በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በሕይወት እንድትኖር ሕይወትን ምረጥ’

‘በሕይወት እንድትኖር ሕይወትን ምረጥ’

‘በሕይወት እንድትኖር ሕይወትን ምረጥ’

“ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ [አስቀምጫለሁ።] . . . እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ።”—ዘዳግም 30:19

1, 2. ሰው በአምላክ መልክ የተፈጠረው በምን መንገዶች ነው?

 “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ።” አምላክ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። ከዚያም “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው” በማለት ዘፍጥረት 1:26, 27 ይናገራል። ስለዚህ የመጀመሪያው ሰው በምድር ላይ ካሉት ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የተለየ ነበር። አዳም በማመዛዘን ችሎታው እንዲሁም እንደ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል ያሉ ባሕርያትን በማሳየት ረገድ የአምላክን ዓይነት አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የሚችል በመሆኑ ፈጣሪውን ይመስል ነበር። ራሱን የሚጠቅምና በሰማይ የሚኖረውን አባቱን የሚያስደስት ውሳኔ እንዲያደርግ የሚረዳው ሕሊና ተሰጥቶታል። (ሮሜ 2:15) በአጭር አነጋገር አዳም የመምረጥ ነጻነት ነበረው። ይሖዋ የምድራዊ ልጁን አፈጣጠር ከተመለከተ በኋላ “እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል።ዘፍጥረት 1:31፤ መዝሙር 95:6

2 እኛም የአዳም ዝርያዎች እንደመሆናችን መጠን የተሠራነው በአምላክ መልክና አምሳል ነው። ሆኖም የምናደርገውን ነገር በተመለከተ በእርግጥ የመምረጥ መብት አለን? እንዴታ! ይሖዋ ወደፊት ምን እንደሚከሰት አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ቢኖረውም እንኳን የእያንዳንዳችንን ድርጊትና የሚያስከተለውን ውጤት አስቀድሞ አልወሰነም። የምድራዊ ልጆቹን ዕጣ አስቀድሞ ወስኖላቸው በዚያ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ አያደርግም። የመምረጥ ነጻነታችንን ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግ መጠቀማችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመገንዘብ እንድንችል ከእስራኤል ብሔር የምናገኘውን ትምህርት እንመልከት።ሮሜ 15:4

እስራኤላውያን የመምረጥ ነጻነት ነበራቸው

3. ከአሥርቱ ትእዛዛት የመጀመሪያው ምን ይላል? ታማኝ እስራኤላውያን ይህን ሕግ ለመታዘዝ የመረጡትስ እንዴት ነው?

3 ይሖዋ እስራኤላውያንን “ከባርነት ምድር፣ ከግብፅ ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 5:6) የእስራኤል ብሔር በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከግብጽ ባርነት በተአምር ነጻ በመውጣቱ እነዚህን ቃላት የሚጠራጠርበት ምንም ምክንያት አልነበረውም። ይሖዋ በቃል አቀባዩ በሙሴ በኩል ከሰጣቸው አሥር ትእዛዛት በመጀመሪያው ላይ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ” ብሎ ነበር። (ዘፀአት 20:1, 3) በዚያን ጊዜ የእስራኤል ብሔር አባላት መታዘዝን መርጠውና ይሖዋን ብቻ ለማምለክ በፈቃደኝነት ወስነው ነበር።ዘፀአት 20:5፤ ዘኍልቍ 25:11 የ1980 ትርጉም

4. (ሀ) ሙሴ እስራኤላውያን ምን ሁለት ምርጫዎች እንዳሏቸው አስታውቋቸው ነበር? (ለ) እኛስ ምን ምርጫዎች አሉን?

4 ይህ ከሆነ ከ40 ዓመታት ገደማ በኋላ ሙሴ ለሌላ የእስራኤል ትውልድ በፊቱ የተዘረጋለትን ምርጫ ጠበቅ አድርጎ አስገንዝቧል። እንዲህ አለ:- “ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ።” (ዘዳግም 30:19) እኛም በተመሳሳይ ምርጫ የማድረግ መብት አለን። አዎን፣ የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘን ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል መምረጥ እንችላለን፤ ወይም ደግሞ እርሱን ያለመታዘዝና ውጤቱን የማጨድ ምርጫ አለን። እነዚህን የተለያዩ ምርጫዎች ያደረጉ ሰዎችን በተመለከተ ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት።

5, 6. ኢያሱ ምን ምርጫ አድርጎ ነበር? ምንስ ውጤት አገኘ?

