በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን ለማስፋፋት የተደረገ ድፍረት የተሞላበት ጥረት

መጽሐፍ ቅዱስን ለማስፋፋት የተደረገ ድፍረት የተሞላበት ጥረት

መጽሐፍ ቅዱስን ለማስፋፋት የተደረገ ድፍረት የተሞላበት ጥረት

ስሙ ጎድፎና ተዋርዶ የነበረ አንድ ሰው በጣም ቀዝቃዛ በሆነው የምሥራቅ ሳይቤሪያ ክፍል ሕይወቱ አለፈ። አንዳንዶች ለግሪካውያን መንፈሳዊ እድገት በዋነኝነት አስተዋጽኦ ካደረጉት ሰዎች አንዱ እንደነበረ ያስታውሳሉ። በብዙዎች ዘንድ ችላ የተባለው ይህ ሰው ሴራፊም ይባላል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማስፋፋት ያደረገው ድፍረት የተሞላበት ጥረት ለሞቱ ምክንያት ሆኗል።

ሴራፊም የኖረው ግሪክ የኦቶማን ግዛት አካል በነበረችበት ወቅት ነው። የግሪክ ኦርቶዶክስ ምሑር የሆኑት ጆርጅ ሜታሊኖስ እንዳሉት ከሆነ፣ በዚያ ዘመን “ተስማሚ የሆኑ ትምህርት ቤቶች እጥረት” የነበረ ሲሆን ቀሳውስትን ጨምሮ “ብዙኃኑ ሕዝብ ያልተማረ” ነበር።

በኮይኔ (በተራ ግሪክኛ) እና በርካታ ቀበልኛዎች ባለው የዘመኑ ግሪክኛ መካከል ሰፊ ልዩነት ነበር። ይህ ልዩነት እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የተጻፉበት ኮይኔ፣ መደበኛ ትምህርት ያላገኙ ሰዎች የማይረዱት ቋንቋ እስከመሆን ደርሶ ነበር። በዚህ የተነሳ ውዝግብ ቢፈጠርም ቤተ ክርስቲያን በብዙዎች ዘንድ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነውን የኮይኔን ግሪክኛ ለመጠቀም ወሰነች።

በ1670 አካባቢ በሌዝቮስ ደሴት ይኖር በነበረ አንድ ታዋቂ ቤተሰብ ውስጥ ስቲፋኖስ ኢዮኒስ ፖጎናቶስ የተባለ ሕፃን ሲወለድ በአገሪቱ የነበረው ሁኔታ ይህን ይመስል ነበር። በወቅቱ በደሴቲቱ ላይ ድህነትና መሃይምነት ተንሰራፍቶ ነበር። ትምህርት ቤቶች በበቂ ሁኔታ ስላልነበሩ ስቲፋኖስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአካባቢው ባለ ገዳም ውስጥ ለመከታተል ተገደደ። ገና ትንሽ ልጅ ሳለ በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዲያቆን ሆኖ ተሾመና ሴራፊም የሚል ስም ተሰጠው።

ሴራፊም የማወቅ ጉጉት ስለነበረው በ1693 ገደማ ወደ ቁስጥንጥንያ (የአሁኗ ኢስታንቡል፣ ቱርክ) ተጓዘ። ያካበተው እውቀት ውሎ አድሮ የግሪክ ታላላቅ ሰዎችን አክብሮት አተረፈለት። ብዙም ሳይቆይ በሕቡዕ ይንቀሳቀስ የነበረ አንድ የግሪክ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ሴራፊምን መልእክተኛው አድርጎ ወደ ሩሲያው ዛር ወደ ታላቁ ፒተር ላከው። ወደ ሞስኮ ያደረገው ይህ ጉዞ ሴራፊም ብዙዎቹን የአውሮፓ አገሮች ተዘዋውሮ እንዲመለከትና በሃይማኖትና በሌሎች ጉዳዮች ረገድ እየተደረገ ከነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር እንዲተዋወቅ አስችሎታል። በ1698 ሴራፊም ወደ እንግሊዝ በመጓዝ በለንደንና በኦክስፎርድ ከሚኖሩ ታላላቅ ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ችሎ ነበር። በወቅቱ የአንግሊካንን ቤተ ክርስቲያን ይመሩ ከነበሩት የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ጋር የተዋወቀ ሲሆን ይህም ብዙም ሳይቆይ ለገጠመው ጉዳይ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቶታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ማሳተም

ሴራፊም በእንግሊዝ ሳለ ግሪኮች በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት በአዲስ መልክ የተተረጎመ “አዲስ ኪዳን” (የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች) በጣም ያስፈልጋቸዋል የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰ። ከዚያም ከግማሽ ምዕተ ዓመት ቀደም ብሎ ማክሲመስ በተባለ መነኩሴ የተዘጋጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት በማድረግ ከስህተት የጸዳና ለመረዳት ቀላል የሆነ አዲስ ትርጉም ለማዘጋጀት ይጥር ጀመር። ሴራፊም ሥራውን የጀመረው በጋለ ስሜት ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ የገንዘብ እጥረት ገጠመው። ያም ሆኖ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ስለገቡለት ተስፋው እንደገና ለመለመ። ሴራፊም እንዲህ ባለው ድጋፍ በመበረታታት ለሕትመቱ አስፈላጊ የሆኑትን የማተሚያ ወረቀቶች ከገዛ በኋላ ከሚያትምለት ድርጅት ጋር ተዋዋለ።

ይሁንና ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከማቴዎስና ከማርቆስ እንዲሁም ከሉቃስ ወንጌል አጋማሽ በላይ ሊያሳትም አልቻለም። በወቅቱ በእንግሊዝ የነበረው ፖለቲካዊ ለውጥ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ተጨማሪ እርዳታ እንዳያደርጉ አግዷቸው ነበር። ሴራፊም ተስፋ ባለመቁረጥ ከአንዳንድ ሀብታሞች እርዳታ ካሰባሰበ በኋላ በ1703 የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉሙን ለማሳተም በቃ። ከወጣው ወጪ ውስጥ ግማሽ ያህሉን የሸፈነው ወንጌልን በባዕድ አገር የማስፋፋት ዓላማ ያለው አንድ ማኅበር ነበር።

ቀደም ሲል በማክሲመስ የተዘጋጀው ባለ ሁለት ጥራዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የግሪክኛውን በኩረ ጽሑፍም የያዘ በመሆኑ ትልቅና ከባድ ነበር። ሴራፊም ለሕትመት ያበቃው በአዲስ መልክ እንደገና የተዘጋጀው ትርጉም ግን አነስ ባሉ ፊደላት የተጻፈ፣ ዘመናዊውን የግሪክኛ ትርጉም ብቻ የያዘ እንዲሁም ብዙ ገጾች የሌሉትና ዋጋውም ርካሽ ነበር።

ውዝግቡን አባባሰው

ጆርጅ ሜታሊኖስ የተባሉ አንድ ምሑር እንደሚከተለው ብለዋል:- “ተሻሽሎ የወጣው ይህ ጽሑፍ ሕዝቡ በጣም የሚፈልገውን ነገር ያሟላ ቢሆንም ሴራፊም፣ ይህን አጋጣሚ መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሙን የሚቃወሙ ቀሳውስትን ለማጥቃት ተጠቅሞበታል።” ሴራፊም በመቅድሙ ላይ እንደገለጸው ይህን ትርጉም ያዘጋጀው ‘[ኮይኔ] ግሪክኛን መረዳት ለማይችሉ አንዳንድ ቀሳውስት ሲሆን እነዚህ ቀሳውስት የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ታክሎበት በኩረ ጽሑፉን አንብበውና ተረድተው መልእክቱን ለተራው ክርስቲያን እንዲያስተላልፉ’ በማሰብ ነው። (ዘ ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ባይብል ኢንቱ ሞደርን ግሪክ—ዲዩሪንግ ዘ ናይንቲንዝ ሴንቸሪ) እንዲህ ማለቱ ቀሳውስቱን በጣም አስቆጣቸው። በመሆኑም ሴራፊም በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሙን አስመልክቶ በተነሳው ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገባ።

በዚህ ውዝግብ፣ በአንድ ወገን የሕዝቡ መንፈሳዊ እድገትና የሥነ ምግባር መሻሻል የተመካው መጽሐፍ ቅዱስን በማወቃቸው ላይ መሆኑን የተገነዘቡ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች፣ ቀሳውስቱም ቢሆን የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀታቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው ይሰማቸው ነበር። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሙን የሚደግፉት ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች በየትኛውም ቋንቋ መገለጽ ይችላሉ የሚል እምነት ነበራቸው።—ራእይ 7:9

መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሙን የሚቃወሙ ሰዎች ደግሞ ይህ ሥራ የመጽሐፉ ይዘት እንዲበረዝ ከማድረጉም ባሻገር ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎምና ድንጋጌዎችን በማውጣት ረገድ ያላትን ሥልጣን ያሳጣታል የሚሉ ሰበቦችን ያቀርቡ ነበር። ይሁንና ዋናው ፍርሃታቸው ፕሮቴስታንቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ተጠቅመው የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ሥልጣን ቀስ በቀስ ይሸረሽሩታል የሚል ነበር። አብዛኞቹ ቀሳውስት ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዳ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት ጨምሮ፣ ፕሮቴስታንቶችን ሊደግፍ ይችላል ብለው ያሰቡትን ማንኛውም ሁኔታ የመቃወም ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸው ነበር። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሙ በፕሮቴስታንትና በኦርቶዶክስ መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳ ጉዳይ ሆነ።

ሴራፊም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ትቶ የመውጣት ሐሳብ ባይኖረውም እንኳ የሚቃወሙትን ቀሳውስት ድንቁርናና ጭፍን አስተሳሰብ በይፋ አውግዟል። በተረጎመው “አዲስ ኪዳን” መቅድም ላይ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ፈሪሃ አምላክ ያለው ማንኛውም ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይኖርበታል።” ይህም “የክርስቶስን ምሳሌ ለመኮረጅና ትምህርቶቹን ለመታዘዝ ያስችለዋል።” ሴራፊም ቅዱሳን ጽሑፎች እንዳይነበቡ ማገድ የዲያብሎስ ሥራ መሆኑን አመልክቷል።

ሴራፊም የተቃውሞ ማዕበል ገጠመው

የሴራፊም ትርጉም ግሪክ ሲደርስ በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቁጣ ስለተቀሰቀሰ አዲሱ ቅጂ ታገደ። የዚህ ትርጉም ቅጂዎች ተቃጠሉ እንዲሁም ይህ ትርጉም ያለው አሊያም ጽሑፉን የሚያነብ ሰው ከቤተ ክርስቲያኗ እንደሚገለል ተነገረ። ፓትሪያርክ ጋብሪኤል ሳልሳዊ፣ የሴራፊም ትርጉም አላስፈላጊና እርባና ቢስ ነው በማለት እንዳይሰራጭ አገዱ።

ሴራፊም በሁኔታው ተስፋ ባይቆርጥም ብልህ መሆን እንደሚገባው ተገንዝቦ ነበር። ቤተ ክርስቲያኗ እገዳ ብትጥልም በርካታ ቀሳውስትና ተራው ሕዝብ የሴራፊምን ትርጉም አግኝቶ የነበረ ሲሆን ሴራፊምም ትርጉሙን በተሳካ ሁኔታ ማሰራጨት ችሏል። ሆኖም ኃያል ከሆኑት ጠላቶቹ ጋር የተፈጠረው ግጭት ገና መጀመሩ ነበር።

ለሴራፊም መሞት ምክንያት የሆኑ ነገሮች

ሴራፊም መጽሐፍ ቅዱስን ከማሰራጨት ባሻገር በአብዮታዊና በብሔራዊ እንቅስቃሴዎችም ይካፈል ነበር። ይህን ዓላማውን ለማሳካት ሲል በ1704 የበጋ ወራት ላይ በድጋሚ ወደ ሞስኮ ተጓዘ። ከዚያም የታላቁ ፒተር ታማኝ ወዳጅና ለጊዜውም ቢሆን የሩሲያ ሮያል አካዳሚ ፕሮፌሰር መሆን ቻለ። ይሁንና የተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ጉዳይ ስላሳሰበው በ1705 ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ።

በዚሁ ዓመት ትርጉሙን በድጋሚ ያሳተመ ሲሆን በመጀመሪያው እትሙ ላይ ባወጣው ትችት አዘል መቅድም ፋንታ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን የሚያበረታታ ቀለል ያለ የመግቢያ ሐሳብ ብቻ እንዲሰፍር አደረገ። ይህ እትም በሰፊው የተሰራጨ ሲሆን ፓትሪያርኩ ያስነሱት ተቃውሞ እንደነበር የሚገልጽ መረጃም አናገኝም።

የሆነ ሆኖ በ1714 መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎሙን ይቃወም ከነበረ አሌክሳንደር ሄላዲየስ ከተባለ ግሪካዊ ተጓዥ አስደንጋጭ ውርጅብኝ ደረሰበት። ይህ ሰው ስታቱስ ፕረኽዘንስ ኤክሌዝያ ግራካ (የግሪክ ቤተ ክርስቲያን አሁን ያለችበት ሁኔታ) በተባለው መጽሐፉ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቹንም ሆነ ተርጓሚዎቹን ክፉኛ ነቅፏል። ሄላዲየስ ስለ ሴራፊም አንድ ምዕራፍ ሙሉ የጻፈ ሲሆን ሴራፊምን ቀማኛ፣ አጭበርባሪ እንዲሁም መሃይምና ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል። እነዚህ ክሶች እውነት ነበሩ? ደራሲ የሆኑት ስቲሊያኖስ ባይራክታሪስ፣ ሴራፊም በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ይልቅ አስተሳሰቡ የመጠቀ በመሆኑ ለጥቃት የተዳረገ ‘ታታሪ ሠራተኛና ፈር ቀዳጅ የሆነ ታላቅ ምሑር’ እንደነበረ በመግለጽ ከሌሎች በርካታ ምሑራን አስተሳሰብ ጋር የሚመሳሰል አስተያየት ሰንዝረዋል። ያም ሆኖ የሄላዲየስ መጽሐፍ ለሴራፊም አስከፊ መጨረሻ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የጥርጣሬ ደመና አጠላበት

በ1731 ሴራፊም ወደ ሩሲያ ሲመለስ ታላቁ ፒተር ሞቶ ነበር። በመሆኑም ይህ ግሪካዊ ዲያቆን የባለ ሥልጣናቱን ከለላ ማግኘት አልቻለም። በወቅቱ እቴጌ የነበረችው አና ኢቫኖቭና ግዛቷን ሊያናጋ የሚችል ማንኛውንም እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ትመለከት ነበር። በጥር 1732 አንድ የግሪክ ሰላይ መንግሥትን የሚጻረር ነገር በማድረግ ላይ መሆኑን የሚገልጽ ወሬ በሴይንት ፒተርስበርግ ተናፈሰ። ተጠርጣሪው ሴራፊም ነበር። በመሆኑም ታሰረና ለምርመራ ወደ ኔቭስኪ ገዳም ተላከ። ገዳሙ ውስጥ ሄላዲየስ ሴራፊምን በተለያዩ ወንጀሎች የከሰሰበት መጽሐፍ ይገኝ ነበር። ዲያቆኑ የቀረበበትን ውንጀላ ለማስተባበል የመከላከያ ሐሳቡን ሦስት ጊዜ በጽሑፍ አቀረበ። ምርመራው ለአምስት ወራት የቀጠለ ሲሆን በእርሱ ላይ ያጠላውን የጥርጣሬ ደመና መግፈፍ ቀላል አልነበረም።

ሊያስቀጣው የሚችል ምንም ተጨባጭ መረጃ ሊቀርብበት ባለመቻሉ ከሞት ቅጣት ሊተርፍ ቻለ። ይሁንና በሄላዲየስ ውንጀላ ሳቢያ ባለ ሥልጣናቱ ሴራፊምን በነጻ ሊያሰናብቱት አልፈለጉም። ስለዚህ ይህ ግሪካዊ ዲያቆን ሕይወቱን በሙሉ በሳይቤሪያ በግዞት እንዲያሳልፍ ተበየነበት። በሴራፊም ላይ የተበየነው ፍርድ እንደሚገልጸው ውሳኔው የተላለፈው “በግሪኩ ጸሐፊ በሄላዲየስ በታተመው መጽሐፍ” ላይ የተሰነዘረበትን ክስ መሠረት በማድረግ ነው። ይህም በመሆኑ ሴራፊም፣ ሐምሌ 1732 በእግር ብረት ታስሮ ምሥራቅ ሳይቤሪያ ደረሰ፤ ከዚያም አስከፊ በሆነው በኧኮተስክ እስር ቤት ተጣለ።

ጠያቂና አስታዋሽ ያጣው ሴራፊም ከሦስት ዓመት በኋላ በሞት አንቀላፋ። ያደረጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎችና የተጠቀመባቸው ዘዴዎች የተሳሳቱና ጥበብ የጎደላቸው ቢሆኑም ለሕትመት ያበቃው ትርጉም ግን በዘመናዊ ግሪክኛ ከተዘጋጁት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል። a ለመረዳት ቀላል የሆነው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ከእነዚህ ዘመናዊ የግሪክኛ ትርጉሞች መካከል የሚመደብ ሲሆን በሌሎች ቋንቋዎችም ይገኛል። ይሖዋ አምላክ በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች “እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” ለማድረግ ሲል ቃሉን እስከ ዘመናችን ጠብቆ ስላቆየልን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል!—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ግሪክኛ ለማዘጋጀት የተደረገ ተጋድሎ” የሚል ርዕስ ያለውን የኅዳር 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 26-29 ተመልከት።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታላቁ ፒተር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፎቶግራፎቹ:- Courtesy American Bible Society