በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ማሳሰቢያህ ለእኔ ደስታዬ ነው”

“ማሳሰቢያህ ለእኔ ደስታዬ ነው”

“ማሳሰቢያህ ለእኔ ደስታዬ ነው”

“ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” —ሮሜ 15:4

1. ይሖዋ ማሳሰቢያ የሚሰጠን እንዴት ነው? እነዚህ ማሳሰቢያዎች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?

 ይሖዋ፣ ይህ አስቸጋሪ ጊዜ የሚፈጥረውን ጫና መቋቋም እንዲችሉ የሚረዷቸውን ማሳሰቢያዎች ለአገልጋዮቹ ይሰጣል። ከእነዚህ ማሳሰቢያዎች መካከል አንዳንዶቹን የምናገኛቸው በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወቅት ሲሆን ሌሎቹን ደግሞ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሚቀርቡት ትምህርቶች ወይም ወንድሞች በሚሰጧቸው ሐሳቦች አማካኝነት ነው። በእነዚህ መንገዶች ከምናገኘው ትምህርት ውስጥ አብዛኛው ለእኛ አዲስ አይደለም። ቀደም ሲል ተመሳሳይ ሐሳብ አጋጥሞን ሊሆን ይችላል። ሆኖም የመርሳት ባሕርይ ስላለን የይሖዋን ዓላማ፣ ሕግጋትና መመሪያዎች በተመለከተ በየጊዜው ማሳሰቢያ ማግኘት ያስፈልገናል። የአምላክን ማሳሰቢያዎች ማድነቅ ይገባናል። እነዚህ ማሳሰቢያዎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ሕይወት እንድንመራ ባደረጉን ምክንያቶች ላይ እንድናተኩር በመርዳት መንፈሳችንን ያድሱልናል። መዝሙራዊው “ምስክርነትህ [“ማሳሰቢያህ፣” NW] ለእኔ ደስታዬ ነው” ሲል ለይሖዋ የዘመረው በዚህ ምክንያት ነው።መዝሙር 119:24

2, 3. (ሀ) ይሖዋ እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስከ አሁን ተመዝግበው እንዲቆዩ ያደረገው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እናያለን?

2 የአምላክ ቃል የተጻፈው ከበርካታ ምዕተ ዓመታት በፊት ቢሆንም አሁንም ኃይል አለው። (ዕብራውያን 4:12) መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የተገለጹትን ሰዎች እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ይዘግባል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ባሕልና አስተሳሰብ ከአሁኑ በእጅጉ የተለየ ቢሆንም በዚያ ዘመን የኖሩ ሰዎች ያጋጠሟቸውና እኛ የሚያጋጥሙን ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው። ለእኛ ጥቅም ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት በርካታ ታሪኮች፣ ይሖዋን ይወዱና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም እንኳን በታማኝነት ያገለግሉት ስለነበሩ ሰዎች ልብ የሚነኩ ምሳሌዎችን ይዘውልናል። ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ አምላክ የሚጠላውን ባሕርይ ይገልጻሉ። ይሖዋ ማሳሰቢያ እንዲሆኑ ሲል ጥሩና መጥፎ የሆኑ የሰዎች ታሪኮችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩ አድርጓል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በማስመልከት እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።”ሮሜ 15:4

3 እስቲ ዳዊት ከሳኦል ጋር ስለነበረው ግንኙነት፣ ስለ ሐናንያና ሰጲራ እንዲሁም ዮሴፍ የጲጥፋራ ሚስት በተፈታተነችው ጊዜ ምን እንዳደረገ የሚገልጹትን ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እንመልከት። ከሦስቱም ታሪኮች በጣም ጠቃሚ ትምህርቶች እናገኛለን።

ለአምላክ ዝግጅቶች ታማኝ መሆን

4, 5. (ሀ) በንጉሥ ሳኦልና በዳዊት መካከል ምን ተፈጥሮ ነበር? (ለ) ዳዊት፣ ሳኦል ላሳየው ጥላቻ ምን ዓይነት ስሜት ነበረው?

