በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ ማወቄ ሕይወቴን ለውጦታል

አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ ማወቄ ሕይወቴን ለውጦታል

የሕይወት ታሪክ

አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ ማወቄ ሕይወቴን ለውጦታል

ሃሪ ፐሎያን እንደተናገረው

አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ? ይህ ጥያቄ ከልጅነቴ ጀምሮ ያስጨንቀኝ ነበር። ወላጆቼ ጠንካራ ሠራተኞች፣ ሐቀኞች እንዲሁም ለቤተሰባቸው ደኅንነት ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ነበሩ። ይሁን እንጂ አባቴ ለሃይማኖት ግድ የለሽ የነበረ ሲሆን እናቴም ብትሆን ያን ያህል ሃይማኖተኛ አልነበረችም። በዚህም ምክንያት ለዚህ ጥያቄዬ መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም።

ሦስት ዓመት በላይ በዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ማለትም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደም ሆነ ከዚያ በኋላ ይህን ጥያቄ መጠየቄን አላቆምኩም ነበር። ጦርነቱ ካበቃም በኋላ ወደ ቻይና የሚላክ የእርዳታ ቁሳቁስ የጫነች መርከብ ላይ እንድሠራ ተመደብኩ። እዚያም ወደ አንድ ዓመት ገደማ የቆየሁ ሲሆን ብዙ ሰዎች ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው ተመልክቻለሁ።

ቻይናውያን ታታሪና ጥሩ የአእምሮ ችሎታ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። ነገር ግን ብዙዎቹ በድህነት እንዲሁም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ባስከተለው ብጥብጥ ምክንያት ለከባድ መከራ ተዳርገዋል። በተለይ ረሃብ ያጠቃቸውና የተቦጫጨቀ ልብስ የለበሱ የሚያማምሩ ልጆች ከመርከብ እንደወረድን ለመለመን ወደ እኛ ሲመጡ ስመለከት በጣም አዘንኩ።

ለምን?

የተወለድኩት በ1925 ሲሆን ያደግሁት በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው። በመሆኑም በቻይና ያየሁትን የመሰለ ነገር ከዚህ ቀደም አይቼ አላውቅም ነበር። ስለዚህ ‘ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ካለ ሰዎችን በተለይ ደግሞ ምንም የማያውቁ ልጆችን ለሥቃይ የሚዳርጉ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ለምን ፈቀደ?’ በማለት በተደጋጋሚ እጠይቅ ነበር።

በተጨማሪም ‘አምላክ በእርግጥ ካለ እንዲህ ያለ ጥፋት፣ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ሞትና ሥቃይ ለዘመናት በሰው ልጆች ላይ እንዲደርስ ለምን ፈቀደ? በተለይ ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከ50 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ ለምን ዝም አለ?’ እያልኩ እጠይቅ ነበር። ከዚህም በላይ በዚያ ጦርነት ወቅት በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ሰዎች ዜግነታቸው የተለያየ ስለሆነ ብቻ በቀሳውስት ገፋፊነት እርስ በርስ የተጨፋጨፉት ለምንድን ነው?

የሠራሁት ቴሌስኮፕ

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ፈንድቶ በርካታ የዓለም ሕዝቦችን በጨረሰበት ወቅት አምላክ ሊኖር አይችልም የሚል ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ በሳይንስ ትምህርት ላይ ሁላችንም አንድ ዓይነት ሳይንሳዊ መሣሪያ እንድንሠራ ታዘዝን። ሥነ ፈለክ ይማርከኝ ስለነበር መሃል ለመሃል 20 ሴንቲ ሜትር የሆነ ሌንስ ያለው ትልቅ ቴሌስኮፕ መሥራት ጀመርኩ።

ይህን ቴሌስኮፕ ለመሥራት ውፍረቱ 2.5 ሴንቲ ሜትር ስፋቱ ደግሞ 20 ሴንቲ ሜትር የሆነ መስተዋት ገዛሁና ክብ ቅርጽ እንዲኖረው አድርጌ አስቆረጥሁት። ከዚያም መስተዋቱ ስርጉድ (concave) ቅርጽ እንዲይዝ ለማድረግ በሻካራ ነገር መሞረድ ጀመርኩ፤ ይህን የማከናውነው በእጄ በመሆኑ ሥራው አድካሚ ነበር። ይህም በአንድ ሴሚስተር ውስጥ ያለኝን ትርፍ ጊዜ በሙሉ ወሰደብኝ። መስተዋቱን ቅርጽ ካስያዝኩት በኋላ በረዥም የብረት ቱቦ ውስጥ ገጠምኩት፤ ከዚያም ለማየት የሚያገለግል መነጽር አበጀሁለት።

ጨረቃ በሌለችበትና ሰማዩ ጥርት ብሎ በሚታይበት አንድ ምሽት የሠራሁትን ቴሌስኮፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሰማይ አነጣጥሬ ከዋክብትንና በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያሉትን ፕላኔቶች ማየት ቻልኩ። የሰማይ ፍጥረታትን ብዛት ብሎም በሚገባ የተደራጁ መሆናቸውን ስመለከት በጣም ተደነቅሁ። ያየኋቸው አንዳንድ “ከዋክብት” በእርግጥ ከዋክብት ሳይሆኑ እንደ እኛዋ ሚልክዌይ (ፍኖተ ሐሊብ) እያንዳንዳቸው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን የያዙ ጋላክሲዎች መሆናቸውን ሳውቅ በጣም ተገረምኩ።

‘እነዚህ ሁሉ ፈጽሞ እንዲሁ በራሳቸው ሊገኙ አይችሉም። በሚገባ የተደራጀ ማንኛውም ነገር በአጋጣሚ ሊገኝ ስለማይችል ጽንፈ ዓለም ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ባለው አካል የተሠራ መሆን አለበት። ስለዚህም አምላክ አለ ማለት ነው?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። በሠራሁት ቴሌስኮፕ የተመለከትኩት ነገር አምላክ የለም የሚለውን ጭፍን እምነቴን እንዳስተካክል ረድቶኛል።

ከዚያም ራሴን እንዲህ እያልኩ መጠየቅ ጀመርኩ:- ‘ይህን አስደናቂ ጽንፈ ዓለም የፈጠረ ታላቅ ኃይል ያለውና ጥበበኛ አምላክ ካለ በምድር ላይ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ለምን አይቀይረውም? ገና ከጅምሩ ይህን የመሰለ አሰቃቂ ነገር እንዲኖር ለምን ፈቀደ?’ እነዚህን ጥያቄዎቼን ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎችን ብጠይቅም አጥጋቢ መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁና በኮሌጅ የተወሰኑ ዓመታት ከቆየሁ በኋላ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ውስጥ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ይሁን እንጂ በጦር ሠራዊት ውስጥ ያሉት ቀሳውስትም ቢሆኑ ለጥያቄዎቼ መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም። አብዛኛውን ጊዜ ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች “የአምላክ ሥራ ምስጢር ነው” ብለው መልስ መስጠታቸው የተለመደ ነው።

ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት የማደርገውን ጥረት ቀጠልኩ

ከቻይና ከተመለስኩ በኋላም አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ የሚለው ጥያቄ ወደ አእምሮዬ መምጣቱ አልቀረም። በተለይ ፓስፊክን አቋርጠን ወደ አሜሪካ ስንመለስ ባረፍንባቸው ደሴቶች ላይ የወታደሮች መካነ መቃብር ባየሁ ቁጥር እነዚህ ጥያቄዎች ይመጡብኝ ነበር። ሁሉም መቃብሮች ማለት ይቻላል ገና ምኑንም ያላዩ ወጣቶች የተቀበሩባቸው ነበሩ።

