በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያለ ነቀፋ መኖር የሚያስገኘው ደስታ

ያለ ነቀፋ መኖር የሚያስገኘው ደስታ

ያለ ነቀፋ መኖር የሚያስገኘው ደስታ

“የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም።”—ምሳሌ 10:22

1, 2. ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ የማሰብ ዝንባሌን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?

 አንድ አሜሪካዊ ፈላስፋ “ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ ማሰብ . . . ዛሬን በአግባቡ እንዳናጣጥም ያደርገናል” በማለት ተናግሯል። ይህ አባባል፣ ትልቅ ሰው ሲሆኑ ሊያከናውኑ በሚችሉት ነገር ላይ በጣም ከማተኮራቸው የተነሳ የልጅነት ጊዜያቸው ሳያጣጥሙት በሚያልፍባቸው ልጆች ላይ በትክክል ይሠራል።

2 የይሖዋ አምላኪዎችም የዚህ ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል። እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ አስብ። አምላክ ምድርን ገነት እንደሚያደርጋት የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ለማየት እንጓጓለን። እንዲሁም ሕመም፣ እርጅና፣ ሥቃይና መከራ የሌለበትን ሕይወት በናፍቆት እንጠባበቃለን። እንደዚህ ያሉትን ነገሮች ለማግኘት መጓጓቱ ተገቢ ቢሆንም ወደፊት በምናገኛቸው ሥጋዊ በረከቶች ላይ ከሚገባው በላይ ትኩረት ከማድረጋችን የተነሳ በዛሬው ጊዜ ያገኘናቸውን መንፈሳዊ በረከቶች ማስተዋል ቢያቅተንስ? ይህ ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል! እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ካለን መጽሐፍ ቅዱስ “ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል” በማለት እንደሚናገረው፣ የጠበቅነው ነገር ካሰብነው በላይ በመዘግየቱ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። (ምሳሌ 13:12) ከዚህም በላይ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮች ስለ ራሳችን ከሚገባው በላይ የመጨነቅ ዝንባሌ እንዲኖረን ሊያደርጉን ይችላሉ። የሚያጋጥሙንን መጥፎ ሁኔታዎች ለመወጣት ከመጣር ይልቅ ማጉረምረም እንጀምራለን። በአሁኑ ጊዜ ባገኘናቸው በረከቶች ላይ የምናሰላስል ከሆነ ግን ይህንን ሁሉ ማስቀረት እንችላለን።

3. በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ በየትኛው ነጥብ ላይ ትኩረት እናደርጋለን?

3 ምሳሌ 10:22 “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” ይላል። በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ያገኙት መንፈሳዊ ብልጽግና እንድንደሰት የሚያደርግ በረከት አይደለም? እስቲ በመንፈሳዊ ያገኘነው ብልጽግና አንዳንድ ገጽታዎች በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም እንዳላቸው እንመልከት። ይሖዋ ‘ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ለሚመሩ ጻድቃን’ አትረፍርፎ በሰጣቸው በረከቶች ላይ ማሰላሰላችን በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን በደስታ ማገልገላችንን እንድንቀጥል አቋማችንን ያጠናክርልናል።—ምሳሌ 20:7

በአሁኑ ጊዜ ‘ብልጽግና ያመጡልን በረከቶች’

4, 5. አንተ በግልህ ከፍተኛ ቦታ የምትሰጠው ለየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው? ለምንስ?

4 ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አለን። በጥቅሉ ሲታይ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ረገድ እርስ በርስ አይስማሙም። ሌላው ቀርቶ የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት እንኳ ስለ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያላቸው አመለካከት አብዛኛውን ጊዜ የተለያየ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች ያሉበት ሁኔታ ከዚህ በጣም የተለየ ነው! በብሔር፣ በባሕል ወይም በጎሣ ብንለያይም ሁላችንም በስሙ የምናውቀውን እውነተኛውን አምላክ እናመልካለን። አምላካችን ምሥጢራዊ የሆነ ሥላሴ አይደለም። (ዘዳግም 6:4፤ መዝሙር 83:18 NW፤ ማርቆስ 12:29) ከዚህም በላይ ከአምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ትልቅ ጉዳይ በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኝና እኛም ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ለተነሳው ጥያቄ በግለሰብ ደረጃ መልስ መስጠት እንደምንችል እንገነዘባለን። በሞት ያንቀላፉትን ሰዎች በተመለከተ እውነቱን ስለምናውቅ አምላክ ሰዎችን በሲኦል እሳት ያቃጥላል ወይም ወደ መንጽሔ ይልካቸዋል የሚለው ትምህርት ፍርሃት አያሳድርብንም።—መክብብ 9:5, 10

