በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድህነት ዛሬ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ድህነት ዛሬ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ድህነት ዛሬ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

በብራዚል የሚኖረው ቪሴንቴ፣ a በሳኦ ፓውሎ ጎዳናዎች ላይ ብዙ ዕቃ የተጫነበት ጋሪ እየጎተተ ሲሄድ ማየት የተለመደ ነው። ይህ ሰው ካርቶኖችን፣ ቆርቆሮዎችንና ፕላስቲኮችን ይለቃቅማል። ጨለምለም ሲል ደግሞ ካርቶን አነባብሮ ከጋሪው ሥር ያነጥፍና እዚያ ላይ ይተኛል። በተጨናነቀው መንገድ ዳር ሲያድር የመኪኖችና የአውቶቡሶች ድምፅ የሚረብሸው አይመስልም። ቪሴንቴ በአንድ ወቅት ሥራ፣ ቤትና ቤተሰብ የነበረው ቢሆንም አሁን ግን ሁሉንም አጥቶ በጎዳና ላይ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት ይመራል።

የሚያሳዝነው ነገር በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ቪሴንቴ በከፋ ድህነት ይማቅቃሉ። በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የጎዳና ተዳዳሪ ለመሆን አሊያም ችምችም ባሉ የቆረቆዙ መንደሮች ውስጥ ለመኖር ተገደዋል። አካል ጉዳተኞች፣ ማየት የተሳናቸው ሰዎች እንዲሁም የሚያጠቡ ሴቶች በልመና ተሠማርተው መመልከት የተለመደ ሆኗል። ልጆች ደግሞ ጥቂት ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የሚሸጥ ከረሜላ ይዘው ትራፊክ ባስቆማቸው መኪኖች መካከል ሲሮጡ ይታያሉ።

እንዲህ ዓይነቱ የከፋ ድህነት የኖረበትን ምክንያት ማስረዳት ቀላል አይደለም። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው የብሪታንያ መጽሔት እንዲህ ሲል አስተያየት ሰጥቷል:- “የሰው ዘር የአሁኑን ዘመን ያክል ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችል ሀብት ወይም የሕክምና እውቀት፣ የቴክኖሎጂ እድገትና ጥበብ ኖሮት አያውቅም።” ብዙዎች የሰው ልጅ ባካበተው ከፍተኛ እውቀት መጠቀማቸው እሙን ነው። በበርካታ ታዳጊ አገሮች ውስጥ የትላልቅ ከተሞች አውራ ጎዳናዎች በሚያማምሩ አዳዲስ መኪኖች ተጣበዋል። የገበያ ማዕከሎች በጣም ዘመናዊ በሆኑ ሸቀጦች የተጨናነቁ ሲሆን ሸማችም ቢሆን ሞልቷል። ለአብነት ያህል፣ በብራዚል የሚገኙ ሁለት የገበያ ማዕከሎች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ልዩ ዝግጅት አድርገው ነበር። ታኅሣሥ 23 እና 24, 2004 የ24 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታወቁ። አንደኛው የገበያ ማዕከል ሸማቾችን ለማዝናናት የባሕል ተወዛዋዦችን ቀጠረ። ይህ ዝግጅት 500,000 የሚያህሉ ገበያተኞችን ቀልብ ስቦ ነበር!

ይሁንና በጣም ብዙ ሰዎች አንዳንዶች ከሚያገኙት ሀብት አይቋደሱም። በሀብታሞችና በድሆች መካከል የተፈጠረው በጣም ሰፊ ልዩነት፣ ብዙዎች ድህነትን ለማስወገድ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ቬጃ የተባለ የብራዚል መጽሔት “በዚህ ዓመት [በ2005] ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረገው ትግል የዓለም መሪዎች ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን ይገባዋል” ብሏል። አክሎም፣ በተለይ በአፍሪካ የሚገኙትን በጣም ድሀ አገሮች ለመርዳት አዲስ ማርሻል ፕላን እንዲነደፍ ሐሳብ መቅረቡን ሪፖርት አድርጓል። b እንደዚህ ያሉት እቅዶች አስደናቂ መሻሻል እንደሚያመጡ ይታመናል። ይሁን እንጂ ይኸው መጽሔት እንደተናገረው “ጥሩ ውጤት መገኘቱን አጠራጣሪ የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶችም አሉ። አብዛኞቹ አገሮች እንዲህ ላለው እቅድ መዋጮ ማድረግ የማይፈልጉት የሚያዋጡት ገንዘብ በትክክል ወደሚያስፈልጋቸው ሰዎች ስለማይደርስ ነው።” መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከሚለግሱት ገንዘብ አብዛኛው በሙስናም ሆነ በቢሮክራሲ ምክንያት እርዳታው በእርግጥ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አይሰጥም።

ኢየሱስ ድህነት እንደሚቀጥል ያውቅ ስለነበር “ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 26:11) ይህ ሲባል ታዲያ ድህነት ሁልጊዜም በምድር ላይ ይኖራል ማለት ነው? ሁኔታውን ለማሻሻልስ ምን ማድረግ ይቻላል? ክርስቲያኖች ድሆችን ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስሙ ተቀይሯል።

b ማርሻል ፕላን የሚባለው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአውሮፓ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ለመርዳት የተነደፈ በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፍ ፕሮግራም ነበር።