር ካለባቸው ጭንቀትና ጫና የተነሳ ሸክም የከበዳቸው ሰዎች በሚያንጹ ትምህርቶቹና በግሩም ባሕርያቱ እረፍት አግኝተው ነበር። (ማቴዎስ 11:28-30) ልጆች ከእርሱ ጋር መሆን አይከብዳቸውም ነበር። ትሑትና አስተዋይ ሰዎች በደስታ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሆነዋል። (ማቴዎስ 4:18-22፤ ማርቆስ 10:13-16) አሳቢነቱና የሚያስከብር ጠባዩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው በርካታ ሴቶች ታማኝ እንዲሆኑለት አነሳስቷቸዋል፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ኢየሱስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ቁሳዊ ንብረታቸውን እርሱን ለመንከባከብ አውለዋል።—ሉቃስ 8:1-3
6. አልዓዛር በሞተበት ወቅት የትኞቹ የኢየሱስ መልካም ባሕርያት ታይተዋል?
6 የቅርብ ጓደኛው አልዓዛር በሞተ ጊዜ በጣም ግሩም ከሆኑት የክርስቶስ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ በግልጽ ታይተዋል። ማርያምና ማርታ አዝነው ሲያያቸው መንፈሱ ታወከበት፤ ከዚያም “እንባውን አፈሰሰ።” ከጥቂት ቆይታ በኋላ አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሳው ቢያውቅም ከልብ ‘አዝኗል።’ ከዚያም ኢየሱስ በፍቅሩና በርኅራኄው ተገፋፍቶ አምላክ የሰጠውን ኃይል በመጠቀም አልዓዛርን ከሞት አስነሳው።—ዮሐንስ 11:11-15, 33-35, 38-44
7. ለኢየሱስ ታማኝ መሆናችን ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (በገጽ 31 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
7 ኢየሱስ ትክክለኛ ለሆነው ነገር የነበረው ጠንካራ ፍቅር እንዲሁም ለግብዝነትና ለክፋት የነበረው ጥላቻ በጣም ያስደንቃል። ስግብግብ ነጋዴዎችን ከቤተ መቅደሱ ሁለት ጊዜ በማባረር ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ወስዷል። (ማቴዎስ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 2:14-17) ከዚህም በላይ ሰው ሆኖ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜ ሁሉንም ዓይነት መከራ መቅመሱ እኛ የሚያጋጥመንን ጭንቀትና ችግር በሚገባ ለማወቅ አስችሎታል። (ዕብራውያን 5:7-9) እንዲሁም ኢየሱስ የጥላቻና የግፍ ዒላማ መሆን ምን ስሜት እንደሚፈጥር ያውቃል። (ዮሐንስ 5:15-18፤ 11:53, 54፤ 18:38 እስከ 19:16) በኋላም የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸምና ለተገዢዎቹ የዘላለም ሕይወት ለማስገኘት ሲል በድፍረት ለአሰቃቂ ሞት ራሱን አቅርቧል። (ዮሐንስ 3:16) እንዲህ ያሉት የክርስቶስ ባሕርያት እርሱን በታማኝነት ማገልገልህን እንድትቀጥል አያነሳሱህም? (ዕብራውያን 13:8፤ ራእይ 5:6-10) ታዲያ የንጉሡ የክርስቶስ ተገዢ ለመሆን የሚያስፈልገው ምንድን ነው?
የክርስቶስ ተገዢ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ማሟላት
8. የክርስቶስ ተገዢዎች ምን ይጠበቅባቸዋል?
