ደስተኛ ለመሆን የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ
ደስተኛ ለመሆን የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ
የዩናይትድ ስቴትስ የነጻነት ድንጋጌ አርቃቂዎች “ደስታን ለማግኘት መጣር” የሁሉም ሰው መብት እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ መጣር ግቡ ላይ ከመድረስ የተለየ ነገር ነው። ብዙ ወጣቶች በመዝናኛና በስፖርቱ ዓለም ስኬታማ ለመሆን ቢጥሩም አጥብቀው የሚፈልጉት ግብ ላይ የደረሱ ምን ያህል ሰዎችን ታውቃለህ? የተዋጣለት አቀንቃኝ ለመሆን የሚደረገውን ትግል የሚያውቅ አንድ ታዋቂ ዘፋኝ “ላይሳካላችሁ ይችላል” በማለት ተናግሯል።
ደስታ ማግኘትን በተመለከተ እንደዚህ ከተሰማህ ተስፋ አትቁረጥ። ደስታን በትክክለኛው መንገድ ከፈለግከው ታገኘዋለህ። እንዲህ ማለት የምንችለው ለምንድን ነው? ከዚህ በፊት የነበረው ርዕስ ይሖዋን “ደስተኛ አምላክ” በማለት ጠርቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) አምላክ ደስታን ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ተስፋ አስቆራጭ እንዳይሆን የሚረዳህን መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አዘጋጅቶልሃል። ይሖዋ ለሐዘን የሚዳርጉ የተለመዱ ችግሮችን እንድትወጣ ሊረዳህ ይችላል። የምትወደው ሰው በሚሞትበት ጊዜ አምላክ የሚሰጥህን ማጽናኛ እንደ ምሳሌ እንመልከት።
የምትወደው ሰው ሲሞት
ስለ ሞት ምን ጥሩ ነገር መናገር ይቻላል? ሞት ወላጆችን ከልጆች እንዲሁም ልጆችን ከወላጆች ይለያል። የቅርብ ጓደኛሞች እንዲነጣጠሉና ተቀራርበው የሚኖሩ ኅብረተሰቦች ሥጋት ላይ እንዲወድቁ ያደርጋል። ሞት በሚያጋጥምበት ጊዜ ደስተኛ የነበረ ቤተሰብ በሐዘን ሊዋጥ ይችላል።
ሞት አሳዛኝ መሆኑ የታወቀ ነገር ነው። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች የሞትን አሳዛኝ እውነታ ባለመቀበል ሞት በረከት እንደሆነ ይናገራሉ። በነሐሴ 2005 የሜክሲኮን ባሕረ ሰላጤ ከመታችው ካትሪና የተባለች አውሎ ነፋስ በኋላ ምን እንደተከሰተ እንመልከት። በዚሁ አውሎ ነፋስ
ሳቢያ በሞተ የአንድ ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ አንድ ቄስ “ይህን ሰው ካትሪና አልገደለውም። አምላክ ወደ ሰማይ ወስዶት ነው” በማለት ተናግረዋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ አንዲት አሳቢ የሆስፒታል ሠራተኛ፣ ለአንዲት ልጅ አምላክ እናቷን ወደ ሰማይ ስለወሰዳት እንዳትጨነቅ ነገረቻት። ልጅቷም እያለቀሰች “ለምን? እናቴን ከእኔ ነጥሎ የወሰዳት ለምንድን ነው?” በማለት ተናገረች።በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ስለ ሙታን የሚነገሩት እንደዚህ ያሉ የተሳሳቱ ሐሳቦች ያዘነውን ግለሰብ ሊያጽናኑት አይችሉም። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ሐሳቦች ስለ ሞት እውነቱን አይናገሩም። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ አምላክ የምንወዳቸውን የቤተሰባችንን አባላትና ወዳጆቻችንን በጭካኔ በመንጠቅ እንድናዝን እንደሚያደርገን መግለጻቸው ነው። በዚህ መንገድ አምላክ እንደ አጽናኝ ሳይሆን እንደ ክፉ አካል ተደርጎ ይገለጻል። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ስለ ሞት ትክክለኛውን ነገር ይነግረናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ጠላት ብሎ ይጠራዋል፤ እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ እየገዛ እንዳለ ንጉሥ አድርጎ ይገልጸዋል። (ሮሜ 5:17፤ 1 ቆሮንቶስ 15:26) ሞት ከፍተኛ ኃይል ያለው ባላጋራ በመሆኑ ማንም ሰው ሊገታው አይችልም፤ በሞት የተለየን የምንወደው ሰው ሥፍር ቁጥር ከሌላቸው የሞት ሰለባዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት፣ የምንወደው ሰው ሲሞት የምናዝነውና ረዳት የማጣት ስሜት የሚያድርብን ለምን እንደሆነ ግልጽ የሚያደርግልን ከመሆኑም በላይ ይህ ዓይነቱ ስሜት ስህተት እንዳልሆነ ያሳያል። ታዲያ አምላክ የምንወዳቸውን ሰዎች ወደ ሰማይ ለመውሰድ ጠላት በሆነው በሞት ይጠቀማል? እስቲ የዚህን ጥያቄ መልስ መጽሐፍ ቅዱስ ይስጠን።
