“ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”
“ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”
“አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።”—መዝሙር 119:97
1, 2. (ሀ) መዝሙር 119ን በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ የጻፈው ሰው ምን ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር? (ለ) ችግር ቢደርስበትም ምን ስሜት ነበረው? ለምንስ?
የመዝሙር 119 ጸሐፊ በርካታ ችግሮችን ያሳለፈ ሰው ነው። ለአምላክ ሕግ ደንታ ቢስ የሆኑ እብሪተኛ ጠላቶቹ ያፌዙበትና ስሙን ያጠፉ ነበር። ገዥዎች እርሱን ለማጥቃት ይዶልቱና ያሳድዱት እንዲሁም በዙሪያው የሚገኙ ክፉ ሰዎች እንደሚገድሉት ያስፈራሩት ነበር። መዝሙራዊው የደረሰበት ነገር ሁሉ ‘በሐዘን እንዲዝለፈለፍ’ አድርጎታል። (መዝሙር 119:9, 23, 28, 51, 61, 69, 85, 87, 161) ይህ ችግር ቢደርስበትም “አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 119:97
2 “የአምላክ ሕግ ለመዝሙራዊው የብርታትና የመጽናናት ምንጭ የሆነለት እንዴት ነው?” ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እንዲጽናና የረዳው ይሖዋ እንደሚያስብለት እርግጠኛ መሆኑ ነው። መዝሙራዊው ጠላቶቹ ችግር ቢያደርሱበትም እንኳን የአምላክን ፍቅራዊ ሕግ መታዘዝ የሚያስገኘውን ጥቅም ማወቁ ደስተኛ እንዲሆን አስችሎታል። ይሖዋም በደግነት እንደያዘው ተገንዝቦ ነበር። ከሁሉም በላይ በአምላክ ሕግ ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ በሥራ ላይ ማዋሉ ከጠላቶቹ ይልቅ አስተዋይና ሕያው አድርጎታል። በተጨማሪም ሕጉን መታዘዙ ሰላምና ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው አድርጓል።—መዝሙር 119:1, 9, 65, 93, 98, 165
3. በዛሬው ጊዜ የአምላክን የአቋም ደረጃዎች መጠበቅ ለክርስቲያኖች ከባድ የሚሆነው ለምንድን ነው?
3 ዛሬም አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በእምነታቸው ምክንያት ከባድ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። ምናልባት እኛ እንደ መዝሙራዊው ለሕይወት የሚያሰጋ ችግር አልገጠመን ይሆናል፤ ነገር ግን የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ነው። በዙሪያችን ያሉ ብዙ ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ግድ የላቸውም፤ ግባቸው በራስ ወዳድነትና በፍቅረ ነዋይ ላይ ያተኮረ ሲሆን የትዕቢት አስተሳሰብ ያላቸውና አክብሮት የጎደላቸው ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ወጣት ክርስቲያኖች የሥነ ምግባር አቋማቸውን እንዲያላሉ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ያለማቋረጥ መታገል አለባቸው። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ለይሖዋና ለትክክለኛው ነገር ያለንን ፍቅር እንደያዝን መቀጠል ሊከብደን ይችላል። ታዲያ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
4. መዝሙራዊው ለአምላክ ሕግ አድናቆት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? ክርስቲያኖችስ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል?