4 ንጉሥ ሳኦል ለይሖዋ ታማኝ እንዳልሆነ በመረጋገጡ የአምላክን ሕዝብ ለመግዛት የሚበቃ ሆኖ አልተገኘም። በዚህም ምክንያት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጣ፤ ከዚያም ይሖዋ ወደፊት የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ዳዊትን እንዲቀባው ነቢዩ ሳሙኤልን ላከው። ዳዊት በውጊያ ወቅት ታላቅ ጀብዱ በመፈጸሙ ሕዝቡ አወድሶት ነበር፤ ከዚያ በኋላ ሳኦል ዳዊትን እንደ ተቀናቃኝ አድርጎ ይመለከተው ጀመር። በተደጋጋሚ ሊገድለውም ሞክሮ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ከዳዊት ጋር ስለነበር ከተደረገበት የግድያ ሙከራ ሁሉ ሊያመልጥ ችሏል።1 ሳሙኤል 18:6-12, 25፤ 19:10, 11

5 ዳዊት ለበርካታ ዓመታት እየተሰደደ ለመኖር ተገድዶ ነበር። ሳኦልን መግደል የሚችልበትን አጋጣሚ ሲያገኝ አብረውት ያሉት ሰዎች፣ ይሖዋ ጠላቱን በእጁ አሳልፎ እንደሰጠው በመናገር አጋጣሚውን እንዲጠቀምበት ያበረታቱት ነበር። ዳዊት ግን እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። ይህ የሆነው ለይሖዋ ታማኝ ስለነበረና ሳኦል በአምላክ ሕዝብ ላይ እንዲነግሥ የተቀባ በመሆኑ ምክንያት ያከብረው ስለነበረ ነው። ሳኦልን የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የቀባው ይሖዋ አይደለም? ልክ እንደዚሁ ይሖዋ ተገቢ ነው በሚለው ጊዜ ከሥልጣን ያወርደዋል። ዳዊት በዚህ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት መብት እንደሌለው ተናግሯል። ንጉሥ ሳኦል ለእርሱ ያለውን ጥላቻ እንዲያለዝብ ሲል አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ካደረገ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል። እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ!”1 ሳሙኤል 24:3-15፤ 26:7-20

6. የዳዊትንና የሳኦልን ታሪክ መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

6 ይህ ታሪክ ትልቅ ትምህርት ይዟል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች ለምን ይነሳሉ ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ? የችግሩ መንስኤ አንድ ሰው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት መፈጸሙ ሊሆን ይችላል። ይህ ሰው የፈጸመው ስህተት ከባድ ላይሆን ቢችልም ድርጊቱ ግን አንተን ይረብሽሃል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ለክርስቲያን ወንድምህ ባለህ አሳቢነትና ለይሖዋ ባለህ ታማኝነት ተነሳስተህ ግለሰቡን በደግነት በማነጋገር ችግሩን ለመፍታት ትፈልግ ይሆናል። ሆኖም ችግሩ ቢቀጥልስ? አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ካደረግክ በኋላ ጉዳዩን ለይሖዋ ለመተው ትወስን ይሆናል። ዳዊትም ያደረገው ይህንኑ ነው።

7. በደል ቢፈጸምብን ወይም በጭፍን ብንጠላ የዳዊትን ምሳሌ በመኮረጅ ምን ማድረግ ይገባናል?

7 በተጨማሪም በማኅበራዊ ኑሮ ረገድ በደል ሊፈጸምብህ ወይም ጭፍን ሃይማኖታዊ ጥላቻ ሊደርስብህ ይችላል። ምናልባት በዚህ ረገድ ማድረግ የምትችለው ነገር ውስን ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ምንም ማድረግ አትችል ይሆናል። እንዲህ ያለውን ሁኔታ መቋቋም ሊከብድ ቢችልም ዳዊት በደል ሲፈጸምበት የያዘው አቋም ትምህርት ይሆነናል። ዳዊት የጻፋቸው ስሜትን የሚነኩ መዝሙሮች፣ አምላክ በሳኦል ከመያዝ እንዲጠብቀው ያቀረባቸው ልባዊ ጸሎቶች ብቻ ሳይሆኑ ለይሖዋ ታማኝ እንደሆነና ስሙ እንዲወደስ እንደሚፈልግ የሚያሳዩ ናቸው። (መዝሙር 18:1-6, 25-27, 30-32, 48-50፤ 57:1-11) ዳዊት፣ ሳኦል ተገቢ ያልሆነ ድርጊት መፈጸሙን ለዓመታት ቢቀጥልም እንኳን ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት አላጓደለም። እኛም ብንሆን በደል ቢፈጸምብንም እንዲሁም ሰዎች የተለያዩ ችግሮች ቢያደርሱብንም ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኝ ሆነን መቀጠል አለብን። ይሖዋ ሁኔታችንን በሚገባ እንደሚያውቅ እርግጠኛ መሆን እንችላለን።መዝሙር 86:2

8. በሞዛምቢክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ ያላቸው ታማኝነት ሲፈተን ምን አደረጉ?