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተመለስኩና ከባሕር ኃይል ከተሰናበትኩ በኋላ ካምብሪጅ፣ ማሳቹሴትስ በሚገኘው ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የቀረኝን የአንድ ዓመት ትምህርት አጠናቅቄ ዲግሪዬን አገኘሁ። ይሁን እንጂ የኮሌጅ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ካሊፎርኒያ ወደሚገኘው ቤታችን አልተመለስኩም። ለጥያቄዎቼ መልስ እስካገኝ ድረስ በምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስ ለመቆየት ወሰንኩ። በኒው ዮርክ ብዙ ሃይማኖቶች ስላሉ ወደዚያ ሄጄ በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ በመገኘት ምን እንደሚያስተምሩ ለማወቅ ፈለግሁ።

በኒው ዮርክ የምትኖረው ኢዛቤል ካፒጀን የተባለችው አክስቴ እርሷ ቤት እንዳርፍ ጋበዘችኝ። እርሷ እንዲሁም ሮዝና ሩት የተባሉት ሁለት ልጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። እምነታቸው ያን ያህል የሚስብ ሆኖ ስላልተሰማኝ ወደ ሌሎች ቤተ ክርስቲያኖች መሄድና ከሰዎቹ ጋር መነጋገር እንዲሁም ጽሑፎቻቸውን ማንበብ ጀመርኩ። በዚያ የማገኛቸውን ሰዎች ብዙውን ጊዜ፣ አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ ብዬ እጠይቃቸው ነበር። ይሁን እንጂ እነርሱም ቢሆኑ ከእኔ የተሻለ እውቀት አልነበራቸውም። ከዚያም ምናልባት አምላክ ስለሌለ ይሆናል ወደሚል መደምደሚያ ደረስኩ።

መልስ አገኘሁ

የይሖዋ ምሥክሮችን አመለካከት ማወቅ ስለፈለግሁ አክስቴንና ልጆቿን አንዳንድ የማነባቸው ጽሑፎች እንዲሰጡኝ ጠየቅኋቸው። ጽሑፎቹን ካነበብኩ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖቶች በጣም የተለዩ መሆናቸውን ለማስተዋል ጊዜ አልወሰደብኝም። መልስ የሚሰጡት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመሆኑም በላይ በጣም አሳማኝ ናቸው። በአጭር ጊዜ ውስጥ አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ ተረዳሁ።

ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን መልሳቸውን በተግባር እንደሚደግፉት አስተዋልኩ። ለምሳሌ ያህል፣ አክስቴን ‘በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን የነበሩ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ምን አደረጉ? ወታደር ሆነው ነበር? ሃይል ሂትለር! (ሂትለር አዳኝ ነው!) ብለዋል? ለስዋስቲካ ባንዲራ ሰላምታ ሰጥተው ነበር?’ በማለት ጠየቅኋት። እርሷም በፍጹም ስትል መለሰችልኝ። ከዚህ ይልቅ ባላቸው የገለልተኝነት አቋም ምክንያት ወደ ማጎሪያ ካምፖች የተወሰዱ ከመሆናቸውም ሌላ እዚያም ብዙዎች እንደተገደሉ ነገረችኝ። አክስቴ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በጦርነት ወቅት ያላቸው አቋም አንድ እንደሆነ ይኸውም ፍጹም ገለልተኞች እንደሆኑ አብራራችልኝ። ሌላው ቀርቶ ዲሞክራሲያዊ ናቸው በሚባሉ አገሮች እንኳ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በገለልተኝነት አቋማቸው የተነሳ ወኅኒ ወርደዋል።

ከዚያም አክስቴ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” የሚለውን ዮሐንስ 13:35ን እንዳነብ ነገረችኝ። እውነተኛ ክርስቲያኖች የትም ይኑሩ የት የክርስትና መለያ ምልክት የሆነው ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል። ዜግነታቸው የተለያየ ስለሆነ ብቻ በተቃራኒ ጎራዎች ውስጥ ተሰልፈው በፍጹም እርስ በርስ አይገዳደሉም! ከዚያም “ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በሮማውያን ጦርነት ወቅት የተለያየ ጎራ ይዘው እርስ በርስ ይዋጋሉ ብለህ ታስባለህ?” ስትል ጠየቀችኝ።

በመቀጠልም 1 ዮሐንስ 3:10-12 ላይ ያለውን ሐሳብ እንዳነብ ጠየቀችኝ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው:- ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። . . . እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል . . . የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ።”

በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት ግልጽ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች በየትኛውም አገር ቢኖሩ እርስ በርስ መዋደድ አለባቸው። ስለዚህ መንፈሳዊ ወንድማቸውንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ሰው አይገድሉም። ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ “እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም” ብሎ የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው።—ዮሐንስ 17:16

አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ ተማርኩ

ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት እንደሚናገር ተማርኩ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ፍጹም አድርጎ ከመፍጠሩም ሌላ በዔደን ገነት እንዳኖራቸው ያብራራል። (ዘፍጥረት 1:26፤ 2:15) በተጨማሪም በጣም አስደናቂ የሆነ ስጦታ ማለትም የፈለጉትን የመምረጥ ነጻነት ሰጥቷቸዋል። ይህ ስጦታ ግን ኃላፊነትም ያስከትል ነበር። አምላክንና እርሱ ያወጣውን ሕግ ከታዘዙ ፍጹም እንደሆኑ ለዘላለም በገነት መኖር ይችላሉ። ከዚህም ሌላ የገነትን ወሰን በመላው ምድር ማስፋት ይችሉ ነበር። የሚወልዷቸውም ልጆች ፍጹማን ስለሚሆኑ ከጊዜ በኋላ ምድር ፍጹማንና ደስተኛ በሆኑ ሰዎች ትሞላ ነበር።—ዘፍጥረት 1:28

ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን ከአምላክ መንገድ ርቀው ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት ከመረጡ ፍጹማን ሆነው እንዲቀጥሉ አይፈቀድላቸውም። (ዘፍጥረት 2:16, 17) የሚያሳዝነው ግን ወላጆቻችን የመምረጥ ነጻነታቸውን ያላግባብ በመጠቀም ከአምላክ ርቀው በራሳቸው መመራትን መረጡ። ይህንን እንዲያደርጉም የገፋፋቸው ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራ አንድ ዓመጸኛ መንፈሳዊ ፍጡር ነው። ሰይጣን ከአምላክ አገዛዝ ነጻ ለመሆንና ለአምላክ ብቻ መሰጠት የሚገባውን አምልኮ ለራሱ ለማድረግ ተመኘ።—ዘፍጥረት 3:1-19፤ ራእይ 4:11

በዚህ መንገድ ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” ሆነ። (2 ቆሮንቶስ 4:4) መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለምም በክፉው ሥር” ነው በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) ኢየሱስም ቢሆን ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ጠርቶታል። (ዮሐንስ 14:30) መላው የሰው ልጅ ፍጽምናውን ያጣው እንዲሁም ለዓመጽ፣ ለሞት፣ ለሐዘንና ለመከራ የተዳረገው ሰይጣንና የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ታዛዥ ባለመሆናቸው ምክንያት ነው።—ሮሜ 5:12

‘ሰው አካሄዱን በራሱ ማቃናት አይችልም’

የፈጣሪን ሕግ ችላ ማለት ምን ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል መላው የሰው ዘር እንዲያይ አምላክ የኃጢአት ውጤቶች በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት እንዲኖሩ ፈቀደ። ይህ ረጅም ጊዜ መላው የሰው ዘር ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እውነተኝነት እንዲያስተውል ሰፊ አጋጣሚ ፈጥሮለታል:- “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ቅጣኝ።”—ኤርምያስ 10:23, 24

ዛሬ በርካታ ዓመታት ካለፉ በኋላም ከአምላክ የራቀ አገዛዝ ውድቀት እንደሚያስከትል ሁላችንም ማየት ችለናል። በመሆኑም አምላክ፣ የሰው ዘር ከእርሱና ከሕጉ ርቆ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያደርገው አጥፊ ሙከራ እንዲቀጥል አይፈቅድም።

አስደሳች ተስፋ

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚያመለክቱት በቅርቡ አምላክ ይህንን ክፉ ሥርዓት ወደ መደምደሚያው ያመጣዋል። “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:10, 11