4 መዝሙራዊው ይደረግበት የነበረውን ጫና እንዲቋቋም የረዳው ነገር የአምላክን ሕግ ለማጥናትና በእርሱም ላይ በጥልቀት ለማሰላሰል ጊዜ መመደቡ ነው። በዚህ መንገድ ለአምላክ ሕግ ፍቅር ማዳበር ችሏል። የመዝሙር 119 እያንዳንዱ ቁጥር የይሖዋን ሕግ አንዳንድ ገጽታዎች ይገልጻል ለማለት ይቻላል። a በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች ይሖዋ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር በሰጠው የሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። (ቈላስይስ 2:14) ነገር ግን በሕጉ ውስጥ የተገለጹት መሠረታዊ ሥርዓቶች አሁንም ጠቀሜታ አላቸው። እነዚህ መመሪያዎች መዝሙራዊውን እንዳጽናኑት ሁሉ ከችግሮቻቸው ጋር እየታገሉ ላሉ የዘመናችን የአምላክ አገልጋዮችም መጽናኛ ሊሆኑ ይችላሉ።
5. በሙሴ ሕግ ውስጥ ካሉት ትእዛዛት መካከል የትኞቹን እንመለከታለን?
5 በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተጠቀሱት መመሪያዎች መካከል ከሦስቱ ምን ማበረታቻ እንደምናገኝ እንመልከት፤ እነርሱም ሰንበትን ስለማክበር የሚገልጸውና ቃርሚያን በተመለከተ የተሰጠው ሕግ እንዲሁም ስግብግብነትን የሚያወግዘው ሕግ ናቸው። በዘመናችን ያሉትን ችግሮችና የሚደርሱብንን ጫናዎች መቋቋም እንድንችል እነዚህን ሕግጋት አንድ በአንድ በመመርመር ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት መገንዘባችን በጣም አስፈላጊ ነው።
መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካት
6. ሁሉም ሰው ምን መሠረታዊ ፍላጎቶች አሉት?
6 የሰው ልጅ በተፈጥሮው በርካታ ፍላጎቶች አሉት። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ጥሩ አካላዊ ጤንነት እንዲኖረው ምግብ፣ መጠለያና የሚጠጣውን ነገር ማግኘት አለበት። ነገር ግን የሰው ልጅ ‘መንፈሳዊ ፍላጎቱንም’ ማርካት አለበት። እንዲህ ካላደረገ እውነተኛ ደስታ ማግኘት አይችልም። (ማቴዎስ 5:3 NW) ይሖዋ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘውን ይህንን ፍላጎቱን ማርካቱ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ እስራኤላውያን ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ትኩረት ለመስጠት እንዲችሉ በየሳምንቱ ለአንድ ሙሉ ቀን የተለመደ ተግባራቸውን ከማከናወን እንዲቆጠቡ አዝዞ ነበር።
7, 8. (ሀ) አምላክ በሰንበትና በሌሎች ቀናት መካከል ልዩነት ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) ሰንበት ለምን ዓላማ አገልግሏል?
7 የሰንበት ሕግ የመንፈሳዊ ጉዳዮችን አስፈላጊነት ያጎላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሰንበት” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው እስራኤላውያን በበረሃ እያሉ ከተሰጣቸው መና ጋር በተያያዘ ነው። እስራኤላውያን ይህንን ተዓምራዊ እንጀራ መሰብሰብ ያለባቸው ለስድስት ቀናት ብቻ እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር። በስድስተኛው ዕለት “ለሁለት ቀን የሚሆን እንጀራ” መሰብሰብ ነበረባቸው፤ ምክንያቱም በሰባተኛው ቀን መና አይወርድላቸውም ነበር። ሰባተኛው ቀን “ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሰንበት” ስለሚሆን እያንዳንዱ ሰው ቤቱ ውስጥ መቀመጥ ነበረበት። (ዘፀአት 16:13-30) ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል አንዱ በሰንበት ምንም ሥራ መሠራት እንደሌለበት ያዝዛል። ይህ ቀን ቅዱስ ነበር። ይህንን ትእዛዝ መጣስ የሞት ቅጣት ያስከትል ነበር።—ዘፀአት 20:8-11፤ ዘኍልቍ 15:32-36
8 የሰንበት ሕግ ይሖዋ ለሕዝቡ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ደኅንነት እንደሚያስብ ያሳያል። ኢየሱስ “ሰንበት ለሰው ተፈጠረ” ብሏል። (ማርቆስ 2:27) ይህ ሕግ እስራኤላውያን እረፍት እንዲያደርጉ ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪያቸው ጋር ይበልጥ እንዲቀራረቡና ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳዩ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። (ዘዳግም 5:12) ቀኑ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ብቻ የተወሰነ ነበር። ከሚያደርጓቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካከል በቤተሰብ ሆኖ አምልኮ ማቅረብ፣ መጸለይና በአምላክ ሕግ ላይ ማሰላሰል ይገኙበታል። የሰንበት ዝግጅት፣ እስራኤላውያን ጊዜያቸውንና ኃይላቸውን ሁሉ ቁሳዊ ነገሮችን ለማሳደድ ከማዋል እንዲቆጠቡ አድርጓል። እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ ከማንኛውም ነገር የበለጠ ቦታ የሚሰጠው ከይሖዋ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደሆነ አስገንዝቧቸዋል። ኢየሱስ “‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” በማለት የማይለወጠውን መሠረታዊ ሥርዓት በድጋሚ ተናግሯል።—ማቴዎስ 4:4
9. የሰንበት ዝግጅት ለክርስቲያኖች ምን ትምህርት ይዟል?