5 ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ሕልውና የመጣነው በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት እንዳልሆነ ማወቁ ምንኛ ያስደስታል! ከዚህ በተቃራኒ በአምላክ አምሳል የተሠራን የእርሱ ፍጥረቶች እንደሆንን እንገነዘባለን። (ዘፍጥረት 1:26፤ ሚልክያስ 2:10) መዝሙራዊው እንዲህ በማለት አምላኩን አወድሷል:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።”—መዝሙር 139:14

6, 7. አንተም ሆንክ ሌሎች የምታውቃቸው ሰዎች በሕይወታችሁ ውስጥ ምን ለውጦች በማድረግ ተባርካችኋል?

6 ጎጂ ከሆኑ ልማዶችና ድርጊቶች ነጻ መሆን ችለናል። እንደ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ መጠጣት እንዲሁም ልቅ የሆነ የጾታ ግንኙነት መፈጸም የመሳሰሉት ድርጊቶች የሚያስከትሉትን አደጋ በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን ብዙ ሲባል ብንሰማም አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች እነዚህን ማሳሰቢያዎች በቸልታ ያልፏቸዋል። ይሁን እንጂ ቅን ልብ ያለው ሰው፣ እውነተኛው አምላክ እነዚህን ልማዶች እንደሚያወግዛቸውና እንዲህ ዓይነት ድርጊት በሚፈጽሙ ሰዎችም እንደሚያዝን ሲማር ምን ያደርጋል? ግለሰቡ እነዚህን ነገሮች እርግፍ አድርጎ ይተዋቸዋል! (ኢሳይያስ 63:10፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ኤፌሶን 4:30) ይህን የሚያደርግበት ዋነኛ ምክንያት ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት ስለሚፈልግ ቢሆንም ከእነዚህ ልማዶች በመላቀቁ የተሻለ ጤና እንዲሁም የአእምሮ ሰላም ስለሚኖረው ተጨማሪ ጥቅሞችም ያገኛል።

7 ብዙ ሰዎች ጎጂ ከሆኑ ልማዶች መላቀቅ በጣም ይከብዳቸዋል። ያም ሆኖ ግን በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ እያደረጉ ነው። ሕይወታቸውን ለአምላክ ወስነው በሕዝብ ፊት በውኃ በመጠመቅ አምላክን የሚያሳዝኑ ልማዶችን ማስወገዳቸውን ያሳያሉ። ይህ ለሁላችንም እንዴት የሚያበረታታ ነው! እነዚህ ሰዎች የሚወስዱት እርምጃ ጎጂ ለሆኑ የኃጢአት ድርጊቶች ባሪያ ላለመሆን ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።

8. አስደሳች ቤተሰብ ለመመሥረት የሚረዳን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ነው?

8 ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት መመሥረት እንችላለን። በብዙ አገሮች ውስጥ የቤተሰብ ሕይወት እየተንኮታኮተ ነው። በርካታ ባለ ትዳሮች ጋብቻቸውን የሚያፈርሱ ሲሆን ይህም በልጆቻቸው ላይ የስሜት ጠባሳ ያስከትላል። በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ከሚገኙት ቤተሰቦች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ናቸው። ይሖዋ በዚህ ረገድ ያለ ነቀፋ እንድንመላለስ የረዳን እንዴት ነው? ከኤፌሶን 5:22 እስከ 6:4 የሚገኘውን ሐሳብ አንብብና የአምላክ ቃል ለባሎች ለሚስቶችና ለልጆች የሚሰጠውን ግሩም ምክር ልብ በል። በዚህ ጥቅስም ሆነ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የጋብቻን ጥምረት ያጠናክራል፣ ልጆችን በሚገባ ለማሳደግ ይረዳል እንዲሁም የቤተሰብ ሕይወታችን አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይህ ደስተኞች እንድንሆን የሚያደርግ በረከት አይደለም?

9, 10. ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለን አመለካከት ከዓለም የሚለየው እንዴት ነው?

