በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጤና እክል እያለብኝም በደስታ ማገልገል

የጤና እክል እያለብኝም በደስታ ማገልገል

የሕይወት ታሪክ

የጤና እክል እያለብኝም በደስታ ማገልገል

ቫርናቨስ ስፔትስዮቲስ እንደተናገረው

በ1990፣ በ68 ዓመቴ ሙሉ ለሙሉ ሽባ ሆንኩ። ያም ቢሆን በቆጵሮስ ደሴት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኜ በደስታ ማገልገል ከጀመርኩ አሁን 15 ዓመት ገደማ ይሆነኛል። የጤና እክል እያለብኝም በይሖዋ አገልግሎት መካፈሌን እንድቀጥል ጥንካሬ የሰጠኝ ምንድን ነው?

ተወለድኩት ጥቅምት 11, 1922 ሲሆን ቤተሰባችን አራት ወንዶችና አምስት ሴቶች ልጆችን ያቀፈ ነበር። ቆጵሮስ ውስጥ በምትገኝ ክሲሎፋጉ በተባለች መንደር ውስጥ እንኖር ነበር። ወላጆቼ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ ሀብታሞች ቢሆኑም ይህን ትልቅ ቤተሰብ ለማስተዳደር የእርሻ ሥራቸውን በትጋት ማከናወን ይጠበቅባቸው ነበር።

አባቴ አንዶኒስ በተፈጥሮው አንባቢና መጠየቅ የሚወድ ሰው ነበር። እኔ ከተወለድኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ መንደሩ አስተማሪ ሄዶ እያለ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ በነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ፒፕልስ ፑልፒት የሚል ትራክት ተመለከተ። ትራክቱ ላይ ባነበበው መልእክት ተመሰጠ። በዚህም የተነሳ አባቴና አንትሪአስ ክሬስቱ የተባለ ጓደኛው በደሴቲቱ ከተገኙት የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ለመሆን በቁ።

ስደት እያለም የተገኘ እድገት

ከጊዜ በኋላ አባቴና ጓደኛው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ተጨማሪ ጽሑፎችን ከይሖዋ ምሥክሮች አገኙ። ወዲያውኑ ሁለቱም የተማሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በመንደራቸው ለሚኖሩት ሰዎች ማካፈል ጀመሩ። ሆኖም የስብከት እንቅስቃሴያቸው ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስትም ሆነ የይሖዋ ምሥክሮች መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ከተሰማቸው ሌሎች ሰዎች ከባድ ስደት አስነሳባቸው።

ብዙዎቹ የመንደሩ ነዋሪዎች ግን እነዚህን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ያከብሯቸው ነበር። አባቴ በደግነቱና በልግስናው የታወቀ ነበር። ብዙ ጊዜ ድሀ ቤተሰቦችን ይረዳል። አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመሸ በኋላ ከቤት ሹልክ ብሎ ይወጣና ችግረኛ ወደሆኑ ቤተሰቦች ሄዶ ስንዴ ወይም ዳቦ በራቸው ላይ ያስቀምጣል። እንደዚህ የመሰለው ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ክርስቲያናዊ ምግባር እነዚህ ሁለት አገልጋዮች የሚናገሩት መልእክት ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን አድርጎታል።—ማቴዎስ 5:16

በዚህም ምክንያት አሥራ ሁለት የሚያህሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ተቀበሉ። ስለ እውነት ያላቸው ግንዛቤ ይበልጥ እያደገ ሲመጣ መጽሐፍ ቅዱስን በቡድን ሆነው ለማጥናት በተለያዩ ቤቶች መሰብሰብ እንዳለባቸው ተሰማቸው። ኒኮስ ማቴአኪስ የተባለ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በ1934 አካባቢ ከግሪክ ወደ ቆጵሮስ ሲመጣ በክሲሎፋጉ የነበረውን ቡድን አገኘ። ወንድም ማቴአኪስ በትዕግሥትና በቆራጥነት ቡድኑን ያደራጀ ከመሆኑም ሌላ ቅዱሳን ጽሑፎችን በተሻለ ሁኔታ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ይህ ቡድን በቆጵሮስ ለተቋቋመው የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መሠረት ሆኗል።

ክርስቲያናዊው ሥራ እያደገ ሲሄድና ተጨማሪ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲቀበሉ ወንድሞች ስብሰባዎቻቸውን በቋሚነት የሚያደርጉበት ቦታ እንደሚያስፈልጋቸው ተሰማቸው። ትልቁ ወንድሜ ጆርጅና ባለቤቱ እሌኒ መጋዘናቸውን ለመሰብሰቢያነት እንዲውል ሰጡ። ከቤታቸው ጎን የሚገኘው ይህ መጋዘን ለጉባኤ ስብሰባዎች እንደሚመች ተደርጎ ታደሰ። በዚህም ምክንያት ወንድሞች በደሴቲቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥት አዳራሽ ሊኖራቸው ቻለ። ለዚህም በጣም አመስጋኞች ነበሩ! ይህ ደግሞ ተጨማሪ እድገት እንዲገኝ መንገድ ከፍቷል!

እውነትን የራሴ ማድረግ

በ1938 ማለትም 16 ዓመት ሲሆነኝ አናጢ ለመሆን ወሰንኩ። በመሆኑም አባቴ የቆጵሮስ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ኒኮስያ ላከኝ። እንዲሁም ስለ ወደፊት ሕይወቴ በማሰብ ከወንድም ኒኮስ ማቴአኪስ ጋር እንድኖር ዝግጅት አደረገ። በደሴቲቷ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ይህን ታማኝ ወንድም በቅንዓቱና በእንግዳ ተቀባይነቱ እስካሁን ድረስ ያስታውሱታል። በዚያን ወቅት በቆጵሮስ የሚኖር ማንኛውም ክርስቲያን ያስፈልገው የነበረው ግለትና የማያወላውል ድፍረት በወንድም ማቴአኪስ ላይ በግልጽ ይታይ ነበር።

ወንድም ማቴአኪስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ እንዲጎለብትና መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ይህ ነው የማይባል እርዳታ አበርክቶልኛል። ከእርሱ ጋር በቆየሁባቸው ጊዜያት በቤቱ በሚካሄዱት በሁሉም ስብሰባዎች ላይ እገኝ ነበር። ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር እያደገ መምጣቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ታወቀኝ። ከአምላክ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ለመመሥረት ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ጥቂት ወራት እንዳለፉ ወንድም ማቴአኪስን አብሬው ወደ መስክ አገልግሎት መውጣት እችል እንደሆነ ጠየቅሁት። ይህ የሆነው በ1939 ነበር።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ወደ ቤት ተመለስኩ። ከአባቴ ጋር ያሳለፍኩት ጥቂት ጊዜ እውነትን እንዳገኘሁና የሕይወትን ትርጉም እንደተገነዘብኩ ይበልጥ እርግጠኛ እንድሆን አደረገኝ። መስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀመረ። በእኔ ዕድሜ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች ወደ ጦር ግንባር ለመሄድ ራሳቸውን አቀረቡ፤ እኔ ግን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመከተል ገለልተኛ አቋም ለመያዝ ወሰንኩ። (ኢሳይያስ 2:4፤ ዮሐንስ 15:19) በዚያው ዓመት ራሴን ለይሖዋ የወሰንኩ ሲሆን በ1940 ተጠመቅሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰው ፍርሃት ነጻ እንደሆንኩ ተሰማኝ!