9 በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ቃል በቃል የ24 ሰዓት የሰንበት እረፍት እንዲያደርጉ አይጠበቅባቸውም፤ ሆኖም ሰንበት እንዲሁ ያለፈ ታሪክ ብቻ አይደለም። (ቈላስይስ 2:16) እኛም ብንሆን መንፈሳዊ ጉዳዮችን ማስቀደም እንዳለብን የሚያሳስብ ሕግ አይደለም? ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት መሯሯጥ ወይም መዝናናት ከአምልኮታችን ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ከማከናወን መቅደም የለባቸውም። (ዕብራውያን 4:9, 10) ስለዚህ ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን:- “በሕይወቴ ውስጥ የማስቀድመው ነገር ምንድን ነው? ለጥናት፣ ለጸሎት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ ለመካፈል ቅድሚያውን እሰጣለሁ? ወይስ ሌሎች ጉዳዮች እንዲህ ላሉት እንቅስቃሴዎች ጊዜ አሳጥተውኛል?” መንፈሳዊ ጉዳዮችን የምናስቀድም ከሆነ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደማናጣ ይሖዋ አረጋግጦልናል።—ማቴዎስ 6:24-33
10. ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ በመመደብ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
10 መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማጥናት እንዲሁም ስላነበብናቸው ነገሮች በጥልቀት በማሰላሰል የምናሳልፈው ጊዜ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊረዳን ይችላል። (ያዕቆብ 4:8) ወደ 40 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ጀምሮ አዘውትራ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጊዜ የመደበች ሱዛን የተባለች እህት መጀመሪያ ላይ ጥናቱ የማያስደስትና አሰልቺ ሆኖባት እንደነበረ በግልጽ ተናግራለች። ነገር ግን ብዙ ባነበበች መጠን ጥናቷን እየወደደችው መጣች። አሁን በሆነ ምክንያት የግል ጥናት ካላደረገች በጣም ቅር ይላታል። እንዲህ ብላለች:- “ጥናት ይሖዋን እንዳውቀውና እንደ አባት አድርጌ እንዳየው ረድቶኛል። ይሖዋን ልተማመንበት፣ ልመካበትና በነፃነት ወደ እርሱ በጸሎት ልቀርብ እችላለሁ። ይሖዋ አገልጋዮቹን ምን ያህል እንደሚወድ፣ ለእኔ በግሌ እንዴት እንደሚያስብልኝና እንዴት እንደረዳኝ መመልከት መቻሌ በጣም ያስደስተኛል።” እኛም አዘውትረን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማርካት ከጣርን በእርግጥ ታላቅ ደስታ እናገኛለን!
