በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይህችን የወይን ተክል ተንከባከባት”!

“ይህችን የወይን ተክል ተንከባከባት”!

“ይህችን የወይን ተክል ተንከባከባት”!

አሥራ ሁለቱ ሰላዮች ተስፋይቱን ምድር እየተዘዋወሩ ተመልክተዋል። ሙሴ የነዋሪዎቹን ሁኔታ እንዲያጤኑና ምድሪቱ ከምታፈራቸው ፍሬዎች መካከል ለናሙና የሚሆን ይዘው እንዲመጡ ለሰላዮቹ ነግሯቸው ነበር። ትኩረታቸውን የሳበው የትኛው ፍሬ ይሆን? ከኬብሮን ብዙም ሳይርቁ በአንድ የወይን እርሻ ላይ የተንዠረገገ ወይን ተመለከቱ፤ የዚህ ወይን ፍሬዎች በጣም ትላልቅ ከመሆናቸው የተነሳ አንዱን ዘለላ ለሁለት መሸከም ነበረባቸው። ሰላዮቹ በጣም በመደነቃቸው ይህን ለምለም ስፍራ “የኤሽኮል ሸለቆ” ወይም የወይን “ዘለላ” ብለው ሰየሙት።—ዘኍልቍ 13:21-24፤ የግርጌ ማስታወሻ

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጳለስጢናን የጎበኙ አንድ ሰው “ኤሽኮል ወይም የወይን ሸለቆ . . . አሁንም በወይን የተሞላ ሲሆን ወይኑም በጳለስጢና ውስጥ በዓይነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለትና ትላልቅ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። የኤሽኮል ወይን እጅግ ምርጥ ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን መላው ጳለስጢና ጥሩ ወይን በማምረት ይታወቅ ነበር። የግብጽ ፈርኦኖች ከከነዓን ምድር ወይን ያስመጡ እንደነበር ዘገባዎቻቸው ያሳያሉ።

ዘ ናቹራል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ ኤሽኮልን አስመልክቶ እንደሚከተለው ብሏል:- “[የጳለስጢናን] ዓለታማ ሸንተረሮች ያለበሰው አሸዋማ አፈር ለፀሐይ የተጋለጠ ሲሆን የበጋው ሙቀትና በክረምት አፈሩ ዝናቡን በፍጥነት የሚመጠው መሆኑ በአንድነት ተዳምረው ስፍራውን ለወይን ምርት በጣም ምቹ አድርገውታል።” ኢሳይያስ አንድ ሺ የወይን ተክሎች ያሉባቸው አንዳንድ ምርጥ አካባቢዎች እንደነበሩ ጠቅሷል።—ኢሳይያስ 7:23

የወይን ምድር

ሙሴ ለእስራኤላውያን “ወይንና የበለስ ዛፎች [እንዲሁም] ሮማን” በብዛት የሚገኙበትን ምድር እንደሚወርሱ ነግሯቸዋል። (ዘዳግም 8:8) ቤከር ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ባይብል ፕላንትስ እንዳለው “በጥንቷ ጳለስጢና ወይን እንደ ልብ ይመረት ስለነበር በአንዳንድ አካባቢዎች በተደረገ ቁፋሮ የወይን ዘር ማግኘት ተችሏል።” ሌላው ቀርቶ የናቡከደነፆር ሠራዊት በ607 ይሁዳን ባጠፋበት ጊዜ ከጥፋቱ ያመለጡት ሰዎች ‘ወይንና የበጋ ፍሬ በብዛት እንዳከማቹ’ መነገሩ በተስፋይቱ ምድር የሚበቅለው ወይን ምን ያህል ፍሬያማ እንደነበር ያረጋግጣል።—ኤርምያስ 40:12፤ 52:16

እስራኤላውያን ገበሬዎች ከተከሉት ወይን ብዙ ምርት ለማግኘት የወይን እርሻቸውን በተገቢው ሁኔታ መንከባከብ ነበረባቸው። የኢሳይያስ መጽሐፍ ወይን የሚያመርት አንድ እስራኤላዊ ገበሬ በኮረብታ ላይ ያለውን መሬቱን እንደቆፈረና “ምርጥ የሆነውንም ወይን” ከመትከሉ በፊት በማሳው ላይ የነበረውን ትላልቅ ድንጋይ ለቅሞ እንዳስወገደ ይገልጻል። ከዚያም ምናልባት ከማሳው ላይ የለቀመውን ድንጋይ በመካብ አጥር ይሠራል። ይህ የድንጋይ ካብ የወይን እርሻው በከብቶች እንዳይረጋገጥ እንዲሁም የቀበሮ፣ የከርከሮና የሌቦች ሲሳይ እንዳይሆን ይጠብቀዋል። ቀጥሎም የወይን መጭመቂያ ጠርቦ ያዘጋጃል። በተጨማሪም ወይኑ ይበልጥ ጥበቃ ሊደረግለት በሚገባው በመከር ወቅት የሚጠለልበት አንድ አነስተኛ መጠበቂያ ማማ ይሠራ ይሆናል። ይህን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ካደረገ በኋላ ጥሩ የወይን ምርት ለማግኘት ይጠባበቃል።—ኢሳይያስ 5:1, 2 a