5 እስራኤላውያን በኢያሱ መሪነት በ1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ተስፋይቱ ምድር ገቡ። ኢያሱ ከመሞቱ በፊት መላውን ብሔር እንዲህ በማለት አጥብቆ መክሯል:- “እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ።” አክሎም “እኔና ቤቴ . . . እግዚአብሔርን እናመልካለን” በማለት ስለ ራሱ ቤተሰብ ተናገረ።ኢያሱ 24:15

6 ቀደም ሲል ይሖዋ፣ ኢያሱ የአምላክን ሕግ ከመፈጸም ወደኋላ እንዳይል በማዘዝ ደፋርና ጠንካራ እንዲሆን ነግሮት ነበር። ኢያሱ የሕጉን መጽሐፍ በቀንና በሌሊት በማንበብ ያሰበውን ማቃናት ይችላል። (ኢያሱ 1:7, 8) ኢያሱ እንዲህ በማድረጉ ተሳክቶለታል። ያደረገው ምርጫ በረከት አስገኝቶለታል። “እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከሰጠው መልካም የተስፋ ቃል አንዳችም አልቀረም፤ ሁሉም ተፈጽሞአል” ብሏል።ኢያሱ 21:45

7. በኢሳይያስ ዘመን አንዳንድ እስራኤላውያን ምን ምርጫ አድርገው ነበር? ውጤቱስ ምን ሆነ?

7 በተቃራኒው ከ700 ዓመታት ገደማ በኋላ በእስራኤል የነበረው ሁኔታ ምን እንደሚመስል እንመልከት። በዚያን ጊዜ በርካታ እስራኤላውያን አረማዊ ልማዶችን ይከተሉ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በዓመቱ የመጨረሻ ቀን ላይ ሰዎች ተሰብስበው ግብዣ በማዘጋጀት ጥሩ ጥሩ ምግቦች ይመገቡና ጣፋጭ ወይን ይጠጡ ነበር። ይህ ቤተሰቦች የሚያደርጉት ተራ ግብዣ ሳይሆን ሁለት የአረማውያን አማልክትን ለማክበር የሚዘጋጅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ ያሰፈረው “እግዚአብሔርን ለተዋችሁት ለእናንተ፣ የተቀደሰ ተራራዬን ለረሳችሁት፣ ‘ዕጣ ፈንታ’ ለተባለ ጣዖት ቦታ [“ማዕድ፣” የ1954 ትርጉም] ላዘጋጃችሁት፣ ‘ዕድል’ ለተባለም ጣዖት ድብልቅ የወይን ጠጅ በዋንጫ ለሞላችሁት” የሚለው መግለጫ አምላክ እንዲህ ያለውን እምነት የማጉደል ተግባር እንዴት እንደሚመለከተው ያሳያል። የዓመቱን ምርት የሚያገኙት በይሖዋ በረከት ሳይሆን “ዕጣ ፈንታ” እና “ዕድል” የተባሉትን ጣዖታት በማስደሰት እንደሆነ ያምኑ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሚፈጽሙት የዓመጽ ተግባርና ሆን ብለው ያደረጉት ምርጫ መጨረሻቸው እንደማያምር ያሳይ ነበር። ይሖዋ እንዲህ አላቸው:- “ተጣርቼ ስላልመለሳችሁ፣ ተናግሬ ስላልሰማችሁ፣ በፊቴ ክፉ ነገር ስላደረጋችሁ፣ የሚያስከፋኝን ነገር ስለ መረጣችሁ፣ ለሰይፍ እዳርጋችኋለሁ፤ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ።” (ኢሳይያስ 65:11, 12) ያደረጉት ጥበብ የጎደለው ምርጫ ጥፋት አስከትሎባቸዋል፤ ዕጣ ፈንታና ዕድል የተባሉት ጣዖታትም ከጥፋት ሊታደጓቸው አልቻሉም።

ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ

8. በዘዳግም 30:20 ላይ እንደተገለጸው ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይጨምራል?

8 ሙሴ እስራኤላውያን ሕይወትን እንዲመርጡ ባሳሰባቸው ጊዜ “አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከእርሱ ጋር እንድትጣበቅ” በማለት ሦስት እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባቸው ጠቅሷል። (ዘዳግም 30:20) እኛም ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ እንድንችል እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመርምር።

9. ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እንዴት ማሳየት እንችላለን?

