በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምን ያህል ደስተኛ ነህ?

ምን ያህል ደስተኛ ነህ?

ምን ያህል ደስተኛ ነህ?

ምናልባት አንተም ‘ምን ያህል ደስተኛ ነኝ?’ እያልክ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል። የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያዎች አንተም ሆንክ ሌሎች ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ እንደምትሰጡ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ሆኖም ሥራቸው ቀላል አይደለም። ሰዎች ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ለማወቅ መሞከር አንድ ባል ለሚስቱ ያለውን ፍቅር ወይም አንድ የቤተሰብ አባል በሚሞትበት ጊዜ የሚከሰተውን ሐዘን መጠን ለመለካት እንደመሞከር ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ስሜትን በትክክል መለካት አዳጋች ነው። ሆኖም ሳይንቲስቶች አንድ ሐቅ ያስገነዝቡናል:- ሁሉም ሰው ደስተኛ መሆን ይችላል።

የሰው ልጆች ደስተኛ መሆን እንዲችሉ ሆነው የተፈጠሩ ቢሆንም የሚደርሱባቸው ከባድ ችግሮች ደስተኞች እንዳይሆኑ ያደርጓቸዋል። የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት:- በአንዳንድ ከተማዎች፣ በኤድስ ምክንያት ብዙ ሰዎች በመሞታቸው ለቀብር እንኳ ቦታ ታጥቷል። በመሆኑም የቆዩት መቃብሮች ተቆፍረው በቅርቡ የሞቱት ሰዎች እንዲቀበሩ ባለ ሥልጣናት ፈቃድ ሰጥተዋል። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የሬሳ ሣጥን መሥራት ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሞያ ሆኗል። የምትኖረው የትም ይሁን የት፣ የማይድን በሽታ የያዛቸው ሰዎች እንዲሁም የሚወዷቸው የቤተሰባቸው አባላትና ጓደኞቻቸው የሞቱባቸው ሰዎች ፊት ላይ የሚነበበውን ሐዘን ሳትመለከት አትቀርም።

በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁኔታስ ምን ይመስላል? ሁኔታዎች በድንገት ተለውጠው ሰዎች ሳያስቡት ንብረታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ በርካታ ጡረተኞች፣ የጡረታ አበላቸውን በማጣታቸው ምክንያት ተመልሰው ወደ ሥራ ለመግባት ተገደዋል። ብዙውን ጊዜ ለሕክምና የሚወጣ ወጪ ቤተሰቡ ያለውን ገንዘብ በሙሉ የሚያሟጥጥ ሆኗል። አንድ የሕግ አማካሪ “ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች [ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ምክር ለመጠየቅ] ሲመጡ አንጀትህን ይበሉሃል” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “አብዛኛውን ጊዜ ‘[በቂ ገንዘብ ማግኘት እንድትችል] ቤትህን መሸጥ ሊኖርብህ ነው’ እያልክ መንገር ይኖርብሃል” ብለዋል። ሆኖም የገንዘብ ጉዳይ የማያሳስባቸው ሰዎችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እነርሱም ደስታ ያጡ ይሆን?

የአንዳንድ ግለሰቦች ሕይወት ታዋቂ ከሆነው የሙዚቃ ደራሲ ከሪቻርድ ሮጀርስ ጋር ተመሳሳይነት አለው። እርሱን በተመለከተ እንዲህ ተብሎለት ነበር:- “[የእርሱን ያህል] ብዙዎችን ያስደሰቱ ሰዎች ጥቂት ናቸው።” ዘፈኖቹ ለሌሎች ሰዎች ደስታ የሚያስገኙ ቢሆኑም እርሱ ግን በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይሠቃይ ነበር። ብዙ ሰዎች እንደሚመኙት ገንዘብ ማግኘትና ዝናን ማትረፍ ችሎ ነበር፤ ይሁን እንጂ ደስተኛ ነበር? አንድ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “[ሮጀርስ] በሥራው የተዋጣለትና የተንደላቀቀ ኑሮ የነበረው ከመሆኑም በላይ ከሥራ ባልደረባው ጋር በመሆን ሁለት የፑሊትጸር ሽልማቶችን አግኝቷል። አብዛኛውን ጊዜ [ግን] ደስታ የራቀውና በጭንቀት የተዋጠ ሰው ነበር።”

ደስታ ለማግኘት ወደ ሀብት ዞር ማለት አብዛኛውን ጊዜ አታላይ መሆኑን ሳታስተውል አትቀርም። በቶሮንቶ፣ ካናዳ የሚወጣው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለ ጋዜጣ ዘጋቢ ብዙ ሀብታም ሰዎች “ብቸኝነትና ባዶነት” እንደሚሰማቸው ገልጿል። ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ ምክር የሚለግሱ አንድ ሰው እንዳሉት ሀብታም ወላጆች ልጆቻቸውን በገንዘብና ገንዘብ ሊገዛቸው በሚችላቸው ነገሮች ሲያንበሸብሿቸው ‘የልጆቻቸውን የወደፊት ሕይወት እያበላሹ እንደሆነ’ አይገነዘቡም።

ደስተኛ ለመሆን የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ይኖር ይሆን?

አንድ ተክል እንዲያብብ ከተፈለገ ጥሩ አፈር፣ ውኃና ተስማሚ አየር ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጉ አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ ተመራማሪዎች ተገንዝበዋል። ከእነዚህም መካከል ጥሩ ጤንነት፣ ትርጉም ያለው ሥራ፣ በቂ ምግብ፣ መጠለያና ልብስ እንዲሁም አዲስ ነገር የመሥራት ፍላጎታችንን ማሟላትና እውነተኛ ወዳጆችን ማፍራት ይገኙበታል።

እነዚህ ሁኔታዎች አንድ ሰው ደስተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ቢባል ሳትስማማ አትቀርም። ሆኖም ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። ይኸውም “ደስተኛ አምላክ” ስለሆነው ስለ ይሖዋ ማወቅ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ይህ እውቀት ደስተኛ ለመሆን የሚረዳው እንዴት ነው? ደስተኞች ለመሆን እንድንችል አድርጎ የፈጠረን ይሖዋ ነው። በመሆኑም ደስተኛ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልገን ጠንቅቆ ያውቃል። ይሖዋ፣ ሰዎች በማንኛውም ቦታ ወይም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም ዘላቂ ደስታ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ የሚጠቁማቸው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

© Gideon Mendel/CORBIS

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ አበባ እንደሚያወጣ ተክል፣ ደስታም እንዲያብብ ከተፈለገ በደንብ መያዝ ያስፈልገዋል