9 በዓለም ላይ ያሉ ችግሮች በቅርቡ እንደሚወገዱ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። በዛሬው ጊዜ በሳይንስና በቴክኖሎጂ መስክ ሰፊ እውቀት ከመኖሩም ባሻገር አንዳንድ መሪዎች ችግሮችን ለመቅረፍ ከልባቸው ጥረት ያደርጋሉ፤ ሆኖም ከባድ የሆኑ ችግሮችን ማስወገድ አልተቻለም። የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም መሥራች የሆኑት ክላውስ ሽዋብ “በዓለም ላይ ያሉት ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ሲሆን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ግን ጊዜ እያጣን ነው” በማለት በቅርቡ ተናግረው ነበር። ሽዋብ “እንደ ሽብርተኝነት፣ የአካባቢ ብክለት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ያሉ ሁሉንም ብሔራት የሚነኩ አደጋዎች” መኖራቸውን ከተናገሩ በኋላ “ዓለማችን የተደቀኑባትን ችግሮች ለመፍታት ከምንጊዜውም ይበልጥ ዛሬ፣ ሰዎች ተባብረው ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል” በማለት ደምድመዋል። ሃያ አንደኛው መቶ ዘመን ውስጥ ብንገባም የሰው ዘር የወደፊት ሁኔታ በአጠቃላይ ሲታይ እንደጨለመ ነው።

10 ይሖዋ የሰውን ዘር ችግሮች በሙሉ ለማስወገድ የሚያስችል ዝግጅት እንዳደረገ ማወቁ ምንኛ የሚያስደስት ነው! የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ለችግሮቻችን መፍትሔ ያመጣል። እውነተኛው አምላክ በዚህ መንግሥት አማካኝነት “ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል” እንዲሁም ‘ሰላም እንዲበዛ’ ያደርጋል። (መዝሙር 46:9፤ 72:7) የተቀባው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ችግረኛውን፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ከጭቈናና ከግፍ ይታደገዋል።’ (መዝሙር 72:12-14) እርሱ በሚገዛበት ወቅት የምግብ እጥረት አይኖርም። (መዝሙር 72:16) ይሖዋ “እንባን ሁሉ [ከዐይናችን] ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአል።” (ራእይ 21:4) ይህ መንግሥት በሰማይ ከተቋቋመ የተወሰኑ ዓመታት ያለፉ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በምድር ላይ ያሉ ችግሮችን በሙሉ ያስወግዳል።—ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 11:15

11, 12. (ሀ) አዝናኝ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ያለልክ መካፈል ዘላቂ ደስታ ያስገኛል? አብራራ። (ለ) እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

11 እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምን እንደሆነ እናውቃለን። እውነተኛ ደስታ የሚገኘው እንዴት ነው? አንድ የሥነ ልቦና ሊቅ ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሦስት ነገሮች መኖራቸውን የተናገሩ ሲሆን እነርሱም አዝናኝ የሆኑ እንቅስቃሴዎች፣ እንደ ሥራና የቤተሰብ ግንኙነት ያሉ ነገሮች እንዲሁም ዓላማ (ሌሎችን ለመርዳት የሚያስችል አንድ ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣር) ናቸው። እኚህ ሰው፣ ለደስታ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለው ከጠቀሷቸው ሦስት ነገሮች መካከል አዝናኝ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ለሚለው የመጨረሻውን ደረጃ የሰጡት ከመሆኑም በላይ “በጣም ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ያለልክ በመካፈል ላይ ያተኮረ በመሆኑ ይህ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው” በማለት ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን ይላል?

12 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን እንዲህ ብሏል:- “እኔም በልቤ፣ ‘መልካም የሆነውን ለማወቅ፣ በተድላ ደስታ እፈትንሃለሁ’ አልሁ፤ ነገር ግን ያም ከንቱ ነበረ። ደግሞም፣ ‘ሣቅ ሞኝነት ነው፤ ተድላ ደስታስ ምን ይጠቅማል?’ አልሁ።” (መክብብ 2:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ አዝናኝ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ያለልክ በመካፈል የሚገኘው ደስታ ጊዜያዊ እንደሆነ ይገልጻል። በሥራ መጠመድስ ደስታ ያስገኛል? ስለ አምላክ መንግሥት እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠን ተልእኮ ከየትኛውም ሥራ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነ ተግባር ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የመዳን መልእክት ለሌሎች በማካፈል ራሳችንንም የሚሰሙንንም በሚያድን ሥራ መጠመድ እንችላለን። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) “ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ” በመሆናችን “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ” ወይም ደስተኛ መሆኑን መመልከት እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 3:9፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35) ይህ ሥራ ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ፈጣሪያችን፣ ለሚሰድበው ለሰይጣን ዲያብሎስ መልስ እንዲሰጥ ያስችለዋል። (ምሳሌ 27:11) በእርግጥም ይሖዋ፣ ለእርሱ ያደሩ መሆን እውነተኛና ዘላቂ ደስታ እንደሚያስገኝ አሳይቶናል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8 NW

13. (ሀ) ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በረከት የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ምን ጥቅም አግኝተሃል?

