በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስታ ማግኘት ትችላለህ

ደስታ ማግኘት ትችላለህ

ደስታ ማግኘት ትችላለህ

ደስታ ማለትም እውነተኛና ዘላቂ ደስታ ማግኘት አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ይህም የሆነው ብዙ ሰዎች ደስታ ለማግኘት የሚጥሩት ከትክክለኛው ምንጭ ስላልሆነ ነው። እምነት የሚጥሉበትና ጥሩ ችሎታ ያለው ወዳጅ ቢኖራቸው ትክክለኛውን አቅጣጫ ያሳያቸው ነበር!

እንዲህ ያለውን አስፈላጊ መመሪያ የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። እስቲ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመዝሙርን መጽሐፍ ብቻ እንመልከት። ይህ መጽሐፍ ለይሖዋ አምላክ የቀረቡ 150 ቅዱስ መዝሙሮችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ግማሹን ያቀናበረው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ነው። የጸሐፊዎቹን ማንነት ከማወቅ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ግን መጽሐፉ በመንፈሱ አነሳሽነት እንዲጻፍ ያደረገው ከማንም በላይ የሰው ልጆች ወዳጅ የሆነው ይሖዋ መሆኑን ማወቁ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ የሆነ መለኮታዊ መመሪያ እንደያዘና ደስታ ለማግኘት የሚያስችለንን መንገድ እንደሚጠቁመን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

የመዝሙር ጸሐፊዎች፣ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለው ጥሩ ዝምድና ደስታ ሊያስገኝለት እንደሚችል እርግጠኞች ነበሩ። መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ . . . የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 112:1) ከሰዎች ጋር የመሠረትነው ማንኛውም ዝምድናም ሆነ ያለን ቁሳዊ ንብረት አሊያም ያገኘነው ስኬት “እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ” ከሚያገኘው ደስታ ጋር አይወዳደርም። (መዝሙር 144:15) በዘመናችን የሚገኙ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ያሳለፉት ሕይወት የዚህን አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል።

ከእነዚህ መካከል በ40ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ዙዛን አንዷ ናት። a እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “በዛሬው ጊዜ ተመሳሳይ ግቦች ወይም ፍላጎቶች ያሏቸው ብዙዎች ያሰቡትን ለማሳካት የአንድ ቡድን አባል ይሆናሉ። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ በቡድኑ ውስጥ ያሉትን ሰዎች እንደ ወዳጅ አድርገው አይመለከቷቸውም። ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መሆን ግን በጣም የተለየ ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር እርስ በርሳችን እንድንዋደድ አድርጎናል። በየትኛውም ቦታ ብንገኝ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ስንሆን እንግድነት አይሰማንም። ይህ ዓይነቱ አንድነት እጅግ አስደሳች ሕይወት እንድንመራ ያደርገናል። ፈጽሞ የተለየ አስተዳደግ ካላቸው እንዲሁም ከበርካታ አገራት ከተውጣጡ ሰዎች ጋር ወዳጅ ነኝ ሊል የሚችል ይኖራል? በይሖዋ ሕዝቦች መካከል መሆን ደስታ እንደሚያስገኝ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ።”

የስኮትላንድ ተወላጅ የሆነችው ማሪ አንድን ሰው ደስተኛ እንዲሆን የሚያደርገው ዋነኛው ነገር ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት እንደሆነ ትናገራለች። እንዲህ ትላለች:- “የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከመማሬ በፊት አስፈሪ ፊልሞችን ማየት እወድ ነበር። ሆኖም በፊልም የማያቸው ጣረሞቶችና ጭራቆች ማታ ማታ በሕልሜ እየመጡ እንዳይረብሹኝ መስቀል ሳልይዝ አልተኛም ነበር። እውነትን ካወቅኩና እንደነዚህ ዓይነቶቹን ፊልሞች ማየት ካቆምኩ በኋላ ግን ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና ስተኛ እንዳልፈራ አድርጎኛል። ከአጋንንትም ሆነ በምናብ ከተፈጠሩ ጭራቆች ይበልጥ ኃይል ያለውን አምላክ በማገልገሌ ደስተኛ ሆኛለሁ።”