መክብብ 9:5, 10 እንዲህ ይላል:- “ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ . . . ልትሄድበት ባለው መቃብር [“ሲኦል፣” የግርጌ ማስታወሻ] ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።” ሲኦል ምንድን ነው? ሰዎች ሲሞቱ የሚሄዱበት የሰው ልጆች መቃብር ነው። በመቃብር ውስጥ የሚገኙ ሙታን በድን ናቸው፤ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አያደርጉም፣ የሚሰማቸው ወይም የሚያስቡት ነገር የለም። ሙታን ኃይለኛ እንቅልፍ የወሰዳቸው ያህል ነው። a ስለዚህ አምላክ የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት በመንጠቅ በሰማይ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ እንደማይወስዳቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። ሰዎች ሲሞቱ ከሕልውና ውጭ ሆነው ወደ መቃብር ይወርዳሉ።
ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ይህን እውነት አረጋግጧል። ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። አልዓዛር ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ለመሆን ወደ ሰማይ ሄዶ ቢሆን ኖሮ፣ ኢየሱስ አልዓዛርን ከጊዜ በኋላ እንደገና እንዲሞት ወደ ምድር መልሶ ማምጣቱ ደግነት የጎደለው ድርጊት ይሆን ነበር። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ ኢየሱስ በመቃብሩ ሥፍራ ድምፁን ከፍ አድርጎ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” በማለት ሲጣራ ‘የሞተው ሰው እንደወጣ’ ይናገራል። አልዓዛር እንደገና በሕይወት መኖር ጀመረ። አልዓዛር ምድርን ትቶ የትም እንዳልሄደ ኢየሱስ አውቋል፤ ከዚህ ይልቅ በድን ሆኖ በመቃብር ውስጥ ነበር።—ዮሐንስ 11:11-14, 34, 38-44
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ አምላክ ሰዎችን ከምድር
ወደ ሰማይ ለማዛወር በሞት እንደማይጠቀም ለመረዳት ያስችለናል። ለሐዘን የዳረገን አምላክ አለመሆኑን ስለምናውቅ ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን። ጠላታችን የሆነው ሞት የሚያስከትልብንን ሐዘንና ጉዳት አምላክ ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳልን መተማመን እንችላለን። ሙታን ስላሉበት ሁኔታ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሲኦል እሳትም ሆነ በመንጽሔ እንደማይሠቃዩ ከዚህ ይልቅ በድን ሆነው በመቃብር ውስጥ እንደሚገኙ ይነግረናል። በመሆኑም በሞት ስለተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ስናስብ በአምላክ ላይ ጥላቻ ሊያድርብን ወይም ሙታን የት እንዳሉ ስለማናውቅ ፍርሃት ሊሰማን አይገባም። ከዚህም በላይ ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ተጨማሪ ማጽናኛ ይሰጠናል።ተስፋ ደስታ ያስገኛል
ከላይ ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች ተስፋ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያሳዩናል። “ተስፋ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት መልካም ነገርን በእርግጠኝነት መጠባበቅን ለማመልከት ነው። ተስፋ በአሁኑ ጊዜ እንዴት ደስታ ሊያስገኝልን እንደሚችል ለማየት ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሳው ወደሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንመለስ።
ኢየሱስ ይህንን ተአምር የፈጸመው ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው በማርታ፣ በማርያምና በወዳጆቻቸው ላይ የደረሰውን ሐዘን ለማስወገድ ሲሆን እነዚህ ሰዎች አልዓዛር ከተነሳ እንደገና ከሚወዱት ሰው ጋር አብረው መሆን ይችላሉ ማለት ነው። ሆኖም ኢየሱስ ሁለተኛውንና ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ምክንያት ሲገልጽ ለማርታ እንዲህ ብሏታል:- “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽም?” (ዮሐንስ 11:40) በጄ ቢ ፊሊፕስ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔርን ክብር” የሚለውን ዓረፍተ ነገር “አምላክ ሊፈጽም የሚችለውን ድንቅ ነገር” በማለት ተርጉሞታል። ኢየሱስ አልዓዛርን ማስነሳቱ ይሖዋ አምላክ ሊያከናውን የሚችለውንና ወደፊትም የሚፈጽመውን ነገር የሚያሳይ ነበር። ከዚህ በታች “አምላክ ሊፈጽም የሚችለውን ድንቅ ነገር” በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ቀርበዋል።