8 እስቲ ስለሚከተለው ንጽጽር አስብ:- የሌላ አገር ዜግነት ለማግኘት ብዙውን ጊዜ አንዳንድ መሠረታዊ ብቃቶችን ማሟላት ያስፈልጋል። ዜግነት ለማግኘት ጥያቄ ያቀረቡት ሰዎች መልካም ምግባር እንዲኖራቸውና የሚደረጉላቸውን አንዳንድ የጤና ምርመራዎች እንዲያልፉ ይጠበቅባቸው ይሆናል። በተመሳሳይም የክርስቶስ ተገዢዎች ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋሞችን ሊጠብቁና ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት ሊኖራቸው ይገባል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ገላትያ 5:19-23
9. ለክርስቶስ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ክርስቶስ ተገዢዎቹ ለእርሱና ለመንግሥቱ ታማኝ እንዲሆኑ መጠበቁ ተገቢ ነው። እንዲህ ያለውን ታማኝነት የሚያሳዩት እጩ ንጉሥ ሆኖ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ካስተማረው ትምህርት ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቁሳዊ ሀብትን ከማሳደድ ይልቅ የመንግሥቱን ፍላጎቶችና የአምላክን ፈቃድ ያስቀድማሉ። (ማቴዎስ 6:31-34) እንዲሁም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም እንኳን የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ ለማንጸባረቅ ከልብ ይጥራሉ። (1 ጴጥሮስ 2:21-23) በተጨማሪም የክርስቶስ ተገዢዎች ለሌሎች መልካም በማድረግ ረገድ ቀዳሚ በመሆን የእርሱን ምሳሌ ይከተላሉ።—ማቴዎስ 7:12፤ ዮሐንስ 13:3-17
10. (ሀ) በቤተሰብ ውስጥ (ለ) በጉባኤ ውስጥ ለክርስቶስ ያለንን ታማኝነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
10 የኢየሱስ ተከታዮች ለእርሱ ታማኝ መሆናቸውን የሚያሳዩበት ሌላው መንገድ በቤተሰብ ውስጥ ባሕርያቱን በማንጸባረቅ ነው። ለአብነት ያህል፣ ባሎች የክርስቶስን ባሕርይ በሚያንጸባርቅ መንገድ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በመያዝ በሰማይ ለሚገኘው ንጉሣቸው ታማኝ እንደሆኑ ያሳያሉ። (ኤፌሶን 5:25, 28-30፤ 6:4፤ 1 ጴጥሮስ 3:7) ሚስቶች ደግሞ በንጹሕ ሥነ ምግባር በመመላለስ እንዲሁም “ገርና ጭምት መንፈስ” በማንጸባረቅ ለክርስቶስ ታማኝ እንደሆኑ ያሳያሉ። (1 ጴጥሮስ 3:1-4፤ ኤፌሶን 5:22-24) ልጆችም እንዲሁ የክርስቶስን የታዛዥነት ምሳሌ በመከተል ለእርሱ ታማኝ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ኢየሱስ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳን ወጣት እያለ ለወላጆቹ ይታዘዝላቸው ነበር። (ሉቃስ 2:51, 52፤ ኤፌሶን 6:1) የክርስቶስ ተገዢዎች ‘እርስ በርሳቸው በመተሳሰብ፣ እንደ ወንድማማቾች በመዋደድና ርኅሩኆች በመሆን’ እርሱን ለመምሰል በታማኝነት ጥረት ያደርጋሉ። ‘ትሑት በመሆንና ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ ባለመመለስ’ ክርስቶስን ለመምሰል ይጣጣራሉ።—1 ጴጥሮስ 3:8, 9፤ 1 ቆሮንቶስ 11:1
ሕግ አክባሪ ተገዢዎች
11. የክርስቶስ ተገዢዎች ለየትኞቹ ሕግጋት ይገዛሉ?
11 ዜግነት የጠየቁ ሰዎች የአዲሱን አገራቸውን ሕግ እንደሚታዘዙ ሁሉ፣ የክርስቶስ ተገዢዎችም ሕይወታቸውን ኢየሱስ ካስተማረውና ካዘዘው ነገር ሁሉ ጋር በማስማማት “የክርስቶስን ሕግ” ያከብራሉ። (ገላትያ 6:2) በተለይ “ክቡር ሕግ” በተባለው በፍቅር ሕግ በታማኝነት ይመራሉ። (ያዕቆብ 2:8) እነዚህ ሕግጋት ምንን ይጨምራሉ?
12, 13. “የክርስቶስን ሕግ” በታማኝነት የምንታዘዘው እንዴት ነው?
