በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በሙሴ ሕግ ውስጥ፣ ከፆታ ግንኙነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንድ ተፈጥሯዊ ነገሮች ሰውን ‘እንደሚያረክሱ’ የተገለጸው ለምንድን ነው?

አምላክ የፆታ ግንኙነትን የፈጠረው የሰው ልጆች እንዲዋለዱና ባልና ሚስቶች እንዲደሰቱ ሲል ነው። (ዘፍጥረት 1:28፤ ምሳሌ 5:15-18) ነገር ግን በዘሌዋውያን ምዕራፍ 12 እና 15 ላይ በወንድ ዘር መፍሰስ፣ በወር አበባና ልጅ በመውለድ ምክንያት ስለሚከሰቱት ርኩሰት የተባሉ ነገሮች ዝርዝር ሕግጋት ተጽፈው እናገኛለን። (ዘሌዋውያን 12:1-6፤ 15:16-24) ለጥንት እስራኤላውያን የተሰጡት እንዲህ ያሉት ሕጎች ሕዝቡ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖረው አስችለውታል፤ እንዲሁም ላቅ ያለ የሥነ ምግባር አቋም እንዲይዝ ረድተውታል። በተጨማሪም የደምን ቅድስና እንዲሁም ደም ለኃጢአት ሥርየት አስፈላጊ እንደሆነ በሚገባ እንዲገነዘብ አድርገውታል።

በተጨማሪም ሕጉ ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ ከፆታ ግንኙነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች በተመለከተ የሚሰጣቸው መመሪያዎች የእስራኤል ብሔር አጠቃላይ የጤንነት ሁኔታ እንዲሻሻል ረድቷል። ዘ ባይብል ኤንድ ሞደርን ሜድስን የተባለ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በወር አበባ ወቅት የፆታ ግንኙነት ከማድረግ ስለ መታቀብ የተሰጠውን ሕግ ማክበር በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ አንዳንድ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ዓይነተኛ ዘዴ እንደሆነ . . . እንዲሁም የማኅፀን ጫፍ ካንሰር መከሰትንና መባባስን እንደሚከላከል ተረጋግጧል።” እንዲህ ያሉት ሕግጋት የአምላክ ሕዝቦች ምንነቱን እንኳን ለይተው በማያውቁት በሽታ ከመያዝ ጠብቀዋቸዋል። ይሖዋ እንደሚያበዛቸውና እንደሚያበለጽጋቸው ቃል የገባላቸው እስራኤላውያን ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ንጽሕናቸውን መጠበቃቸው ዘር በመተካት ይበልጥ እንዲባዙ አስችሏቸዋል። (ዘፍጥረት 15:5፤ 22:17) እንዲሁም ሕጎቹ ሕዝቡ በስሜትም ረገድ ጤናማ እንዲሆን ረድተዋል። ባሎችና ሚስቶች እነዚህን ሕግጋት በማክበራቸው የፆታ ፍላጎታቸውን መቆጣጠርን ተምረዋል።

ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ መርከስን የሚያስከትለው ሌላው ዋነኛ ጉዳይ ደግሞ የደም መፍሰስ ነው። ይሖዋ ደምን አስመልክቶ ያወጣው ሕግ፣ ስለ ደም ቅድስና ብቻ ሳይሆን በይሖዋ አምልኮ ውስጥ የሚጫወተው ልዩ ሚናም እንዳለ ማለትም ለኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ እንደሚቀርብና ሥርየት እንደሚያስገኝ በእስራኤላውያን አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጽ አድርጓል።ዘሌዋውያን 17:11፤ ዘዳግም 12:23, 24, 27

በመሆኑም በዚህ ረገድ የተሰጡት ዝርዝር ሕግጋት ከሰው ልጅ አለፍጽምና ጋር የቅርብ ተዛማጅነት አላቸው። እስራኤላውያን አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ፍጹማን ልጆችን መውለድ እንዳልቻሉ ያውቃሉ። ዘሮቻቸው ኃጢአትን መውረሳቸው አለፍጽምናና ሞት አስከትሎባቸዋል። (ሮሜ 5:12) የሰው ልጆች የመራቢያ አካላት መጀመሪያ የተፈጠሩት በጋብቻ ዝግጅት አማካኝነት ፍጹም ሕይወት እንዲያስተላልፉ ቢሆንም ወላጆች በወረሱት ኃጢአት ምክንያት ማስተላለፍ የሚችሉት ፍጽምና የጎደለው ኃጢአተኛ ሕይወት ብቻ ነው።

ስለ መንጻት በሚገልጸው የሕጉ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት ግዴታዎች እስራኤላውያን በዘር የተወረሰ ኃጢአት እንዳለባቸው እንዲያስታውሱ ብቻ ሳይሆን ኃጢአትን ለመሸፈንና የሰው ልጅን ወደ ፍጽምና ለማድረስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደሚያስፈልግ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ያቀርቡት የነበረው የእንስሳ መሥዋዕት ይህንን ዓላማ እንዳላሳካ የተረጋገጠ ነው። (ዕብራውያን 10:3, 4) የሙሴ ሕግ የተሰጠበት ዓላማ እስራኤላውያንን ወደ ክርስቶስ ለማድረስ ነው፤ በተጨማሪም ሕጉ ታማኝ ሰዎች ለዘላለም ሕይወት እንዲበቁ የሚያስችላቸውን እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት የሚችሉት ፍጹም በሆነው የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት መሥዋዕት አማካኝነት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።ገላትያ 3:24፤ ዕብራውያን 9:13, 14