በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” ይናገራል

ይሖዋ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” ይናገራል

ይሖዋ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” ይናገራል

“የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ።” —ኢሳይያስ 46:10

1, 2. ከባቢሎን መውደቅ ጋር በተያያዘ አስደናቂ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ይህ ሐቅ ስለ ይሖዋ ምን ያሳያል?

 ኮቴ ሳያሰሙ የሚጓዙት የጠላት ወታደሮች፣ ወደ ኃያሏ የባቢሎን ከተማ ለመግባት በውድቅት ሌሊት የኤፍራጥስን ወንዝ በማቋረጥ ላይ ናቸው። ወደ ከተማዋ መግቢያ ሲቃረቡ አንድ አስደናቂ ነገር ተመለከቱ። ግዙፍ የሆነውና ባለ ሁለት ተካፋቹ የባቢሎን ከተማ በር አልተዘጋም! ከወንዙ መውረጃ ሽቅብ በመውጣት ወደ ከተማዋ ገቡና ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር አደረጓት። የጠላት ጦር መሪ የነበረው ቂሮስ ድል ያደረጋትን አገር ወዲያውኑ ማስተዳደር የጀመረ ሲሆን በኋላም ምርኮኛ የነበሩ እስራኤላውያን ነፃ እንዲወጡ የሚፈቅድ ድንጋጌ አወጣ። በሺዎች የሚቆጠሩ ግዞተኞች የይሖዋን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።2 ዜና መዋዕል 36:22, 23፤ ዕዝራ 1:1-4

2 ከ539 እስከ 537 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተፈጸሙት እነዚህ ክንውኖች ትክክል መሆናቸውን የታሪክ ተመራማሪዎች በሚገባ አረጋግጠዋል። በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ እነዚህ ክስተቶች ከመፈጸማቸው ከ200 ዓመታት በፊት የሚታወቁ የነበረ መሆኑ ነው። ይሖዋ ነቢዩ ኢሳይያስን ከብዙ ጊዜያት አስቀድሞ ስለ ባቢሎን መውደቅ እንዲናገር በመንፈሱ አነሳስቶት ነበር። (ኢሳይያስ 44:24 እስከ 45:7) አምላክ ከባቢሎን መውደቅ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን ብቻ ሳይሆን ድል የሚያደርጋትን ንጉሥ ስም ጭምር ገልጿል። a ይሖዋ በዚያን ጊዜ ምሥክሮቹ ለነበሩት እስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “የጥንቱን፣ የቀደመውን ነገር አስታውሱ፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔ ያለ የለም። የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ።” (ኢሳይያስ 46:9, 10ሀ) በእርግጥም ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ ማወቅ የሚችል አምላክ ነው።

3. የየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ይብራራል?

3 አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚያውቀው ምን ያህል ነው? ይሖዋ እያንዳንዳችን ምን እንደምናደርግ አስቀድሞ ያውቃል? የወደፊቱ ዕጣችን በእርግጥ አስቀድሞ ተወስኗል? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህና ተያያዥነት ላላቸው ሌሎች ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

ይሖዋ—የትንቢት አምላክ

4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች ምንጭ ማን ነው?

4 ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ ማወቅ የሚችለው ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ አገልጋዮቹን በርካታ ትንቢቶች እንዲጽፉ በመንፈሱ አነሳስቷቸዋል፤ ይህም ለወደፊቱ ምን ዓላማ እንዳለው አስቀድመን እንድናውቅ አስችሎናል። ይሖዋ “እነሆ፤ የቀድሞው ነገር ተፈጽሞአል፤ እኔም አዲስ ነገር እናገራለሁ፤ ከመብቀሉም በፊት፣ ለእናንተ አስታውቃለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 42:9) የአምላክ ሕዝቦች ምንኛ ታድለዋል!

5. ይሖዋ የሚያደርገውን ነገር አስቀድሞ ማወቅ ምን ኃላፊነት ያስከትላል?