አምላክ ቃርሚያን በተመለከተ የሰጠው ሕግ
11. ስለ ቃርሚያ የተሰጠው ሕግ ምን ምን እንዲደረግ ያዝዛል?
11 በሁለተኛ ደረጃ የምንመለከተው የሙሴ ሕግ ክፍል ደግሞ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው የመቃረም መብት ነው፤ ይህ መብት አምላክ ለሕዝቡ ደኅንነት አሳቢ እንደሆነ ያሳያል። ይሖዋ፣ አንድ እስራኤላዊ ገበሬ ምርቱን በሚሰበስብበት ጊዜ አጫጆች ትተውት ያለፉትን ችግረኞች እንዲሰበስቡ እንዲፈቀድላቸው አዝዞ ነበር። ገበሬዎች የእርሻቸውን ዳርና ዳር ሙልጭ አድርገው ማጨድ እንዲሁም ትተውት ያለፉትን የወይን ወይም የወይራ ፍሬ ለመልቀም መመለስ አይፈቀድላቸውም ነበር። በተጨማሪም ሳያውቁት ሜዳ ላይ ጥለውት የሄዱትን ክምር ተመልሰው መውሰድ አይችሉም ነበር። ይህ ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸው፣ ለመጻተኞች፣ ወላጅ ለሌላቸው ልጆችና ለመበለቶች የተደረገ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። ሥራው ለሚቃርሙት ሰዎች ትጋት የሚጠይቅባቸው መሆኑ ባያጠራጥርም ለልመና እንዳይዳረጉ ይረዳቸዋል።—ዘሌዋውያን 19:9, 10፤ ዘዳግም 24:19-22፤ መዝሙር 37:25
12. የቃርሚያ ዝግጅት ለገበሬዎች ምን አጋጣሚ ይሰጣቸው ነበር?
12 የቃርሚያ ሕግ ገበሬዎች ለችግረኞች ምን ያህል እህል መተው እንዳለባቸው አይወስንም። ገበሬዎቹ በእርሻቸው ዳርና ዳር ላይ የፈለጉትን ያህል እህል ሳያጭዱ የመተው መብት ነበራቸው። ይህ መብታቸው ልግስናን እንዲማሩ ረድቷቸዋል። እንዲሁም ገበሬዎቹ ምርት የሚሰጣቸውን ይሖዋን የሚያመሰግኑበት አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ለተቸገሩ የሚራራ ሁሉ . . . አምላክን ያከብራል” ይላል። (ምሳሌ 14:31) ቦዔዝ እንዲህ አድርጎ ነበር። በእርሱ እርሻ ላይ ትቃርም የነበረችው መበለቷ ሩት በርከት ያለ እህል እንድትሰበስብ እንዲፈቅዱላት ሠራተኞቹን አዝዞ ነበር። ይሖዋም ቦዔዝ ላሳየው ልግስና አብዝቶ ባርኮታል።—ሩት 2:15, 16፤ 4:21, 22፤ ምሳሌ 19:17
13. ከጥንቱ የቃርሚያ ሕግ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13 ቃርሚያን በተመለከተ ከተሰጠው ሕግ በስተጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት አልተለወጠም። ይሖዋ ሕዝቦቹ በተለይ ለችግረኞች ልግስና እንዲያሳዩ ይፈልጋል። ቸርነት ባደረግን መጠን የዚያኑ ያህል እንባረካለን። “ስጡ፤ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ስለሚሰፈርላችሁ፣ ጫን በተደረገ፣ በተነቀነቀና በተትረፈረፈ መልካም መስፈሪያ ተሰፍሮ በዕቅፋችሁ ይሰጣችኋል” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል።—ሉቃስ 6:38
14, 15. ልግስና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ለጋስ መሆናችን ለራሳችንም ሆነ ለምንረዳቸው ሰዎች ምን ጥቅሞች ሊያስገኝ ይችላል?
14 ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ” ሲል አሳስቦናል። (ገላትያ 6:10) ስለዚህ ክርስቲያን ወንድሞቻችን በእምነታቸው ምክንያት ፈተና አጋጥሟቸው መንፈሳዊ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ አሳቢነት ልናሳያቸው እንደሚገባ አያጠራጥርም። ነገር ግን ወደ መንግሥት አዳራሽ ለመሄድ ወይም ዕቃ ለመሸመት በሚፈልጉበት ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸው ይሆን? በጉባኤህ ውስጥ፣ ቤታቸው ሄደህ ብትጠይቃቸው ወይም ብትረዳቸው የሚደሰቱ በዕድሜ የገፉ፣ የታመሙ ወይም ከቤታቸው መውጣት የማይችሉ ሰዎች አሉ? እንዲህ ያለ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ትኩረት ለመስጠት የምንጥር ከሆነ፣ ይሖዋ ችግረኛ ሰዎች ለሚያቀርቡለት ጸሎት መልስ ለመስጠት ሊጠቀምብን ይችላል። ስለዚህ እርስ በርስ መተሳሰብ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፤ አስፈላጊውን እርዳታ ለሚሰጠውም ሰው ቢሆን ይጠቅማል። ለወንድሞቻችን ልባዊ ፍቅር ማሳየት ታላቅ ደስታና እርካታ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ሞገስ ያስገኝልናል።—ምሳሌ 15:29
15 ክርስቲያኖች ራስ ወዳዶች እንዳልሆኑ የሚያሳዩበት ሌላው ትልቁ መንገድ ደግሞ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ስለ አምላክ ዓላማ ለመናገር በማዋል ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) አንድን ሰው ራሱን ለይሖዋ ወደ መወሰን ደረጃ እንዲደርስ በመርዳት የሚገኘውን እርካታ የቀመሰ ሰው “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት እውነተኝነት መመልከት ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
ከስግብግብነት መጠበቅ
16, 17. አሥረኛው ትእዛዝ ምንን ያወግዛል? ለምንስ?
16 አሁን የምንመለከተው ሦስተኛው ሕግ ደግሞ አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ስግብግብነትን የሚያወግዘው አሥረኛው ትእዛዝ ነው። ሕጉ እንዲህ ይላል:- “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ።” (ዘፀአት 20:17) የሌላውን ልብ ማንበብ የሚችል ሰው ባለመኖሩ አንድ ሰው እንዲህ የመሰለውን ሕግ አውጥቶ ሌሎች እንዲያከብሩት ማስገደድ አይችልም። ስለዚህ አሥረኛው ትእዛዝ፣ የሙሴ ሕግ ከሰብዓዊ ሕግ የላቀ እንደሆነ ያሳያል። ሕጉ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የልብን ዝንባሌ ማንበብ በሚችለው በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ እንደሆነ እንዲገነዘብ አድርጎታል። (1 ሳሙኤል 16:7) ከሁሉም በላይ ይህ ትእዛዝ ተገቢ ላልሆኑ ድርጊቶች ዋነኛ ምክንያት በሆነው ነገር ላይ ያነጣጥራል።—ያዕቆብ 1:14
17 ስግብግብነትን የሚከለክለው ሕግ የአምላክ ሕዝቦች ከፍቅረ ነዋይ፣ ከስስትና ኑሯቸውን ከማማረር እንዲቆጠቡ ረድቷቸዋል። እንዲሁም ለመስረቅና የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም ከመፈተን ጠብቋቸዋል። ምንጊዜም ቢሆን እኛ ትልቅ ግምት የምንሰጠው ሀብት ያላቸው ወይም በሆነ መንገድ ከእኛ በተሻለ የተሳካላቸው የሚመስሉ ሰዎች መኖራቸው የማይቀር ነው። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች አስተሳሰባችንን እንዲቆጣጠሩ የምንፈቅድ ከሆነ ደስታችንን የምናጣ ከመሆኑም በላይ በሌሎች እንቀናለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስግብግብነት ‘የማይረባ አእምሮ’ መገለጫ እንደሆነ ይናገራል። በመሆኑም ከስግብግብነት መራቃችን በጣም ጥሩ ነው።—ሮሜ 1:28-30
18. በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ምን ዓይነት መንፈስ ተንሰራፍቷል? ምን ጎጂ ውጤቶችንስ ሊያስከትል ይችላል?
