በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተለያዩ ሕዝቦች በሚኖሩባት በኡጋንዳ የታየ እድገት

የተለያዩ ሕዝቦች በሚኖሩባት በኡጋንዳ የታየ እድገት

የተለያዩ ሕዝቦች በሚኖሩባት በኡጋንዳ የታየ እድገት

በታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ምሥራቃዊና ምዕራባዊ ክፍሎች መካከል የምትገኘው እንዲሁም የምድር ወገብ የሚያቋርጣት ኡጋንዳ አስደናቂ ውበት የተጎናጸፈች አገር ናት። የአገሪቱ መልክዓ ምድር ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ ሲሆን ልምላሜ የተላበሰችና ድንቅ በሆኑ እንስሳት የተሞላች ነች። አገሪቱ በአፍሪካ ከሚገኙት ከፍተኛ ቦታዎች መካከል የምትመደብ እንደመሆኗ መጠን ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት ከመሆኗም ሌላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን የሸፈኑ ማራኪ ሸንተረሮች ተንጣለው ይታዩባታል።

በአነስተኛ የቆዳ ስፋት ውስጥ በረዷማም ሆነ ሞቃታማ ክልሎችን አካትተው የያዙ አገራት እጅግ ውስን ሲሆኑ ከእነዚህም አንዷ ኡጋንዳ ነች። ኡጋንዳ፣ በምዕራብ በኩል ከሚገኙትና አናታቸው በበረዶ ከተሸፈኑት ከማውንቴንስ ኦቭ ዘ ሙን ወይም ከሩዌንዞሪ የተራራ ሰንሰለት አንስቶ በምሥራቅ በኩል እስካለው ከፊል በረሃማ ምድር ድረስ ያለውን አካባቢ ትሸፍናለች። በኡጋንዳ ዝሆን፣ ጎሽና አንበሳ ማግኘት ይቻላል። ተራራዎቹና ጥቅጥቅ ያሉት ደኖች ለጉሬላዎች፣ ለቺምፓንዚዎችና ከ1,000 በላይ ለሚሆኑ የአእዋፍ ዝርያዎች በመኖሪያነት ያገለግላሉ። አብዛኛው የአፍሪካ አህጉር ለድርቅና ለረሃብ የተጋለጠ መሆኑ ባይካድም፣ ኡጋንዳ በዓለማችን ጨዋማ ካልሆኑት ሐይቆች መካከል በስፋቱ የሁለተኛነት ደረጃ የያዘውን የቪክቶሪያን ሐይቅ ጨምሮ በርካታ ሐይቆችና ወንዞች ይገኙባታል። የቪክቶሪያ ሐይቅ በስተ ሰሜን በኩል ለአባይ ወንዝ ገባር ነው። የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል ይህቺን አገር “የአፍሪካ ዕንቁ” ሲሉ መጥራታቸው አያስገርምም።

‘ዕንቁዋ’ አሁንም ታንጸባርቃለች

የኡጋንዳ ዋነኛ መስህብ ግን ተግባቢና እንግዳ ተቀባይ የሆኑት እንዲሁም የተለያየ ባሕል ያላቸው ሕዝቦቿ ናቸው። “የክርስቲያን” አገር እንደሆነች የሚነገርላት ኡጋንዳ የበርካታ ጎሳዎችና አሁንም ሳይቀር በወጋቸው እንዲሁም በአለባበሳቸው ተለይተው የሚታወቁ ልዩ ልዩ ባሕል ያላቸው ሕዝቦች መኖሪያ ናት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በርካታ ኡጋንዳውያን በመላው ምድር ላይ ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበትን ጊዜ አስመልክቶ እየታወጀ ላለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሥራች ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። (መዝሙር 37:11፤ ራእይ 21:4) ሆኖም ከታላቋ ብሪታንያ ጋር ተቀራራቢ የሆነ የቆዳ ስፋት ባላት በዚህች አገር ውስጥ መልእክቱን ለሁሉም ሰው ማዳረስ ብርቱ ጥረት ይጠይቃል።

ከአገሬው ተወላጆች መካከል የመጀመሪያው ሰው የይሖዋ ምሥክር ሆኖ በቪክቶሪያ ሐይቅ ከተጠመቀበት ከ1955 አንስቶ “ታናሽ የሆነው” ሕዝብ ቁጥሩ እየጨመረ ሄዶ በ1992 አንድ ሺህ ለመሆን በቅቷል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቀጣይ የሆነ እድገት ሲደረግ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ አምላክ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ጊዜውም ሲደርስ ይህን በፍጥነት አደርጋለሁ” ሲል ከተናገራቸው የማበረታቻ ቃላት ጋር ይስማማል።—ኢሳይያስ 60:22

