በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመዳን የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርገሃል?

ለመዳን የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርገሃል?

ለመዳን የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርገሃል?

“በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ።”—ዘፍጥረት 7:1

1. ይሖዋ በኖኅ ዘመን ሰዎችን ለማዳን ምን ዝግጅት አድርጎ ነበር?

 በኖኅ ዘመን ይሖዋ ‘በኀጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ ቢያመጣም’ ለመዳን የሚያስችል ዝግጅትም አድርጎ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በፊት እውነተኛው አምላክ፣ ለጻድቁ ለኖኅ ሕይወት ለማዳን የሚያስችል መርከብ እንዴት እንደሚሠራ ዝርዝር መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (ዘፍጥረት 6:14-16) ታማኝ ከሆነ አንድ የይሖዋ አገልጋይ እንደሚጠበቀው ሁሉ “ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።” በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዛሬ በሕይወት ለመገኘት የቻልነው ኖኅ ታዛዥ በመሆኑ ምክንያት ነው።—ዘፍጥረት 6:22

2, 3. (ሀ) በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ኖኅ ያከናወነውን ሥራ ቢመለከቱም ምን አላደረጉም? (ለ) ኖኅ ወደ መርከቧ ሲገባ ምን እምነት ነበረው?

2 መርከቧን መሥራት ቀላል አልነበረም። በወቅቱ የነበሩ ብዙ ሰዎች ኖኅና ቤተሰቡ በሚሠሩት ነገር ሳይገረሙ አይቀሩም። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የተመለከቱት ነገር፣ መዳናቸው የተመካው መርከቧ ውስጥ በመግባታቸው ላይ መሆኑን እንዲያምኑ አላደረጋቸውም። በመጨረሻም አምላክ ለዚያ ክፉ ዓለም የነበረው ትዕግሥት ተሟጠጠ።—ዘፍጥረት 6:3፤ 1 ጴጥሮስ 3:20

3 ኖኅና ቤተሰቡ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት አድካሚ የሆነ የግንባታ ሥራ ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ ይሖዋ ኖኅን “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ” አለው። በይሖዋ ቃል በመተማመን “ኖኀና ወንዶች ልጆቹ፣ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች . . . ወደ መርከቧ ገቡ።” ከዚያም ይሖዋ አምላኪዎቹን ከሚመጣው ጥፋት ለመጠበቅ ሲል በሩን ዘጋው። ምድር በጥፋት ውኃው በተጥለቀለቀችበት ወቅት፣ አምላክ ሕዝቦቹን ለማዳን ያዘጋጃት መርከብ አስተማማኝ መሆኗ በግልጽ ታይቷል።—ዘፍጥረት 7:1, 7, 10, 16

ጊዜያችንን ከኖኅ ዘመን ጋር የሚያመሳስሉት ነገሮች

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ እርሱ በሚገኝበት ወቅት የሚኖረውን ሁኔታ ከየትኛው ጊዜ ጋር አመሳስሎታል? (ለ) በኖኅ ዘመንና በጊዜያችን መካከል ምን ተመሳሳይነት ይታያል?

4 “ልክ በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:37) ኢየሱስ ከላይ ያሉትን ቃላት ሲናገር እርሱ በማይታይ ሁኔታ የሚገኝበት ወቅት ከኖኅ ዘመን ጋር እንደሚመሳሰል መግለጹ ነበር፤ ይህም በትክክል ተፈጽሟል። በተለይ ከ1919 ወዲህ ኖኅ ከሰበከው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የማስጠንቀቂያ መልእክት ለሰዎች ሁሉ እየታወጀ ነው። በጥቅሉ ሲታይ የሰዎች ምላሽ በኖኅ ዘመን ከነበረው የተለየ አይደለም።