በ1948 ከኤፍፕረፒአ ጋር የተጋባን ሲሆን ከጊዜ በኋላ አራት ልጆች በማግኘት ተባርከናል። ብዙም ሳንቆይ ልጆቻችንን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ለማሳደግ ጠንክረን መሥራት እንዳለብን ተገነዘብን። (ኤፌሶን 6:4) ልጆቻችን ይሖዋን ከልባቸው እንዲወዱ እንዲሁም ለሕግጋቱና ለመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጥልቅ አክብሮት እንዲኖራቸው ለመርዳት አጥብቀን ከመጸለያችንም በላይ ከፍተኛ ጥረት እናደርግ ነበር።

የጤና እክል ፈተና ሆነብኝ

በ1964 በ42 ዓመቴ ቀኝ እጄንና እግሬን ይደነዝዘኝ ጀመር። ይህ የመደንዘዝ ስሜት ቀስ በቀስ ወደ ግራ ጎኔ ተዛመተ። መስል አትሮፊይ በተባለ ጡንቻን የሚያመነምን በሽታ እንደያዘኝ ተነገረኝ። ይህ በሽታ የማይድን ከመሆኑም በላይ መጨረሻ ላይ ሙሉ ለሙሉ ሽባ ያደርጋል። ስለ በሽታዬ ሲነገረኝ በጣም ደነገጥኩ። ሁሉም ነገር የሆነው ሳይታሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር! በብስጭትና በንዴት ተውጬ ‘ይህ በእኔ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው? የዚህን ያህልስ የምቀጣው ምን አጥፍቼ ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። ይሁን እንጂ መጀመሪያ ላይ ስለ በሽታዬ ስሰማ የነበረኝ ድንጋጤ አለፈና በኋላ ላይ መረጋጋት ቻልኩ። ከዚያ ደግሞ በጭንቀትና ግራ በመጋባት ስሜት ተወጠርኩ። በርካታ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ይመላለሱ ነበር። ሙሉ ለሙሉ ሽባ ሆኜ ያለ ሌሎች ድጋፍ መኖር ሊያቅተኝ ነው ማለት ነው? ይህን ሁኔታ እንዴት አድርጌ ነው የምቋቋመው? ቤተሰቤን ማለትም ባለቤቴንና አራት ልጆቼን ማስተዳደር እችል ይሆን? እንደዚህ ያሉት ሐሳቦች በጣም ይረብሹኝ ጀመር።

ይህ ክፉ አጋጣሚ በሕይወቴ ላይ ሲደርስ፣ የሚያሳስቡኝንና የሚያስጨንቁኝን ነገሮች በሙሉ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ለይሖዋ በግልጽ መንገር እንደሚኖርብኝ ተሰማኝ። ቀን ከሌት እያነባሁ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እየተጽናናሁ መጣሁ። በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኙት አጽናኝ ቃላት እውነት መሆናቸውን ከራሴ ሁኔታ ተመልክቻለሁ:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”

ከበሽታዬ ጋር መታገል

እያደር ሁኔታዬ ይበልጥ እየተባባሰ መጣ። ከሁኔታዬ ጋር ቶሎ ራሴን ማስማማት እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። አናጺ ሆኜ መቀጠል ስለማልችል ለጤንነቴ የሚስማማና አድካሚ ያልሆነ እንዲሁም ቤተሰቤን ለመደገፍ የሚያስችለኝ ሥራ ለመፈለግ ወሰንኩ። መጀመሪያ ላይ በአንዲት አነስተኛ መኪና አይስ ክሬም መሸጥ ጀመርኩ። በተሽከርካሪ ወንበር ለመጠቀም እስከተገደድኩበት ጊዜ ድረስ ይህንን ሥራ ለስድስት ዓመታት ማከናወን ችያለሁ። ከዚያም ልሠራቸው የምችላቸውን የተለያዩ ቀለል ያሉ ሥራዎች አከናውን ነበር።

በ1990 ጤንነቴ በጣም ስላሽቆለቆለ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ወደማልችልበት ደረጃ ደረስኩ። አሁን ሙሉ ለሙሉ የሌሎች እርዳታ ያስፈልገኛል፤ ሌላው ቀርቶ አንድ ጤነኛ ሰው ሁልጊዜ የሚያከናውናቸውን ዕለታዊ ተግባሮች እንኳ መፈጸም አልችልም። ወደ አልጋ ለመሄድ፣ ለመታጠብም ሆነ ልብስ ለመልበስ የሚረዳኝ ሰው ያስፈልገኛል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ሆኜ እየገፉኝ ወደ መኪናው ካደረሱኝ በኋላ ተሸክመው መኪናው ውስጥ ያስገቡኛል። መንግሥት አዳራሽ ስንደርስ ደግሞ ከመኪናው አውጥተው ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ያስቀምጡኝና ወደ አዳራሹ ያስገቡኛል። በስብሰባው ወቅት እግሬ እንዲሞቅ ከአጠገቤ የኤሌክትሪክ ማሞቂያ ይቀመጥልኛል።