9 አምላካችንን ይሖዋን በመውደድ:- ይሖዋን ለማገልገል የመረጥነው ስለምንወደው ነው። ከጥንት እስራኤላውያን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምህርት በመቅሰም ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም የሚቀርቡልንን ፈተናዎች በሙሉ እንቋቋማለን፤ እንዲሁም በዓለም የፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ውስጥ እንድንወድቅ የሚያደርገንን የአኗኗር ዘይቤ ከመከተል እንቆጠባለን። (1 ቆሮንቶስ 10:11፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-10) ይሖዋን አጥብቀን እንይዛለን፤ ሥርዓቱንም እንጠብቃለን። (ኢያሱ 23:8፤ መዝሙር 119:5, 8) እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ እንዲህ ሲል አሳስቧቸው ነበር:- “ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ። በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙ . . . ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና።” (ዘዳግም 4:5, 6) በሕይወታችን ለይሖዋ ፈቃድ የመጀመሪያውን ደረጃ በመስጠት ለእርሱ ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ጊዜ አሁን ነው። እንዲህ ለማድረግ ከመረጥን እንደምንባረክ ምንም ጥርጥር የለውም።ማቴዎስ 6:33

10-12. በኖኅ ዘመን የተከሰተውን ነገር በመመርመር ምን ትምህርት እናገኛለን?

10 ቃሉን በማዳመጥ:- ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) ከጥፋት ውኃ በፊት የነበሩት ሰዎች በሙሉ ለማለት ይቻላል፣ ሐሳባቸው በተለያዩ ነገሮች ተከፋፍሎ ስለነበር ለኖኅ ማስጠንቀቂያ ትኩረት አልሰጡም። ውጤቱ ምን ሆነ? ‘የጥፋት ውሃ አጥለቀለቃቸው።’ ኢየሱስ በእኛ ዘመን ማለትም “የሰው ልጅ ሲመጣ” ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚኖር አስጠንቅቋል። በኖኅ ዘመን የተከሰተው ነገር ዛሬ የአምላክን መልእክት ሰምተው እርምጃ መውሰድ ለማይፈልጉ ሰዎች ከባድ ማስጠንቀቂያ ነው።ማቴዎስ 24:39

11 በዚህ ዘመን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በሚያሰሙት መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ላይ የሚያፌዙ ሰዎች፣ ማሳሰቢያውን ሰምቶ እርምጃ አለመውሰድ ምን እንደሚያስከትል መገንዘብ አለባቸው። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ያሉትን ፌዘኞች በተመለከተ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “እነዚህ ሰዎች ሰማያት ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥረው እንደሚኖሩ፣ መሬትም በውሃ መካከልና በውሃም እንደ ተሠራች ሆን ብለው ይክዳሉ፤ በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ። በዚያው ቃል ደግሞ አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር፣ ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል።”2 ጴጥሮስ 3:3-7

12 የእነዚህን ሰዎች ሁኔታ ኖኅና ቤተሰቡ ካደረጉት ምርጫ ጋር አነጻጽር። “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ . . . መርከብን በእምነት ሠራ።” ማስጠንቀቂያውን ሰምቶ እርምጃ መውሰዱ ለቤተሰቡ መዳንን አስገኝቷል። (ዕብራውያን 11:7) እኛም የአምላክን መልእክት በማዳመጥና አስፈላጊውን እርምጃ በታዛዥነት በመውሰድ ረገድ ፈጣኖች እንሁን።ያዕቆብ 1:19, 22-25

13, 14. (ሀ) ‘ከይሖዋ ጋር መጣበቅ’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ‘ሠሪያችን’ ይሖዋ እንዲቀርጸን መፍቀድ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ከይሖዋ ጋር በመጣበቅ:- ‘ሕይወትን መርጦ በሕይወት ለመኖር’ የሚያስፈልገው ይሖዋን መውደድና እርሱን ማዳመጥ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ በተጨማሪ ‘ከይሖዋ ጋር መጣበቅ’ ማለትም ፈቃዱን በመፈጸም መቀጠል ያስፈልገናል። ኢየሱስ “ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:19) እንደ እውነቱ ከሆነ በዚህ ረገድ የምናደርገው ምርጫ በልባችን ውስጥ ምን እንዳለ ይገልጻል። ምሳሌ 28:14 “እግዚአብሔርን ዘወትር የሚፈራ ሰው ቡሩክ ነው፤ ልቡን የሚያደነድን ግን መከራ ላይ ይወድቃል” ይላል። በጥንቷ ግብጽ የነበረው ንጉሥ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። በግብጽ ላይ አሥሩ መቅሰፍቶች በየተራ በወረዱ ቁጥር ፈርዖን አምላካዊ ፍርሃት ከማሳየት ይልቅ ልቡ የባሰ ይደነድን ነበር። ይሖዋ፣ ፈርዖን ታዛዥ እንዳይሆን አላስገደደውም፤ ነገር ግን ይህ ትዕቢተኛ ገዢ የራሱን ምርጫ እንዲያደርግ ፈቅዶለታል። ያም ሆነ ይህ የይሖዋ ፈቃድ ተፈጽሟል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ ለፈርዖን የነበረውን አመለካከት ሲገልጽ “ኀይሌ በአንተ እንዲታይ፣ ስሜም በምድር ሁሉ እንዲነገር ለዚህ አስነሣሁህ” ማለቱ ይህንን ያሳያል።ሮሜ 9:17

