በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው’

‘ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው’

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!”

‘ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው’

ተቀናቃኝ የሆኑ ሁለት ብሔራት ሠራዊቶቻቸውን ከሸለቆው ወዲያና ወዲህ አስፍረው ለውጊያ ተዘጋጅተዋል። የፍልስጥኤማውያን ጀግና የሆነው ጎልያድ ለ40 ቀናት ያህል በእስራኤላውያን ላይ የስድብ ውርጅብኝ ሲያዘንብባቸው ስለቆየ ወታደሮቹ በፍርሃት ርደዋል።—1 ሳሙኤል 17:1-4, 16

ጎልያድ እስራኤላውያንን በመገዳደር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አላቸው:- “አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤ ከእኔ ጋር ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፣ እኛ ባሪያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባሪያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ። . . . ዛሬ የእስራኤልን ሰራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ።”—1 ሳሙኤል 17:8-10

በጥንት ዘመን የነበሩ ጀግኖች ሠራዊታቸውን በመወከል በተቃራኒው ወገን ከሚገኝ ሰው ጋር አንድ ለአንድ መጋጠማቸው የተለመደ ነበር። ያሸነፈው ሰው ሠራዊት ድል ይጎናጸፋል። ሆኖም እስራኤላውያንን የሚገዳደረው ጦረኛ ተራ ወታደር አይደለም። ይህ ወታደር በጣም ግዙፍና ክፉ የሆነ አስፈሪ ጠላት ነው። ይሁን እንጂ ጎልያድ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ሲዘባበት በራሱ ላይ መፍረዱ ነበር።

ይህ ግጥሚያ በሁለቱ ሠራዊቶች መካከል የሚደረግ ተራ ውጊያ አይደለም። ውጊያው በይሖዋና በፍልስጥኤማውያን አማልክት መካከል የሚደረግ ነው። የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል የአምላክን ጠላቶች ለመውጋት ሠራዊቱን በድፍረት ከመምራት ይልቅ በፍርሃት ተሽመድምዷል።—1 ሳሙኤል 17:11

አንድ ወጣት በይሖዋ ታመነ

በዚህ ፍጥጫ ወቅት፣ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን አስቀድሞ የተቀባ አንድ ወጣት ወንድሞቹን ለማየት ወደ ሳኦል ሠራዊት መጣ። ይህ ወጣት ዳዊት ይባላል። ወጣቱ፣ ጎልያድ የተናገረውን ከሰማ በኋላ “‘የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?’ ሲል ጠየቀ።” (1 ሳሙኤል 17:26) በዳዊት አመለካከት ጎልያድ ፍልስጥኤማውያንንና አማልክቶቻቸውን ይወክላል። የጽድቅ ቁጣ ያደረበት ዳዊት፣ ጎልያድ በይሖዋና በእስራኤላውያን ላይ የሰነዘረውን ነቀፋ ለማስወገድና ይህን ግዙፍ አረማዊ ለመዋጋት ተነሳ። ሆኖም ንጉሥ ሳኦል “አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፣ . . . ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው።—1 ሳሙኤል 17:33

የሳኦልና የዳዊት አመለካከት ምን ያህል እንደሚለያይ ማየት ይቻላል! በሳኦል ዓይን እረኛው ዳዊት ግዙፍ ከሆነው ፍልስጥኤማዊ ጋር ለመዋጋት የተነሳ አንድ ፍሬ ልጅ ነበር። ዳዊት ግን ጎልያድን የተመለከተው ሉዓላዊ ጌታ የሆነውን ይሖዋን የሚገዳደር ተራ ሰው አድርጎ ነው። ዳዊት ደፋር ሊሆን የቻለው አምላክ በስሙም ሆነ በሕዝቦቹ ላይ የሚሳለቅን ሰው ያለ ቅጣት እንደማይተወው እርግጠኛ ስለነበረ ነው። ጎልያድ በራሱ ኃይል ሲመካ ዳዊት ግን ሁኔታውን በአምላክ ዓይን በማየት በይሖዋ ተማምኗል።

“እኔ ግን . . . ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ”

የዳዊት እምነት ጠንካራ መሠረት ነበረው። በጎቹን ከድብና ከአንበሳ ለማዳን አምላክ እንዴት እንደረዳው አስታውሷል። ወጣቱ እረኛ ይህን አስፈሪ ፍልስጥኤማዊ ጠላት ሲገጥም ይሖዋ እንደሚረዳው እርግጠኛ ነበር። (1 ሳሙኤል 17:34-37) ዳዊት ከጎልያድ ጋር ለመዋጋት ወንጭፍና አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ብቻ ይዞ ሄደ።

ወጣቱ ዳዊት ከጎልያድ ጋር መዋጋት የሚችል ባይመስልም እንኳ ይሖዋ በሚሰጠው ጥንካሬ በመታመን ይህን ግዙፍ ሰው ለመፋለም ወሰነ። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን በድፍረት እንዲህ ብሎ ተናገረው:- “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፣ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት አምላክ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ . . . ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአብሔር [ነው]።”—1 ሳሙኤል 17:45-47

ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም።” (1 ሳሙኤል 17:50) ዳዊት በእጁ ሰይፍ ባይዝም ኃያል የሆነው የይሖዋ አምላክ ድጋፍ ነበረው። a

ዳዊት በይሖዋ መታመኑ ተገቢ እንደነበር በውጊያው ላይ ታይቷል! ሰውን በመፍራትና በይሖዋ የማዳን ኃይል በመታመን መካከል ምርጫ እንድናደርግ የሚያስገድደን ሁኔታ ሲያጋጥመን ‘ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ እንደሚገባ’ ግልጽ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) ከዚህም በተጨማሪ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችንም እንኳ በይሖዋ አምላክ ዓይን ከተመለከትናቸው ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ እንችላለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ግንቦት/ሰኔ የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ጎልያድ ምን ያህል ግዙፍ ነበር?

በ1 ሳሙኤል 17:4-7 ላይ የሚገኘው ዘገባ ጎልያድ ቁመቱ ከዘጠኝ ጫማ በላይ ማለትም 3 ሜትር ገደማ እንደነበር ይነግረናል። ሃምሳ ሰባት ኪሎ ግራም የሚመዝን የናስ ጥሩር መልበሱ ጎልያድ ምን ያህል ግዙፍና ጠንካራ እንደነበር ያሳያል! የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ወፍራም ሲሆን የጦሩም ብረት 7 ኪሎ ግራም ይመዝን ነበር። በጣም የሚገርመው ነገር የጎልያድ የጦር ትጥቅ ከራሱ ከዳዊት የሚበልጥ ክብደት የነበረው መሆኑ ነው!