ኢየሱስ በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ . . . [በመቃብር ያሉት] ይወጣሉ” በማለት ተናግሯል። ይህ ማለት ደግሞ የምንወዳቸውን ሰዎች ጨምሮ በሲኦል ውስጥ ያሉት ሁሉ ይነሳሉ ማለት ነው። የሐዋርያት ሥራ 24:15 ስለዚህ አስደናቂ ክስተት ሲገልጽ “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን [ይነሳሉ]” ይላል። ስለሆነም “ኀጥአን” ማለትም ይሖዋን ሳያውቁና ሳያገለግሉት የሞቱትም ሁሉ ወደፊት የአምላክን ሞገስ የማግኘት አጋጣሚ ተዘርግቶላቸዋል።
ታዲያ ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው የት ነው? መዝሙር 37:29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ይናገራል። እስቲ ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስብ! በሞት ምክንያት የተለያዩ ቤተሰቦችና ጓደኛሞች በምድር ላይ በድጋሚ ይገናኛሉ። ከምትወዳቸው ወዳጆችህ ጋር እንደገና አብረህ ጊዜ ማሳለፍ እንደምትችል ስታስብ ልብህ በደስታ መሞላቱ ምክንያታዊ ነው።
ይሖዋ ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል
ችግሮች ቢኖሩብህም ይሖዋ ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን የሚያደርግባቸውን ሁለት መንገዶች ተመልክተናል። በመጀመሪያ፣ መከራን በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት እንድትችል የሚረዳህን እውቀትና መመሪያ የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስን አዘጋጅቶልሃል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሞት ያስከተለብንን ሐዘን እንድንቋቋም ከመርዳቱም በላይ በኢኮኖሚና በጤና ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን እንዴት እንደምንወጣ ይነግረናል። ማኅበራዊ አድልዎንና የፖለቲካ አለመረጋጋትን እንድትቋቋም ኃይል ይሰጥሃል። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በሕይወትህ ውስጥ በሥራ ላይ የምታውለው ከሆነ በግል የሚደርሱብህን ሌሎች ችግሮች እንድትወጣ ሊረዳህ ይችላል።
ሁለተኛው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትህ የሰው ልጅ ማኅበረሰብ ሊሰጥህ ከሚችለው እጅግ የላቀ ተስፋ ታገኛለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን ትንሣኤ እንደሚያገኙ ተስፋ ይሰጣል። ራእይ 21:3, 4 ይበልጥ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ራሱም [ከሰዎች] ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።” ይህም በሕይወትህ ውስጥ ለሐዘን የሚዳርግህ ማንኛውም ነገር በቅርቡ ለዘላለም ይወገዳል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ ይፈጸማል፤ አንተም ይህን ማየት ትችላለህ። የወደፊቱ ጊዜ አሁን ካለንበት የተሻለ እንደሚሆን ማወቁ እንኳ እረፍት ይሰጣል። ከሞት በኋላ ለዘላለም እንደማትሠቃይ ማወቅህ ደስተኛ እንድትሆን ያደርግሃል።
በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት የማሪያ ባለቤት ለረጅም ጊዜ በካንሰር ሲሠቃይ ከቆየ በኋላ በሞት አንቀላፋ። ማሪያ ባለቤቷ ከሞተ ብዙም ሳይቆይ የገንዘብ ችግር በመከሰቱ ሦስት ሴቶች ልጆቿን ይዛ ከቤቷ ለመውጣት ተገደደች። ከሁለት ዓመት በኋላ ማሪያ ካንሰር እንደያዛት አወቀች። ሁለት ከባድ ቀዶ ሕክምናዎችን ያደረገች ሲሆን በየቀኑ በከፍተኛ ሕመም ትሠቃያለች። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩባትም አዎንታዊ አመለካከት መያዟ ሌሎችን ለማበረታታት አስችሏታል። ታዲያ ደስታዋን ጠብቃ መኖር የቻለችው እንዴት ነው?