በይሖዋ መታመን ደስተኛ ያደርጋል

ፈጣሪ ገደብ የሌለው ጥበብ ያለውና ሁሉን ቻይ መሆኑን ለመጠራጠር የሚያበቃ ምንም ምክንያት የለንም። ዳዊት በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ማሳደርና እሱን መጠጊያ ማድረግ እንደሚችል ያውቅ ስለነበር “እግዚአብሔርን መታመኛው ያደረገ . . . ሰው ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 40:4

ማሪያ እንዲህ ትላለች:- “በስፔንና በሌሎች ቦታዎች ካጋጠሙኝ ነገሮች እንደተመለከትኩት ስሜታችን ወይም አመለካከታችን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊያዘነብል ቢችልም ነገሮችን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ የምናከናውን ከሆነ ከሁሉ የላቀ ውጤት እናገኛለን። የይሖዋ መንገዶች ምንጊዜም ቢሆን የተሻሉ በመሆናቸው ደስተኛ እንድንሆን ያደርጉናል።”

በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ያገለገለውና የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌ የሆነው አንድሬአስ በይሖዋ መታመን እንደምንችል ከራሱ ተሞክሮ ለመገንዘብ ችሏል። እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ታላቅ ወንድሜ ዳጎስ ያለ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ እንድይዝ በማበረታታት በወጣትነቴ ወቅት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርግብኝ ነበር። አስተማማኝ እንደሆነ የሚታሰበውን ጥሩ የጡረታ አበል የሚያስገኝ ሰብዓዊ ሥራ ከመያዝ ይልቅ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ስጀምር በጣም ተበሳጨ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በምካፈልበት ወቅት የሚያስፈልገኝን ነገር ፈጽሞ አጥቼ አላውቅም፤ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች የሚመኙትን በረከት ማግኘት ችያለሁ።”

ፌሊክስ በ1993 በሴልተርስ፣ ጀርመን የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለማስፋፋት በሚደረገው ሥራ ላይ እንዲረዳ ተጠራ። ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ቋሚ የቤቴል ቤተሰብ አባል እንዲሆን ተጋበዘ። በዚህ ጊዜ ምን ተሰማው? “አንዳንድ እርግጠኛ ያልሆንኩባቸው ነገሮች ቢኖሩም ግብዣውን ተቀበልኩ። ሆኖም አሁን በቤቴል ማገልገል ከጀመርኩ አሥር ዓመት ገደማ ይሆነኛል፤ ይሖዋ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ እርግጠኛ ነኝ። ለእኔ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደርና እሱ እንዲመራኝ በመፍቀድ ከእኔ ምን እንደሚፈልግ እንዲያሳየኝ አጋጣሚ ሰጥቼዋለሁ።”

ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ዙዛን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ማለትም አቅኚ ለመሆን ብትፈልግም የግማሽ ቀን ሥራ ለማግኘት ተቸግራ ነበር። ለአንድ ዓመት ያህል የዚህ ዓይነት ሥራ ስትፈልግ ከቆየች በኋላ በይሖዋ በመታመን እርምጃ ወሰደች። እንዲህ ትላለች:- “የዘወትር አቅኚ ለመሆን አመለከትኩ። የአንድ ወር መሠረታዊ ወጪዎቼን ለመሸፈን የሚበቃኝን ገንዘብ አጠራቅሜ ነበር። በዚያ ወር በጣም ደስ የሚል ጊዜ አሳለፍኩ! በአገልግሎቴ ከፍተኛ ደስታ ባገኝም ሥራ ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት ግን አልተሳካልኝም። ሆኖም ይሖዋ ቃል እንደገባው አልተወኝም። በወሩ የመጨረሻ ቀን ላይ የሥራ ኮንትራት ለመፈራረም ቻልኩ። አሁን በይሖዋ ላይ የምመካበት በቂ ምክንያት እንዳለኝ ተገንዝቤያለሁ! በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስካፈል የገጠመኝ ይህ የመጀመሪያ ተሞክሮ አርኪና ደስተኛ ሕይወት እንድመራ አስተዋጽኦ አበርክቶልኛል።”

አምላክ የሚሰጠንን ምክር መቀበል ደስታ ያስገኛል

ንጉሥ ዳዊት ከባድ ኃጢአት ሠርቶ ነበር። አልፎ አልፎም ጥበብ ያዘለ ምክር ማግኘት አስፈልጎት ነበር። ታዲያ እኛ ልክ እንደ ዳዊት ምክርና መመሪያ ሲሰጠን ለመቀበል ፈቃደኞች ነን?