በሽታዬ የባሰብኝ ቢሆንም በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ እገኛለሁ። ይሖዋ የሚያስተምረን በስብሰባዎች ላይ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ደግሞም ከመንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር መሆኔ መሸሸጊያ እንዲሁም የብርታትና የመጽናናት ምንጭ ሆኖልኛል። (ዕብራውያን 10:24, 25) በመንፈሳዊ የጎለመሱ የእምነት ባልደረቦቼ አዘውትረው የሚጠይቁኝ መሆኑ ብርታት ሆኖልኛል። በእርግጥም እንደ ዳዊት “ጽዋዬም ሞልቶ ይፈስሳል” ማለት እችላለሁ።—መዝሙር 23:5

ውድ ባለቤቴ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ግሩም ረዳት ሆናልኛለች። ልጆቼም ቢሆኑ ብዙ እርዳታ አድርገውልኛል። ለበርካታ ዓመታት ዕለታዊ ፍላጎቶቼን አሟልተውልኛል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ እኔን መንከባከብ አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ የሚያደርጉልኝ ነገር ቀላል አይደለም። ትዕግሥት በማሳየትም ሆነ እኔን በመንከባከብ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። በመሆኑም ይሖዋ እነርሱን መባረኩን እንዲቀጥል እጸልያለሁ።

ይሖዋ አገልጋዮቹ እንዲጽናኑ ያዘጋጀው ሌላው አስደናቂ ዝግጅት ጸሎት ነው። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ ወደ እርሱ ለማቀርበው ከልብ የመነጨ ልመና ምላሽ በመስጠት በእነዚህ ዓመታት ሁሉ በእምነት እንድቀጥል ጥንካሬ ሰጥቶኛል። በተለይ ተስፋ ስቆርጥ፣ የማቀርበው ጸሎት እፎይታ እንዳገኝና ደስታዬን እንዳላጣ ይረዳኛል። ከይሖዋ ጋር መነጋገሬ መንፈሴን የሚያድሰው ከመሆኑም ሌላ በእውነት ውስጥ ለመቀጠል ያደረግሁትን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልኛል። ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጸሎት እንደሚሰማና የሚያስፈልጋቸውን የአእምሮ ሰላም እንደሚሰጣቸው ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ።—መዝሙር 51:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:7

ከሁሉም በላይ አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት አማካኝነት በገነት ውስጥ የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሁሉ በመጨረሻ ከሕመማቸው እንደሚፈውሳቸው ሳስታውስ ብርታት አገኛለሁ። በዚህ ድንቅ ተስፋ ላይ ሳሰላስል ብዙ ጊዜ የደስታ እንባ አነባለሁ።—መዝሙር 37:11, 29፤ ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:3, 4

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል

በ1991 አካባቢ ያለሁበትን ሁኔታ በደንብ ካመዛዘንኩ በኋላ፣ ስለ ራሴ በማብሰልሰል በጭንቀት እንዳልዋጥ የሚያስችለኝ በጣም ጥሩው መንገድ ውድ የሆነውን የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ማካፈል መሆኑን ተገነዘብኩ። በዚያው ዓመት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ።