5 ነቢዩ አሞጽ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምስጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣ ምንም ነገር አያደርግም” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ነገሮችን አስቀድሞ የማወቅ መብት ኃላፊነትም ያስከትላል። አሞጽ ሐሳቡን ሲቀጥል የተጠቀመበትን ትልቅ ትርጉም ያለው ምሳሌ ተመልከት:- “አንበሳ አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው?” የአንበሳ ግሣት በአካባቢው የሚገኙት ሰዎችና እንስሳት ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ እንደሚያነሳሳቸው ሁሉ ይሖዋ በተናገራቸው ጊዜ እንደ አሞጽ ያሉ ነቢያት ፈጣን ምላሽ በመስጠት መልእክቱን ወዲያውኑ አውጀዋል። አሞጽ “ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?” ብሏል።አሞጽ 3:7, 8

የይሖዋ ‘ቃል ይፈጸማል’

6. ከባቢሎን መውደቅ ጋር በተያያዘ የይሖዋ “ዐላማ” የተፈጸመው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ ብሏል:- “ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ።” (ኢሳይያስ 46:10ለ) ይሖዋ ባቢሎንን በተመለከተ ያለው ፈቃድ ወይም “ዐላማ” ባቢሎንን እንዲይዝ ቂሮስን ከፋርስ መጥራትንና ኃያሏ ከተማ እንድትወድቅ ማድረግን ይጨምራል። ይሖዋ ይህን ዓላማውን ከብዙ ጊዜ አስቀድሞ አሳውቋል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ትንቢቱ በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሙሉ በሙሉ ተፈጽሟል።

7. የይሖዋ ‘ቃል’ ምንጊዜም እንደሚፈጸም መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

7 ቂሮስ ባቢሎንን ድል ከማድረጉ ከአራት መቶ ዘመናት ገደማ በፊት የኖረው የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከአሞንና ከሞዓብ ጥምር ኃይል ጋር ተፋጥጦ ነበር። በሙሉ እምነት እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በሰማይ የምትኖር አምላክ አይደለህምን? የምድር ሕዝቦችን መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ ነህ፤ ኀይልና ሥልጣን በእጅህ ነው፤ ሊቋቋምህም የሚችል ማንም የለም።” (2 ዜና መዋዕል 20:6) ኢሳይያስም በተመሳሳይ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አስቦአል፤ ማንስ ያግደዋል? እጁም ተዘርግቶአል? ማንስ ይመልሰዋል?” በማለት የነበረውን እምነት ገልጿል። (ኢሳይያስ 14:27) በኋላም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ካጋጠመው የአእምሮ መታወክ ካገገመ በኋላ “እጁን [የአምላክን] መከልከል የሚችል የለም፤ ‘ምን ታደርጋለህ?’ ብሎ የሚጠይቀውም የለም” ሲል በትሕትና አምኗል። (ዳንኤል 4:35) አዎን፣ ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷል:- “ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።” (ኢሳይያስ 55:11) ምንጊዜም ቢሆን የይሖዋ “ቃል” እንደሚፈጸም ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። የአምላክ ዓላማ ሳይፈጸም አይቀርም።

የአምላክ “ዘላለማዊ ዓላማ”

8. የአምላክ “ዘላለማዊ ዓላማ” ምንድን ነው?

8 ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ “ዘላለማዊ ዓላማ” እንዳለው ገልጿል። (ኤፌሶን 3:11 NW) ይህ ሲባል ግን አምላክ አንድን ነገር የሚያከናውንበትን መንገድ በዝርዝር በማስቀመጥ እቅድ ነድፏል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለሰው ልጆችና ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ዳር ለማድረስ ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያመለክት ነው። (ዘፍጥረት 1:28) የአምላክ ዓላማ እንደሚፈጸም ያለንን እርግጠኝነት ከፍ ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጀመሪያ ትንቢት እንመልከት።