በዳንኤል 2:44 ላይ እንዲህ የሚል ትንቢት ይገኛል:- “በነዚያ ነገሥታት [ዛሬ ባሉት ሰብዓዊ መንግሥታት] ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” ከዚያ በኋላ የሰው አገዛዝ እንዲኖር አይፈቀድም። መላዋ ምድር በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ትሆናለች። በዚህ አስተዳደር ሥር መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች፤ እንዲሁም የሰው ዘር ለዘላለም ደስተኛ ሆኖ እንዲኖር ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም” በማለት ተስፋ ይሰጣል። (ራእይ 21:4) አምላክ ያዘጋጀልን ተስፋ እንዴት አስደናቂ ነው!

ከበፊቱ የተለየ ሕይወት

ለጥያቄዎቼ አጥጋቢ መልስ ማግኘቴ ሕይወቴን ለወጠው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አምላክን የማገልገል እንዲሁም ሌሎች ሰዎች የዚህን ጥያቄ መልስ እንዲያውቁ የመርዳት ፍላጎት አደረብኝ። በ1 ዮሐንስ 2:17 ላይ የሚገኘው “ዓለምና [ሰይጣን አምላኩ የሆነለት ይህ ሥርዓት] ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለው ሐሳብ የያዘውን ከፍተኛ ቁም ነገር ተገነዘብኩ። አምላክ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ጓጓሁ። በኒው ዮርክ ለመቆየት ወሰንኩና በዚያ ካለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር አንድ ላይ መሰብሰብ ጀመርኩ። እንዲሁም እኔ የተማርኩትን ለሌሎች በማስተማር ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎችን አግኝቻለሁ።

በ1949 ሮዝ ሜሪ ሊዊስ ከተባለች እህት ጋር ተዋወቅሁ። እርሷ፣ እናቷ ሳዲያ እንዲሁም ስድስት እህቶቿ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ሮዝ በስብከቱ ሥራ ሙሉ ጊዜዋን በማሳለፍ አምላክን ታገለግል ነበር። ሮዝ በርካታ ጥሩ ባሕርያት ስላሏት ወዲያውኑ በእርሷ ተማረክሁ። ከዚያም ሰኔ 1950 ተጋባንና ኑሯችንን በኒው ዮርክ አደረግን። እየሠራን ባለነው ሥራና ወደፊት አምላክ ባዘጋጀው አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስላለን በጣም ተደስተን እንኖር ነበር።

በ1957 እኔና ሮዝ ሜሪ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት እንድናገለግል ተጠራን። ሰኔ 2004 ደስታ የሞላበትን የትዳር ሕይወታችንን 54ኛ ዓመት ያከበርን ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 47ቱን ዓመታት ያሳለፍናቸው በብሩክሊን ቤቴል ነው። በሺህ ከሚቆጠሩ ወንድሞች ጋር አብረን ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍናቸው ዓመታት አርኪ ነበሩ።

የደረሰብኝ እጅግ አስከፊ መከራ

በታኅሣሥ 2004 ሮዝ ሜሪ በአንደኛው ሳንባዋ ላይ እጢ እንዳለና ወደ ካንሰር እንደተለወጠ በምርመራ ታወቀ። የሕክምና ባለሙያዎችም እጢው በፍጥነት እያደገ ስለሆነ ቶሎ መወገድ እንዳለበት ተስማሙ። ቀዶ ሕክምናውም በታኅሣሥ ወር መጨረሻ አካባቢ ተደረገላት። ከአንድ ሳምንት በኋላ ዶክተሩ ሮዝ ወደተኛችበት ክፍል መጥቶ “ሮዝ ሜሪ፣ አሁን ስለዳንሽ ወደ ቤትሽ መሄድ ትችያለሽ!” አላት።