የቋንቋ ልዩነት ያስከተለውን መሰናክል መወጣት

የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ እንግሊዝኛ ሲሆን በተለይም ደግሞ በትምህርት ቤቶች አካባቢ በሰፊው ይሠራበታል። ያም ሆኖ እንግሊዝኛ የብዙዎቹ ኡጋንዳውያን አፍ መፍቻ ቋንቋ አይደለም። በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ለሰዎች ለማድረስ ሲሉ በስፋት የሚሠራባቸውን ሌሎች ቋንቋዎችም ግምት ውስጥ ማስገባት ነበረባቸው። ሃያ አምስት ሚሊዮን ከሚያክለው የአገሪቱ ሕዝብ መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው በገጠር አሊያም በአነስተኛ ከተሞች ውስጥ የሚኖር በመሆኑ እንዲህ ማድረጉ በእርግጥም አስፈላጊ ነበር። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው የሚግባቡት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ነው። የተለያዩ ቋንቋዎችን ለሚናገሩ ሰዎች ምሥራቹን ማዳረስና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን ማርካት ብርቱ ጥረት ይጠይቃል።

የሆነ ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች ለእነዚህ ሕዝቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመመሥከርና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በበርካታ ቋንቋዎች በማዘጋጀት የሰዎቹን ፍላጎት ለማርካት የቻሉትን ያህል ጥረት ያደርጋሉ። በዋና ከተማው ካምፓላ ውስጥ ባለው ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኙት የትርጉም ክፍሎች በአራት ቋንቋዎች ማለትም በአቾሊ፣ በሉኮንዞ፣ በሉጋንዳና በሩንያንኮሬ ጽሑፎችን ይተረጉማሉ። ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቋንቋዎች በሚዘጋጁት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በርካታ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን ቁጥራቸውም በኡጋንዳ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች በእጥፍ ይበልጣል። ይህም ምሥራቹን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማዳረስ እየተደረገ ያለው ጥረት ፈጣን መንፈሳዊ እድገት እያስገኘ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ይሁንና ይህን እድገት ያስገኘው የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ለመመሥከር የተደረገው ጥረት ብቻ አይደለም።

አቅኚዎች ሥራውን በግንባር ቀደምትነት ያከናውናሉ

ጉባኤዎች ገለልተኛ ክልሎችን ለመሸፈን ለሦስት ወራት የሚደረገውን ዓመታዊ ዘመቻ በደስታ ይደግፋሉ። (የሐዋርያት ሥራ 16:9) ይህን ሥራ በግንባር ቀደምትነት የሚመሩት ቀናተኛ የሆኑ ወጣት አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ናቸው። እነዚህ አቅኚዎች ምሥራቹ ጭራሽ ተሰምቶ ወደማይታወቅባቸው ራቅ ያሉ አካባቢዎች ጭምር ይሄዳሉ።

ሁለት ልዩ አቅኚ እህቶች በምዕራብ ኡጋንዳ በምትገኝ ቡሼኒ የተባለች አነስተኛ መንደር ለሦስት ወራት እንዲያገለግሉ ተመድበው ነበር። በዚያም፣ በአካባቢው ለመመሥከርና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት ብቻዋን ከምትጥር እህት ጋር ተገናኙ። እነዚህ እህቶች በአንድ ወር ውስጥ 40 ለሚያህሉ ሰዎች ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የጀመሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 17ቱ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀምረዋል። አቅኚዎቹ እንደሚከተለው ሲሉ ተናግረዋል:- “አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? a የተባለውን ብሮሹር ያበረከትንላቸው አንዳንድ ሰዎች ከጥቂት ቀናት በኋላ በብሮሹሩ ላይ ላሉት ጥያቄዎች መልሶቻቸውን የጻፉባቸውን ብዙ ወረቀቶች ይዘው ቤታችን ድረስ መጡ። የሰጡት መልስ ትክክል መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይፈልጉ ነበር።” ዛሬ በዚህ ከተማ ውስጥ የራሱ የመንግሥት አዳራሽ ያለው ጉባኤ ተቋቁሟል።

ሁለት አቅኚዎች ምሥራቹ ከዚህ ቀደም ወዳልተሰበከበት የምዕራባዊ ኡጋንዳ ክልል ተጉዘው ነበር። አቅኚዎቹ “በእርግጥም ሰዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙ ናቸው። እዚህ በቆየንባቸው ሦስት ወራት ውስጥ 86 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ችለናል” ሲሉ ጽፈዋል። ብዙም ሳይቆይ በዚህ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ተመሥርቷል።