13 ጠቃሚና ውጤታማ የሆነ የሥልጠና ፕሮግራም አለን። ገርሃርት በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። የወጣትነቱን ጊዜ በሚመለከት እንዲህ ይላል:- “ወጣት ሳለሁ ከባድ የሆነ የመናገር ችግር ነበረብኝ። በምጨነቅበት ጊዜ በግልጽ መናገር ስለሚያስቸግረኝ እንተባተብ ነበር። ራሴን ዝቅ አድርጌ ከመመልከቴም በላይ የመንፈስ ጭንቀት አደረብኝ። ወላጆቼ አጥርቶ ለመናገር የሚረዳ ሥልጠና እንድወስድ ቢያደርጉም ጥረታቸው ምንም ለውጥ አላመጣም። ችግሬ በአእምሮዬ የፈጠርኩት ነገር እንጂ አካላዊ አልነበረም። ሆኖም ይሖዋ በሰጠን ግሩም ዝግጅት ማለትም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈሌ ድፍረት እንዳገኝ ረዳኝ። የተማርኩትን ተግባራዊ ለማድረግ የቻልኩትን ያህል እጥር የነበረ ሲሆን ውጤትም አግኝቼበታለሁ! በግልጽ መናገር ቻልኩ፤ ጭንቀቴ ለቀቀኝ እንዲሁም በአገልግሎት በድፍረት መካፈል ጀመርኩ። አሁን የሕዝብ ንግግር እንኳ አቀርባለሁ። ይሖዋ በዚህ ትምህርት ቤት አማካኝነት ሕይወቴ እንዲታደስ ስለረዳኝ ከልቤ አመሰግነዋለሁ።” ይሖዋ ሥራውን ማከናወን እንድንችል የሚሰጠን ሥልጠና የሚያስደስት አይደለም?

14, 15. የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን ምን ሊረዳን ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።

14 ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ከሆነው የወንድማማች ማኅበር ድጋፍ ማግኘት ችለናል። በጀርመን የምትኖረው ካትሪን፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ እንደተከሰተና በዚህም ምክንያት አካባቢው በሱናሚ እንደተመታ ስትሰማ በጣም ተጨንቃ ነበር። ይህ አደጋ በደረሰበት ወቅት ሴት ልጅዋ ወደ ታይላንድ ሄዳ ነበር። ካትሪን ልጅዋ በሕይወት ትኑር ወይም ቁጥራቸው በየሰዓቱ ከሚጨምረው የአደጋው ሰለባዎቸ መካከል ትሁን ሳታውቅ 32 ሰዓታት አለፉ። በመጨረሻም ልጅዋ ደህና መሆኗን በስልክ ስትሰማ ትልቅ እፎይታ ተሰማት!

15 ካትሪን በጭንቀት ባሳለፈቻቸው በእነዚያ ሰዓታት እንድትረጋጋ የረዳት ምን ነበር? እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ሙሉውን ጊዜ ማለት ይቻላል ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። በተደጋጋሚ እንደተመለከትሁት እንዲህ ማድረጌ ብርታትና የአእምሮ ሰላም እንዳገኝ ረድቶኛል። ከዚህም በላይ አፍቃሪ የሆኑ መንፈሳዊ ወንድሞቼ ይጠይቁኝና ያበረታቱኝ ነበር።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ይህቺ እህት ወደ ይሖዋ ባትጸልይና አፍቃሪ ከሆኑ መንፈሳዊ ወንድሞቿ ማበረታቻ ባታገኝ ኖሮ ጭንቀቷ የከፋ በሆነ ነበር! ከይሖዋና ከልጁ ጋር ያለን የቀረበ ዝምድና እንዲሁም ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ያለን ኅብረት ተወዳዳሪ የማይገኝለት በረከት ነው፤ ይህን ውድ ሀብት አቅልለን ልንመለከተው አይገባም።