ገበሬው መልካም ውጤት ለማግኘት ከፈለገ፣ ፍሬያማ እንዲሆንለት በየጊዜው ወይኑን መግረዝ እንዲሁም አረም፣ እሾሃማ ቁጥቋጦና ኩርንችት እንዳይወርሰው ማሳውን መኮትኮት ነበረበት። በቂ የበልግ ዝናብ በማይኖርበት የበጋ ወቅት የወይን እርሻውን ውኃ ማጠጣት ያስፈልገው ነበር።—ኢሳይያስ 5:6፤ 18:5፤ 27:2-4

የወይኑ መከር የሚሰበሰብበት የበጋው ወራት መገባደጃ ታላቅ የደስታ ጊዜ ነበር። (ኢሳይያስ 16:10) በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ምዕራፎች አናት ላይ “በጌቲት ላይ” የሚል ሐረግ ሰፍሮ እናገኛለን። (መዝሙር 8, 81 እና 84 የ1879 ትርጉም) ይህ ትርጉሙ በውል የማይታወቅ ከሙዚቃ ጋር ግንኙነት ያለው አገላለጽ በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ላይ “የወይን መጭመቂያ” ተብሎ ተተርጉሟል። በመሆኑም እስራኤላውያን እነዚህን መዝሙሮች የሚዘምሩት በወይን መከር ጊዜ ሊሆን ይችላል። ወይን በዋነኝነት ያገለግል የነበረው የወይን ጠጅ ለመሥራት ቢሆንም እስራኤላውያን ወይኑ እንደተቆረጠ አሊያም በዘቢብ መልክ አድርቀው ይመገቡት ነበር።—2 ሳሙኤል 6:19፤ 1 ዜና መዋዕል 16:3

በወይን የተመሰለው እስራኤል

ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሕዝቦች በወይን ይመስላቸዋል፤ ይህ ደግሞ ወይን ለእስራኤላውያን ይሰጣቸው ከነበረው ጥቅም አንጻር ሲታይ ተስማሚ ምሳሌ ነው። አሳፍ በመዝሙር ምዕራፍ 80 ላይ የእስራኤልን ብሔር ይሖዋ በከነዓን ምድር እንደተከለው ወይን አድርጎ ገልጾታል። እንደ ወይን ተክል የሆነው እስራኤል ሥር እንዲሰድና እንዲጠነክር መሬቱ ተመንጥሮለት ነበር። ሆኖም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ መከላከያ ሆኖ ሲያገለግለው የነበረው ካብ መፈራረስ ጀመረ። ብሔሩ በይሖዋ ላይ መተማመኑን ስለተወ ይሖዋ ጥበቃውን ነፈጋቸው። በዚህ ጊዜ የእስራኤላውያን ጠላቶች የሆኑ ብሔራት ልክ የወይንን እርሻ እንደሚያጠፉ ከርከሮዎች ሀብታቸውን ይመዘብሩት ገቡ። አሳፍ ብሔሩ ቀድሞ የነበረውን ክብር ዳግም ያገኝ ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳቸው ጸልዮአል። “ይህችን የወይን ተክል ተንከባከባት” ሲልም ተማጽኖአል።—መዝሙር 80:8-15

ኢሳይያስ ‘የእስራኤልን ቤት’ ውሎ አድሮ “ኮምጣጣ ፍሬ [“የዱር ወይን፣” NW]” ካፈራ የወይን ተክል ጋር አመሳስሎታል። (ኢሳይያስ 5:2, 7) ጫካ ውስጥ የሚበቅል ወይን የሚያፈራው ፍሬ መጠኑ አነስተኛ ከመሆኑም በላይ በፍሬው ውስጥ ያለው ዘር ትልቅ ነው። በመሆኑም የወይን ጠጅ ለመሥራትም ይሁን ለምግብነት የማይውለው ይህ የጫካ ወይን ከጽድቅ ይልቅ ዓመጸኝነትን ላፈራው ከሃዲ ብሔር ተስማሚ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል። ፍሬው እርባና ቢስ የሆነው በወይን አምራቹ ስህተት አይደለም። ይሖዋ ብሔሩ ፍሬያማ እንዲሆን የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። በመሆኑም “ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር?” ሲል ጠይቋል።—ኢሳይያስ 5:4