በመስኩ ላይ የተሰማሩ ሌሎች ቀናተኛ ሠራተኞች

ከእነዚህ ቀናተኛ አቅኚዎች መካከል አንዳንዶቹ ለብዙ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው። ፓትሪክ የይሖዋ ምሥክር ከመሆኑ በፊት የኡጋንዳው መሪ በነበሩት በኢዲ አሚን የአየር ኃይል ሙዚቃ ባንድ ውስጥ ክላርኔት ይጫወት ነበር። ፓትሪክ በ1983 ከተጠመቀ ከስድስት ወራት በኋላ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ። በአሁኑ ጊዜ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግል ሲሆን ጉባኤዎችን በመጎብኘትና በማበረታታት ላይ ይገኛል።

እህት ማርጋሬት የተጠመቁት በ1962 ነው። በአሁኑ ጊዜ በሰባዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን እግራቸውን ስለሚያማቸው እንደ ልባቸው መንቀሳቀስ አይችሉም። ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋ ለጎረቤቶቻቸው በማካፈል በየወሩ 70 ሰዓት ያህል ያሳልፋሉ። ከቤታቸው ፊት ለፊት ባለ መቀመጫ ላይ ጽሑፎችን ይደረድሩና በአቅራቢያቸው የሚያልፍ ማንኛውም መንገደኛ ወደፊት ስለሚመጣው ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም የሚናገረውን ምሥራች ለመስማት ፈቃደኛ ከሆነ ያወያዩታል።

በምሥራቃዊ ኡጋንዳ በግብርና ሥራ የሚተዳደረው ሳይመን ለ16 ዓመታት ያህል እውነትን ሲፈልግ ከቆየ በኋላ በ1995 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ አንዳንድ ጽሑፎችን አገኘ። ያነበበው ነገር ስለ አምላክ መንግሥትና ይሖዋ ለምድር ስላለው አስደናቂ ዓላማ ይበልጥ ለማወቅ እንዲጓጓ አደረገው። በሚኖርበት ከተማ በካሙሊ የይሖዋ ምሥክሮች ስላልነበሩ ሳይመን እነርሱን ለማግኘት 140 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ካምፓላ ተጓዘ። አሁን በመንደሩ ውስጥ ጉባኤ ተቋቁሟል።

“እዚሁ እንቆያለን”

በሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዳሉት ሰዎች ሁሉ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎችም አንድ የሃይማኖት ቡድን ጥሩ የሆነ የአምልኮ ሥፍራ ሊኖረው ይገባል የሚል አመለካከት አላቸው። ይህ ደግሞ ተስማሚ የሆኑ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ለሌላቸው አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ለመወጣት አዳጋች የሚመስል ችግር ይፈጥርባቸዋል። በ1999 መጨረሻ አካባቢ የመንግሥት አዳራሾችን ግንባታ ለማፋጠን የሚያስችል ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ወንድሞች የተሰማቸውን የምስጋና ስሜት መግለጽ ያስቸግራል። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በኡጋንዳ 40 የሚሆኑ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ተገነቡ። በዛሬው ጊዜ ሁሉም ጉባኤዎች ለማለት ይቻላል መጠነኛ ሆኖም ተስማሚ የመንግሥት አዳራሽ አላቸው። እነዚህ ግንባታዎች ለአካባቢው ነዋሪዎች “እዚሁ እንቆያለን” የሚል መልእክት የሚያስተላልፉ ሲሆን ለተገኘው እድገትም የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል።

በሰሜን ኡጋንዳ በሚገኝ አንድ አነስተኛ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች ስብሰባዎችን የሚያደርጉት በማንጎ ዛፎች ጥላ ሥር ነበር። ሆኖም አነስተኛ መሬት ሲገኝ ሥራው በፍጥነት መካሄድ ጀመረ። በግንባታ ቡድን ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞች በአካባቢው ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመተባበር የመንግሥት አዳራሹን መገንባት ጀመሩ። በአካባቢው የሚገኝ ታዋቂ ፖለቲከኛ የነበረ አንድ ሰው በሁኔታው እጅግ በመደነቁ የመንግሥት አዳራሹን ሠርተው እስኪያጠናቅቁ ድረስ በእርሱ ጋራዥ ውስጥ እንዲሰበሰቡ ፈቀደላቸው። ከዚህም በላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ከሆነ አንድ ወንድም ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ይህ ሰው በአሁኑ ጊዜ ተጠምቆ ቀናተኛ አስፋፊ ሲሆን አዲስ በተገነባው ውብ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ይሖዋን ማምለክ በመቻሉ ደስተኛ ነው!

በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል በተከናወነው የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ ደግሞ፣ የግንበኝነት ሙያ ያለው አንድ ሰው በወንድሞች መካከል ባየው የወዳጅነት፣ የፍቅርና የትብብር መንፈስ በጥልቅ በመነካቱ እነርሱን ለመርዳት ፈቃደኛ ሆኗል። በፕሮጀክቱ ማጠቃለያ ላይ በቀጣዩ ቀን ወንድሞች ለሚያደርጉት የውሰና ፕሮግራም የመንግሥት አዳራሹን ዝግጁ ለማድረግ ሲል ሌሊቱን በሙሉ ሲሠራ አድሯል። ይህ ሰው “በቃል ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ ከልብ የሚዋደዱ እንደ እናንተ ያሉ ሰዎችን አይቼ አላውቅም” ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል።

ችግሮች ቢኖሩም ተጨማሪ እድገት ማግኘት

በኡጋንዳ ውስጥ የሚገኙ አዳዲስ ክልሎች ገና እየተሸፈኑ በመሆኑ የምሥክሮቹ ቁጥር እያደገ ከመሆኑም በላይ ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ሰዎች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ኡጋንዳ በመፍለስ ላይ ያሉት እጅግ ብዙ ስደተኞች ጉዳይ አፋጣኝ ትኩረት ይሻ ነበር። በጎረቤት አገሮች ውስጥ የሚደረገው የእርስ በርስ ጦርነት በይሖዋ ሕዝቦች ላይም ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። ያም ሆኖ በስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። በአቅራቢያው ባለች አንዲት አገር ቀደም ብሎ ባለ ሥልጣን የነበረ አንድ ሰው በዚያች አገር የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታግዶ በነበረበት ወቅት ወንድሞችን ያሳድድ ነበር፤ እንዲሁም የቅንጦት ኑሮ ይመራ እንደነበር ያስታውሳል። ይህ ሰው በስደተኞች ጣቢያ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ አጥንቶ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “በዚህ ዓለም ውስጥ ቁሳዊ ብልጽግናና ከፍተኛ ሥልጣን ዋጋ ቢስ ነገሮች ናቸው። አሁን ታማሚና ድሃ ብሆንም ሕይወቴ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የተሻለ ነው። ይሖዋን አውቄያለሁ፤ ላገኘሁት የጸሎት መብትም አመስጋኝ ነኝ። ተስፋው እንደሚፈጸም ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ከመሆኔም በላይ አሁን የሚደርሱብንን ፈተናዎች በጽናት መወጣት ያለብን ለምን እንደሆነ አውቄያለሁ። በመሆኑም መቼም አግኝቼው የማላውቀው ውስጣዊ ሰላም አለኝ።”

በኡጋንዳ ለም መሬት ላይ አንድ ደረቅ እንጨት ምሽት ላይ ብትተክል ጠዋት ሥር ሰዶ ታገኘዋለህ የሚል ብሂል አለ። በአገሪቱ ውስጥ በመታየት ላይ ያለው መንፈሳዊ እድገት መንፈሳዊው መሬትም እጅግ ለም እንደሆነ ያሳያል። የተለያየ ባሕል ያላቸው በርካታ ኡጋንዳውያን ስለ መንግሥቱ ማወቅ እንዲችሉ ጊዜውን በመፍቀዱ ይሖዋ አምላክን እናመሰግነዋለን። ኢየሱስ የመንግሥቱን እውነት ዋጋማነት ‘እጅግ ውድ ከሆነ ዕንቊ’ ጋር አመሳስሎታል፤ ይህንንም ብዙዎቹ ኡጋንዳውያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገነዘቡት መጥተዋል።—ማቴዎስ 13:45, 46

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሱዳን

ኡጋንዳ

የናይል ወንዝ

ካሙሊ

ቶሮሮ

ካምፓላ

ቡሼኒ

የቪክቶሪያ ሐይቅ

ኬንያ

ታንዛኒያ

ሩዋንዳ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀናተኛ ከሆኑት አቅኚዎች መካከል ሦስቱ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓትሪክ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርጋሬት

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳይመን

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቶሮሮ የተደረገ የአውራጃ ስብሰባ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከጀርባ ያለው ሥዕል:- © Uganda Tourist Board