በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በድፍረት’ የመናገር ችሎታ አለህ?

‘በድፍረት’ የመናገር ችሎታ አለህ?

‘በድፍረት’ የመናገር ችሎታ አለህ?

በ235 አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ዓይነት ‘በድፍረት’ የመናገር ችሎታ አላቸው። (ፊልጵስዩስ 1:20፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:13፤ ዕብራውያን 3:6 የ1954 ትርጉም፤ 1 ዮሐንስ 3:21) ‘በድፍረት’ የመናገር ችሎታ ምን ያመለክታል? ይህን ችሎታ ለማዳበርስ ምን ሊረዳን ይችላል? ይህ ችሎታ በየትኞቹ መስኮች በድፍረትና በግልጽነት እንድንናገር ይረዳናል?

በቫይን በተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ መሠረት ‘በድፍረት’ መናገር ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የመናገር ነፃነት፣ ያለ ገደብ መናገር፣ . . . ያለፍርሃት መናገር እንዲሁም ከንግግር ጋር የተያያዘ ባይሆንም እንኳ ልበ ሙሉ፣ ፍርሃት የለሽ እና ደፋር መሆን” ማለት ነው። ሆኖም በግልጽ መናገር ሲባል ሥርዓት በሌለው መንገድ ወይም እንደፈለጉ መናገር ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ንግግራችሁ . . . ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን” ይላል። (ቈላስይስ 4:6) በድፍረት መናገር፣ የሰው ፍርሃት ወይም የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሳያግዱን በዘዴ ሐሳባችንን መግለጽን ያመለክታል።

በድፍረት መናገር በተፈጥሮ የምናገኘው መብት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙት ክርስቲያኖች የጻፈውን እንመልከት። እንዲህ ብሏል:- “ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ።” ጳውሎስ በመቀጠልም ይህ መብት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያገኘነው እንደሆነ ሲገልጽ “በእርሱ ላይ ባለን እምነት አማካይነት፣ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን” በማለት ተናግሯል። (ኤፌሶን 3:8-12) በድፍረት መናገር በተፈጥሮ የተሰጠን መብት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናችን ምክንያት ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትነው ዝምድና ያስገኘልን ችሎታ ነው። ድፍረት ለማግኘት ምን ሊረዳን እንደሚችል እንዲሁም ስንሰብክ፣ ስናስተምርና ስንጸልይ ይህን ችሎታ እንዴት ማሳየት እንደምንችል እንመልከት።

በድፍረት ለመስበክ ምን ሊረዳን ይችላል?

ኢየሱስ ክርስቶስ በድፍረት በመስበክ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ምሳሌ ነው። የነበረው ቅንዓት ለመስበክ የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች እንዲጠቀምባቸው አድርጎታል። በሚያርፍበትም ሆነ ተጋብዞ በሚመገብበት ወይም በሚጓዝበት ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት ለመናገር የሚያስችለውን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀም ነበር። ኢየሱስ ፌዝና ቀጥተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም ፈርቶ ዝም አላለም። ከዚህ ይልቅ በጊዜው የነበሩትን የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች በድፍረት አጋልጧል። (ማቴዎስ 23:13-36) ኢየሱስ ተይዞ ለፍርድ በቀረበበት ጊዜም እንኳ ያለ ፍርሃት ተናግሯል።—ዮሐንስ 18:6, 19, 20, 37

የኢየሱስ ሐዋርያትም ልክ እንደ ኢየሱስ በግልጽና በድፍረት የመናገር ችሎታን አዳብረዋል። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት ጴጥሮስ 3,000 የሚሆኑ ሰዎች በተሰበሰቡበት በድፍረት ተናግሯል። የሚያስገርመው ጴጥሮስ ቀደም ብሎ አንዲት አገልጋይ ባወቀችው ጊዜ በፍርሃት ተውጦ ነበር። (ማርቆስ 14:66-71፤ የሐዋርያት ሥራ 2:14, 29, 41) ጴጥሮስና ዮሐንስ በሃይማኖት መሪዎች ፊት በቀረቡ ጊዜ በፍርሃት አልራዱም። ምንም ሳያመነቱ ከሞት ስለተነሳው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በድፍረት መሥክረዋል። እንዲያውም የሃይማኖት መሪዎቹ ጴጥሮስና ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩ ማወቅ የቻሉት በግልጽና በድፍረት በመናገራቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 4:5-13) ታዲያ በድፍረት መናገር እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው?

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ በማለት ቃል ገብቶላቸው ነበር:- “በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤ በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁም።” (ማቴዎስ 10:19, 20) ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በድፍረት እንዳይናገሩ ሊያደርጓቸው የሚችሉትን እንደ ዓይን አፋርነት ወይም ፍርሃት የመሳሰሉትን ባሕርያት ለማስወገድ መንፈስ ቅዱስ ረድቷቸዋል። ይህ ኃይል እኛንም ሊረዳን ይችላል።

ከዚህም በተጨማሪ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ተልእኮ ለተከታዮቹ የሰጣቸው ኢየሱስ ነበር። ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” የተሰጠው በመሆኑ ይህን ተልእኮ መስጠቱ ተገቢ ነው። እንዲሁም ለደቀ መዛሙርቱ ቃል እንደገባው ‘ከእነሱ ጋር ነው።’ (ማቴዎስ 28:18-20) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የኢየሱስን ድጋፍ እንደሚያገኙ መገንዘባቸው፣ ባለ ሥልጣናት የስብከት ሥራቸውን ለማገድ በሚሞክሩበት ጊዜ ልበ ሙሉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 4:18-20፤ 5:28, 29) ኢየሱስ እንደሚደግፈን ማወቃችን በእኛም ላይ ተመሳሳይ ውጤት ሊኖረው ይችላል።

ጳውሎስ ተስፋን ‘ከድፍረት’ ጋር በማያያዝ በግልጽ ለመናገር የሚረዳንን ሌላ ነጥብ ጠቁሟል። (2 ቆሮንቶስ 3:12፤ ፊልጵስዩስ 1:20) ተስፋው እጅግ ግሩም በመሆኑና ክርስቲያኖችም ሰምተው ዝም ማለት ስላልቻሉ ለሌሎች ይናገራሉ። እውነትም ተስፋችን በድፍረት ለመናገር ምክንያት ይሆነናል።—ዕብራውያን 3:6 የ1954 ትርጉም

በድፍረት መስበክ

በሚያስፈሩ ሁኔታዎች ውስጥ እያለንም እንኳ በድፍረት መስበክ የምንችለው እንዴት ነው? የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። በሮም እስረኛ በነበረበት ወቅት የእምነት ባልደረቦቹን “አፌን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በድፍረት እንድናገር ቃል ይሰጠኝ ዘንድ” እንዲሁም “መናገር የሚገባኝን ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ” በማለት ጠይቋቸው ነበር። (ኤፌሶን 6:19, 20) ታዲያ እነዚህ ጸሎቶች መልስ አግኝተው ነበር? እንዴታ! ጳውሎስ ታስሮ እያለ “የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ . . . በፍጹም ግልጽነት ያስተምር ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 28:30, 31

በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ወይም በምንጓዝበት ወቅት አጋጣሚዎቹን ተጠቅመን ለመስበክ በምንሞክርበት ወቅት ድፍረታችን ይታያል። ዓይን አፋርነት፣ ሌሎች የሚሰጡንን መልስ መፍራት ወይም በችሎታችን አለመተማመን ዝም እንድንል ሊያደርጉን ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድም ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። “ብርቱ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን” በማለት ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 2:2) ጳውሎስ ከእርሱ ችሎታ በላይ የሆነውን ነገር ማድረግ የቻለው በራሱ አቅም ሳይሆን በይሖዋ በመታመኑ ነው።

ሼሪ የተባለች ክርስቲያን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ በሚፈጠርበት ጊዜ በድፍረት እንድትናገር የረዳት ጸሎት ነው። አንድ ቀን ባለቤቷን እየጠበቀች ሳለ ሌላ ሴት እንዲሁ ሰው ስትጠብቅ ተመለከተች። “በጣም ፈርቼ ስለነበር ድፍረት እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ” በማለት ሼሪ ትናገራለች። ሼሪም ወደ ሴትየዋ እየሄደች ሳለ አንድ የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ቄስ መጣ። ሼሪ ቄስ ያጋጥመኛል ብላ አላሰበችም ነበር። ሆኖም እንደገና በመጸለይ ለመመሥከር ችላለች። ለሴትየዋ ጽሑፍ ያበረከተችላት ከመሆኑም በላይ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ቀጠሮ ያዘች። ምሥክርነት ለመስጠት በሚያስችሉን አጋጣሚዎች በምንጠቀምበት ጊዜ በይሖዋ ከታመንን በድፍረት ልንናገር እንደምንችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

በምናስተምርበት ጊዜ በድፍረት መናገር

በድፍረት መናገር ከማስተማር ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። በጉባኤ ውስጥ ‘በአግባቡ የሚያገለግሉ’ ወንዶችን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ለራሳቸው ትልቅ ክብርን፣ በክርስቶስ ኢየሱስም ባላቸው እምነት ብዙ ድፍረትን ያገኛሉ” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 3:13) ለሌሎች የሚያስተምሩትን ነገር ራሳቸው የሚሠሩበት ከሆነ ለመናገር ድፍረት ይኖራቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ለጉባኤው ጥበቃና ማበረታቻ ይሆናል።

የምናስተምረውን ትምህርት በሥራ ማዋላችን ሌሎችን ለመምከር ድፍረት የሚሰጠን ሲሆን ይህም ምክሩ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ያደርጋል። አድማጮች፣ ተናጋሪው በሥራ ላይ ያላዋለውን ነገር እያስተማረ ነው በማለት ስለ እርሱ ከማሰብ ይልቅ እየተማሩት ያለውን ነገር እንደሚሠራበት ማወቃቸው ያበረታታቸዋል። ይህ ዓይነቱ የመናገር ድፍረት መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንድሞች የእምነት ባልንጀራቸው ከባድ ችግር ውስጥ ከመግባቱ በፊት ‘እንዲመለስ’ ለመርዳት ያስችላቸዋል። (ገላትያ 6:1) ከዚህ በተቃራኒ ግን ጥሩ ምሳሌ የማይሆን ሰው ምክር ለመስጠት መብት እንደሌለው ሆኖ ሊሰማው ይችላል። አስፈላጊውን ምክር ከመስጠት መዘግየቱ ደግሞ በወንድሞቹ ላይ የከፋ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።

በድፍረት መናገር ሲባል በሌሎች ላይ የምንፈርድ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለን ድርቅ የምንል ወይም ሐሳበ ግትር መሆን ማለት አይደለም። ጳውሎስ ፊልሞናን “በፍቅር” መክሮታል። (ፊልሞና 8, 9) በመሆኑም የሐዋርያው ቃላት መልካም ውጤት ሳያስገኝ አልቀረም። ሽማግሌዎች ማንኛውንም ምክር የሚሰጡት በፍቅር ተገፋፍተው መሆን አለበት!

ምክር በሚሰጥበት ጊዜም በድፍረትና በግልጽነት የመናገር ችሎታ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። በሌሎች ጊዜያትም ይህ ችሎታ ያስፈልጋል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኘው ጉባኤ “[“እናንተን በግልጽ ማናገር ምንም አይከብደኝም፤” NW] በእናንተም ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 7:4) ጳውሎስ ወንድሞቹንና እህቶቹን አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ከማመስገን ወደኋላ አላለም። የእምነት ባልንጀሮቹ ጉድለት እንዳለባቸው ቢያውቅም ለእነርሱ የነበረው ፍቅር መልካም ጎናቸው ላይ እንዲያተኩር አስችሎታል። በዛሬው ጊዜ ባለው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ከልብ ሲያመሰግኗቸውና ሲያበረታቷቸው ይታነጻሉ።

ሁሉም ክርስቲያኖች በማስተማሩ ሥራ የተዋጣላቸው እንዲሆኑ በድፍረት የመናገር ችሎታ ያስፈልጋቸዋል። ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ሼሪ ልጆቿ ትምህርት ቤት ውስጥ መመሥከር እንዲችሉ ለማበረታታት ፈለገች። እንዲህ ትላለች:- “በእውነት ውስጥ ያደግኩ ብሆንም ትምህርት ቤት ውስጥ መሥክሬ አላውቅም። መደበኛ ባልሆነ መንገድ የምመሠክረውም አልፎ አልፎ ነበር። በመሆኑም ‘ለልጆቼ ምን ዓይነት ምሳሌ እሆናቸዋለሁ?’ በማለት ራሴን ጠየቅሁ።” ይህ ደግሞ ሼሪ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ከፍተኛ ጥረት እንድታደርግ አስችሏታል።

አዎን፣ ሌሎች የምናደርገውን ነገር የሚያስተውሉ ሲሆን የምናስተምረውን ነገር በሥራ ላይ ሳናውል ስንቀርም ይመለከቱናል። እንግዲያው ተግባራችን ከምንናገረው ነገር ጋር የሚጣጣም እንዲሆን በማድረግ በድፍረት የመናገር ችሎታን ለማዳበር እንጣር።

ሳንሸማቀቅ መጸለይ

በተለይ ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ሳንሸማቀቅ ሐሳባችንን መግለጽ አስፈላጊ ነው። ጸሎቶቻችንን ሰምቶ እንደሚመልስልን እርግጠኞች በመሆን ያለ ምንም ገደብ የልባችንን አውጥተን መናገር እንችላለን። እንዲህ ካደረግን በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ጋር ሞቅ ያለና የተቀራረበ ዝምድና ይኖረናል። የማንረባ እንደሆንን ተሰምቶን ወደ ይሖዋ ከመቅረብ ፈጽሞ ወደኋላ ማለት የለብንም። ስህተት ወይም ኃጢአት በመሥራታችን ምክንያት ያደረብን የጥፋተኝነት ስሜት በልባችን ውስጥ ያለውን አውጥተን እንዳንናገር ቢያግደን ምን ማድረግ እንችላለን? በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳ የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ በነጻነት ማነጋገር እንችላለን?

ኢየሱስ ሊቀ ካህን ሆኖ ከፍተኛ ቦታ መያዙ በጸሎት ላይ ያለንን እምነት ያጠነክርልናል። ዕብራውያን 4:15, 16 እንዲህ ይላል:- “በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት [“ሳንሸማቀቅ፣” NW] እንቅረብ።” የኢየሱስ ሞትና ሊቀ ካህን ሆኖ የሚጫወተው ሚና ይህን የመሰለ ጥቅም አስገኝቶልናል።

ይሖዋን ለመታዘዝ ከልብ የምንጥር ከሆነ ጸሎታችንን ሰምቶ ምላሽ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ወዳጆች ሆይ፤ ልባችን የማይፈርድብን ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ድፍረት አለን፤ ትእዛዛቱንም ስለምንጠብቅና በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን ስለምናደርግ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እንቀበላለን።”—1 ዮሐንስ 3:21, 22

በጸሎት አማካኝነት ያለ ምንም ገደብ ወደ ይሖዋ መቅረብ ሲባል ማንኛውንም ነገር መንገር ማለት ነው። ያደረብንን ፍራቻ እንዲሁም የሚያሳስቡንን፣ የሚያሰጉንን ወይም የሚያስጨንቁንን ነገሮች ለይሖዋ ስንነግረው ልባዊ ጸሎታችንን ሁልጊዜ እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከባድ ኃጢአት ብንሠራ እንኳ ከልባችን ንስሐ እስከገባን ድረስ የጥፋተኝነት ስሜት ጸሎታችንን ሊገድብብን አይገባም።

በእርግጥም በድፍረትና በግልጽነት የመናገር ችሎታ፣ ይገባናል የማንለውና ውድ የሆነ የይሖዋ ስጦታ ነው። በዚህ ችሎታ በመጠቀም በስብከቱም ሆነ በማስተማሩ ሥራ ለአምላክ ክብር ማምጣት እንችላለን፤ እንዲሁም በጸሎት አማካኝነት ሳንሸማቀቅ ይበልጥ ወደ እርሱ መቅረብ እንችላለን። እንግዲያው “ታላቅ ብድራት” ይኸውም የዘላለም ሕይወት ሽልማት ‘ያለውን ድፍረታችንን አንጣል።’—ዕብራውያን 10:35 የ1954 ትርጉም

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዋርያው ጳውሎስ በድፍረት ተናግሯል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር በድፍረት የመናገር ችሎታ ያስፈልጋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ሳንሸማቀቅ ሐሳባችንን መግለጽ አስፈላጊ ነው