በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አረጋውያን የሚገኙበት አሳዛኝ ሁኔታ

አረጋውያን የሚገኙበት አሳዛኝ ሁኔታ

አረጋውያን የሚገኙበት አሳዛኝ ሁኔታ

አካባቢውን እየቃኘ የነበረው የሌሊት ጠባቂ ባየው ዘግናኝ ነገር በጣም በመደንገጡ ክው ብሎ ቀረ። ይህ ጠባቂ የተመለከተው ከአንድ የሚያምር የመኖሪያ ሕንፃ ስምንተኛ ፎቅ ላይ በመስኮት ራሳቸውን ወርውረው የገደሉ አረጋውያን ባልና ሚስት ሬሳ ነበር። ድርጊቱ አስደንጋጭ ቢሆንም ራሳቸውን እንዲገድሉ ምክንያት የሆናቸው ነገር ደግሞ ይበልጥ ዘግናኝ ነው። ከባልየው ኪስ የተገኘው ወረቀት እንዲህ ይላል:- “ራሳችንን እንድናጠፋ ምክንያት የሆነን ወንድ ልጃችንና ባለቤቱ የሚያደርሱብን በደል እንዲሁም ለእኛ ያላቸው ጥላቻ ነው።”

እንዲህ ያለው ክስተት ምናልባት ያልተለመደ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ለድርጊታቸው መንስኤ የሆነው ነገር ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም መሆኑ ያሳዝናል። ዛሬ በአረጋውያን ላይ የሚደርሰው በደል በዓለም ዙሪያ እንደ ወረርሽኝ የተዛመተ ሆኗል። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን መረጃዎች ተመልከት:-

• በአንድ ጥናት ላይ በካናዳ ከሚኖሩ አዛውንት መካካል 4 በመቶ የሚሆኑት፣ አብዛኛውን ጊዜ የቤተሰባቸው አባላት እንደሚበድሏቸው ወይም መጠቀሚያ እንደሚያደርጓቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ብዙ አረጋውያን ስላሉበት አሳዛኝ ሁኔታ ለሌላ ሰው ለመናገር ያፍራሉ አሊያም ይፈራሉ። እንዲያውም አንዳንድ ባለሙያዎች ችግሩ እየደረሰባቸው ያሉት አረጋውያን ቁጥር ወደ 10 በመቶ ሊጠጋ እንደሚችል ይናገራሉ።

ኢንዲያ ቱዴይ የተሰኘው መጽሔት እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “የሕንድ ሕዝብ ጠንካራ የሆነ የቤተሰብ ትስስር ያለው ቢመስልም እንኳ በልጆቻቸው የማይፈለጉ አረጋውያን ቁጥር እያደገ በመምጣቱ የቤተሰብ ሕይወት መፈራረስ ጀምሯል።”

• “ዕድሜያቸው 65 ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ከ1 እስከ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ አሜሪካውያን ጥበቃ ወይም እንክብካቤ በሚያደርግላቸው ሰው ጉዳት እንደሚደርስባቸው፣ መጠቀሚያ እንደሚደረጉ እንዲሁም እንደሚበደሉ” በቅርብ የተገኘ ግምታዊ አኃዝ እንደሚያሳይ ናሽናል ሴንተር ኦን ኤልደር አቢዩዝ የተባለው ድርጅት ዘግቧል። በሳን ዲያጎ፣ ካሊፎርኒያ ምክትል አቃቤ ሕግ የሆኑ አንድ ግለሰብ በአረጋውያን ላይ የሚፈጸመው በደል “በዛሬው ጊዜ ሕግ አስከባሪዎችን ከሚገጥሟቸው ችግሮች ሁሉ አሳሳቢ” እንደሆነ ተናግረዋል። አክለውም “በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህ ጉዳይ እየተባባሰ እንደሚሄድ ይታየኛል” ብለዋል።

• በካንተርበሪ፣ ኒው ዚላንድ ንብረታቸውን ለመውሰድ ሲባል አረጋውያን ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑ አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። በተለይ ዕፅ የሚወስድ፣ የአልኮል ወይም የቁማር ሱሰኛ የሆነ ሰው ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ችግሩ የጎላ ነው። በካንተርበሪ በ2002 ጥቃት ደርሶባቸዋል ተብሎ ሪፖርት የተደረገው የአረጋውያን ቁጥር 65 የነበረ ሲሆን በ2003 ደግሞ ወደ 107 አሻቅቧል። እንዲህ ያለውን በደል ለማስቀረት የተቋቋመ አንድ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ፣ ይህ ቁጥር “የችግሩን ሙሉ ገጽታ የሚያሳይ” እንዳልሆነ ተናግረዋል።

• “በልጆች ላይ ከሚደርስ በደልም ሆነ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ሌሎች ጥቃቶች በበለጠ አረጋውያን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ትኩረት ያሻዋል” በማለት የጃፓን የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ሐሳብ እንዳቀረበ ዘ ጃፓን ታይምስ ዘግቧል። እንዲህ ለማለት የቻለው ለምንድን ነው? ታይምስ አንደኛውን ምክንያት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “አረጋውያን፣ በደል የሚያደርስባቸው ግለሰብ ልጃቸው ከሆነ ጥፋቱ የእነርሱ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲሁም መንግሥትም ሆነ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም። ስለዚህ በአረጋውያን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በልጅ ወይም በትዳር ጓደኛ ላይ ከሚደርሰው በደል ጋር ስናነጻጽረው የአረጋውያን ችግር እስኪታወቅ ድረስ ረጅም ጊዜ ይወስዳል።”

እነዚህ በዓለም ዙሪያ ምን እየተከሰተ እንዳለ የሚያሳዩ ናሙናዎች እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች እንድናነሳ ያደርጉናል:- ብዙ አረጋውያን ችላ የተባሉትና በደል እየደረሰባቸው ያለው ለምንድን ነው? እነዚህ ነገሮች ይስተካከላሉ ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን? ለአረጋውያን የሚሆን ምን ማጽናኛ አለ?