8 በመከራ ጊዜ ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ረገድ ምሳሌ ከሚሆኑን አንዳንድ የዘመናችን የአምላክ አገልጋዮች መካከል በሞዛምቢክ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ይገኙበታል። የአንድ ሽምቅ ተዋጊ ቡድን የታጠቁ አባላት በ1984 መንደሮቻቸውን በተደጋጋሚ በማጥቃት ይዘርፉ፣ ቤቶችን ያቃጥሉና ግድያ ይፈጽሙ ነበር። እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለመጠበቅ ምንም ማድረግ የሚችሉ አይመስልም ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎች በወታደራዊ እንቅስቃሴው ውስጥ እንዲገቡ ወይም በሌሎች መንገዶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ያስገድዷቸው ነበር። በዚያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ማድረጋቸው ከክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ጋር እንደሚጋጭ አሰቡ። ስለዚህ የተባሉትን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም፤ ይህም ሽምቅ ተዋጊዎቹን አስቆጣቸው። በዚያ የችግር ወቅት ወደ 30 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ተገድለዋል፤ ነገር ግን የአምላክ ሕዝቦች የግድያ ዛቻ እንኳን ታማኝነታቸውን ሊያስጥሳቸው አልቻለም። a ልክ እንደ ዳዊት በደል ቢፈጸምባቸውም ጸንተዋል፤ በኋላም ድል አድራጊ ለመሆን በቅተዋል።

የማስጠንቀቂያ ምሳሌ

9, 10. (ሀ) ከአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሐናንያና ሰጲራ የፈጸሙት ድርጊት ስህተቱ ምን ላይ ነበር?

9 በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ግለሰቦች ልናስወግደው የሚገባንን ባሕርይ በተመለከተ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆኑናል። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተሳሳተ ነገር አድርገው መጥፎ ውጤት የመጣባቸውን የአምላክ አገልጋዮችና የሌሎች በርካታ ሰዎችን ታሪክ ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) ከእነዚህ ዘገባዎች መካከል በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የሆኑ ሐናንያና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስት ታሪክ ይገኝበታል።

10 በ33 የጰንጠቆስጤ በዓል ከተከበረ በኋላ፣ ከሐዋርያት ጋር አብረው በመቆየት ከእነርሱ ለመጠቀም በኢየሩሳሌም ለቀሩ አዳዲስ አማኞች ቁሳዊ እርዳታ ማቅረብ አስፈልጎ ነበር። አንዳንድ የጉባኤው አባላት ማንም የሚያስፈልገውን ነገር እንዳያጣ ሲሉ ንብረታቸውን በመሸጥ እርዳታ ያደርጉ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:41-45) ሐናንያና ሰጲራ መሬታቸውን ከሸጡ በኋላ ከሽያጩ ያገኙትን ገንዘብ ሁሉ የሰጡ በማስመሰል ከተቀበሉት ግማሽ ያህሉን ብቻ ወደ ሐዋርያት ወሰዱ። ሐናንያና ሰጲራ የፈለጉትን ያህል የመስጠት መብት እንዳላቸው አያጠራጥርም፤ ነገር ግን ለመስጠት የተነሳሱበት ዓላማ የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ የማታለል ድርጊት ፈጽመዋል። የሌሎችን አድናቆት ለማትረፍና ያልሆኑትን ሆነው ለመታየት ፈልገው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ አታላይነታቸውንና ግብዝነታቸውን አጋለጠ፤ ይሖዋም ቀስፏቸው ሞቱ።የሐዋርያት ሥራ 5:1-10

11, 12. (ሀ) ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ሐቀኝነት ከሚሰጧቸው ማሳሰቢያዎች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ። (ለ) ሐቀኝነት ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

11 ሰዎች እንዲያደንቁን ብለን ሐሰት ለመናገር ተፈትነን የምናውቅ ከሆነ የሐናንያና የሰጲራ ታሪክ ትልቅ ማሳሰቢያ ይሆነናል። ሰዎችን ማታለል እንችል ይሆናል፤ ይሖዋን ግን ፈጽሞ ማታለል አንችልም። (ዕብራውያን 4:13) ውሸታሞች ከዓመጸኞች በምትጸዳው ምድር ላይ መኖር ስለማይችሉ አንዳችን ለሌላው ሐቀኛ መሆን እንዳለብን ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ይመክሩናል። (ምሳሌ 14:2፤ ራእይ 21:8፤ 22:15) ይህ የሆነበት ምክንያት ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። ሐሰት የሆኑ ነገሮችን ሁሉ የሚያስፋፋው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።ዮሐንስ 8:44

12 ሐቀኞች መሆናችን በርካታ ጥቅሞች ያስገኝልናል። ከእነዚህም መካከል ንጹሕ ሕሊናንና በሌሎች ዘንድ ተአማኒነት በማትረፍ የሚገኘውን እርካታ መጥቀስ ይቻላል። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ሐቀኞች ስለሆኑ ሥራ ያገኛሉ ወይም ከሥራቸው የመፈናቀል አደጋ አይገጥማቸውም። ሐቀኝነት የሚያስገኘው ከሁሉ የላቀው ጥቅም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ወዳጅነት እንድንመሠርት የሚረዳን መሆኑ ነው።መዝሙር 15:1, 2

ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅ

13. ዮሴፍ ምን አጋጥሞት ነበር? ምንስ አደረገ?