12 የክርስቶስ ተገዢዎች አለፍጽምናና ድክመት አለባቸው። (ሮሜ 3:23) ስለዚህ ‘እርስ በርሳቸው አጥብቀው ከልብ መዋደድ’ እንዲችሉ ‘ለወንድሞቻቸው ቅን ፍቅርን’ እያዳበሩ ለመሄድ ዘወትር ይጥራሉ። (1 ጴጥሮስ 1:22) “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር” ክርስቲያኖች ‘እርስ በርስ በመቻቻልና ይቅር በመባባል’ የክርስቶስን ሕግ በታማኝነት ይፈጽማሉ። ይህንን ሕግ መታዘዛቸው የሰዎችን አለፍጽምና አጋንኖ ከመመልከት ሊጠብቃቸውና እርስ በርስ እንዲዋደዱ በሚገፋፏቸው ምክንያቶች ላይ እንዲያተኩሩ ሊረዳቸው ይችላል። “በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን” ፍቅርን ለብሰው ለአፍቃሪው ንጉሣችን በታማኝነት ከሚገዙ ሰዎች መካከል በመሆንህ አመስጋኝ ነህ?—ቈላስይስ 3:13, 14
13 በተጨማሪም ኢየሱስ እርሱ ያሳየው ፍቅር ሰዎች ብዙውን ጊዜ እርስ በርሳቸው ከሚያሳዩት ፍቅር እንደሚልቅ ገልጿል። (ዮሐንስ 13:34, 35) የሚወዱንን ብቻ የምንወድ ከሆነ ‘ከሌሎች በምንም አንሻልም።’ እንዲህ ከሆነ ፍቅራችን የተሟላ አይሆንም። ኢየሱስ ለሚጠሉንና ለሚያሳድዱን ጠላቶቻችን እንኳ ሳይቀር በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅር በማሳየት የአባቱን ፍቅር እንድንኮርጅ አሳስቦናል። (ማቴዎስ 5:46-48) በተጨማሪም ይህ ፍቅር የመንግሥቱ ተገዢዎች ዋነኛ ሥራቸውን በታማኝነት ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ ይገፋፋቸዋል። ይህ ሥራ ምንድን ነው?
ታማኝነታቸው እየተፈተነ ነው
14. የስብከቱ ሥራ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ‘ስለ አምላክ መንግሥት የመመሥከር’ አንገብጋቢ ሥራ አለባቸው። (የሐዋርያት ሥራ 28:23) የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጠው ይህ መሲሐዊ መንግሥት በመሆኑ እንዲህ ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:24-28) ምሥራቹን ስንሰብክ የሚያዳምጡን ሰዎች የአምላክ መንግሥት ተገዢ የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። እንዲሁም ሰዎች ለምንሰብከው መልእክት የሚሰጡት ምላሽ ንጉሡ ክርስቶስ ለሰዎች ፍርድ ለመስጠት የሚያስችለው መመዘኛ ሆኖ ያገለግላል። (ማቴዎስ 24:14፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-10) ስለዚህ ለክርስቶስ ታማኝነታችንን ማሳየት የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ለሌሎች ስለ መንግሥቱ እንድንናገር እርሱ የሰጠንን ትእዛዝ መፈጸም ነው።—ማቴዎስ 28:18-20
15. የክርስቲያኖች ታማኝነት የሚፈተነው ለምንድን ነው?
15 ሰይጣን አቅሙ በፈቀደለት መጠን የስብከቱን ሥራ እንደሚቃወም ምንም አያጠራጥርም፤ ሰብዓዊ ገዢዎችም ክርስቶስ ከአምላክ ላገኘው ሥልጣን እውቅና አልሰጡም። (መዝሙር 2:1-3, 6-8) በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹን “‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ . . . እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል” ብሎ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:20) ስለዚህ የክርስቶስ ተከታዮች ታማኝነታቸው እንዲፈተን በሚያደርግ መንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ይገኛሉ።—2 ቆሮንቶስ 10:3-5፤ ኤፌሶን 6:10-12
16. የመንግሥቱ ተገዢዎች “የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” የሚሰጡት እንዴት ነው?
16 የሆነ ሆኖ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች በዓይን ለማይታየው ንጉሣቸው ታማኝ ሆነው ይኖራሉ፤ ለመንግሥት ባለ ሥልጣናትም ቢሆን አክብሮት አላቸው። (ቲቶ 3:1, 2) ኢየሱስ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” ሲል ተናግሯል። (ማርቆስ 12:13-17) ስለሆነም የኢየሱስ ተገዢዎች ከአምላክ ሕግ ጋር የማይጋጩትን የመንግሥት ሕጎች ይታዘዛሉ። (ሮሜ 13:1-7) የአይሁዳውያን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከአምላክ ሕግ ጋር በመቃረን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መስበካቸውን እንዲያቆሙ ባዘዛቸው ጊዜ፣ በጥብቅ ሆኖም በአክብሮት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚል መልስ ሰጥተዋል።—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ 5:27-32
17. የታማኝነት ፈተናዎችን በድፍረት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
17 ክርስቲያን ተገዢዎች ስደት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ለንጉሣቸው ታማኝ ሆነው ለመቀጠል ትልቅ ድፍረት እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው። ቢሆንም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ።” (ማቴዎስ 5:11, 12) ጥንት የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት ተመልክተዋል። መስበካቸውን ባለማቆማቸው ምክንያት ሲገረፉ “ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው” ደስ አላቸው። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 5:41, 42) አንተም ችግር ሲደርስብህ፣ ሕመም ሲያጋጥምህ፣ ዘመድህን በሞት በማጣትህ ምክንያት ሐዘን ሲደርስብህ ወይም ተቃውሞ ሲያጋጥምህ የምትጸና ከሆነ ተመሳሳይ የታዛዥነት መንፈስ እያሳየህ በመሆኑ ልትመሰገን ይገባሃል።—ሮሜ 5:3-5፤ ዕብራውያን 13:6
18. ኢየሱስ ለጳንጥዮስ ጲላጦስ የተናገራቸው ቃላት ምን ያሳያሉ?