16. የትንሣኤ ተስፋ ምን ያህል ውድ መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

16 በሞት ያንቀላፉ የምንወዳቸውን ሰዎች እንደገና የማየት ተስፋ አለን። (ዮሐንስ 5:28, 29) ማቲያስ የተባለ አንድ ወጣት ያደገው በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ሆኖም ላገኛቸው በረከቶች አድናቆት ስላልነበረው ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ከክርስቲያን ጉባኤ ራቀ። በቅርቡ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከአባቴ ጋር በቁም ነገር ተጫውተን አናውቅም። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱም ብዙ ጊዜ እንጋጭ ነበር። ያም ሆኖ ግን አባቴ ምንጊዜም ቢሆን ጥሩ ሕይወት እንዲኖረኝ ይፈልግ ነበር። በወቅቱ ባይገባኝም እንኳ በጣም ይወደኝ ነበር። በ1996 አልጋው አጠገብ ተቀምጬ እጁን በመያዝ አምርሬ እያለቀስሁ ባደረግሁት ነገር ምን ያህል እንደተጸጸትኩና በጣም እንደምወደው ነገርሁት። ሆኖም በዚያ ወቅት ሊሰማኝ አይችልም ነበር። ለጥቂት ጊዜ ታምሞ ከቆየ በኋላ በሞት አንቀላፋ። አባቴ በትንሣኤ ሲነሳ ለማየት ከበቃሁ ያለፈውን ጊዜ ማካካስ እንችላለን። እርሱም ቢሆን አሁን ሽማግሌ ሆኜ እንደማገለግልና እኔና ባለቤቴ አቅኚዎች እንደሆንን ሲያውቅ በጣም እንደሚደሰት አልጠራጠርም።” የትንሣኤ ተስፋ እንዴት ያለ በረከት ነው!

“መከራንም አያክልባትም”

17. በይሖዋ በረከቶች ላይ ማሰላሰላችን የሚረዳን እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሰማይ ስለሚኖረው አባቱ ሲናገር “እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 5:45) ይሖዋ ለኃጢአተኞችና ለክፉዎች እንኳ በረከቱን የሚሰጥ ከሆነ ያለ ነቀፋ የሚመላለሱትንማ ምን ያህል አትረፍርፎ ይባርካቸው! መዝሙር 84:11 “እግዚአብሔር በቅንነት [ወይም ያለ ነቀፋ] የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም” ይላል። ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች ምን ያህል እንደሚያስብላቸውና ልዩ እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ስናስብ ልባችን በአመስጋኝነትና በደስታ ይሞላል!

18. (ሀ) ይሖዋ የሚሰጠን በረከት መከራን አይጨምርም ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

18 “የእግዚአብሔር በረከት” ሕዝቦቹ መንፈሳዊ ብልጽግና እንዲኖራቸው አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ “መከራንም አያክልባትም” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ምሳሌ 10:22) ይህ ከሆነ ታዲያ በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ብዙ ሥቃይና መከራ የሚያስከትል ፈተና የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? ችግሮችና የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙን በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ ነው። (1) ኃጢአተኛው ዝንባሌያችን። (ዘፍጥረት 6:5፤ 8:21፤ ያዕቆብ 1:14, 15) (2) ሰይጣንና አጋንንቱ። (ኤፌሶን 6:11, 12) (3) ክፉው ዓለም። (ዮሐንስ 15:19) ይሖዋ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱብን ቢፈቅድም እነዚህን ነገሮች የሚያመጣብን እርሱ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ” ይላል። (ያዕቆብ 1:17) የይሖዋ በረከት መከራን አይጨምርም።

19. ያለ ነቀፋ የሚመላለሱ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል?

19 መንፈሳዊ ብልጽግና ሲባል ወደ አምላክ መቅረብንም ይጨምራል። ከእርሱ ጋር የቀረበ ዝምድና ስንመሠርት ደግሞ ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት [የዘላለም ሕይወት] ለማግኘት፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳችን እናከማቻለን።’ (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 17-19) ወደፊት አምላክ በሚያዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ ከመንፈሳዊ ሀብት በተጨማሪ ሌሎች በረከቶችም እናገኛለን። በዚያን ጊዜ ‘አምላካቸውን እግዚአብሔርን የሚታዘዙ’ ሁሉ እውነተኛ ሕይወት ያገኛሉ። (ዘዳግም 28:2) አቋማችንን በማጠናከር ደስተኞች ሆነን ያለ ነቀፋ መመላለሳችንን እንቀጥል።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ ማሰብ የጥበብ እርምጃ የማይሆነው ለምንድን ነው?

• በአሁኑ ጊዜ ምን በረከቶች አግኝተናል?

• የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]