14 እስራኤላውያን ከፈርዖን ቁጥጥር ነጻ ከወጡ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ሸክላዎች፣ አንተም ሸክላ ሠሪ ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።” (ኢሳይያስ 64:8) በግል ጥናትና የአምላክን ቃል በተግባር በማዋል ይሖዋ እንዲቀርጸን ከፈቀድን ቀስ በቀስ አዲሱን ሰው እንለብሳለን። ይበልጥ ትሑቶችና መስተካከል የምንችል እንሆናለን፤ ይህም ከልባችን ይሖዋን ማስደሰት እንድንፈልግ ስለሚያደርገን ከእርሱ ጋር በታማኝነት መጣበቅ ቀላል ይሆንልናል።ኤፌሶን 4:23, 24፤ ቈላስይስ 3:8-10

“አስተምሯቸው”

15. በዘዳግም 4:9 ላይ እንደተዘገበው ሙሴ እስራኤላውያን ያለባቸውን የትኛውን ድርብ ኃላፊነት አስታውቋቸዋል?

15 ሙሴ፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበው የነበሩትን እስራኤላውያን አንድ ላይ በመሰብሰብ እንዲህ አላቸው:- “ዐይኖቻችሁ ያዩዋቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ። እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው።” (ዘዳግም 4:9) ሕዝቡ፣ የይሖዋን በረከት እንዲያገኙና በሚወርሷት ምድር ብልጽግና እንዲኖራቸው ከፈለጉ በአምላካቸው በይሖዋ ፊት ያለባቸውን ድርብ ኃላፊነት መወጣት ነበረባቸው። ይኸውም ይሖዋ ዓይናቸው እያየ ያደረገውን ድንቅ ነገር መርሳት አልነበረባቸውም፤ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ይህንኑ ማስተማር ነበረባቸው። እኛም የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ‘በሕይወት እንድንኖር ሕይወትን ከመረጥን’ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አለብን። አንተ በግልህ ይሖዋ ያደረገልህ ነገር የለም?

16, 17. (ሀ) በጊልያድ የሠለጠኑ ሚስዮናውያን የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ ምን አከናውነዋል? (ለ) የማይቀዘቅዝ ቅንዓት ያላቸውን የአምላክ አገልጋዮች ተሞክሮ ተናገር።

16 ይሖዋ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራችንን እንዴት እየባረከው እንዳለ ስንመለከት በጣም እንደሰታለን። ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት ከ1943 ጀምሮ የተመረቁት ሚስዮናውያን በበርካታ አገሮች በሚካሄደው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ሲሳተፉ ቆይተዋል። የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተመራቂዎች ምንም እንኳን ዕድሜያቸው የገፋና አንዳንዶቹም አቅማቸው ውስን ቢሆንም ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ ያላቸው ቅንዓት አሁንም አልቀዘቀዘም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑን መካከል በ1944 ከጊልያድ የተመረቁት ሜሪ ኦልሰን ይገኙበታል። ሜሪ ኦልሰን በመጀመሪያ በኡራጓይ ከዚያም በኮሎምቢያ አሁን ደግሞ በፖርቶ ሪኮ እያገለገሉ ይገኛሉ። እህት ኦልሰን የዕድሜ መግፋት የሚያስከትለው አንዳንድ አካላዊ ችግር አቅማቸው ውስን እንዲሆን ቢያደርግባቸውም ለስብከቱ ሥራ ያላቸው ቅንዓት እንዳለ ነው። ስፓንኛ ቋንቋ ስለሚችሉ ከአካባቢው አስፋፊዎች ጋር በየሳምንቱ በመስክ አገልግሎት የሚሳተፉበት ፕሮግራም አላቸው።