የእስራኤል ወይን ፍሬ ቢስ መሆኑ በግልጽ በመታየቱ፣ ይሖዋ በሕዝቡ ዙሪያ የገነባውን የመከላከያ አጥር እንደሚያፈርስ አስጠነቀቃቸው። ይሖዋ ምሳሌያዊ ወይኑን መግረዝም ሆነ መኮትኮት አቁሞ ነበር። ለወይኑ ሕልውና አስፈላጊ የሆነው የበልግ ዝናብ ካለመዝነቡም በላይ እርሻውን አረም ወርሶት ነበር።—ኢሳይያስ 5:5, 6

ሙሴ እስራኤላውያን በክህደታቸው ሳቢያ ቃል በቃል የወይን ተክሎቻቸው እንደሚደርቁ ትንቢት ተናግሯል። “ወይን ትተክላለህ ታበጀውማለህ ትልም ይበላዋልና ከእርሱ ምንም አትሰበስብም፣ የወይን ጠጁንም አትጠጣም።” (ዘዳግም 28:39 የ1954 ትርጉም) በአንድ የወይን ተክል ግንድ ውስጥ ትል ገብቶ ውስጡን ከቦረቦረው በጥቂት ቀናት ውስጥ ይደርቃል።—ኢሳይያስ 24:7

“እውነተኛው የወይን ተክል”

ይሖዋ ሥጋዊ እስራኤላውያንን ከወይን ተክል ጋር እንዳመሳሰላቸው ሁሉ ኢየሱስም ተመሳሳይ የሆነ ምሳሌ ተጠቅሞል። ኢየሱስ በሕይወት ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ “እውነተኛው የወይን ተክል እኔ ነኝ፤ አትክልተኛውም አባቴ ነው” በማለት ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:1) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከወይን ቅርንጫፎች ጋር አመሳስሏቸዋል። የአንድ የወይን ተክል ቅርንጫፍ ጥንካሬ የተመካው በግንዱ ላይ እንደሆነ ሁሉ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም ከእርሱ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው መኖር ነበረባቸው። ኢየሱስ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ሲል ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:5) ገበሬዎች ወይን የሚተክሉት ለፍሬው ሲሉ ነው፤ ይሖዋም ቢሆን ሕዝቦቹን መንፈሳዊ ፍሬ እንዲያፈሩ ይጠብቅባቸዋል። ይህም የወይኑ አትክልተኛ ለሆነው አምላክ እርካታና ክብር ያስገኝለታል።—ዮሐንስ 15:8

የወይን ተክል ፍሬያማነት የተመካው ወይኑ በመገረዙና በመጥራቱ ላይ ሲሆን ኢየሱስ ስለ እነዚህ ሁለት ክንውኖች ተናግሯል። አንድ ወይን አብቃይ ገበሬ ብዙ ምርት ለማግኘት ወይኑን በዓመት ሁለት ጊዜ ይገርዘው ይሆናል። በክረምት ወራት አብዛኛው የወይኑ ቅርንጫፍ ይቆረጣል። በዚህ ጊዜ አትክልተኛው ቀደም ባለው ዓመት ያደጉትን ብዙዎቹን ቅርንጫፎች ያስወግዳቸዋል። ብዙውን ጊዜ በግንዱ ላይ ሦስት ወይም አራት ዋና ቅርንጫፎችና በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ላይ ደግሞ አንድ ወይም ሁለት ቀንበጦችን ይተዋል። ካለፈው ዓመት የተገኙት እነዚህ ለጋ ቀንበጦች በቀጣዩ የበጋ ወቅት ፍሬ የሚያፈሩ ቅርንጫፎች ይሆናሉ። ገበሬው ወይኑን ገርዞ ከጨረሰ በኋላ የተቆረጡትን ቅርንጫፎች ሰብስቦ ያቃጥላቸዋል።

ኢየሱስ እንዲህ የመሰለውን ግርዛት አስመልክቶ የሚከተለውን ብሏል:- “በእኔ የማይኖር ተጥሎ እንደሚደርቅ ቅርንጫፍ ነው፤ እንዲህ ያሉት ቅርንጫፎች ተለቅመው ወደ እሳት ይጣላሉ፤ ይቃጠላሉም።” (ዮሐንስ 15:6) በዚህ ጊዜ ወይኑ የተመለመለ ቢሆንም የጸደይ ወራት ሲደርስ ደግሞ አንዳንዶቹ ቅርንጫፎች በድጋሚ መገረዛቸው አይቀርም።

