በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ብሎ ሲነግረው ምን ማለቱ ነበር?—ዮሐንስ 3:13

በጊዜው ኢየሱስ ገና ምድር ላይ የነበረ ሲሆን ወደ ሰማይ አልወጣም ወይም አልተመለሰም ነበር። ያም ሆኖ ስለ ኢየሱስ የምናውቃቸው ነገሮችና በጥቅሱ ዙሪያ የተናገራቸው ሐሳቦች ለምን እንደዚህ እንዳለ ለመረዳት ያስችሉናል።

ኢየሱስ ቀደም ሲል ከአባቱ ጋር በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ይኖር ስለነበረና የተወሰነው ዘመን ሲደርስ ወደ ማርያም ማኅፀን ተዛውሮ ሰው ሆኖ በመወለዱ ‘ከሰማይ እንደወረደ’ ተገልጿል። (ሉቃስ 1:30-35፤ ገላትያ 4:4፤ ዕብራውያን 2:9, 14, 17) ኢየሱስ ከሞተ በኋላም መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በመነሳት ከይሖዋ ጋር ለመሆን ወደ ሰማይ ይመለሳል። በመሆኑም ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ እንደሚከተለው ሲል ጸልዮአል:- “አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ።”—ዮሐንስ 17:5፤ ሮሜ 6:4, 9፤ ዕብራውያን 9:24፤ 1 ጴጥሮስ 3:18

ኢየሱስ በእስራኤል ይኖር ከነበረው ፈሪሳዊና አስተማሪ ከሆነው ከኒቆዲሞስ ጋር በተነጋገረበት ጊዜ ወደ ሰማይ አልሄደም ነበር። በእርግጥም ከሞተ በኋላ በሰማይ ወደሚገኘው መንፈሳዊ ዓለም የሄደ አንድም ሰው አልነበረም። ኢየሱስ ራሱ መጥምቁ ዮሐንስ ከአምላክ ነቢያት መካከል ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መሆኑን ከጠቀሰ በኋላ “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል” ሲል አክሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:11) ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ ታማኝ የነበረው ንጉሥ ዳዊት እንኳ በመቃብር ውስጥ እንደሚገኝ ገልጿል፤ በመሆኑም ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም። (የሐዋርያት ሥራ 2:29, 34) እንደ ዳዊትና መጥምቁ ዮሐንስ ያሉ ከኢየሱስ በፊት የሞቱ የእምነት ሰዎች ወደ ሰማይ ያልሄዱበት ምክንያት ነበረ። እነዚህ ሰዎች የሞቱት ኢየሱስ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ ለመኖር የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ከመክፈቱ በፊት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ‘አዲስና ሕያው የሆነውን መንገድ ለመክፈት’ ቀዳሚ መሆኑን ጽፏል።—ዕብራውያን 6:19, 20፤ 9:24፤ 10:19, 20

ታዲያ ኢየሱስ ገና ሳይሞትና ከሞት ሳይነሳ “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ብሎ ለኒቆዲሞስ መናገሩ ምን ያመለክታል? (ዮሐንስ 3:13) ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲወያይ የነበረው ስለ ምን ጉዳይ እንደሆነ ወይም በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ምን እንደሚል ተመልከት።

የአይሁድ መሪ የነበረው ይህ ሰው ጨለማን ተገን አድርጎ ወደ እርሱ ሲመጣ ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ሲል ነገረው። (ዮሐንስ 3:3) ኒቆዲሞስም በምላሹ ‘ይህ እንዴት ይሆናል? አንድ ሰው እንዴት ዳግመኛ ሊወለድ ይችላል?’ በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ወደ አምላክ መንግሥት መግባትን አስመልክቶ የተነገረውን ይህን መለኮታዊ ትምህርት ለመረዳት አልቻለም ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ሊማር የሚችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? ስለዚህ ጉዳይ ከሰዎች መማር የማይቻል ነበር፤ ማንኛውም ሰው በሰማይ ኖሮ ስለማያውቅ ስለ ሁኔታው ሊያስተምረውና ወደ አምላክ መንግሥት መግባት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ሊነግረው አይችልም። የኢየሱስ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። እርሱ ከሰማይ የወረደ በመሆኑና ስለዚህ ጉዳይ ለማስተማር ብቃቱ ስላለው ኒቆዲሞስንም ሆነ ሌሎችን ሊያስተምር ይችላል።

በዚህ ጥቅስ ላይ የተነሳው ጥያቄ የአምላክን ቃል በማጥናት ረገድ ጠቃሚ ሐሳብ ይዟል። አንድ ሰው የሚያነበው ነገር ስላልገባው ብቻ ቅዱስ ጽሑፉን መጠራጠር ቢጀምር ምክንያታዊ አይሆንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ አንድ ሐሳብ ከሌላው የመጽሐፉ ክፍል ጋር መገናዘብና መስማማት ይኖርበታል። ከዚህም ባሻገር በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ማለትም ሁኔታው ወይም እየተብራራ ያለው ነጥብ፣ ውስብስብ ለሚመስሉ ጥቅሶች ምክንያታዊ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል።