ይሖዋ የመንጋውን እረኞች ያሠለጥናል
ይሖዋ የመንጋውን እረኞች ያሠለጥናል
“እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል።”—ምሳሌ 2:6
1, 2. የተጠመቁ ወንዶች በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ለማግኘት የሚጣጣሩት ለምንድን ነው?
ከሰባት ዓመት በላይ የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለው ኒክ “ሽማግሌ ሆኜ ስሾም በጣም ተደስቼ ነበር” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ያገኘሁትን መብት ለይሖዋ የማቀርበውን አገልግሎት ለማስፋት እንደሚረዳኝ አጋጣሚ አድርጌ እቆጥረውና እርሱ ላደረገልኝ ነገሮች ሁሉ ውለታውን የመክፈል ግዴታ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። እንዲሁም በተቻለኝ አቅም ሁሉ የጉባኤውን አባላት መርዳትና ሽማግሌዎች ለእኔ እንዳደረጉት ሌሎችን መደገፍ እፈልግ ነበር።” ይሁንና ኒክ ደስ ቢለውም አንዳንድ የሚያስጨንቁት ነገሮች ነበሩ። “በዚያን ጊዜ በ20ዎቹ ዕድሜዬ መገባደጃ ላይ ስለነበርኩ ጉባኤውን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንከባከብ የሚረዳኝ በቂ ችሎታ ማለትም ማስተዋልና ጥበብ አይኖረኝ ይሆናል የሚል ጭንቀት ነበረብኝ” በማለት ተናግሯል።
2 ይሖዋ መንጋውን እንዲንከባከቡ የሾማቸው ሰዎች ደስ የሚሰኙባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በማለት ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ጠቅሶ የኤፌሶን ሽማግሌዎች ሊደሰቱ ከሚችሉባቸው ምክንያቶች አንዱን ጠቁሟቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) የተጠመቁ ወንዶች የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው ማገልገላቸው ለይሖዋና ለጉባኤው መስጠት የሚችሉበትን ተጨማሪ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የጉባኤ አገልጋዮች ከሽማግሌዎች ጋር ይሠራሉ። እንዲሁም በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሆኖም ጊዜ የሚወስዱ ሌሎች በርካታ ሥራዎችን ያከናውናሉ። እንዲህ ያሉት ወንድሞች ለአምላክና ለባልንጀሮቻቸው ላቅ ያለ ዋጋ ያለው አገልግሎት የሚያቀርቡት በፍቅር ተነሳስተው ነው።—ማርቆስ 12:30, 31
3. አንዳንዶች በጉባኤ ውስጥ መብት ማግኘት የማይፈልጉት ለምንድን ነው?
3 ብቃት እንደሌላቸው የሚሰማቸው በመሆኑ ምክንያት የጉባኤ አገልጋይ ብሎም ሽማግሌ መሆን ስለማይፈልጉ ክርስቲያን ወንዶችስ ምን ማለት ይቻላል? ልክ እንደ ኒክ እነዚህ ወንድሞች ውጤታማ እረኛ ለመሆን የሚያስፈልገው ችሎታ እንደሌላቸው ይሰማቸው ይሆናል። አንተስ የተጠመቅህ ወንድም ብትሆንም እንኳን እንዲህ ይሰማሃል? ይህንን የመሰለ ስጋት ቢያድርብህ ምንም አያስደንቅም። ምክንያቱም ይሖዋ፣ የሾማቸውን እረኞች መንጋውን ስለያዙበት መንገድ በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል። ኢየሱስ “ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራም ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 12:48
4. ይሖዋ በጎቹን እንዲንከባከቡ የሾማቸውን ሰዎች የሚደግፋቸው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ የጉባኤ አገልጋይና ሽማግሌ አድርጎ የሾማቸው ወንዶች ያለባቸውን ኃላፊነት ብቻቸውን እንዲሸከሙ ይተዋቸዋል? በጭራሽ፤ ከዚህ ይልቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ተግባራዊ እርዳታም ይሰጣቸዋል። ባለፈው ርዕስ ውስጥ እንደተብራራው ይሖዋ፣ በጎቹን በርኅራኄ እንዲንከባከቡ የሚያስችል ፍሬ እንዲያፈሩ የሚረዳቸውን ቅዱስ መንፈሱን ይለግሳቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28፤ ገላትያ 5:22, 23) በተጨማሪም ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋል ይሰጣቸዋል። (ምሳሌ 2:6) ይህንን የሚያደርገው እንዴት ነው? ይሖዋ በጎቹን እንዲንከባከቡ የሾማቸውን ግለሰቦች የሚያሠለጥንባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።
ተሞክሮ ባካበቱ እረኞች ይሠለጥናሉ
5. ጴጥሮስና ዮሐንስ ውጤታማ እረኞች ሊሆኑ የቻሉት ለምንድን ነው?
5 ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረቡ ጊዜ፣ ዓለማዊ ጥበብ ያካበቱት ዳኞች ከፊታቸው የቆሙትን ሐዋርያት “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” እንደሆኑ አድርገው ቆጥረዋቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች ማንበብና መጻፍ ቢችሉም ረቢዎች ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡትን ትምህርት አልተማሩም። ቢሆንም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት፣ ያዳምጧቸው የነበሩ ሰዎች አማኞች እንዲሆኑ በመርዳታቸው ውጤታማ አስተማሪዎች መሆናቸው ተረጋግጧል። እነዚህ ተራ ሰዎች እጅግ የተዋጣላቸው አስተማሪዎች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ሸንጎው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ካዳመጠ በኋላ ‘ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩ ተገንዝቧል።’ (የሐዋርያት ሥራ 4:1-4, 13) መንፈስ ቅዱስን መቀበላቸው እውነት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) ከዚህ በተጨማሪ ግን ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች እንዳሠለጠናቸው በመንፈሳዊ ለታወሩት ዳኞች ሳይቀር ግልጽ ሆኖ ነበር። ኢየሱስ ምድር ላይ አብሯቸው በነበረበት ጊዜ ሐዋርያቱ በግ መሰል ሰዎችን እንዴት መሰብሰብ እንደሚችሉ ብቻ ሳይሆን ሰዎቹ የመንጋው አባላት ከሆኑ በኋላም እንዴት መንከባከብ እንደሚቻል ጭምር አስተምሯቸዋል።—ማቴዎስ 11:29፤ 20:24-28፤ 1 ጴጥሮስ 5:4
6. ሌሎችን በማሠልጠን ረገድ ኢየሱስና ጳውሎስ ምን ምሳሌ ትተዋል?
6 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳም በኋላ በእረኝነት የሾማቸውን ወንዶች ማሠልጠኑን ቀጥሎ ነበር። (ራእይ 1:1፤ 2:1 እስከ 3:22) ለአብነት ያህል፣ ጳውሎስን የመረጠው ራሱ ሲሆን የተሰጠውንም ሥልጠና ይቆጣጠር ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 22:6-10) ጳውሎስ ያገኘውን ሥልጠና በቁም ነገር ይመለከተው የነበረ ከመሆኑም ባሻገር የተማረውን ለሌሎች ሽማግሌዎች አካፍሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:17-35) ለምሳሌ፣ ጢሞቴዎስ በአምላክ አገልግሎት ‘እንደማያፍር ሠራተኛ’ እንዲሆን ለማሠልጠን ሲል ብዙ ጊዜና ጉልበት አጥፍቷል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) በኋላም ጳውሎስና ጢሞቴዎስ የቅርብ ጓደኛሞች ሆነዋል። ቀደም ሲል ጳውሎስ ስለ ጢሞቴዎስ ሲጽፍ “ልጅ ከአባቱ ጋር እንደሚያገለግል፣ ከእኔ ጋር በወንጌል ሥራ አገልግሎአልና” ብሎ ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:22) ጳውሎስ ጢሞቴዎስንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን የእርሱ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ፍላጎት አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ የእምነት ባልንጀሮቹን ‘እርሱ የክርስቶስን ምሳሌ እንደሚከተል እነርሱም የእርሱን እንዲከተሉ’ አበረታቷቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 11:1
7, 8. (ሀ) ሽማግሌዎች የኢየሱስንና የጳውሎስን ምሳሌ ቢከተሉ መልካም ውጤት እንደሚገኝ የሚያሳየው የትኛው ተሞክሮ ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ወደፊት የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች የመሆን ተስፋ ያላቸውን ወንድሞች ማሠልጠን መጀመር ያለባቸው መቼ ነው?
7 ተሞክሮ ያካበቱ እረኞች የኢየሱስንና የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል የተጠመቁ ወንድሞችን ለማሠልጠን ቀዳሚ ይሆናሉ፤ ይህም ቢሆን ጥሩ ውጤት ያስገኛል። እስቲ የቻድን ተሞክሮ እንመልከት። ቻድ የተለያዩ ሃይማኖቶች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ቢያድግም በቅርቡ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ተሹሟል። እንዲህ ብሏል:- “ባለፉት ዓመታት፣ ተሞክሮ ያላቸው በርካታ ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ረድተውኛል። አባቴ የማያምን በመሆኑ እነዚህ ወንድሞች ልዩ አሳቢነት ያሳዩኝ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ልክ እንደ መንፈሳዊ አባት ሆነውልኛል። ጊዜ መድበው ለአገልግሎት ያሠለጥኑኝ ነበር፤ በኋላም በተለይ አንድ ሽማግሌ የተቀበልኩትን የጉባኤ ኃላፊነት እንዴት መወጣት እንደምችል አሠልጥኖኛል።”
8 የቻድ ተሞክሮ እንደሚያሳየው አስተዋይ እረኞች ወደፊት የጉባኤ አገልጋይና ሽማግሌ የሚሆኑ ወንዶችን ማሠልጠን የሚጀምሩት፣ እነዚህ ወንዶች መብቶቹን ለማግኘት የሚያስፈልጋቸውን ብቃት ከማሟላታቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። እንዲህ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የጉባኤ አገልጋዮችም ሆኑ ሽማግሌዎች እንዲያገለግሉ ከመሾማቸው በፊት ከፍተኛ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ የአቋም ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለባቸው ያዝዛል። እነዚህ ወንድሞች ‘አስቀድመው ሊፈተኑ’ ይገባል።—1 ጢሞቴዎስ 3:1-10
9. የጎለመሱ እረኞች ምን ኃላፊነት አለባቸው? ለምንስ?
9 የተጠመቁ ወንድሞች መፈተን ካለባቸው እነርሱን አስቀድሞ ማሠልጠን ይገባል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ተማሪ ቀደም ሲል አስተማሪዎቹ ምንም ትምህርት ያልሰጡበትን ከባድ ፈተና ቢፈተን ሊያልፍ ይችላል? በፈተናው የመውደቅ አጋጣሚው በጣም ሰፊ ነው። ስለዚህ ማስተማር አስፈላጊ ነው። የሆነ ሆኖ ጠንቃቃ አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸው ፈተና እንዲያልፉ ብቻ ሳይሆን ያገኙትን እውቀት እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም ጭምር ያስተምሯቸዋል። በተመሳሳይም ትጉህ የጉባኤ ሽማግሌዎች የተጠመቁ ወንድሞች፣ ከተሾሙ ወንዶች የሚጠበቁትን ባሕርያት እንዲያዳብሩ ልዩ ማሠልጠኛ ይሰጧቸዋል። እንዲህ የሚያደርጉት እነዚህ ወንድሞች ሹመት እንዲያገኙ ለማስቻል ብቻ ሳይሆን መንጋውን በብቃት መንከባከብ እንዲችሉ ለመርዳት ጭምር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:2) እርግጥ ነው፣ የተጠመቁ ወንድሞች ከሽማግሌዎች ወይም ከጉባኤ አገልጋዮች የሚፈለገውን ብቃት ለማሟላት የበኩላቸውን ጥረት ማድረግና ጠንክረው መሥራት ይገባቸዋል። (ቲቶ 1:5-9) ቢሆንም ተሞክሮ ያካበቱ እረኞች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለማግኘት የሚጣጣሩትን እነዚህን ወንድሞች በፈቃደኝነት በማሠልጠን ፈጣን እድገት እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይችላሉ።
10, 11. መንፈሳዊ እረኞች፣ ሌሎች ተጨማሪ መብት እንዲያገኙ ሥልጠና መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው?
10 በተለይ ተሞክሮ ያካበቱ እረኞች ሌሎች ወንድሞች የጉባኤ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ በጉባኤው ከሚገኙት ወንድሞች ጋር አዘውትረው በማገልገልና “የእውነትን ቃል በትክክል” የማስረዳት ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በማገዝ ከልብ እንደሚያስቡላቸው ማሳየት ይገባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) የጎለመሱ እረኞች፣ ሌሎችን ማገልገል ስለሚያስገኘው ደስታ እንዲሁም መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣታቸውና እነዚህ ግቦች ላይ መድረሳቸው ስላመጣላቸው እርካታ አንስተው ከእነዚህ ወንድሞች ጋር ሊጫወቱ ይችላሉ። እንዲሁም አንድ ወንድም ‘ለመንጋው ምሳሌ’ እንዲሆን የሚረዳውን ማሻሻያ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ በደግነት ሐሳብ ይሰጡታል።—1 ጴጥሮስ 5:3, 5
11 አንድ ወንድም በጉባኤ አገልጋይነት ከተሾመ በኋላም ቢሆን ጥበበኛ እረኞች እርሱን ማሠልጠናቸውን ይቀጥላሉ። ለአሥርተ ዓመታት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለው ብሩስ እንዲህ ብሏል:- “አዲስ ከተሾመ አገልጋይ ጋር ሆኜ ታማኝና ልባም ባሪያ ያዘጋጃቸውን መመሪያዎች መከለስ ያስደስተኛል። እንዲሁም ለእርሱ የተሰጠውን ሥራ የሚመለከት ማንኛውንም መመሪያ እናነባለን፤ በተጨማሪም ሥራውን እስኪለምድ ድረስ አብሬው መሥራት ደስ ይለኛል።” አንድ የጉባኤ አገልጋይ ተሞክሮ እያካበተ ሲሄድ ደግሞ እንዴት እረኝነት እንደሚያደርግ ሊሠለጥን ይችላል። ብሩስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “አንድን የጉባኤ አገልጋይ እረኝነት በማደርግበት ጊዜ ይዤው ስሄድ፣ የምንጎበኘውን ግለሰብ ወይም ቤተሰብ የሚያበረታቱና ለተግባር የሚያንቀሳቅሱ ጥቅሶችን እንዲመርጥ እረዳዋለሁ። አንድ አገልጋይ የተዋጣለት እረኛ እንዲሆን ከተፈለገ ልብን በሚነካ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ በዚህ መንገድ መማሩ በጣም አስፈላጊ ነው።”—ዕብራውያን 4:12፤ 5:14
12. ተሞክሮ ያካበቱ እረኞች አዳዲስ ሽማግሌዎችን ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?
12 አዲስ የተሾሙ እረኞችም ቢሆኑ ተጨማሪ ሥልጠና ቢሰጣቸው በጣም ይጠቀማሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኒክ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል:- “በተለይ በዕድሜ የሚበልጡኝ ሁለት የበላይ ተመልካቾች የሰጡኝ ማሠልጠኛ እጅግ ጠቃሚ ነበር። እነዚህ ወንድሞች አንዳንድ ጉዳዮች እንዴት ሊያዙ እንደሚገባ በደንብ ያውቃሉ። የምሰጠውን አስተያየት ባይስማሙበትም እንኳን ምንጊዜም ቢሆን በትዕግሥት የሚያዳምጡኝ ከመሆኑም በላይ ሐሳቤን በቁም ነገር ይመለከታሉ። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ወንድሞችና እህቶች በትሕትናና በአክብሮት ሲይዟቸው በመመልከቴ ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ። እነዚህ ሽማግሌዎች ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ማበረታቻ ለመስጠት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ አድርጎ የመጠቀምን አስፈላጊነት በሚገባ እንዳውቅ አድርገዋል።”
በአምላክ ቃል መሠልጠን
13. (ሀ) አንድ ወንድም ውጤታማ እረኛ ለመሆን ምን ያስፈልገዋል? (ለ) ኢየሱስ ‘የማስተምረው ትምህርት ከራሴ አይደለም’ ያለው ለምን ነበር?
13 አዎን፣ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እረኞች “ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ” እንዲሆኑ የሚረዷቸውን ሕጎች፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምሳሌዎች ይዟል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) አንድ ወንድም ጥሩ ዓለማዊ ትምህርት ተምሮ ይሆናል፤ ውጤታማ እረኛ ለመሆን የሚያስችለው ግን የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀቱና ይህንን እውቀቱን በተግባር የሚያውልበት መንገድ ነው። የኢየሱስን ምሳሌ ተመልከት። ኢየሱስ ከማንም የላቀ እውቀት ያለው፣ በጣም አስተዋይና እጅግ ጥበበኛ እረኛ ቢሆንም የይሖዋን በጎች የሚያስተምረው በራሱ ጥበብ ላይ ተመርኩዞ አልነበረም። ኢየሱስ “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው” ብሎ ነበር። ኢየሱስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱ ክብር የሰጠው ለምንድን ነው? “ከራሱ የሚናገር፣ ያን የሚያደርገው ለራሱ ክብርን ስለሚሻ ነው” በማለት ገልጿል።—ዮሐንስ 7:16, 18
14. እረኞች የራሳቸውን ክብር ከመፈለግ የሚቆጠቡት እንዴት ነው?
14 ታማኝ እረኞች ለራሳቸው ክብር ከመፈለግ ይቆጠባሉ። ምክርና ማበረታቻ የሚሰጡት የራሳቸውን ጥበብ ተመርኩዘው ሳይሆን በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተው ነው። የእረኞች ሥራ በጎች “የክርስቶስ ልብ” ወይም አስተሳሰብ እንዲኖራቸው መርዳት እንጂ የሽማግሌዎችን አስተሳሰብ እንዲይዙ ማድረግ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። (1 ቆሮንቶስ 2:14-16) ለአብነት ያህል፣ በትዳራቸው ውስጥ ችግር ያጋጠማቸውን ባልና ሚስት እየረዳ ያለ ሽማግሌ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና “ታማኝና ልባም ባሪያ” ባዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ ተመርኩዞ ምክር ከመስጠት ይልቅ ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ምክር ቢሰጣቸው ምን ችግር ይፈጠራል? (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) የሚሰጠው ምክር የአካባቢው ባሕል ተጽዕኖ የሚንጸባረቅበትና ውስን በሆነው የራሱ እውቀት የተገደበ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ባሕሎች በራሳቸው መጥፎ እንዳልሆኑና ሽማግሌው ከሕይወቱ ያገኘው ተሞክሮ ሊኖር እንደሚችል እሙን ነው። ነገር ግን በጎች ይበልጥ የሚጠቀሙት እረኞቹ፣ በሰዎች አስተሳሰብ ወይም በአካባቢያቸው ባሕል እንዲመሩ ሲነግሯቸው ሳይሆን የኢየሱስን ድምፅ እንዲሰሙና የይሖዋን ቃል እንዲያዳምጡ ሲያበረታቷቸው ነው።—መዝሙር 12:6፤ ምሳሌ 3:5, 6
‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ ሠልጥነዋል
15. ኢየሱስ ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ ምን ሥራ ሰጥቶታል? የባሪያው ክፍል እንዲሳካለት ያደረገው አንዱ ነገር ምንድን ነው?