13 የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በ17 ዓመቱ በባርነት ተሸጦ ነበር። በኋላ ላይ በግብፃዊው ባለ ሥልጣን በጲጥፋራ ቤት መሥራት ጀመረ፤ የጌታውም ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለችበት። ይህች ሴት መልከ መልካም ወጣት ከሆነው ከዮሴፍ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም በመፈለጓ በየዕለቱ “አብረኸኝ ተኛ” እያለች ትጎተጉተው ነበር። ዮሴፍ የሚገኘው ቤተሰቡ ከሚኖርበት በጣም በሚርቅ አገር ሲሆን በአካባቢውም እርሱን የሚያውቀው ሰው አልነበረም። በመሆኑም ማንም ሰው ሳያውቅበት ከዚህች ሴት ጋር ግንኙነት ማድረግ ይችል ነበር። ነገር ግን በኋላ ላይ የጲጥፋራ ሚስት ልብሱን ጨምድዳ በያዘች ጊዜ አምልጧት ከቤት ወጣ።ዘፍጥረት 37:2, 18-28፤ 39:1-12

14, 15. (ሀ) የዮሴፍ ታሪክ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? (ለ) አንዲት ክርስቲያን የአምላክን ማሳሰቢያዎች በመስማቷ አመስጋኝ የሆነችው ለምንድን ነው?

14 ዮሴፍ ያደገው ፈሪሃ አምላክ ባለው ቤተሰብ ውስጥ በመሆኑ ወንድና ሴት ሳይጋቡ የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንደማይገባቸው ያውቅ ነበር። “እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” በማለት ጠይቋል። ዮሴፍ እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ የደረሰው፣ አምላክ በዔድን ገነት ለሰው ልጆች ስላወጣው ደንብ ማለትም መጋባት የሚገባቸው አንድ ወንድና አንዲት ሴት ብቻ መሆን እንዳለባቸው ያውቅ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። (ዘፍጥረት 2:24) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ዮሴፍ ያጋጠመውን ሁኔታ የተወጣበትን መንገድ በመኮረጅ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። በአንዳንድ ቦታዎች ስለ ፆታ ግንኙነት በጣም ልል የሆነ አመለካከት ስላለ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣቶች የእኩዮቻቸው ማፌዣ ይሆናሉ። አዋቂዎችም ቢሆኑ የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው የተለመደ ነው። ስለዚህ የዮሴፍ ታሪክ ለዘመናችንም የሚጠቅም ማሳሰቢያ ይዟል። አሁንም ቢሆን ዝሙትና ምንዝር በአምላክ የአቋም ደረጃ መሠረት የኃጢአት ድርጊቶች ናቸው። (ዕብራውያን 13:4) ተገቢ ያልሆነ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ለተደረገባቸው ጫና እጃቸውን የሰጡ በርካታ ሰዎች፣ ይህን ድርጊት መፈጸም እንደማይገባ የሚያረጋግጡ አጥጋቢ ምክንያቶች እንዳሉ ይስማማሉ። ከሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች መካከል ሐፍረት፣ የሕሊና መቆሸሽ፣ ቅናት፣ እርግዝናና በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳስቡን ዝሙት የሚፈጽም ሰው “በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል።”1 ቆሮንቶስ 5:9-12፤ 6:18፤ ምሳሌ 6:23-29, 32