ኤዴ የተባለች ፈረንሳዊት በአንድ ወቅት ከባድ ስህተት ፈጽማ ነበር። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በዋነኝነት ያሳሰበኝ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ማደስ ነበር፤ ሌላው ነገር ብዙም አላስጨነቀኝም።” በመሆኑም ወደ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሄዳ እርዳታ ጠየቀች። ለአሥራ አራት ዓመት ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ካገለገለች በኋላ አሁን እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ይሖዋ ስህተቴን ይቅር እንዳለኝ ማወቄ የመንፈስ እርካታ አስገኝቶልኛል!”

አምላክ የሚሰጠንን ምክር የምንቀበል ከሆነ መጀመሪያውኑም ስህተት ከመሥራት ሊጠብቀን ይችላል። ዩዲት እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “የሃያ ዓመት ወጣት ሳለሁ እኔን ለመማረክ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ከነበረ አብሮኝ የሚሠራ ጀርመናዊ ጋር ፍቅር ያዘኝ። በሰው ፊት የተከበረና ስኬታማ ከመሆኑም ሌላ ባለትዳር ነበር! የይሖዋን ሕግጋት የመታዘዝ አሊያም መመሪያዎቹን የመጣስ ምርጫ እንደተደቀነብኝ ተገነዘብኩ። ስለ ጉዳዩ ለወላጆቼ ነገርኳቸው። አባቴ፣ ይሖዋ ከእኔ ምን እንደሚጠብቅ በማያሻማ መልኩ ነገረኝ። ሁኔታውን ምንም ሳያድበሰብስ በግልጽ አስረዳኝ፤ እኔም የሚያስፈልገኝ ይኸው ነበር! ይሁን እንጂ በልቤ ያሰብኩትን ለማድረግ ቀዳዳ እፈላልግ ነበር። ለበርካታ ሳምንታት እናቴ የአምላክ ሕግጋት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑና ሕይወታችንን ከአደጋ እንደሚጠብቁልን ማታ ማታ ትነግረኝ ነበር። ልቤ ቀስ በቀስ ወደ ይሖዋ በመመለሱ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ከይሖዋ ተግሣጽና ትምህርት ማግኘቴ በጣም ደስተኛ እንድሆን አስችሎኛል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው ዓመታት ብዙ ተባርኬያለሁ፤ እንዲሁም የሚወደኝና ይሖዋንም በሙሉ ልቡ የሚወድ ግሩም ክርስቲያን የትዳር ጓደኛ አግኝቻለሁ።”

እነዚህ ተሞክሮዎች ዳዊት የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ናቸው:- “መተላለፉ ይቅር የተባለለት፣ ኀጢአቱም የተሸፈነለት፣ እንዴት ቡሩክ [“ደስተኛ፣” NW] ነው! እግዚአብሔር ኀጢአቱን የማይቈጥርበት፣ . . . እርሱ ቡሩክ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።”—መዝሙር 32:1, 2

ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት ደስተኛ መሆን

ዳዊት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ለድኾች የሚያስብ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW] ነው፤ እርሱንም እግዚአብሔር በክፉ ቀን ይታደገዋል። እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል፤ በምድርም ላይ ይባርከዋል።” (መዝሙር 41:1, 2) ዳዊት፣ የወዳጁ የዮናታን ልጅ ለነበረውና ሽባ ለሆነው ለሜምፊቦስቴ ያሳየው ፍቅራዊ አሳቢነት የተለያየ ችግር ላለባቸው ሰዎች ሊኖረን በሚገባው አመለካከት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።—2 ሳሙኤል 9:1-13