15 እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ጳውሎስ ያሉት እረኞች በሙሉ ኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ብሎ የጠራው ቡድን አባላት ነበሩ። ይህ የባሪያ ክፍል ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ ያላቸውን በምድር ላይ የሚገኙ በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ወንድሞችን ያቀፈ ነው። (ራእይ 5:9, 10) እንደሚጠበቀው ሁሉ በዚህ የመጨረሻ ዘመን መደምደሚያ ላይ በምድር ያሉት የክርስቶስ ወንድሞች ቁጥር አሽቆልቁሏል። ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት እንዲፈጽሙት የሰጣቸው ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ግን ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሰፍቷል። ያም ሆኖ ግን የባሪያው ክፍል በሚያስደንቅ ሁኔታ ተሳክቶለታል! ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ለስኬቱ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች አንዱ፣ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል አባላትን በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ እንዲረዱ ማሠልጠኑ ነው። (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 24:14፤ 25:40) በአሁኑ ጊዜ ይህንን ሥራ በአብዛኛው እያከናወነ ያለው ይህ ታማኝ ቡድን ነው።
16. የባሪያው ክፍል የተሾሙ ወንዶችን የሚያሠለጥነው እንዴት ነው?
16 የባሪያው ክፍል ይህንን ማሠልጠኛ የሚሰጠው እንዴት ነው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የባሪያው ክፍል ወኪሎች በጉባኤዎች ውስጥ የበላይ ተመልካቾችን የማሠልጠንና የመሾም መብት ተሰጥቷቸው ነበር፤ የበላይ ተመልካቾቹም በበኩላቸው በጎቹን ያሠለጥኑ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 4:17) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የበላይ አካል በመባል የሚታወቀውና በመንፈስ የተቀቡ ጥቂት ወንድሞችን ያቀፈው የታማኙ ባሪያ ክፍል በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በአሥር ሺዎች በሚቆጠሩ ጉባኤዎች ውስጥ አገልጋዮችንና ሽማግሌዎችን የማሠልጠንና የመሾም መብት ለወኪሎቹ ሰጥቷል። በተጨማሪም የበላይ አካሉ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በጎቹን በተሻለ መንገድ መንከባከብ እንዲችሉ የሚሠለጥኑባቸውን ትምህርት ቤቶች ያዘጋጃል። እንዲሁም በደብዳቤዎች፣ በመጠበቂያ ግንብ ላይ በሚወጡ ርዕሰ ትምህርቶችና የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ a እንደሚለው በመሳሰሉ ሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት ተጨማሪ መመሪያዎች ያቀርባል።
17. (ሀ) ኢየሱስ በባሪያው ክፍል ላይ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) መንፈሳዊ እረኞችስ በባሪያው ክፍል ላይ እምነት እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ በባሪያው ላይ ጠንካራ እምነት ስላለው “በንብረቱ ሁሉ ላይ” ማለትም ምድር በሚገኘው መንፈሳዊ ሀብቱ ሁሉ ላይ ሾሞታል። (ማቴዎስ 24:47) የተሾሙ እረኞችም የበላይ አካሉ የሚሰጣቸውን መመሪያዎች በተግባር በማዋል በባሪያው ክፍል ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። አዎን፣ እረኞች ሌሎችን ሲያሠለጥኑ እንዲሁም ራሳቸው ከአምላክ ቃል ለመማር ፈቃደኞች ሲሆኑና የባሪያው ክፍል የሚሰጣቸውን ሥልጠና ተግባራዊ ሲያደርጉ መንጋው አንድነት እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይሖዋ እያንዳንዱን የክርስቲያን ጉባኤ አባል በሚገባ የሚንከባከቡ ወንዶችን በማሠልጠኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የጎለመሱ መንፈሳዊ እረኞች ሌሎችን የሚያሠለጥኑት እንዴት ነው?
• እረኞች በራሳቸው አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ትምህርት የማይሰጡት ለምንድን ነው?
• እረኞች በባሪያው ክፍል ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩት እንዴትና ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሽማግሌዎች በጉባኤያቸው ውስጥ የሚገኙ ወጣት ወንዶችን ያሠለጥናሉ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ታማኝና ልባም ባሪያ” ለጉባኤ ሽማግሌዎች በርካታ ሥልጠናዎችን ይሰጣል