18 ኢየሱስ ለንግሥና ታጭቶ በነበረበት ወቅት ላይ ለሮማዊው ገዢ ለጳንጥዮስ ጲላጦስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:36) ስለዚህ በሰማይ የሚገኘው መንግሥት ተገዢዎች ከማንም ጋር ለመዋጋት የጦር መሣሪያ አያነሱም፤ በየትኛውም የሰው ልጆች ግጭት ውስጥ አንዱን ወገን ደግፈው አይቆሙም። ‘ለሰላሙ ልዑል’ ታማኝ ስለሆኑ መከፋፈልን ከሚፈጥሩ የዓለም ጉዳዮች ፈጽሞ ገለልተኛ ናቸው።—ኢሳይያስ 2:2-4፤ 9:6, 7
ታማኝ ተገዢዎች የሚያገኙት ዘላለማዊ ሽልማት
19. የክርስቶስ ተገዢዎች የወደፊቱን ጊዜ በሙሉ እምነት መጠበቅ የሚችሉት ለምንድን ነው?
19 “የነገሥታት ንጉሥ” የሆነው የክርስቶስ ታማኝ ተገዢዎች የወደፊቱን ጊዜ በሙሉ እምነት ይጠባበቃሉ። የእርሱ መለኮታዊ አገዛዝ በምድር ላይ የሚጀምርበትን ጊዜ ይናፍቃሉ። (ራእይ 19:11 እስከ 20:3፤ ማቴዎስ 24:30) በመንፈስ የተቀቡት ‘የይሖዋ መንግሥት ልጆች’ ታማኝ ቀሪዎች፣ ውድ የሆነውን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመንገሥ ውርሻቸውን ለማግኘት በተስፋ ይጠብቃሉ። (ማቴዎስ 13:38፤ ሉቃስ 12:32) ታማኝ የሆኑት የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ደግሞ ንጉሣቸው “እናንት አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት [የአምላክ መንግሥት የሚያስተዳድረውን ምድራዊ ገነት] ውረሱ” በማለት የሚናገርበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:34) ስለሆነም የመንግሥቱ ተገዢዎች የሆንን ሁሉ ንጉሡን ክርስቶስን በታማኝነት ማገልገላችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 94-96 ላይ የሚገኘውን “የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንግሥት የተቋቋመችው በ1914 ነው የሚሉት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ክርስቶስ ታማኝ እንድንሆን መጠበቁ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
• የክርስቶስ ተገዢዎች ለእርሱ ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
• ለንጉሡ ለክርስቶስ ታማኝ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ግሩም የሆኑ ሌሎች የክርስቶስ ባሕርያት
የማያዳላ—ዮሐንስ 4:7-30
ርኅሩኅ—ማቴዎስ 9:35-38፤ 12:18-21፤ ማርቆስ 6:30-34
የራስን ጥቅም እስከመሠዋት የሚያደርስ ፍቅር ያለው—ዮሐንስ 13:1፤ 15:12-15
ታማኝ—ማቴዎስ 4:1-11፤ 28:20፤ ማርቆስ 11:15-18
የሌሎችን ችግር እንደራሱ አድርጎ የሚመለከት—ማርቆስ 7:32-35፤ ሉቃስ 7:11-15፤ ዕብራውያን 4:15, 16
ምክንያታዊ—ማቴዎስ 15:21-28
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እርስ በርሳችን በመዋደድ “የክርስቶስን ሕግ” በታማኝነት እንታዘዛለን
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስቶስ ባሕርያት እርሱን በታማኝነት እንድታገለግል ይገፋፉሃል?