17 ምሥራቹን በመስበክ ረገድ ሥራ የበዛላቸው ሌላዋ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ1947 ተመራቂ ደግሞ አሁን መበለት የሆኑት ናንሲ ፖርተር ሲሆኑ እስከ አሁን ድረስ በባሃማስ ያገለግላሉ። የሕይወት ታሪካቸውን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማስተማር ልዩ ደስታ ይሰጠኛል። ሕይወቴ የተረጋጋ እንዲሆንና መልክ እንዲይዝ አስተዋጽኦ ያደረገልኝን ወጥ የሆነ መንፈሳዊ ልማድ እንዳዳብር ረድቶኛል።” a እህት ፖርተርና ሌሎች ታማኝ አገልጋዮች ያሳለፉትን ሕይወት መለስ ብለው ሲያስቡ ይሖዋ ያደረገላቸውን ነገር አይዘነጉም። እኛስ እንዴት ነን? ይሖዋ በአካባቢያችን እየተካሄደ ያለውን የስብከት ሥራ የባረከበትን መንገድ እናደንቃለን?መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም

18. የሚስዮናውያንን የሕይወት ታሪክ በማንበብ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

18 በይሖዋ አገልግሎት ረጅም ዓመታት ያሳለፉት እነዚህ ክርስቲያኖች ባከናወኑትና አሁንም እያከናወኑት ባለው ሥራ በጣም እንደሰታለን። የሕይወት ታሪካቸውን ማንበብ ያበረታታናል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለእነዚህ ታማኝ አገልጋዮቹ ያደረገላቸውን ነገር ስንመለከት እርሱን ለማገልገል ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ይጠናከራል። በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡትን እንዲህ ያሉ አስደሳች ተሞክሮዎችን አዘውትረህ በማንበብ ታሰላስልባቸዋለህ?

19. ክርስቲያን ወላጆች በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡትን ተሞክሮዎች ጥሩ አድርገው መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው?

19 ሙሴ፣ እስራኤላውያን ይሖዋ ያደረገላቸውን ነገር ሁሉ መዘንጋት እንደሌለባቸውና ያዩት ነገር በመላው የሕይወት ዘመናቸው ከልባቸው እንዳይጠፋ አሳስቧቸዋል። ከዚያም “እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው” በማለት ጨምሮ ነግሯቸዋል። (ዘዳግም 4:9) እውነተኛ ታሪኮች በልዩ ሁኔታ ስሜትን ይቀሰቅሳሉ። ታዳጊ ወጣቶች መልካም ምሳሌ ያስፈልጋቸዋል። ያላገቡ እህቶች በመጠበቂያ ግንብ ላይ ታሪካቸው ከሚወጣው በዕድሜ የገፉ ታማኝ እህቶች ምሳሌነት ትምህርት ያገኛሉ። ወንድሞችና እህቶች በአገራቸው ሆነው በውጪ አገር ቋንቋዎች በሚካሄደው የስብከት ሥራ መካፈላቸው፣ ምሥራቹን በመስበክ ረገድ ሥራ የበዛላቸው እንዲሆኑ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ክርስቲያን የሆናችሁ ወላጆች፣ የታማኝ ሚስዮናውያንንና የሌሎች ክርስቲያኖችን ተሞክሮ በመጠቀም ልጆቻችሁ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን እንዲመርጡ ለምን አታበረታቷቸውም?

20. ‘ሕይወትን ለመምረጥ’ ምን ማድረግ አለብን?

20 ታዲያ እያንዳንዳችን ‘ሕይወትን መምረጥ’ የምንችለው እንዴት ነው? ድንቅ የሆነውን የመምረጥ ነጻነታችንን አምላክን እንደምንወደው ለማሳየት በመጠቀምና በይሖዋ አገልግሎት እርሱ እስከፈቀደልን ድረስ የቻልነውን ያህል ማከናወናችንን በመቀጠል ነው። ሙሴ እንደተናገረው ይሖዋ ‘ሕይወታችን ነው፣ ረጅም ዕድሜም ይሰጠናል።’ዘዳግም 30:19, 20

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በሰኔ 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-27 ላይ የወጣውን “ልቤ በሃዘን ቢሰበርም ደስተኛና አመስጋኝ ነኝ” የሚል ርዕስ ያለውን ተሞክሮ ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተመለከትናቸው ሁለት ተቃራኒ ምርጫዎች ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ‘ሕይወትን ለመምረጥ’ ምን እርምጃዎችን መውሰድ አለብን?

• ምን ድርብ ኃላፊነት መወጣት አለብን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ሕይወትንና ሞትን በፊትህ አስቀምጫለሁ’

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል ማዳመጥ ለኖኅና ለቤተሰቡ መዳንን አስገኝቷል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሜሪ ኦልሰን

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ናንሲ ፖርተር