5 ይሖዋ ‘በዐመፅ በተሞላው’ ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ በማምጣት እርምጃ ወስዷል። (ዘፍጥረት 6:13) ኖኅና ቤተሰቡ በወቅቱ በነበረው ዓመጽ አለመካፈላቸውና ሰላማዊ ሆነው መርከቧን የመገንባት ሥራቸውን መቀጠላቸው ለሚያዩአቸው ሁሉ ግልጽ ነበር። ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ እንመለከታለን። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች “በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት” ማየት ይችላሉ። (ሚልክያስ 3:18) ቀና አመለካከት ያላቸው ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኞች፣ ደጎች፣ ሰላማውያንና ትጉ ሠራተኞች መሆናቸውን ተመልክተው የሚያደንቋቸው ሲሆን እነዚህ ባሕርያት የአምላክን ሕዝቦች ከሌላው የዓለም ሕዝብ ልዩ ያደርጓቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም መልኩ በዓመጽ የማይካፈሉ ከመሆኑም በላይ በአምላክ መንፈስ ለመመራት ፈቃደኞች ናቸው። ሰላማዊ የሆኑትና በጽድቅ ጎዳና የሚመላለሱትም ለዚህ ነው።—ኢሳይያስ 60:17

6, 7. (ሀ) በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ያልተገነዘቡት ነገር ምን ነበር? ዛሬስ ሁኔታው ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሰዎች የተለዩ እንደሆኑ ተደርገው እንደሚታዩ የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉ?

6 በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች አምላክ ኖኅን እንደሚደግፈውና እርሱም የይሖዋን መመሪያ እንደሚከተል አልተገነዘቡም ነበር። በዚህም ምክንያት የሚሰብከውን መልእክት በቁም ነገር አልተመለከቱትም፤ ማስጠንቀቂያውን ሰምተውም እርምጃ አልወሰዱም። ዛሬስ? ብዙ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት ሥራና በምግባራቸው ቢደነቁም የስብከቱን ሥራም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የማስጠንቀቂያ መልእክት በቁም ነገር አይመለከቱትም። ጎረቤቶች፣ አሠሪዎች ወይም ዘመዶች እውነተኛ ክርስቲያኖች ያሏቸውን መልካም ባሕርያት በጣም የሚያደንቁ ቢሆንም “የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑ ኖሮ ጥሩ ነበር!” በማለት ቅሬታቸውን መግለጻቸው አይቀርም። እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ፍቅር፣ ሰላም፣ ደግነት፣ በጎነት፣ ገርነትና ራስን መግዛት የመሳሰሉትን ባሕርያት ማፍራት የቻሉት በአምላክ መንፈስ ስለሚመሩ መሆኑን አያስተውሉም። (ገላትያ 5:22-25) እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደነዚህ ያሉትን ባሕርያት ማንጸባረቃቸው ሰዎች መልእክታቸውን ለመቀበል ይበልጥ ፈቃደኛ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር።

7 ለአብነት ያህል፣ ሩሲያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ይገነቡ ነበር። አንድ ሰው ቆም ብሎ ከሠራተኞቹ አንዱን እንዲህ አለው:- “በጣም አስገራሚ የግንባታ ቦታ ነው፤ የሚያጨስም ሆነ የሚሳደብ ወይም ደግሞ የሰከረ ሰው የለም! የይሖዋ ምሥክር ነህ እንዴ?” ሠራተኛውም መልሶ “አይደለሁም ብልህ ታምነኛለህ?” ሲል ጠየቀው። የሰውየው ምላሽ “በፍጹም” የሚል ነበር። በሌላ የሩሲያ ከተማ ከንቲባው፣ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ሲገነቡ ተመልክቶ በጣም ተገረመ። በአንድ ወቅት ሁሉም ሃይማኖታዊ ቡድኖች ተመሳሳይ እንደሆኑ ያስብ እንደነበረ ከገለጸ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ መንገድ ከልባቸው ሲሠሩ ሲመለከት ግን አመለካከቱን እንደቀየረ ተናገረ። የይሖዋ ሕዝቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ተስማምተው ከማይሄዱ ሰዎች የተለዩ መሆናቸውን እነዚህ ምሳሌዎች ያሳያሉ።

8. ከዚህ ክፉ ሥርዓት ጥፋት መትረፋችን የተመካው በምን ላይ ነው?