ይሁን እንጂ ወደ ቤት ከተመለስን ከጥቂት ቀናት በኋላ ሮዝ ሜሪ ጨጓራዋ አካባቢና ሌሎች ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ሕመም ይሰማት ጀመር። ሕመሙ ስለጠናባት ለተጨማሪ ምርመራ ተመልሳ ወደ ሆስፒታል መሄድ ግድ ሆነባት። መንስኤው ምን እንደሆነ ባይታወቅም እንኳ በአንዳንድ የሰውነቷ ዋና ዋና ክፍሎች የደም ሥር ውስጥ ደም በመርጋቱ ምክንያት ኦክስጅን ማግኘት እንዳልቻሉ ታወቀ። ሐኪሞቹ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ቢያደርጉላትም ሊሳካላቸው አልቻለም። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጥር 30, 2005 በሕይወቴ ሙሉ ገጥሞኝ የማያውቅ መከራ መጋፈጥ ግድ ሆነብኝ። ውዷ ባለቤቴ ሮዝ ሜሪ አረፈች።

በዚያን ወቅት ዕድሜዬ ወደ 80 እየተጠጋ ነበር። በሕይወት ዘመኔ ሰዎች የተለያየ መከራ ሲደርስባቸው የተመለከትኩ ቢሆንም ይህ ግን ፈጽሞ የተለየ ሆነብኝ። እኔና ሮዝ ሜሪ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አንድ ሥጋ” ሆነን ነበር። (ዘፍጥረት 2:24) ሌሎች መከራ ሲደርስባቸው ከማየቴም ባሻገር ዘመዶቼም ሆኑ ጓደኞቼ ሲሞቱ ያለውን ሥቃይ ቀምሻለሁ። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛዬ ስትሞት የተሰማኝ ስሜት ከባድና ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ነበር። የሰው ልጆች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ የሚያስከትልባቸውን ከባድ ሐዘን ሙሉ በሙሉ መረዳት ችያለሁ።

የሆነ ሆኖ የመከራ ምንጩ ምን እንደሆነ መረዳቴና ይህ ችግር እንዴት እንደሚወገድ ማወቄ ከልክ በላይ በሐዘን እንዳልዋጥ ረድቶኛል። መዝሙር 34:18 “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” ይላል። ይህን ሐዘን መቋቋም የሚቻልበት ወሳኙ ዘዴ መጽሐፍ ቅዱስ ትንሣኤ መኖሩን እንደሚያስተምርና በመቃብር ያሉት ከሞት ተነስተው አምላክ ባዘጋጀው አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለዘላላም እንደሚኖሩ መረዳት ነው። የሐዋርያት ሥራ 24:15 “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” ይናገራል። ሮዝ ሜሪ ለአምላክ የጠለቀ ፍቅር ነበራት። እርሱም በጣም እንደሚወዳትና በቀጠረው ሰዓት አስታውሶ በትንሣኤ እንደሚያስነሳት እርግጠኛ ነኝ፤ ይህንንም በቅርቡ እንደሚያደርገው እተማመናለሁ።—ሉቃስ 20:38፤ ዮሐንስ 11:25

የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት የሚፈጥረው የሐዘን ስሜት እጅግ ከባድ ቢሆንም ሙታን ሲነሱ የሚሰማን ደስታ ግን ያንን ሁሉ ሥቃይ የሚያስረሳ ይሆናል። (ማርቆስ 5:42) የአምላክ ቃል “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ . . . ምድር ሙታንን ትወልዳለች” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 26:19) በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ከተጠቀሱት “ጻድቃን” መካከል ብዙዎቹ ከሌሎች ቀድመው የሚነሱ ይመስላል። ያ ጊዜ እንዴት አስደሳች ይሆናል! በዚያ ወቅት ከሚነሱት መካከል ሮዝ ሜሪ ትገኝበታለች። ያኔ የሚወዷት ሁሉ በደስታ ይቀበሏታል። መከራና ሥቃይ በማይኖርበት ዓለም ውስጥ መኖር እንዴት የሚያስደስት ይሆናል!

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቻይና ተመድቤ በሠራሁበት ወቅት ሰዎች የተለያየ መከራ ሲደርስባቸው ተመልክቻለሁ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከ1957 አንስቶ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ሳገለግል ቆይቻለሁ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1950 ሮዝ ሜሪን አገባሁ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2000 50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላችንን ባከበርንበት ወቅት