ለአርባ ሰባት ዓመታት በሚስዮናዊነት ያገለገለችው ሜርሊስ፣ ለሕይወታቸው የሚያሰጉ ሁኔታዎች በመኖራቸው ምክንያት ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከምሥራቃዊ አውሮፓ ለተሰደዱ ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ ጥሩ አጋጣሚ አግኝታለች። እንዲህ ትላለች:- “እነዚህ ሰዎች የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸው ሲሆን በጥቅሉ ሲታይ በማኅበረሰቡ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዳላገኙና መድሎ እንደሚደረግባቸው ይሰማቸዋል። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን መርዳት ሁልጊዜ ደስታ ያመጣል።”

በአርባዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ማሪና እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “ነጠላ እንደመሆኔ መጠን ሌሎች እኛን ለመርዳት ጓደኛ እንደሚሆኑን ማወቁ በጣም እንደሚያጽናና አውቃለሁ። ይህ ደግሞ ሌሎችን ስልክ በመደወል ወይም ደብዳቤ በመጻፍ እንዳበረታታቸው ያነሳሳኛል። ብዙዎቹ አድናቆታቸውን ይገልጹልኛል። ሌሎችን መርዳቴ ደስታ አስገኝቶልኛል።”

በሃያዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኘው ዲሚታ እንዲህ ይላል:- “እናቴ ያሳደገችኝ ያለ አባት ነው። ወጣት ሳለሁ እኔን ለማሠልጠን በየሳምንቱ ወደ አገልግሎት ይዞኝ የሚሄደውን የመጽሐፍ ጥናታችን የበላይ ተመልካች የሆነውን ወንድም በማግኘቴ በጣም እደሰት ነበር። አሁንም ቢሆን በጽናት ስለረዳኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። እኔን ማበረታታት ሁልጊዜ ቀላል እንዳልነበረ አውቃለሁ።” ዲሚታ ቀደም ብሎ ላገኘው እርዳታ አመስጋኝነቱን ለመግለጽ ሌሎችን የሚረዳ ሲሆን “ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ አብረውኝ እንዲያገለግሉ አደርጋለሁ” በማለት ተናግሯል።

የመዝሙር መጽሐፍ ደስታ ማግኘት የሚቻልባቸው ሌሎች ነገሮችም እንዳሉ ይገልጻል። ከእነዚህም አንዱ በራስ ሳይሆን ከይሖዋ በምናገኘው ብርታት መታመን ነው:- “[ይሖዋን] ብርታታቸው ያደረጉ፣ . . . ቡሩካን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው።”—መዝሙር 84:5

ኮሪና ይህን ሐቅ ከራሷ ተሞክሮ መመልከት ችላለች። በአንድ ወቅት የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄዳ ነበር። እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “በሄድኩበት አካባቢ የሚነገረውን ቋንቋ የማላውቀው ከመሆኑም በላይ የሰዎቹ ባሕልና አስተሳሰብ ለየት ያለ ነበር። ሌላ ፕላኔት ውስጥ የገባሁ መሰለኝ። እንግዳ በሆነው አካባቢ መስበክ አስጨናቂ ሆነብኝ። ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ፣ በመሆኑም ይሖዋ በሰጠኝ ብርታት ገለልተኛ በሆነ ክልል ውስጥ ሙሉ ቀን ለመስበክ ችያለሁ። ከጊዜ በኋላ እየለመድኩት መጣሁ። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ያገኘሁ ሲሆን አሁንም ባገኘሁት ሥልጠና እየተጠቀምሁ ነው። ከባድ የሚመስሉ ችግሮችም እንኳ ከይሖዋ በምናገኘው ብርታት ልንወጣቸው እንደምንችል ተገንዝቤያለሁ።”

አዎን፣ ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል ከአምላክና ከሕዝቦቹ ጋር ወዳጅነት መመሥረት፣ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን፣ የሚሰጠንን መለኮታዊ ምክር መቀበልና ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት ይገኙበታል። በይሖዋ መንገዶች በመሄድና ሕግጋቱን በመታዘዝ ሞገሱን በማግኘት መደሰት እንችላለን።—መዝሙር 89:15፤ 106:3፤ 112:1፤ 128:1, 2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሪያ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሪ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዙዛን እና አንድሬአስ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮሪና

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዲሚታ