በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል

አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ ሳሉ አምላክ የሚከተለውን ኃላፊነት ሰጥቷቸው ነበር:- “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው።”—ዘፍጥረት 1:28

ምድርን መግዛት ሲባል የምድርን የተወሰነ ክፍል ማልማት ወይም መንከባከብ ማለት አልነበረም። አዳምና ሔዋን እንዲሁም ልጆቻቸው መላዋን ምድር ገነት ማድረግ ነበረባቸው። ይሁንና የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ኃጢአት በመሥራታቸው ከኤደን የአትክልት ስፍራ ተባረሩ። (ዘፍጥረት 3:23, 24) ይህ ማለት ግን ምድር መቼም ቢሆን በሰዎች አትገዛም ማለት አልነበረም።

ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች አምላክ ስለሚባርካቸው ምድርን መግዛት ይችላሉ። የጥንቶቹን እስራኤላውያን አምላክ ሲባርካቸው መስኮቻቸው በሰብል ይሸፈኑና ዛፎቻቸውም ጣፋጭ በሆኑ ፍራፍሬዎች ይሞሉ ነበር። ምድራችን ቀስ በቀስ ወደ ገነትነት ስትለወጥ ተመሳሳይ ሁኔታ ይኖራል። አምላክ፣ በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ምድር ፍሬዋን እንደምትሰጥና እግዚአብሔር አምላካችንም እንደሚባርከን’ ተስፋ ይሰጠናል። (መዝሙር 67:6) በመሆኑም መስኩና ተራራው፣ ዛፎችና አበቦች እንዲሁም ወንዞችና ባሕሩ ደስ ይላቸዋል። (መዝሙር 96:11-13፤ 98:7-9) ምድራችን በለመለመ ሣር ቅጠል፣ በኅብረ ቀለማት ባጌጡ አእዋፍ፣ በአስደናቂ እንስሳትና አፍቃሪ በሆኑ ሰዎች ትሞላለች።

በቅርቡ አዲስ ዓለም ይመጣል!

አሁን ይሖዋ አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ደፍ ላይ ደርሰናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:13) አንዳንዶች የጴጥሮስን ቃላት ሲያነቡ ይህቺ ምድር መቼም ቢሆን ገነት ልትሆን አትችልም የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሱ ይሆናል። ግዑዝ የሆኑት ሰማይና ምድር በሌላ ይተካሉ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በእርግጥ ሁኔታው እንዲህ ነው?

“አዲስ ሰማይ” የተባለው ምንድን ነው? ይህ አባባል አምላክ የፈጠረውን ግዑዝ ሰማይ አያመለክትም። (መዝሙር 19:1, 2) ጴጥሮስ ቀደም ባሉት ቁጥሮች ላይ ስለ ምሳሌያዊው “ሰማይ” ማለትም በተገዥዎቻቸው ላይ ከፍ ከፍ ስላሉት ሰብዓዊ መንግሥታት ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 3:10-12) ይህ “ሰማይ” የሰው ልጆችን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር አልቻለም፤ በመሆኑም ከቦታው ይወገዳል። (ኤርምያስ 10:23፤ ዳንኤል 2:44) እርሱን የሚተካው “አዲስ ሰማይ” ንጉሥ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስና ከሞት ተነስተው በሰማይ ሕይወት በሚያገኙት 144,000 ተባባሪ ገዥዎቹ የተገነባው የአምላክ መንግሥት ነው።—ሮሜ 8:16, 17፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3

ጴጥሮስ የጠቀሰው “አዲስ ምድር” አዲስ ፕላኔት አይደለም። ይሖዋ መሬትን የሰው ልጆች ለዘላለም እንዲኖሩባት አድርጎ ያለ አንዳች እንከን ፈጥሯታል። (መዝሙር 104:5) አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር” የሚለውን ቃል ሰዎችን ለማመልከት ይጠቀምበታል። (ዘፍጥረት 11:1 የ1954 ትርጉም) በቅርቡ የሚጠፋው ምድር የዚህ ክፉ ዓለም ክፍል የሆኑትን ሰዎች የያዘው ሥርዓት ነው። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ በኖኅ የጥፋት ውኃ ጊዜ የነበረውና አምላክን የማይፈሩ ሰዎችን ያቀፈው ዓለም ጥፋት ደርሶበታል። (2 ጴጥሮስ 3:5-7) ታዲያ “አዲስ ምድር” የተባለው ምንድን ነው? ይህ ምድር ‘ቀና ልብ’ ባላቸው እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች የሚገነባውን አዲስ ኅብረተሰብ ያመለክታል። (መዝሙር 125:4፤ 1 ዮሐንስ 2:17) ‘አዲሱ ምድር’ የሚተዳደርበት ማንኛውም ሕግ የሚመጣው ‘ከአዲሱ ሰማይ’ ይሆናል። በምድር ላይ ያሉ ታማኝ የሆኑ ሰዎች እነዚህ ሕጎች በተግባር ላይ እንዲውሉ ያደርጋሉ።

አዳዲስና አስደናቂ ለውጦች ይኖራሉ!

ይሖዋ ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያነት ሲያዘጋጅ በጣም ግሩም አድርጎ እንደሠራት አያጠራጥርም። ይሖዋ ራሱ በምድር ላይ የፈጠራቸው ነገሮች “እጅግ መልካም” እንደነበሩ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:31) ይሁንና ሰይጣን ዲያብሎስ አዳምና ሔዋን እንዲያምጹ አደረጋቸው። (ዘፍጥረት 3:1-5፤ ራእይ 12:9) ያም ሆኖ አምላክ በቅርቡ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” እንዲወርሱ ያደርጋል። ይህም ፍጹም በሆነች ገነት ውስጥ የሚያገኙት “የዘላለም ሕይወት” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19) በዚያን ጊዜ የሰው ልጆች ከሚያገኟቸው አስደሳች በረከቶች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ሰይጣን ይታሰራል እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ ወዮታ ማምጣቱን ያቆማል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው ብሏል:- “የጥልቁን መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ [የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ] ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። እርሱም የጥንቱን እባብ፣ ዘንዶውን፣ ማለትም ዲያብሎስን ወይም ሰይጣንን ይዞ ሺህ ዓመት አሰረው። ሺሁ ዓመትም እስኪፈጸምም ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቦችን እንዳያስት ወደ ጥልቁ ጣለው፤ ዘጋውም፤ በእርሱም ላይ ማኀተም አደረገበት።” (ራእይ 20:1-3፤ 12:12) ሰይጣን ወደ ጥልቁ በመጣሉ የሰው ልጆች እርሱ ከሚያደርስባቸው ተጽዕኖ ከመላቀቃቸውም በላይ በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ ሌሎች ተጨማሪ በረከቶችንም ያገኛሉ።

ክፋት፣ ዓመጽና ጦርነት ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:10, 11, 29) ይሖዋ አምላክ “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል።” (መዝሙር 46:9) ወደፊት ሰላምና ደኅንነት እንደሚሰፍን የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ማረጋገጫ ነው!

ለጤንነት ተስማሚ የሆነና ጣፋጭ ምግብ እንደ ልብ ይኖራል። መዝሙራዊው “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 72:16) በዚያን ጊዜ ተርቦ በጠኔ የሚሠቃይ ሰው አይኖርም።

በሕመምና በበሽታ የሚሠቃይ ሰው አይኖርም። በእርግጥም በዚያ “ተቀምጦ፣ ‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6) ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ ሳለ ለምጽ የያዛቸውን፣ አካል ጉዳተኞችንና ማየት የተሳናቸውን ፈውሷል። (ማቴዎስ 9:35፤ ማርቆስ 1:40-42፤ ዮሐንስ 5:5-9) በአዲሱ ዓለም ደግሞ ምን ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ትችላለህ! ማየት ወይም መስማት የተሳናቸው፣ የአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ዲዳዎች ፍጹም ጤናማ ሲሆኑ ምን ያህል እንደሚደሰቱ አስበው።

ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እየቀረቡ ሲሄዱ የዕድሜ መግፋት የሚያስከትለው ጎጂ ተጽዕኖም ይወገዳል። በዚያን ጊዜ መነጽር፣ ዘንግ፣ ምርኩዝ፣ ተሽከርካሪ ወንበር፣ ሆስፒታሎች እንዲሁም መድኃኒቶች አያስፈልጉም። ሰውነታችን ታድሶ እንደገና ወጣት ስንሆን ሁኔታዎች ምን ያህል የተለዩ ይሆናሉ! (ኢዮብ 33:25) ጠዋት ጠዋት መንፈሳችን ታድሶና የሚያስደስተንን ነገር ለመሥራት ተዘጋጅተን ከመኝታችን እንነሳለን።

የቅርብ ዘመዶቻችንን ጨምሮ ብዙዎች ከሞት ሲነሱ ስንመለከት ልባችን በደስታ ይሞላል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) አቤልን፣ ኖኅን፣ አብርሃምን፣ ሣራን፣ ኢዮብን፣ ሙሴን፣ ሩትን፣ ዳዊትን፣ ኤልያስንና አስቴርን የመሳሰሉ በርካታ ሰዎች ከሞት ሲነሱ መመልከት እንዴት ያስደስታል! በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም ከሞት ይነሳሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ይሖዋን የማያውቁ ቢሆኑም ከሞት ሲነሱ የሚቀበሏቸው ሰዎች ስለ አምላክ ማንነት፣ ስለ ዓላማዎቹና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በደስታ ያስተምሯቸዋል። ከሞት የተነሱት ሰዎች ፈጣሪያቸው ማን መሆኑን ሲያውቁ ምድር ይሖዋን በማወቅ ትሞላለች።

ከሁሉም በላይ ደግሞ እውነተኛውን አንድ አምላክ ለዘላለም ማምለክ እንችላለን። ‘እግዚአብሔርን በደስታ የማገልገል’ መብት እናገኛለን፤ በተጨማሪም በኅብረት ሆነን የሚያምሩ ቤቶችን እንሠራለን፣ ምድርን እናለማለን እንዲሁም ውሎ አድሮ መላዋን ምድር እንገዛለን። (መዝሙር 100:1-3፤ ኢሳይያስ 65:21-24) ልምላሜ በተላበሰና ሰላም በሰፈነበት ውብ ገነት ውስጥ ቅዱስ የሆነውን የይሖዋን ስም በሚያስከብር መልኩ ለዘላለም መኖር ምንኛ ያስደስታል!—መዝሙር 145:21፤ ዮሐንስ 17:3

የሰው ልጆች የመጨረሻ ፈተና ይቀርብላቸዋል

ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ከቤዛዊ መሥዋዕቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። ኃጢአት ቀስ በቀስ ይወገድና የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። (1 ዮሐንስ 2:2፤ ራእይ 21:1-4) የአዳም ኃጢአት ያስከተላቸው ተጽዕኖዎች ስለሚወገዱ የሰው ልጆች ፍጹም በመሆን በአካላዊ፣ በአእምሯዊ፣ በሥነ ምግባራዊና በመንፈሳዊ ሁኔታ አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ያሟላሉ። በመሆኑም ምንም ዓይነት ኃጢአት የሌለባቸው ፍጹም ሰዎች በመሆን ሙሉ በሙሉ ‘ከሞት ይነሳሉ።’ (ራእይ 20:5) እንዲህ ያለው ሁኔታና ምድር ገነት መሆኗ ለይሖዋ ምን ያህል ክብር ያስገኝለታል!

የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ካበቃ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ወይም ክፉ የሆኑት መላእክት ለሺህ ዓመት ተገልለው ከታሰሩበት ከጥልቁ ለአጭር ጊዜ ይፈታሉ። (ራእይ 20:1-3) ከዚያም የሰው ልጆችን ከአምላክ ማራቅ ይችሉ እንደሆነ እንዲሞክሩ የመጨረሻ ዕድል ይሰጣቸዋል። በዚህ ጊዜ አንዳንዶች በክፉ ምኞት ቢሸነፉም የሚነሳው ዓመጽ በቀላሉ ይከሽፋል። ይሖዋ በራስ ወዳድነት ያመጹትን ሰዎች ጨምሮ ሰይጣንንና አጋንንቱን ያጠፋቸዋል። ከዚህ በኋላ ክፋት የሚባል ነገር ጨርሶ አይኖርም። ክፉ አድራጊዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲጠፉ ጻድቃን ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።—ራእይ 20:7-10

አንተስ በዚያ ትገኝ ይሆን?

ይሖዋ አምላክን የሚወድዱ ሰዎች ዘላቂ ደስታ የማግኘት ተስፋ አላቸው። በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር አሰልቺ አይሆንም። የይሖዋ አምላክ እውቀት ገደብ ስለሌለው ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን በገነት ውስጥ መኖር ይበልጥ አስደሳች ይሆናል። (ሮሜ 11:33) ምንጊዜም የምትማረው አዲስ ነገር አታጣም፤ እንዲሁም ይህን እውቀት ለመቅሰም የሚያስችል በቂ ጊዜ ይኖርሃል። ለምን? ምክንያቱም የምትኖረው ለ70 ወይም ለ80 ዓመት ሳይሆን ለዘላለም ነው።—መዝሙር 22:26፤ 90:10፤ መክብብ 3:11

አምላክን የምትወደው ከሆነ ዘወትር ፈቃዱን በማድረግ ትደሰታለህ። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:3) ስለሆነም ማንኛውም ነገር ይሖዋ አምላክን ከማስደሰትና መልካም የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንድትል እንዲያደርግህ አትፍቀድ። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ግሩም ተስፋ አትዘንጋ። የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርግ እንዲሁም ፈጽሞ ከመንገዱ ፈቀቅ አትበል። እንዲህ ካደረግክ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ሲፈጸምና ምድራዊ መኖሪያችን ዘላለማዊ ገነት ስትሆን ለማየት ትበቃለህ።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን አምላክ ሲባርካቸው ከእርሻቸው የተትረፈረፈ ምርት ያገኙ ነበር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በገነት ውስጥ ምን በረከቶችን ማግኘት ትፈልጋለህ?