በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴሌቪዥን ለልጆቻችሁ ጥሩ ሞግዚት ሊሆን ይችላል?

ቴሌቪዥን ለልጆቻችሁ ጥሩ ሞግዚት ሊሆን ይችላል?

ቴሌቪዥን ለልጆቻችሁ ጥሩ ሞግዚት ሊሆን ይችላል?

አንዳንዴ ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ ሲባል ልጆችን ቴሌቪዥን እንዲያዩ መተዉ ጥሩ መስሎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም ይህ በልጆቻችሁ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት “ገና ጨቅላ የሆኑ ሕፃናት እንኳ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ስሜት የሚነኩ መልእክቶች ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው ይችላሉ” ሲል ይገልጻል። በቅርቡ በተደረገ ጥናት፣ የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች አንዲት ተዋናይ በፊልሙ ላይ ለሚታየው አሻንጉሊት ያላትን ስሜት በተለያየ መንገድ ስትገልጽ የሚያሳይ አጭር የቴሌቪዥን ትርኢት እንዲመለከቱ ተደርጎ ነበር። መጽሔቱ እንደሚከተለው ይላል:- “ተዋናይዋ አሻንጉሊቱን እንደፈራችው ስታሳይ ልጆቹ በአሻንጉሊቱ ለመጫወት ካለመፈለጋቸውም በላይ መፍራት፣ መኮሳተር፣ የጥላቻ ስሜት ማሳየት ወይም ማልቀስ ጀመሩ። ሆኖም ተዋናይዋ ለአሻንጉሊቱ ጥሩ ስሜት እንዳላት የሚገልጽ ሁኔታ ስታሳይ ሕፃናቱ በአሻንጉሊቱ መጫወት ይፈልጉ ነበር።”

በግልጽ ማየት እንደምንችለው ቴሌቪዥን በሕፃናት ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል። ቴሌቪዥን በልጆች ላይ ስለሚያሳድረው ዘላቂ ውጤትስ ምን ለማለት ይቻላል? በጃፓን፣ ኩራሺኪ በሚገኘው በካዋሳኪ የሕክምና ኮሌጅ የሕፃናት ጤና አጠባበቅ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ናኦኪ ካታኦካ በዝምታ የተዋጡና ፊታቸው ላይ ምንም ስሜት የማይነበብባቸውን ብዙ ልጆች ተመልክተዋል። እነዚህ ልጆች በሙሉ ለረጅም ጊዜ ቴሌቪዥን ወይም ቪዲዮ ሲመለከቱ የቆዩ ናቸው። እኚህ ዶክተር አፍ መፍታት ያቃተው አንድ የሁለት ዓመት ልጅ አጋጥሟቸው የነበረ ሲሆን ይህ ልጅ ከአንድ ዓመቱ ጀምሮ ነጋ ጠባ ቴሌቪዥን ይመለከት ነበር። የዚህ ልጅ የመናገር ችሎታ መዳበር የጀመረው እናትዬው ዶክተር የሰጣትን ምክር ተቀብላ ቴሌቪዥን እንዳይመለከት ካደረገችና ከልጇ ጋር መጫወት ከጀመረች በኋላ ብቻ ነበር። አዎን፣ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መነጋገር ይኖርባቸዋል።

የቤተሰብ መሥራች የሆነው ይሖዋ አምላክ ወላጆችና ልጆች ሊነጋገሩበት የሚገባውን ከሁሉ የበለጠ ጠቃሚ ጉዳይ ገልጿል። ከረጅም ጊዜ በፊት ለሕዝቦቹ፣ የአምላክን ቃል “ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር” ሲል አሳስቧቸዋል። (ዘዳግም 6:7) በቃልም ሆነ በምሳሌ በተሻለ ሁኔታ ለልጁ “የሚሄድበትን መንገድ” ማስተማርና ማሠልጠን የሚችለው ወላጅ እንጂ ቴሌቪዥን አይደለም።—ምሳሌ 22:6