ማሪያ እንዲህ ትላለች:- “ችግሮች ሲገጥሙኝ ስለ ራሴ ከሚገባው በላይ ላለማሰብ እሞክራለሁ። ‘ይህ ችግር በእኔ ላይ ለምን ደረሰ? ይህን ያህል የምሠቃየው ለምንድን ነው? ለምንስ እታመማለሁ?’ እንደሚሉ ያሉ ጥያቄዎችን አላነሳም። አሉታዊ አመለካከት ኃይልን ያሟጥጣል። እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ያለኝን ኃይል ይሖዋን ለማገልገልና ሌሎችን ለመርዳት እጠቀምበታለሁ። ይህ ደግሞ ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል።”
ማሪያ ተስፋ ያላት መሆኑ የረዳት እንዴት ነው? ይሖዋ፣ የሰው ልጆች የሚገጥሟቸውን ሁሉንም ዓይነት በሽታዎችም ሆነ ችግሮች የሚያስወግድበትን የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ትጠባበቃለች። ለመታከም ወደ ሆስፒታል በምትሄድበት ጊዜ እዚያ ለሚገኙ ተስፋቸው ለጨለመባቸው የካንሰር ሕመምተኞች ያላትን ብሩህ ተስፋ ታካፍላቸዋለች። ተስፋ ለማሪያ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? እንዲህ ትላለች:- “ጳውሎስ በዕብራውያን 6:19 ላይ ተስፋ ለነፍሳችን መልሕቅ እንደሆነ የተናገረውን ሐሳብ ሁልጊዜ አስባለሁ። መልሕቅ ከሌለህ በማዕበል እንደምትወሰድ ጀልባ ትሆናለህ። ሆኖም መልሕቁን አጥብቀህ ከያዝክ እንደ ማዕበል ያሉ ችግሮች ቢገጥሙህም እንኳ የሚያሰጋህ ነገር አይኖርም።” ማሪያ ‘የማይዋሸው አምላክ የገባው የዘላለም ሕይወት ተስፋ’ ደስተኛ ሆና እንድትቀጥል ረድቷታል። ይህ ተስፋ አንተም ደስተኛ እንድትሆን ሊያደርግህ ይችላል።—ቲቶ 1:2
ችግሮች ቢኖሩብህም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትህ ያለውን ጥቅም በተመለከተ ጥያቄዎች ይኖሩህ ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንድትችል ለጥያቄዎችህ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶችን እንድታገኝ ይረዱሃል። ይሖዋ የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ለማየት ስትጠባበቅ “ፍሥሓና ሐሤት ያገኛሉ፤ ሐዘንና ትካዜ ከዚያ ይሸሻሉ” ከተባለላቸው ሰዎች መካከል መሆን ትችላለህ።—ኢሳይያስ 35:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (2003) ሲኦልን “ሕመምም ሆነ ደስታ፣ ቅጣትም ሆነ ሽልማት የሌለበት ቦታ” እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሐዘናችን ሊያጽናናን የሚችለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብቻ ነው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ ትንሣኤ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ደስተኛ እንድትሆን ያስችልሃል