የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለድሆች አሳቢነት እናሳይ
የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለድሆች አሳቢነት እናሳይ
ድህነትና ጭቆና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያልነበሩበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል። አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ድሆች ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሚከላከልና ችግራቸውን የሚያቃልል ቢሆንም ይህ ሕግ ብዙ ጊዜ በተግባር አይውልም ነበር። (አሞጽ 2:6) ነቢዩ ሕዝቅኤል፣ በወቅቱ ድሆች የሚያዙበትን መንገድ በማውገዝ እንዲህ ብሏል:- “በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ ይቀማል፤ ይዘርፋል፤ ፍትሕ በማጕደልም ድኻውንና ችግረኛውን ይጨቊናል፤ መጻተኛውንም ይበድላል።”—ሕዝቅኤል 22:29
ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ ለድሀውም ሆነ ለችግረኛው ምንም አሳቢነት አያሳዩም ነበር። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች “የመበለቶችን ቤት የሚያራቍቱ” እንዲሁም አረጋውያንን ከመንከባከብና ችግረኞችን ከመርዳት ይልቅ ወጋቸውን ለመጠበቅ ይበልጥ የሚጨነቁ ስለነበሩ “ገንዘብ የሚወዱ” ተብለዋል። (ሉቃስ 16:14፤ 20:47፤ ማቴዎስ 15:5, 6) ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይ አንድ ካህንና አንድ ሌዋዊ ተደብድቦ የቆሰለ ሰው ሲመለከቱ ቀረብ ብለው ከመርዳት ይልቅ ፈንጠር ብለው መሄዳቸው የሚያስገርም ነው።—ሉቃስ 10:30-37
ኢየሱስ ለድሆች ያስብ ነበር
የኢየሱስን ሕይወት የሚተርኩት የወንጌል ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ የድሆችን ችግር በሚገባ ይረዳና የሚያስፈልጋቸውንም ነገር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ በሰማይ ይኖር የነበረ ቢሆንም መንፈሳዊ ክብሩን በመተውና ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር በመምጣት ‘ለእኛ ሲል ድኻ ሆነ።’ (2 ቆሮንቶስ 8:9) ኢየሱስ ሕዝቡ “እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) ስለ ችግረኛዋ መበለት የሚናገረው ዘገባ እንደሚያሳየው ኢየሱስ የተደነቀው ሀብታሞቹ “ከትርፋቸው” ላይ ባዋጡት ብዙ ገንዘብ ሳይሆን ድሀዋ መበለት በሰጠችው አነስተኛ መዋጮ ነበር። የኢየሱስን ልብ የነካው ሴትየዋ “የሰጠችው በድኻ ዐቅሟ ያላትን መተዳደሪያ በሙሉ” መሆኑ ነበር።—ሉቃስ 21:4
ኢየሱስ ለድሆች ከማዘንም በላይ ለሚያስፈልጋቸው ነገር ትኩረት ይሰጥ ነበር። እርሱና ሐዋርያቱ ለችግረኛ እስራኤላውያን የሚሰጥ ገንዘብ ያጠራቅሙ ነበር። (ማቴዎስ 26:6-9፤ ዮሐንስ 12:5-8፤ 13:29) ኢየሱስ የእርሱ ተከታዮች መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ችግረኞችን የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው ለማስገንዘብ ጥረት አድርጓል። ሀብታም ለነበረው ወጣት አለቃ “ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ መዝገብ ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” ብሎታል። ይህ ሰው ንብረቱን ለመተው አለመፈለጉ ለሀብቱ ያለው ፍቅር ለአምላክና ለሰዎች ካለው ፍቅር እንደሚበልጥ ያሳያል። በመሆኑም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ሳያሟላ ቀርቷል።—ሉቃስ 18:22, 23
የክርስቶስ ተከታዮች ለድሆች ያስባሉ
ኢየሱስ ከሞተ በኋላም ሐዋርያትና ሌሎች የክርስቶስ ተከታዮች በመካከላቸው ላሉ ድሆች አሳቢነት ከማሳየት አልተቆጠቡም። በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ምሥራቹን የመስበክ ተልእኮ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተቀበለ ለያዕቆብ፣ ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ነገራቸው። እነርሱም ጳውሎስና በርናባስ ወደ “አሕዛብ” ሄደው ላልተገረዙት እንዲሰብኩ ተስማሙ። ሆኖም ያዕቆብና ባልደረቦቹ፣ ጳውሎስም ሆነ በርናባስ ‘ድኾችን ማሰባቸውን እንዳያቋርጡ’ አደራ አሏቸው። ጳውሎስም ይህን ‘ለማድረግ ጓጉቶ’ ነበር።—ገላትያ 2:7-10
በንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ ዘመን በተለያዩ የሮማ ግዛቶች ታላቅ ረሀብ ተከስቶ ነበር። በአንጾኪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ለተነሳው ችግር ምላሽ በመስጠት “እያንዳንዳቸው ዐቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በይሁዳ የሚኖሩትን ወንድሞች ለመርዳት ወሰኑ፤ ርዳታውንም በበርናባስና በሳውል እጅ ለሽማግሌዎቹ በመላክ፣ ይህንኑ አደረጉ።”—የሐዋርያት ሥራ 11:28-30
በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም፣ የኢየሱስ ተከታዮች ለድሆችና ለችግረኞች በተለይም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የእምነት ባልደረቦቻቸው አሳቢ መሆን እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። (ገላትያ 6:10) ስለዚህ መሠረታዊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን ለተቸገሩት በመለገስ ልባዊ አሳቢነት ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በ1998 በብራዚል በስተ ሰሜን ምሥራቅ የሚገኘው አብዛኛው ክፍል በከባድ ድርቅ ተመታ። ይህ ድርቅ የሩዝ፣ የባቄላና የበቆሎ ሰብሎችን ያወደመ ሲሆን ከዚያ በፊት በነበሩት 15 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ረሀብ አስከተለ። በአንዳንድ ቦታዎች በቂ የመጠጥ ውሃ እንኳን አልነበረም። በሌሎቹ የብራዚል ክፍላተ አገራት የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በአፋጣኝ የእርዳታ ኮሚቴ በማዋቀር በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ ቶን የሚቆጠር ምግብ ያሰባሰቡ ሲሆን እርዳታውን ለማጓጓዝ የሚያስፈልገውንም ወጪ ሸፍነዋል።
የእርዳታ እጃቸውን የዘረጉት የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ወንድሞቻችንን መርዳት በመቻላችን ሐሴት አድርገናል፤ ለደስታችን ዋነኛው ምክንያት የይሖዋን ልብ እንዳስደሰትን እርግጠኞች መሆናችን ነው። በያዕቆብ 2:15, 16 ላይ የሚገኙትን ቃላት ፈጽሞ አንዘነጋቸውም።” ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንዲህ ይላል:- “አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣ ከእናንተ መካከል አንዱ፣ ‘በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ’ ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል?”
በሳኦ ፓውሎ ከተማ በሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ዝቅተኛ ኑሮ ያላትና ራሷን ችላ መሠረታዊ ፍላጎቶቿን ለማሟላት ደፋ ቀና የምትል አንዲት ቀናተኛ እህት ትገኛለች። ይህቺ እህት እንዲህ ብላለች:- “በድህነት የምኖር ብሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ትርጉም ያለው ሕይወት እንድመራ ረድቶኛል። የእምነት ባልደረቦቼ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ባይረዱኝ ኖሮ ምን እንደሚውጠኝ አላውቅም።” ይህች ትጉ ክርስቲያን ከተወሰነ ጊዜ በፊት የቀዶ ሕክምና ማድረግ ቢያስፈልጋትም የሕክምናውን ወጪ የመሸፈን አቅም አልነበራትም። በዚህ ወቅት በጉባኤዋ የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ለሕክምናዋ የሚያስፈልገውን ወጪ ሸፈኑላት። በዓለም ዙሪያ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለተቸገሩ የእምነት ባልደረቦቻቸው እርዳታ ያበረክታሉ።
ከላይ የተጠቀሱት ተሞክሮዎች የሚያስደስቱ ቢሆኑም እንደነዚህ ያሉት ልባዊ ጥረቶች ድህነትን ማስወገድ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ሌላው ቀርቶ ኃያላን መንግሥታትና ትልልቅ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችም እንኳ በተወሰነ መጠን ቢሳካላቸውም፣ ከሰው ልጅ ታሪክ ተነጥሎ የማያውቀውን ድህነትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አልቻሉም። ስለዚህ፣ ድህነትንም ሆነ የሰውን ዘር የሚያስጨንቁትን ሌሎች ችግሮች ለማስወገድ አስተማማኝ የሆነው መፍትሔ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ይነሳል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ዘላቂ እርዳታ ያበረክታሉ
የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ለድሆች ወይም ሌላ ችግር ለነበረባቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜ መልካም ያደርግ እንደነበር ይናገራሉ። (ማቴዎስ 14:14-21) ይሁንና ኢየሱስ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሰጠው ለየትኛው ተግባር ነው? በአንድ ወቅት ችግረኞችን እየረዳ የተወሰነ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ” አላቸው። ኢየሱስ የስብከት ሥራውን ለመቀጠል ሲል ሕሙማንንና ችግረኞችን መርዳቱን ያቋረጠው ለምንድን ነበር? እርሱ ራሱ “የመጣሁት ለዚሁ [ማለትም ለመስበክ] ነውና” በማለት ምክንያቱን ተናግሯል። (ማርቆስ 1:38, 39፤ ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ የተቸገሩትን መርዳቱ አስፈላጊ እንደሆነ ቢሰማውም በዋነኝነት የተላከው ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሰብክ ነበር።—ማርቆስ 1:14
መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘[የኢየሱስን] ፈለግ እንዲከተሉ’ ስለሚያሳስብ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ሌሎችን በመርዳት ረገድ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዘው ምን መሆን እንዳለበት የሚጠቁም ግልጽ መመሪያ አላቸው። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ እንዳደረገው በችግር ላይ ያሉ ሰዎችን ይረዳሉ። ይሁንና ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሰዎች ለማስተማሩ ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ረገድም የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ። (ማቴዎስ 5:14-16፤ 24:14፤ 28:19, 20) እርዳታ ለመስጠት ከሚደረጉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ይልቅ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መልእክት የመስበኩ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?