9. ዘፍጥረት 3:15 ከአምላክ ዓላማ ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

9 በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተሰጠው ተስፋ ይሖዋ አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንደሠሩ ወዲያውኑ አንዲት ምሳሌያዊት ሴት፣ ዘር ወይም ልጅ እንዲኖራት እንደወሰነ ይገልጻል። በተጨማሪም ይሖዋ በሴቲቱና በሰይጣን መካከል እንዲሁም በዘሮቻቸው መካከል የሚኖረው ጠላትነት ምን ውጤት እንደሚያመጣ አስቀድሞ አውቆ ነበር። ምንም እንኳን ይሖዋ የሴቲቱ ዘር ተረከዝ እንዲቀጠቀጥ የሚፈቅድ ቢሆንም እርሱ በወሰነው ጊዜ ይህ ዘር የእባቡን ወይም የሰይጣን ዲያብሎስን ራስ ይቀጠቅጣል። ኢየሱስ ቃል የተገባው መሲሕ ሆኖ እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ፣ የይሖዋ ዓላማ ምንም እንቅፋት ሳይገጥመው እርሱ በመረጠው የትውልድ ሐረግ በኩል ሲፈጸም ቆይቷል።ሉቃስ 3:15, 23-38፤ ገላትያ 4:4

አምላክ አስቀድሞ የወሰነው ነገር

10. ይሖዋ አዳምና ሔዋን እንዲሳሳቱ አስቀድሞ ወስኖ ነበር? አብራራ።

10 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “እርሱ [ኢየሱስ] አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን አሁን፣ ግን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገለጠ።” (1 ጴጥሮስ 1:20) ይሖዋ ገና ከመጀመሪያው አዳምና ሔዋን እንዲሳሳቱና የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲቀርብ አስቀድሞ ወስኖ ነበር? በፍጹም። ጥቅሱ ላይ ‘መፈጠር’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ዘር መዝራት” የሚል ቀጥተኛ ፍቺ አለው። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት ‘ዘር ተዘርቶ’ ወይም ሰብዓዊ ልጅ ተጸንሶ ነበር? በጭራሽ። ልጆች የወለዱት ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ነው። (ዘፍጥረት 4:1) አዳምና ሔዋን ካመጹ በኋላ፣ ሆኖም ልጅ ከመውለዳቸው በፊት ይሖዋ የሴቲቱ ‘ዘር’ እንዲመጣ ወሰነ። የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ፍቅራዊ የሆነውን የቤዛ ዝግጅት አስገኘ፤ ይህም የወረስነውን ኃጢአት የሚያስወግድ ከመሆኑም በላይ የሰይጣንን ጥረት ያከሽፋል።ማቴዎስ 20:28፤ ዕብራውያን 2:14፤ 1 ዮሐንስ 3:8

11. ይሖዋ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ምን አስቀድሞ የወሰነው ነገር አለ?

11 አምላክ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ አንድ ሌላም ሁኔታ አስቀድሞ ወስኗል። ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ገልጿል። ጥቅሱ አምላክ ‘በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር እንደሚጠቀልል’ ይናገራል። ከዚያም ‘በሰማይ ስላሉት ነገሮች’ ማለትም ከክርስቶስ ጋር ለመውረስ ስለተመረጡት ሲናገር “ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ አስቀድሞ የተወሰንን” ብሏል። (ኤፌሶን 1:10, 11) አዎን፣ ይሖዋ ጥቂት የሰው ልጆች የሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ክፍል ሆነው እንዲደራጁና ከክርስቶስ ጋር የቤዛውን ጥቅሞች ለሰው ዘር እንዲያዳርሱ አስቀድሞ ወስኗል። (ሮሜ 8:28-30) ሐዋርያው ጴጥሮስ እነዚህን ሰዎች “ቅዱስ ሕዝብ” ብሎ ጠርቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:9) ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር ወራሽ የሚሆኑት ሰዎች ቁጥር 144,000 እንደሆነ በራእይ የመመልከት መብት አግኝቷል። (ራእይ 7:4-8፤ 14:1, 3) እነዚህ ሰዎች ንጉሡን ክርስቶስን በመደገፍ ‘ለአምላክ ክብር ምስጋና በመሆን’ ያገለግላሉ።ኤፌሶን 1:12-14

12. የ144,000 አባላት በግለሰብ ደረጃ አስቀድመው እንዳልተወሰኑ እንዴት እናውቃለን?