15 ጄኒ b የተባለች ያላገባች የይሖዋ ምሥክር ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች በጣም አመስጋኝ ነች። መልከ ቀና የሆነ አንድ የሥራ ባልደረባዋ የፍቅር ስሜት ያሳያት ነበር። ሰውየው ከጄኒ ምንም ዓይነት የአጸፋ ምላሽ ሲያጣ ይበልጥ ትኩረት ይሰጣት ጀመር። “የሥነ ምግባር ንጽሕናዬን ለመጠበቅ በጣም እታገል ነበር፤ ምክንያቱም የተቃራኒ ፆታን ትኩረት ማግኘት በጣም አስደሳች ነው” በማለት ሐቁን ተናግራለች። ይሁን እንጂ ሰውየው በርካታ የሴት ጓደኞች እንደነበሩትና እርሷንም ተጨማሪ ጓደኛ ሊያደርጋት እየሞከረ መሆኑን ደረሰችበት። ጄኒ ፈተናውን የምትቋቋምበት አቅም እንዳጣች በሚሰማት ጊዜ ይሖዋን ለእርሱ ታማኝ ሆና ለመጽናት እንዲረዳት ትለምነው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በምትመረምርበት ጊዜ ያገኘቻቸው ትምህርቶች እንዳትዘናጋ የሚያነቁ ማሳሰቢያዎች ሆነው አግኝታቸዋለች። ከእነዚህ ማሳሰቢያዎች መካከል የዮሴፍና የጲጥፋራ ሚስት ታሪክ ይገኝበታል። “ይሖዋን ምን ያህል እንደምወደው እስካስታወስኩ ድረስ እንዲህ ያለውን ክፉ ድርጊትም ሆነ ኃጢአት እፈጽማለሁ ብዬ መፍራት አይገባኝም” ስትል ተናግራለች።

የአምላክን ማሳሰቢያዎች ስማ!

16. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ግለሰቦች ታሪክ በመመርመርና በማሰላሰል ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ሁላችንም፣ ይሖዋ አንዳንድ ታሪኮች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው እንዲቆዩልን ያደረገው ለምን እንደሆነ ለመገንዘብ በመጣር ለእርሱ የአቋም ደረጃዎች ያለንን አድናቆት ከፍ ማድረግ እንችላለን። እነዚህ ታሪኮች ምን ትምህርት ይሰጣሉ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ገጸ ባሕርያት ካሳዩአቸው ጠባዮች ወይም ዝንባሌዎች መካከል የትኞቹን ማንጸባረቅ አለብን? የትኞቹንስ ማስወገድ ይኖርብናል? በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች በአምላክ ቃል ውስጥ ተጠቅሰዋል። መለኮታዊ መመሪያን የምንወድ ሁሉ፣ ይሖዋ በጥሩ ሁኔታ እንዲመዘገቡ ካደረገልን ምሳሌዎች የምናገኘውን ትምህርት ጨምሮ ሕይወት ሰጪ ለሆነው ጥበብ ጥማት በማዳበር ጥቅም ማግኘት እንችላለን። የዚህ መጽሔት የተለያዩ እትሞች ከላይ እንደተገለጹት የመሰሉ ትምህርት የሚሰጡ ታሪኮችን በተደጋጋሚ ይዘው ሲወጡ ቆይተዋል። ለምን እነዚህን ታሪኮች አትመረምርም?

17. የይሖዋን ማሳሰቢያዎች እንዴት ታያቸዋለህ? ለምንስ?

17 ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ለሚጣጣሩ ሰዎች ለሚያሳየው ፍቅራዊ አሳቢነት ምንኛ አመስጋኞች ነን! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሱት ወንዶችና ሴቶች ሁሉ እኛም ፍጹማን እንዳልሆንን የተረጋገጠ ነው። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ያደረጓቸውን ነገሮች በተመለከተ የተጻፈው ዘገባ በጣም ጠቃሚ ትምህርት ይሰጠናል። የይሖዋን ማሳሰቢያዎች በመስማት ከባድ ስህተት ከመፈጸም ልንጠበቅና በጽድቅ ጎዳና የተጓዙ ሰዎችን መልካም ምሳሌነት ለመኮረጅ እንችላለን። እንዲህ ካደረግን እንደ መዝሙራዊው “ምስክርነቱን [“ማሳሰቢያውን፣” NW] የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት የተባረኩ ናቸው፤ ነፍሴ ምስክርነትህን [“ማሳሰቢያህን፣” NW] ትጠብቃለች፤ እጅግ እወደዋለሁና” ብለን መዘመር እንችላለን።መዝሙር 119:2, 167

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የ1996 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 160-162 ተመልከት።

b ስሟ ተቀይሯል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ዳዊት ለሳኦል ከነበረው አመለካከት ምን ትምህርት እናገኛለን?

• የሐናንያና የሰጲራ ታሪክ ምን ያስተምረናል?

• በተለይ በዛሬው ጊዜ የዮሴፍ ታሪክ ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት ሳኦል እንዲገደል ያልፈቀደው ለምንድን ነው?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሐናንያና ከሰጲራ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሴፍ የፆታ ብልግና እንዲፈጽም የቀረበለትን ጥያቄ ያልተቀበለው ለምንድን ነው?