ከዓለም ዙሪያ የተገኙ እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች እንደሚያሳዩት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተረድተው በሥራ ላይ ካዋሉ ድህነትን ጨምሮ በየዕለቱ የሚያጋጥሟቸውን 1 ጢሞቴዎስ 4:8) እንዲህ የተባለለት ተስፋ ምን ይሆን?
ችግሮች በተሻለ መንገድ ለመፍታት ይችላሉ። ከዚህም በላይ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ሰዎች ለወደፊቱ ተስፋ እንዲኖራቸው ይረዳል። ይህ ተስፋ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳ ሕይወት ጣዕም እንዲኖረው ያደርጋል። (የአምላክ ቃል የወደፊት ሕይወታችንን በተመለከተ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ [በአምላክ የተስፋ ቃል] መሠረት እንጠባበቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ለማመልከት “ምድር” እያለ ይናገራል። (ዘፍጥረት 11:1 የ1954 ትርጉም) ስለዚህ እንደሚመጣ የተነገረለት ጽድቅ የሚኖርበት “አዲስ ምድር” የአምላክን ሞገስ የሚያገኘውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክን ሞገስ የሚያገኙት እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ ግዛት ሥር ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚያገኙና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ አርኪ ሕይወት እንደሚመሩ ቃል ገብቷል። (ማርቆስ 10:30) ይህ አስደናቂ ተስፋ የተዘረጋው ድሆችን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች ነው። በዚያች “አዲስ ምድር” ውስጥ ድህነት የሚባል ነገር ለዘላለም ይወገዳል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ኢየሱስ ‘ችግረኛውን የሚታደገው’ እንዴት ነው?—መዝሙር 72:12
ፍትሕ:- “ለተቸገረው ሕዝብ ይሟገታል፤ የድኾችን ልጆች ያድናል፤ ጨቋኙንም ያደቀዋል።” (መዝሙር 72:4) ክርስቶስ በምድር ላይ ሲገዛ ፍትሕ ይሰፍናል። ሀብታም ለመሆን የሚያስችል አቅም ያላቸው ብዙ አገሮችን ለድህነት የሚዳርገው ሙስና ስፍራ አይኖረውም።
ሰላም:- “በዘመኑ ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል።” (መዝሙር 72:7) በዓለማችን ያለው ድህነት በአመዛኙ የሚከሰተው በሰው ልጆች ግጭትና በጦርነት ምክንያት ነው። ክርስቶስ ከድህነት ዋነኛ መንስኤዎች መካከል ግጭትና ጦርነትን በማጥፋት በምድር ላይ ፍጹም ሰላም ያሰፍናል።
ርኅራኄ:- “ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል፤ ደማቸውም በእርሱ ፊት ክቡር ነው።” (መዝሙር 72:12-14) ችግረኞች፣ ድሆችና የተጨቆኑ ሰዎች በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት አንድነት በሚያገኘው የሰው ልጆች ደስተኛ ቤተሰብ ውስጥ ይታቀፋሉ።
ብልጽግና:- “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ።” (መዝሙር 72:16) በክርስቶስ የግዛት ዘመን ቁሳዊ ብልጽግና ይኖራል። ሰዎች፣ በዛሬው ጊዜ ለድህነት ዋነኛ ምክንያት በሆኑት በምግብ እጥረት እና በረሀብ አይሠቃዩም።
[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለድሆች ልባዊ አሳቢነት ያሳይ ነበር
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እውነተኛ ተስፋ ያስገኛል