አካል ጉዳተኛ እንደመሆኔ መጠን አብዛኛውን ጊዜ የምመሠክረው በደብዳቤ ነው። ይሁን እንጂ ደብዳቤ መጻፍ ብዙ ጥረት የሚጠይቅብኝ በመሆኑ ለእኔ ከባድ ሥራ ነበር። በጡንቻ አመንምን በሽታ በተዳከመው እጄ ብዕር መያዝ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። ሆኖም ከብዙ ጥረትና ጸሎት በኋላ ከዛሬ አሥራ አምስት ዓመት በፊት የጀመርኩትን በደብዳቤ ምሥክርነት የመስጠት ሥራ አሁንም ድረስ እያከናወንኩ ነው። በተጨማሪም በስልክ እመሠክራለሁ። ዘመዶቼ፣ ጓደኞቼ እንዲሁም ጎረቤቶቼ እቤት መጥተው በጠየቁኝ ቁጥር ስለ አዲሱ ዓለም ተስፋም ይሁን ገነት ስለምትሆነው ምድር ሳልነግራቸው ቀርቼ አላውቅም።

በውጤቱም ብዙ አበረታች ተሞክሮዎችን ማግኘት ችያለሁ። የዛሬ 12 ዓመት አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናው የነበረው አንዱ የልጅ ልጄ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አድናቆት እያሳየ መሆኑን በመመልከቴ በጣም ተደስቻለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናውን በመከተል በክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ረገድ ታማኝ በመሆን ጽኑ አቋም ይዟል።

በተለይ ደግሞ ደብዳቤ ከጻፍኩላቸው ሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ስገናኝ በጣም እደሰታለሁ። አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን እንድልክላቸው አልፎ አልፎ ይጠይቁኛል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ሴት ደውላ ለባለቤቷ አበረታች ደብዳቤ በመላኬ አመስግናኛለች። በደብዳቤው ውስጥ ያገኘችው ሐሳብ ስላስደሰታት ከባለቤቷ ጋር እቤት ድረስ መጥተው በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ውይይቶችን ልናደርግ ችለናል።

ብሩህ አመለካከትና ድንቅ ተስፋ

በደሴቲቷ ያሉት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት ሲጨምር ተመልክቻለሁ። ከወንድሜ ከጆርጅ ቤት አጠገብ ያለው አነስተኛ የመንግሥት አዳራሽ ለበርካታ ጊዜያት እንዲሰፋ የተደረገ ከመሆኑም በላይ ብዙ ጊዜ ታድሷል። ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የሚሰበሰቡበት ይህ የመንግሥት አዳራሽ በጣም የሚያምር የአምልኮ ቦታ ነው።

አባቴ በ1943 በ52 ዓመቱ በሞት ቢያንቀላፋም ግሩም መንፈሳዊ ውርስ ትቶልናል! ስምንት ልጆቹ በእውነት ውስጥ ሆነው ይሖዋን እያገለገሉ ነው። አባቴ በተወለደባት በክሲሎፋጉና በአቅራቢያዋ ባሉ ሌሎች መንደሮች ያለው የጉባኤዎች ቁጥር ሦስት የደረሰ ሲሆን በጠቅላላው 230 የሚያህሉ አስፋፊዎች ይገኛሉ!

እንዲህ ዓይነት እድገት ማየቴ ደስታዬን ጨምሮልኛል። አሁን 83 ዓመቴ ሲሆን መዝሙራዊው በተናገራቸው በሚከተሉት ቃላት ላይ ሙሉ እምነት አለኝ:- “አንበሶች ሊያጡ፣ ሊራቡም ይችላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጐድልባቸውም።” (መዝሙር 34:10) በኢሳይያስ 35:6 ላይ የሚገኘው “አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል” የሚለው ትንቢት የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የጤና እክል እያለብኝም ይሖዋን በደስታ እያገለገልኩ ለመቀጠል ቆርጫለሁ።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቱርክ

ሶርያ

ሊባኖስ

ቆጵሮስ

ኒኮስያ

ክሲሎፋጉ

የሜድትራንያን ባሕር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በክሲሎፋጉ የሚገኘውን የመጀመሪያውን የመንግሥት አዳራሽ በአሁኑ ጊዜም እንጠቀምበታለን

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኤፍፕረፒአ ጋር በ1946 እና በአሁኑ ጊዜ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስልክና በደብዳቤ ምሥክርነት መስጠት ያስደስተኛል