በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የልጆችን ልብ መንካት

የልጆችን ልብ መንካት

የልጆችን ልብ መንካት

አንድ ልጅ ጦርነት ላይ እንዳለ በማስመሰል ሲጫወት ተመልክተህ ያዘንክበት ወቅት አለ? የመዝናኛው ዓለም በዓመጽ ከመጥለቅለቁ የተነሳ እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች በጣም ትንንሽ በሆኑ ልጆች ዘንድ እንኳ የተለመዱ ሆነዋል። አንድ ልጅ የጦር መሣሪያ መጫወቻዎችን ጥሎ ሰላማዊ በሆኑ ሌሎች መጫወቻዎች እንዲጫወት ለማድረግ ምን ዘዴ መጠቀም ትችላለህ? በአፍሪካ ለብዙ ዓመታት በሚሲዮናዊነት ያገለገለች ቮልትራውት የተባለች የይሖዋ ምሥክር አንድ ልጅ እንዲህ እንዲያደርግ ለመርዳት አንድ ዘዴ ተጠቅማለች።

ቮልትራውት ከዚህ ቀደም ትኖርበት ከነበረው የአፍሪካ አገር ወጥታ አሁን ወደምትኖርበት አገር የተዛወረችው በጦርነት ምክንያት ነው። በዚያም የአምስት ዓመት ልጅ ካላት አንዲት እናት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ይህች እህት እናትየው ጋር በሄደች ቁጥር ልጁ በትንሽ የፕላስቲክ ጠመንጃ ሲጫወት ታየዋለች። ልጁ ከዚህ ሌላ መጫወቻ የለውም። ቮልትራውት ልጁ ለመተኮስ ሲያነጣጥር አይታው ባታውቅም ጥይት እንደሚያጎርስ ሰው ሁልጊዜ ጠመንጃውን ሲከፍትና ሲዘጋ ተመልክታዋለች።

ቮልትራውት ልጁን እንዲህ አለችው:- “ቨርነር፣ በእናንተ አገር የምኖረው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? በነበርኩበት አገር ጦርነት ስለነበር ነው። እዚህ የመጣሁት የአንተ ዓይነት ጠመንጃ ይዘው ሌሎችን ከሚገድሉ አደገኛ ሰዎች ሸሽቼ ነው። ታዲያ ሰዎችን በጠመንጃ መግደል ጥሩ ይመስልሃል?”

ቨርነር በሐዘን “እሱማ ጥሩ አይደለም” አላት።

ቮልትራውትም “በጣም ትክክል ነህ” አለችው። ከዚያም “አንተንና እናትህን በየሳምንቱ እየመጣሁ የምጠይቃችሁ ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?” ብላ ከጠየቀችው በኋላ “የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች ከአምላክም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ ለመርዳት ስለሚፈልጉ ነው” አለችው። ቮልትራውት እናትየውን ካስፈቀደች በኋላ ለቨርነር “ጠመንጃህን እንድጥለው ከሰጠኸኝ የጭነት መኪና የሚመስል መጫወቻ ላመጣልህ ቃል እገባለሁ” አለችው።

ቨርነርም የፕላስቲክ ጠመንጃውን ሰጣት። አዲሱ መጫወቻ እስኪመጣለት አንድ ወር ቢጠብቅም ከእንጨት የተሠራው የጭነት መኪና ሲሰጠው በጣም ተደሰተ።

ልጆችህ የጦር መሣሪያ መጫወቻዎችን እንዲያስወግዱ ልባቸውን ለመንካት በሚያስችልህ መንገድ ጊዜ ወስደህ ታነጋግራቸዋለህ? ከሆነ፣ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የሚጠቅማቸውን ትምህርት እያስተማርካቸው ነው።