12 የ144,000ዎቹ ጉዳይ አስቀድሞ የተወሰነ ነው ሲባል፣ አንዳንድ ሰዎች በዚህ መንገድ አምላክን በታማኝነት እያገለገሉት እንዲኖሩ አስቀድመው ተወስነዋል ማለት አይደለም። እንዲያውም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉት ምክሮች በዋነኝነት የተጻፉት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ጸንተው እንዲቆሙና ‘ለሰማያዊ ጥሪ’ የሚያስፈልገውን ብቃት እንደያዙ እንዲቀጥሉ ለመርዳትና ለማበረታታት ነው። (ፊልጵስዩስ 2:12፤ 2 ተሰሎንቄ 1:5, 11፤ 2 ጴጥሮስ 1:10, 11) ይሖዋ 144,000 ግለሰቦች በዓላማው መሠረት ለማገልገል ብቃት እንደሚኖራቸው አስቀድሞ ያውቃል። የእነዚህን ግለሰቦች ማንነት በትክክል የሚወስነው ግን ከተመረጡ በኋላ የሚመሩት ሕይወት ሲሆን በዚህ ረገድ እያንዳንዳቸው የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ አለባቸው።ማቴዎስ 24:13

ይሖዋ አስቀድሞ የሚያውቀው ነገር

13, 14. ይሖዋ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀመው ከምኑ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው? ለምንስ?

13 ይሖዋ የትንቢትና የዓላማ አምላክ ነው፤ ታዲያ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የአምላክ መንገዶች በሙሉ እውነተኛ፣ ጻድቅና ፍቅራዊ እንደሆኑ አንጠራጠርም። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ የገባው መሐላና የተስፋ ቃል ‘ከቶ ሊዋሽ እንደማይችል የሚያሳዩ ሁለት የማይለወጡ ነገሮች’ መሆናቸውን ገልጿል። (ዕብራውያን 6:17, 18) እንዲሁም ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ቲቶ ‘አምላክ እንደማይዋሽ’ በጻፈ ጊዜ ይህን ሐሳብ ገልጿል።ቲቶ 1:2

14 በተጨማሪም ይሖዋ ገደብ የሌለው ኃይል ቢኖረውም እንኳን ትክክል ያልሆነ ነገር አይፈጽምም። ሙሴ ይሖዋ “የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክ” እንደሆነ ገልጿል። (ዘዳግም 32:4) ይሖዋ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ከድንቅ ባሕርያቱ ጋር የሚስማማ ነው። የሚያደርጋቸው ነገሮች የዋና ዋና ባሕርያቱ ማለትም የፍቅሩ፣ የጥበቡ፣ የፍትሑና የኃይሉ መገለጫ ናቸው።

15, 16. ይሖዋ በዔድን ገነት ውስጥ ለአዳም ምን ምርጫዎች ሰጥቶት ነበር?

15 እነዚህ ዋና ዋና ባሕርያቱ በሙሉ በዔድን ገነት ውስጥ ከተከሰቱት ነገሮች ጋር በተያያዘ እንዴት እንደተንጸባረቁ እንመልከት። ይሖዋ አፍቃሪ አባት እንደመሆኑ መጠን የሰው ልጆች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ ሰጥቷቸው ነበር። ለአዳም የማሰብ፣ የማመዛዘንና ውሳኔ የማድረግ ችሎታ ሰጥቶት ነበር። በአብዛኛው በደመ ነፍስ ከሚመሩት እንስሳት በተለየ የመምረጥ ችሎታ ነበረው። አዳም ከተፈጠረ በኋላ አምላክ ሰማይ ከሚገኘው ዙፋኑ ሆኖ ወደ ታች ሲመለከት ‘ያደረገው ሁሉ እነሆ እጅግ መልካም እንደነበረ’ አየ።ዘፍጥረት 1:26-31፤ 2 ጴጥሮስ 2:12

