ይሖዋ ከእናንተ ጋር ስለሆነ አትፍሩ!
ይሖዋ ከእናንተ ጋር ስለሆነ አትፍሩ!
ከዛሬ 50 ዓመት በፊት፣ የመጀመሪያው የአቶም ቦምብ ከፈነዳ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአቶሚክ ሳይንቲስት የሆኑት የኖቤል ተሸላሚው ሃሮልድ ሲ ዩሬይ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲናገሩ “ፍርሃትን እንበላለን፣ በፍርሃት እንተኛለን፣ በፍርሃት እንኖራለን፣ በፍርሃትም እንሞታለን” ብለው ነበር። ዛሬ ዓለማችን በፍርሃት የተዋጠችበትን ምክንያት መረዳት አዳጋች አይደለም! ጋዜጦች በየዕለቱ ስለ ሽብርተኝነት፣ ስለ አሰቃቂ ወንጀሎችና መፍትሔ ስላልተገኘላቸው በሽታዎች አስፈሪ ዘገባዎችን ይዘው ይወጣሉ።
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይህ ምን ማለት እንደሆነ ይገባናል። ከላይ የተጠቀሱት ክስተቶች መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ብሎ በሚጠራው በዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’ ውስጥ እንደምንኖር ይጠቁሙናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይህም ይሖዋ በቅርቡ ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደሚያመጣ ያለን እምነት እንዲጠናከር ያደርጋል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ታዲያ ይህ ተስፋ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ እኛ ክርስቲያኖች ከፍርሃት ነጻ መሆን እንችላለን?
የአምላክ አገልጋዮችስ ይፈራሉ?
አደገኛ ሁኔታ ባጋጠማቸው ወቅት ፍርሃት ተሰምቷቸው ከነበሩ የአምላክ አገልጋዮች መካከል ያዕቆብ፣ ዳዊትና ኤልያስ ይገኙበታል። (ዘፍጥረት 32:6, 7፤ 1 ሳሙኤል 21:11, 12፤ 1 ነገሥት 19:2, 3) እነዚህ ሰዎች እምነት አጥተው አልነበረም። እንዲያውም በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። የሆነ ሆኖ ያዕቆብ፣ ዳዊትና ኤልያስ ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ፍርሃት የተሰማቸው ጊዜ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ” ሲል ጽፏል።—ያዕቆብ 5:17
እኛም ብንሆን አንድ ዓይነት ችግር ሲገጥመን ወይም ወደፊት ሊደርስብን ስለሚችል አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ ስናስብ ልንፈራ እንችላለን። እንዲህ ያለው ፍርሃት ቢሰማን የሚያስደንቅ አይሆንም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስ ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትንና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙትን ለመዋጋት’ ቆርጦ እንደተነሳ ይነግረናል። (ራእይ 12:17) እነዚህ ቃላት በተለይ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የሚመለከቱ ቢሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) እንዲያም ሆኖ ችግሮች በሚያጋጥሙን ወቅት ፍርሃት ሊያሽመደምደን አይገባም። ለምን?
“የሚያድን አምላክ”
መዝሙራዊው ዳዊት “አምላካችን የሚያድን አምላክ ነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 68:20) ይሖዋ ሕዝቦቹን ካጋጠማቸው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ በማውጣት አሊያም የሚጸኑበትን ኃይል በመስጠት የማዳን አቅም እንዳለው በተደጋጋሚ አሳይቷል። (መዝሙር 34:17፤ ዳንኤል 6:22፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካገኘሃቸው ይሖዋ ሕዝቦቹን ‘ለማዳን’ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ምን ያህሎቹን ማስታወስ ትችላለህ?