18 ዛሬ በዓለማችን የተንሰራፋው መንፈስ ፍቅረ ነዋይንና የፉክክር መንፈስን የሚያበረታታ ነው። የንግዱ ዓለም በማስታወቂያዎች አማካኝነት አዳዲስ ምርቶችን የማግኘት ጉጉት እንዲያድርብን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ‘እነዚህን ነገሮች ካላገኛችሁ ደስተኛ መሆን አትችሉም’ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህ፣ የይሖዋ ሕግ እጅግ የሚያወግዘው መንፈስ ነው። የይሖዋ ሕግ የሚቃወመው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ሌላው መንፈስ ደግሞ የተከፈለው ነገር ተከፍሎ ስኬት የማግኘትና ሀብት የማካበት ምኞት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቋል:- “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ . . . ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጕጕት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
19, 20. (ሀ) የይሖዋን ሕግ የሚወድ ሰው ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ለየትኞቹ ነገሮች ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ስለ ምን ጉዳይ እንመለከታለን?
19 የአምላክን ሕግ የሚወዱ ሰዎች ፍቅረ ነዋይ ምን አደጋ እንዳለው ስለሚገነዘቡ ጥበቃ ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል:- “ከራስ ጥቅም ይልቅ፣ ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል። ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል።” (መዝሙር 119:36, 72) እነዚህ ቃላት እውነት እንደሆኑ ማመናችን እንደ ፍቅረ ነዋይ፣ ስስትና ባለን ኑሮ እርካታ ማጣትን በመሳሰሉ ወጥመዶች ከመያዝ እንድንጠበቅ የሚረዳንን ሚዛናዊ አመለካከት ይዘን እንድንቀጥል ያደርገናል። ትልቅ ትርፍ የሚያስገኘው “እውነተኛ መንፈሳዊነት” እንጂ ሀብት ማካበት አይደለም።—1 ጢሞቴዎስ 6:6
20 ይሖዋ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር ከሰጠው ሕግ በስተጀርባ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ልክ ለሙሴ በተሰጡበት ዘመን እንደነበሩት ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ናቸው። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ባዋልናቸው መጠን ይበልጥ እየተረዳናቸው፣ እየወደድናቸውና ደስተኞች እየሆንን እንሄዳለን። ሕጉ በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን ይዞልናል፤ እነዚህ ትምህርቶች ያላቸው ዋጋማነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ገጸ ባሕርያት ሕይወትና ተሞክሮ ላይ ተንጸባርቋል። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ከእነዚህ ታሪኮች መካከል ጥቂቶቹን እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ መዝሙር ላይ ከሚገኙት 176 ቁጥሮች ውስጥ በ172ቱ ላይ የይሖዋ ትእዛዛት፣ ፍርዶች፣ ሕግጋት፣ ሥርዓቶች፣ ምሥክርነቶች (ማሳሰቢያዎች)፣ ቃል ወይም መንገዶች ተገልጸዋል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የመዝሙር 119 ጸሐፊ የይሖዋን ሕግ ይወድ የነበረው ለምንድን ነው?
• ክርስቲያኖች ከሰንበት ዝግጅት ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
• አምላክ ስለ ቃርሚያ ያወጣው ሕግ ምን ዘላቂ ጠቀሜታ አለው?
• ስግብግብነትን የሚያወግዘው ትእዛዝ ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰንበት ሕግ የትኛውን ነጥብ ያጎላል?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቃርሚያን በተመለከተ የተሰጠው ሕግ ምን ያስተምረናል?