16 ይሖዋ፣ አዳም “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” እንዳይበላ ሲያዘው ውሳኔ ማድረግ የሚያስችለውን በቂ መመሪያ ሰጥቶታል። ከአንዱ በስተቀር “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ” እንዲበላ የፈቀደለት ሲሆን ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ መብላት ሞት እንደሚያስከትል አስጠንቅቆታል። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ይሖዋ ለአዳም ድርጊቱ የሚያስከትለውን ውጤት ነግሮታል። አዳም ምን ያደርግ ይሆን?

17. ይሖዋ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሲፈልግ ነው ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

17 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ቢኖረውም አዳምና ሔዋን ምን እንደሚያደርጉ አስቀድሞ ላለማወቅ ሳይመርጥ አልቀረም። ስለዚህ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ ማወቅ መቻሉ ምንም አያጠያይቅም፤ ዋናው ነገር ግን ስለ ወደፊቱ አስቀድሞ ማወቅ ይፈልጋል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ፍቅር እንደመሆኑ መጠን ሆን ብሎና በጭካኔ አዳምና ሔዋን አሳዛኝ ውጤት የሚያስከትል ዓመጽ እንዲፈጽሙ አስቀድሞ አልወሰነም ብሎ መደምደም ይቻላል። (ማቴዎስ 7:11፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ስለዚህ ይሖዋ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሲፈልግ ነው።

18. ይሖዋ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሲፈልግ መሆኑ ጉድለት እንዳለበት የማያሳየው ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሲፈልግ ነው ሲባል በሆነ መንገድ ኃይል ያንሰዋል ወይም ጉድለት አለበት ማለት ነው? በጭራሽ። ሙሴ ስለ ይሖዋ ሲገልጽ “እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው” ብሏል። የሰው ልጆች ኃጢአት ላስከተለው ውጤት ተጠያቂው እርሱ አይደለም። ዛሬ ሁላችንም እየቀመስነው ላለነው መጥፎ የኃጢአት ውጤት መሠረቱ ዓመጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ምክንያቱን እንዲህ በማለት ግልጽ አድርጎታል:- “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል።”ዘዳግም 32:4, 5፤ ሮሜ 5:12፤ ኤርምያስ 10:23

19. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

19 እስከ አሁን እንደተወያየነው ይሖዋ ፍትሕን አያጓድልም። (መዝሙር 33:5) እንዲያውም የይሖዋ ችሎታዎች፣ ባሕርያትና የአቋም ደረጃዎች ዓላማውን የሚደግፉ ናቸው። (ሮሜ 8:28) ይሖዋ የትንቢት አምላክ እንደመሆኑ መጠን “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ” ይናገራል። (ኢሳይያስ 46:9, 10) እንዲሁም ይሖዋ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት ሲፈልግ እንደሆነ ተመልክተናል። ታዲያ ይህ እኛን የሚነካን እንዴት ነው? የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ከአምላክ ፍቅራዊ ዓላማ ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ምን በረከት ያስገኝልናል? እነዚህን ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር ገጽ 28 ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ምንጊዜም ቢሆን የአምላክ ‘ቃል እንደሚፈጸም’ የሚያረጋግጡት የትኞቹ የጥንት ምሳሌዎች ናቸው?

• ይሖዋ ‘ከዘላለማዊ ዓላማው’ ጋር በተያያዘ አስቀድሞ የወሰነው ነገር ምንድን ነው?

• ይሖዋ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮሣፍጥ በይሖዋ ይተማመን ነበር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አስቀድሞ ተናግሯል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ አዳምና ሔዋን የሚያደርጉትን ነገር አስቀድሞ ወስኖ ነበር?