ኢየሱስ “እርሱም በእኔ ያለውን፣ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቈርጦ ይጥለዋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:2) ይህ አባባሉ ወይኑ ብዙ አዳዲስ ቅርንጫፎችን ካበቀለና ትናንሽ የወይን ፍሬዎች እጅብ እጅብ ብለው በግልጽ መታየት ከጀመሩ በኋላ የሚካሄደውን የኋለኛውን ግርዘት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። የወይኑ ገበሬ ያፈሩትንና ያላፈሩትን ቅርንጫፎች ለመለየት በጥንቃቄ ይመረምራል። ፍሬ አልባ የሆኑት ቅርንጫፎች ባሉበት ከተተዉ ከግንዱ የሚመጣውን ንጥረ ምግብና ውኃ መሻማታቸው አይቀርም። በመሆኑም የወይኑ ገበሬ ምግቡ ፍሬ ላፈሩት ቅርንጫፎች ብቻ እንዲደርስ ለማድረግ ሲል ፍሬ አልባ የሆኑትን ቅርንጫፎች ቆርጦ ያስወግዳቸዋል።

በመጨረሻም ኢየሱስ የማጥራቱን ሂደት አስመልክቶ እንደሚከተለው ሲል ገልጿል:- “ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል።” (ዮሐንስ 15:2 የ1954 ትርጉም) ፍሬ አልባ የሆኑት ቅርንጫፎች ከተወገዱ በኋላ የወይኑ ገበሬ ያፈራውን እያንዳንዱን ቅርንጫፍ በጥንቃቄ መመርመሩን ይቀጥላል። በዚህ ጊዜ በፍሬያማው ቅርንጫፍ ላይ የሚገኙትን መወገድ ያለባቸው ለጋ ቀንበጦች ማየቱ አይቀርም። እነዚህ ቀንበጦች እንዲያድጉ ቢተዉ ለወይኑ ፍሬ እርጥበት ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን ንጥረ ምግብ የያዘ ፈሳሽ ይሻማሉ። በተጨማሪም ለጋዎቹ ፍሬዎች በቂ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኙ ለማድረግ አንዳንድ ሰፋፊ ቅጠሎች እንዲወገዱ ይደረጋል። እነዚህ ሁሉ፣ ፍሬያማ የሆኑት ቅርንጫፎች ብዙ ምርት እንዲሰጡ ለማድረግ ሲባል የሚወሰዱ አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው።

‘ብዙ ፍሬ ማፍራታችሁን ቀጥሉ’

የምሳሌያዊው ‘እውነተኛ የወይን ተክል’ ቅርንጫፎች ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያመለክታሉ፤ ሆኖም ‘ሌሎች በጎችም’ ቢሆኑ ፍሬያማ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን ማስመስከር ይጠበቅባቸዋል። (ዮሐንስ 10:16) እነርሱም “ብዙ ፍሬ” በማፍራት በሰማይ የሚኖረውን አባታቸውን ማስከበር ይችላሉ። (ዮሐንስ 15:5, 8) ኢየሱስ እውነተኛውን የወይን ተክል አስመልክቶ የተናገረው ምሳሌ መዳናችን የተመካው ከክርስቶስ ጋር ያለንን አንድነት አጽንተን በመያዛችንና መልካም የሆኑ መንፈሳዊ ፍሬዎች በማፍራታችን ላይ መሆኑን እንድንረዳ ያስችለናል። ኢየሱስ “እኔ የአባቴን ትእዛዝ ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር፣ እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 15:10

አምላክ፣ በዘካርያስ ዘመን ይኖሩ ለነበሩት ታማኝ እስራኤላውያን ቀሪዎች ምድሪቱ ዳግመኛ ‘ሰላም የሚዘራባት፤ ወይኑ ፍሬውን የሚሰጥባትና አዝመራ የሚወጣባት’ እንደምትሆን ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘካርያስ 8:12 የ1954 ትርጉም) ከዚህም በተጨማሪ ወይኑ የአምላክ ሕዝቦች በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ የሚያገኙትን ሰላም ለማመልከት ተሠርቶበታል። ሚክያስ እንደሚከተለው ሲል ተንብዮአል:- “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት አፍ ተናግሮአልና።”—ሚክያስ 4:4

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ እንደሚለው እስራኤላውያን ገበሬዎች የሚመርጡት የወይን ጠጅ ቀለም ያለውን ሶሬክ የተባለውን የወይን ዝርያ ሲሆን ይህ ዝርያ በኢሳይያስ 5:2 ላይ ተጠቅሶ ከሚገኘው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነም ይገመታል። እነዚህ የወይን ዝርያዎች ጣፋጭ ጣዕም ያለው ቀይ የወይን ጠጅ ያስገኛሉ።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቅርቡ የጠወለገ የወይን ተክል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በክረምት ወራት የሚካሄድ የወይን ግርዛት

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አላስፈላጊዎቹን ቅርንጫፎች ማቃጠል