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫን a (እንግሊዝኛ) በመጠቀም በኖኅ ዘመን ስለደረሰው የጥፋት ውኃ፣ ሎጥና ሴቶች ልጆቹ ከሰዶምና ከገሞራ ጥፋት ስለዳኑበት መንገድ፣ እስራኤላውያን ከግብጽ ነፃ ስለመውጣታቸውና ቀይ ባሕርን ስለመሻገራቸው ወይም ሐማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት የሸረበው ሴራ ስለመክሸፉ በሚናገሩት እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች ላይ ለምን ምርምር አታደርግም። እነዚህን አስደናቂ ዘገባዎች ማንበብህ ብሎም በእነርሱ ላይ ማሰላሰልህ ይሖዋ አዳኝ አምላክ ስለመሆኑ ያለህን እምነት ያጠናክርልሃል። ይህ ደግሞ የሚያጋጥሙህን የእምነት ፈተናዎች በድፍረት እንድትወጣቸው ይረዳሃል።
ዘመናዊ ምሳሌዎች
በዛሬው ጊዜ አንተ በምትኖርበት አካባቢ ስላሉት የጽናት
ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ክርስቲያኖች አስበህ ታውቃለህ? ምናልባት ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ለመገኘት ሲል ወኅኒ የወረደ አንድ ሰው ታውቅ ይሆናል። ወይም አንድ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያን የጤና ችግር እያለባቸውም ይሖዋን እንደሚያገለግሉ አይተህ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውን ኃይለኛ ተጽዕኖ ተቋቁመው ከዓለም የተለዩ ሆነው ለመኖር ስለሚጥሩ ወጣቶች አስብ። ከዚህም ሌላ ልጆቻቸውን ለብቻቸው እያሳደጉ ያሉ ነጠላ የሆኑ ወላጆችን ወይም ከብቸኝነት ስሜት ጋር እየታገሉ ይሖዋን የሚያገለግሉ ያላገቡ ወንድሞችንና እህቶችን ማሰብ ትችላለህ። ከእነዚህ ምን ትማራለህ? እነርሱ በተከተሉት የታማኝነት አካሄድ ላይ ማሰላሰል እንድትጸና የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ ከፊትህ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥምህ ያለ ፍርሃት እንድትቋቋመው ያስችልሃል።ድፍረት የሚያስፈልገን ተቃውሞና ስደት ሲያጋጥመን ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ፍቅር መጠራጠር ስንጀምር ጭምር ነው። የክርስቶስ ቤዛ በግለሰብ ደረጃ እንደሚጠቅመን እምነት ልናዳብር ይገባናል። (ገላትያ 2:20) እንዲህ ካደረግን ተገቢ ያልሆነ ፍርሃትን አስወግደን ወደ ይሖዋ መቅረብ እንችላለን። የይሖዋን ፍቅር ማግኘት የማይገባን ሰዎች እንደሆንን ከተሰማን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም። የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው። ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው” ሲል በተናገራቸው ቃላት ላይ ማሰላሰላችን እንድንበረታ ይረዳናል።—ማቴዎስ 10:29-31
መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በድፍረት ስለተቋቋሙ የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪክ በተደጋጋሚ አስነብበውናል። እነዚህ ክርስቲያኖች ያጋጠማቸውን ችግር በድፍረት ተወጥተዋል ስንል ምንም ዓይነት አሉታዊ ስሜት አልነበራቸውም ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲያስቆማቸው አልፈቀዱም። በጽሑፎች ላይ የወጡት የእነዚህ ወንድሞች ተሞክሮዎች አንተም ችግር ቢገጥምህ በድፍረት እንድትቋቋመው ይረዳሃል። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።
የደረሰበት አደጋ ሕይወቱን ለወጠው
የግንቦት 2003 ንቁ! መጽሔት “የደረሰብኝ የአካል ጉዳት ሕይወቴን ለወጠው” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ታሪኩ በኬንያ የሚኖር ስታንሊ ኦምቤቫ የተባለ የይሖዋ ምሥክር በፍጥነት በሚሄድ መኪና በመገጨቱ ሳቢያ ያጋጠመውን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዴት እንደተወጣ የሚናገር ነው። ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ሲሄድ ሥራውንም ሆነ ሥራው የሚያስገኝለትን ጥቅማ ጥቅሞች በሙሉ አጣ። ወንድም ኦምቤቫ ስለ ሁኔታው ሲናገር “ያለብኝ ችግር ከባድ መሆኑን ይበልጥ እየተገነዘብኩ ስመጣ በጣም የምበሳጭ፣ ስለ ራሴ ብቻ የማስብና አሉታዊ አመለካከት ያለኝ እንዲሁም በትንሽ በትልቁ የምቆጣና የምናደድ ሆንኩ” ብሏል። ይህ ክርስቲያን መከራ ቢደርስበትም እንኳ በፍርሃት አልተሽመደመደም። እንዲሁም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሙሉ ለሙሉ እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ታምኖ ነበር። “የራሴ ደካማነት እስኪያሳፍረኝ ድረስ [ይሖዋ] ሁልጊዜ ይረዳኝና ይደግፈኝ ነበር” በማለት ወንድም ኦምቤቫ ይናገራል። አክሎም “እንደኔ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚኖርን ሰው እንደሚያጽናኑ የማውቃቸውን ጥቅሶች በሙሉ ለማንበብና ለማሰላሰል ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ” ብሏል።