8 በጥፋት ውኃ የወደመው ‘የቀድሞው ዓለም’ ሊጠፋ አካባቢ፣ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ሆኖ በታማኝነት ያገለግል ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) ይህ ሥርዓት ሊጠፋ በተቃረበባቸው በእነዚህ የመጨረሻ ቀናትም የይሖዋ ሕዝቦች፣ የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች ለሰዎች እያሳወቁና ከጥፋት ተርፎ ወደ አዲሱ ዓለም መግባት እንደሚቻል የሚገልጸውን ምሥራች እየሰበኩ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:9-13) ኖኅና አምላክን የሚፈሩት ቤተሰቦቹ ወደ መርከቧ በመግባት ከጥፋቱ እንደዳኑ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎችም መዳናቸው የተመካው እምነት በማሳየታቸውና ከይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ጋር በታማኝነት በመተባበራቸው ላይ ነው።

ለመዳን እምነት ያስፈልጋል

9, 10. በሰይጣን ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት መትረፍ ከፈለግን እምነት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

9 አንድ ሰው፣ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ዓለም ላይ በቅርቡ ከሚመጣው ጥፋት ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? (1 ዮሐንስ 5:19) በመጀመሪያ ደረጃ ጥበቃና ከለላ ማግኘት እንደሚያስፈልገው መገንዘብ አለበት። በተጨማሪም ጥበቃ እንዲያገኝ በተደረገው ዝግጅት መጠቀም ይኖርበታል። በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች እያንዣበበ ካለው አደጋ ለመዳን ከለላ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ስላልተሰማቸው የተለመዱ ዕለታዊ ጉዳዮቻቸውን በማከናወን ተጠምደው ነበር። ከዚህም በላይ አንድ ነገር ይጎድላቸው ነበር፤ እነዚያ ሰዎች በአምላክ ላይ እምነት አልነበራቸውም።

10 በሌላ በኩል ግን ኖኅና ቤተሰቡ ጥበቃ ማግኘትና ከጥፋት መዳን እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበው ነበር። ከዚህም በላይ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት ነበራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት” በማለት ጽፏል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።”—ዕብራውያን 11:6, 7

11. ይሖዋ ባለፉት ዘመናት ለሕዝቦቹ ጥበቃ ካደረገበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 አሁን ያለው ክፉ ሥርዓት ሲጠፋ ለመዳን ከፈለግን ሥርዓቱ እንደሚጠፋ ከማመን የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። አምላክ ለመዳን ባደረገው ዝግጅት ሙሉ በሙሉ በመጠቀም እምነት እንዳለን ማሳየት አለብን። በአምላክ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመን እንደሚያስፈልገን ጥያቄ የለውም። (ዮሐንስ 3:16, 36) ሆኖም ከጥፋት ውኃው መትረፍ የቻሉት የኖኅ መርከብ ውስጥ የገቡት ብቻ እንደነበሩ ማስታወሳችን የተገባ ነው። በተመሳሳይም በጥንቷ እስራኤል ሳያስበው ሰው የገደለ ግለሰብ በመማጸኛ ከተሞች ውስጥ ጥበቃ ሊያገኝ የሚችለው መጀመሪያውኑ ወደ እነዚያ ከተሞች ከሸሸና ሊቀ ካህኑ እስኪሞት ድረስ ከከተማው ሳይወጣ ከቆየ ብቻ ነው። (ዘኍልቍ 35:11-32) በሙሴ ዘመን በግብጽ ላይ በወረደው በአሥረኛው መቅሰፍት የግብጻውያን የበኩር ልጆች ሲሞቱ የእስራኤላውያን ልጆች ግን ተርፈዋል። ለምን? ይሖዋ፣ እስራኤላውያን “ከደሙ [ለማለፍ በዓል ከታረደው ጠቦት ደም] ወስደው የጠቦቶቹ ሥጋ የሚበላበትን የእያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃንና ጉበን ይቀቡ። . . . ከእናንተ አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ አይውጣ” በማለት ለሙሴ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (ዘፀአት 12:7, 22) ከእስራኤላውያን የበኩር ልጆች መካከል የቤቱ ደጃፍ መቃንና ጉበን ደም ከተቀባበት ቤት በመውጣት አምላክ የሰጠውን ይህንን መመሪያ ችላ ለማለት የደፈረ አልነበረም።

12. እያንዳንዳችን ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል? ለምንስ?

12 እንግዲያው እኛም ስለ ግል ሁኔታችን እንድናስብ የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን። ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ እንድናገኝ ባደረገው ዝግጅት እየተጠቀምን ነው? እንዲህ ካለው ጥበቃ የተጠቀሙ ሰዎች ታላቁ መከራ ሲመጣ በደስታና በአመስጋኝነት ተሞልተው ሲያነቡ ሌሎቹ ግን በሐዘንና በጸጸት ያለቅሳሉ።

በየጊዜው የሚደረጉት ማስተካከያዎች ለመዳን ያዘጋጁናል

13. (ሀ) ድርጅታዊ ማስተካከያዎች ምን ጥቅም አስገኝተዋል? (ለ) ከጊዜ ወደ ጊዜ ከተደረጉት ማስተካከያዎች ጥቂቶቹን ግለጽ።

13 ይሖዋ የአጽናፈ ዓለማዊ ድርጅቱ ምድራዊ ክፍል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተካከለ እንዲሄድ አድርጓል። ይህም መንፈሳዊ ጥበቃ እንድናገኝ ያደረገውን ዝግጅት ለማስዋብና ለማጠናከር እንዲሁም አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ አስችሏል። ከ1870ዎቹ እስከ 1932 ባሉት ዓመታት ሽማግሌዎች እና ዲያቆናት ሆነው የሚያገለግሉት ወንድሞች በጉባኤው አባላት ይመረጡ ነበር። በ1932 ሽማግሌዎችን ሳይሆን የአገልግሎት ኮሚቴ መምረጥ የተጀመረ ሲሆን የዚህ ኮሚቴ ኃላፊነት የተሾመውን የአገልግሎት ዲሬክተር ማገዝ ነበር። በ1938 በጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ሁሉ ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሾም ጀመሩ። ከ1972 አንስቶ በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አመራር ሥር የበላይ ተመልካቾችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሾም የተጀመረ ሲሆን የቀረበው የድጋፍ ሐሳብ ተቀባይነት ካገኘ ይህንን የሚገልጽ ደብዳቤ ለጉባኤዎች ይላካል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የበላይ አካሉ የሚጫወተው ሚና ከማደጉም በላይ ሥራውን ይበልጥ ለማሻሻል የሚረዱ ለውጦች ተደርገዋል።

14. በ1959 ምን ዓይነት የሥልጠና ፕሮግራም ተጀመረ?

14 በ1950 በመዝሙር 45:16 ላይ የተደረገ ጥልቅ ጥናት አንድ ቀጣይ የሥልጠና ፕሮግራም እንዲጀመር መንገድ ከፈተ። ጥቅሱ “ወንዶች ልጆችህ በአባቶችህ እግር ይተካሉ፤ ገዦችም አድርገሽ በምድር ሁሉ ትሾሚያቸዋለሽ” ይላል። በአሁኑ ጊዜ ጉባኤዎችን በመምራት የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች አሁን ላሏቸውና ከአርማጌዶን በኋላም ለሚኖሯቸው ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች ሥልጠና እያገኙ ነው። (ራእይ 16:14, 16) በ1959 የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ተጀመረ። በዚያን ጊዜ የጉባኤ አገልጋዮች ተብለው ይጠሩ የነበሩት ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቾች አንድ ወር የሚፈጅ ሥልጠና ይሰጣቸው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ይህ ትምህርት ቤት ለሁሉም የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ሥልጠና ይሰጣል። እነዚህ ወንድሞች ደግሞ በየጉባኤያቸው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ያሠለጥናሉ። በዚህ መንገድ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች መንፈሳዊ እርዳታ የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ የመንግሥቱን ምሥራች ሲሰብኩ በአገልግሎታቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ ይደረግላቸዋል።—ማርቆስ 13:10

15. የክርስቲያን ጉባኤ ንጽሕና ተጠብቆ እንዲኖር ያስቻሉት ሁለት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

15 የክርስቲያን ጉባኤ አባላት መሆን የሚፈልጉ ግለሰቦች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶች አሉ። በኖኅ ዘመን የነበሩት ዘባቾች ወደ መርከቧ እንዲገቡ እንዳልተፈቀደላቸው ሁሉ በዘመናችን የሚገኙ ዘባቾችም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቦታ የላቸውም። (2 ጴጥሮስ 3:3-7) በተለይ ከ1952 ጀምሮ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን በማስወገድ የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ የተደረገውን ዝግጅት ደግፈዋል። እርግጥ ነው፣ ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች ‘ለእግራቸው ቀና መንገድ እንዲያበጁ’ ፍቅራዊ እርዳታ ይደረግላቸዋል።—ዕብራውያን 12:12, 13፤ ምሳሌ 28:13፤ ገላትያ 6:1

16. የይሖዋ ሕዝቦች የሚገኙበት መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

16 የይሖዋ ምሥክሮች መንፈሳዊ ብልጽግና ሊያገኙ የቻሉት እንዲያው በድንገት ወይም በአጋጣሚ አይደለም። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል:- “ባሮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ ባሮቼ ይጠጣሉ፤ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ ባሮቼ ደስ ይላቸዋል፤ እናንተ ግን ታፍራላችሁ። ባሮቼ፣ ከልብ በመነጨ ደስታ ይዘምራሉ፤ እናንተ ግን፣ ልባችሁ በማዘኑ ትጮኻላችሁ፤ መንፈሳችሁ በመሰበሩም ወዮ ትላላችሁ።” (ኢሳይያስ 65:13, 14) ይሖዋ በወቅቱ ተዘጋጅቶ የሚቀርብና ጤናማ የሆነ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በመስጠት በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንድንሆን የሚረዳንን የማያቋርጥ ዝግጅት አድርጎልናል።—ማቴዎስ 24:45

ለመዳን የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርግ

17. ለመዳን የሚያስፈልገውን ዝግጅት እንድናደርግ ምን ሊረዳን ይችላል?

17 “እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም . . . እርስ በርሳችን እንበረታታ” የሚለውን ምክር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ልንሠራበት ይገባል። (ዕብራውያን 10:23-25) በአሁኑ ጊዜ ከ98,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ጉባኤዎች በአንዱ ውስጥ መሰብሰባችንና ጉባኤው በሚያደርገው እንቅስቃሴ መካፈላችን ለመዳን ራሳችንን እንድናዘጋጅ ይረዳናል። “አዲሱን ሰው” ለመልበስና ይሖዋ ስላደረገው የመዳን ዝግጅት እንዲያውቁ ሌሎችን ለመርዳት በምናደርገው ልባዊ ጥረት የእምነት ባልንጀሮቻችንም ያግዙናል።—ኤፌሶን 4:22-24፤ ቈላስይስ 3:9, 10፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16

18. ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ተቀራርበህ ለመኖር የቆረጥኸው ለምንድን ነው?

18 ሰይጣንና በእርሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ይህ ክፉ ዓለም እኛን ከክርስቲያን ጉባኤ ለማስወጣት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ይሁን እንጂ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መመላለሳችንን መቀጠል እንዲሁም በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት መትረፍ እንችላለን። ለይሖዋ ያለን ፍቅርና ላደረገልን ፍቅራዊ ዝግጅቶች ያለን አድናቆት የሰይጣንን ጥረቶች ለማክሸፍ ከምንጊዜውም በላይ ቆርጠን እንድንነሳ ያድርገን። በአሁኑ ጊዜ ባገኘናቸው በረከቶች ላይ ማሰላሰላችን ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። ከእነዚህ በረከቶች አንዳንዶቹ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ተብራርተዋል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ያለንበት ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

• ለመዳን የትኛውን ባሕርይ ማዳበር ያስፈልገናል?

• ይሖዋ እኛን ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ለማጠናከር ምን ማስተካከያዎች አድርጓል?

• በግለሰብ ደረጃ ለመዳን ዝግጅት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ኖኅ የሚያከናውነውን ሥራ በቁም ነገር አልተመለከቱትም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን የማስጠንቀቂያ መልእክት በትኩረት ማዳመጥ ጠቃሚ ነው

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ዓላማው ምንድን ነው?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ተቀራርበን ለመኖር ጊዜው አሁን ነው