ወንድም ኦምቤቫ በግልጽነት የተናገራቸው ሐሳቦች ሌሎች ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ያለፍርሃት እንዲወጡ ረድቷቸዋል። አንዲት እህት “ይህን ተሞክሮ ሳነብ አለቀስኩ። ይሖዋ በዚህ ተሞክሮ አማካኝነት ፍቅሩን እየገለጸልኝ፣ እንክብካቤ እያደረገልኝ ብሎም እያጽናናኝ እንደሆነ ተሰማኝ” በማለት ተናግራለች። ሌላ የይሖዋ ምሥክር ደግሞ “እንደነዚህ ያሉ ተሞክሮዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የምንገኘውንና ሥቃያችንን አምቀን የምንኖረውን ሰዎች በእጅጉ የሚያጽናኑ ናቸው” በማለት ጽፏል።
ጭንቀትን መቋቋም
“ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁም” በሚል ርዕስ ወጥቶ የነበረው የኸርበርት ጄኒንዝ የሕይወት ታሪክም የብዙዎችን ስሜት ነክቷል። b ወንድም ጄኒንዝ ባይፖላር ሙድ ዲስኦርደር የተባለውን በሽታ መቋቋም አስፈልጎት ነበር። በሽታው እንደ ጀመረው አካባቢ የነበረውን ሁኔታ አስታውሶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንኳ በጣም ይከብደኝ ነበር። የሆነ ሆኖ በመንፈሳዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ሙሉ በሙሉ አምን ነበር። ችግሩን ለማሸነፍ ስል ብዙውን ጊዜ ሰው ሁሉ ቦታ ቦታውን ከያዘ በኋላ ወደ መንግሥት አዳራሽ እገባለሁ፤ እንዲሁም ልክ ፕሮግራሙ እንዳለቀ እወጣለሁ።”
በአገልግሎት መሳተፍም ቢሆን ለእርሱ ከባድ ነበር። ወንድም ጄኒንዝ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አንዳንድ ጊዜ በር ላይ ከደረስኩ በኋላ ደወሉን ለመጫን ድፍረት አጣለሁ። ይሁን እንጂ አገልግሎታችን ለእኛም ሆነ በጎ ምላሽ ለሚሰጡ ሰዎች መዳንን እንደሚያስገኝ ስለማውቅ ማገልገሌን አላቋረጥኩም። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ከጊዜ በኋላ ስሜቴን እንደምንም እየተቆጣጠርኩ ወደሚቀጥለው ቤት ሄጄ አንኳኳለሁ። በአገልግሎት የማደርገውን ተሳትፎ በመቀጠል መንፈሳዊ ጤንነቴን ለመጠበቅና ችግሮችን ለማሸነፍ የሚያስችል አቅም ማግኘት ችያለሁ።”
ወንድም ጄኒንዝ በግልጽ ያስቀመጣቸው እነዚህ ሐሳቦች ብዙ አንባቢያን ያለባቸውን ጭንቀት በድፍረት እንዲቋቋሙት ረድቷቸዋል። ለምሳሌ አንዲት ክርስቲያን እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ለ28 ዓመታት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ያነበብኩ ቢሆንም እንደዚህ ተሞክሮ ስሜቴን በጥልቅ የነካው የለም። ባጋጠመኝ ችግር ሳቢያ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን ማቋረጥ ግድ ሆኖብኛል፤ ሆኖም ‘ጠንካራ እምነት ቢኖረኝ ኖሮ መቀጠል እችል ነበር’ የሚለው ሐሳብ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል። ወንድም ጄኒንዝ ሕክምና ለመከታተል ሲል የተሰጠውን የአገልግሎት ምድብ ትቶ መምጣቱ እኔም ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ይህ በእርግጥም የጸሎቴ መልስ ነው!”
አንድ ወንድም ደግሞ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ለአሥር ዓመት በጉባኤ ሽማግሌነት ካገለገልኩ በኋላ በአእምሮ ሕመም ምክንያት ይህን ልዩ መብት ለማቆም ተገደድኩ። በብዙ መንገዶች እንደተሳካላቸው የሚናገሩ የይሖዋ ሕዝቦችን የሕይወት ታሪኮች በማነብበት ወቅት እኔ ከደረሰብኝ ችግር ጋር በማነጻጸር ስለማዝን እነዚህን ተሞክሮዎች ማንበብ አያስደስተኝም ነበር። ይሁን እንጂ ወንድም ጄኒንዝ ያሳየው ጽናት አበረታቶኛል። ይህን ርዕስ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ።”
በድፍረት ወደፊት መግፋት
እንደ ወንድም ኦምቤቫና እንደ ወንድም ጄኒንዝ ሁሉ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ይሖዋ አምላክን በድፍረት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። አንተም ከእነዚህ ወንድሞች መካከል ከሆንክ ልትመሰገን ይገባሃል። ‘እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር እንደማይረሳ’ እርግጠኛ ሁኑ።—ዕብራውያን 6:10
ይሖዋ የጥንት ሕዝቦቹ ጠላቶቻቸውን ድል እንዲያደርጉ እንደረዳቸው ሁሉ ዛሬም ያሉብህን ችግሮች በድል እንድትወጣ ይረዳሃል። በመሆኑም ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል:- “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።”—ኢሳይያስ 41:10
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
b የታኅሣሥ 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 24-28ን ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ስታንሊ ኦምቤቫ (ከላይ) እና ኸርበርት ጄኒንዝ (በስተ ቀኝ) ሁሉ ብዙዎች ይሖዋን በድፍረት በማገልገል ላይ ይገኛሉ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
USAF photo