መጽናት ደስታ ያስገኛል
የሕይወት ታሪክ
መጽናት ደስታ ያስገኛል
ማሪዮ ሮሻ ዴ ሶዛ እንደተናገረው
“ሚስተር ሮሻ ቀዶ ሕክምና ቢያደርግ የሚተርፍ አይመስለኝም።” አንድ ዶክተር ይህን ተስፋ አስቆራጭ ሐሳብ ከሰነዘረ 20 ዓመታት ቢያልፉም እስካሁን ድረስ በሕይወት ቆይቼ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ችያለሁ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት እንድጸና የረዳኝ ምንድን ነው?
የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት በሰሜናዊ ምሥራቅ ብራዚል፣ በባሃይ ግዛት ውስጥ በምትገኝ ሳንቶ ኢስቲቫኖ የምትባል አንዲት መንደር አቅራቢያ ባለ የእርሻ ቦታ ነበር። ሰባት ዓመት ሲሞላኝ አባቴን በእርሻ ሥራ መርዳት ጀመርኩ። በየቀኑ ከትምህርት ቤት ስመለስ አንድ ሥራ ይሰጠኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ አባቴ የግዛቲቱ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ሳልቫዶር ሲሄድ እርሻውን የመከታተሉን ኃላፊነት ይሰጠኝ ነበር።
በአካባቢያችን የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቧንቧ ውኃም ሆነ ዛሬ የሚታዩ ሌሎች ዘመናዊ ነገሮች ባይኖሩም ደስተኞች ነበርን። እኔና ጓደኞቼ በወላንዶና ከእንጨት በሠራናቸው መኪናዎች እንጫወት ነበር። እንዲሁም በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ክላርኔት ተብሎ የሚጠራውን የሙዚቃ መሣሪያ እጫወታለሁ። በመንደራችን በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን የመዘምራን ቡድን ውስጥ አገለግል በነበረበት ወቅት ኢስቶሪያ ሳግራዳ (ቅዱስ ታሪክ) የሚል መጽሐፍ አየሁ። ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት እንዲኖረኝ አደረገ።
በ1932 የሃያ ዓመት ወጣት ሳለሁ፣ ሰሜናዊው ምሥራቅ ብራዚል ለረጅም ጊዜ በዘለቀ ከባድ ረሃብ ተመታ። ድርቁ ከብቶቻችንን የጨረሰብን ከመሆኑም ሌላ ሰብሉንም አወደመብን። ስለዚህ ወደ ሳልቫዶር ሄድኩና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ሾፌር ሆኜ ተቀጠርኩ። ከዚያም ቤት ተከራየሁና ቤተሰቦቼ ከእኔ ጋር እንዲኖሩ አመጣኋቸው። በ1944 አባቴ ሲሞት እናታችንን እንዲሁም ስምንት እህቶቼንና ሦስት ወንድሞቼን የመንከባከቡ ኃላፊነት በእኔ ላይ ወደቀ።
ከሾፌርነት ወደ ወንጌላዊነት
ወደ ሳልቫዶር እንደመጣሁ መጽሐፍ ቅዱስ ገዛሁ። ከዚያም ለተወሰኑ ዓመታት በባብቲስት ቤተ ክርስቲያን እሰበሰብ ነበር። በዚያን ወቅት የሥራ ባልደረባዬ ከሆነው ዱርቫል ከሚባል ሰው ጋር ጓደኝነት መሥርቼ ስለነበር በተደጋጋሚ ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት እናደርግ ነበር። አንድ ቀን ዱርቫል፣ ዌር አር ዘ ዴድ? (ሙታን የት ናቸው?) a የሚል ርዕስ ያለው ቡክሌት ሰጠኝ። ምንም እንኳ ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው ብዬ የማምን ቢሆንም በቡክሌቱ ላይ ያሉት ጥቅሶች ትክክል መሆናቸውን የማየት ጉጉት አደረብኝ። የሚገርመው መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እንደምትሞት አረጋገጠልኝ።—ሕዝቅኤል 18:4
ዱርቫል የነበረኝን ፍላጎት ስለተመለከተ አንቶኒዮ አንድራዲ የተባለ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤቴ መጥቶ እንዲያነጋግረኝ አደረገ። ሦስት ጊዜ ያህል ከተወያየን በኋላ ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር አብሬው እንድሄድ ጋበዘኝ። ከዚያም ሁለት ቤቶችን አንኳኩተን ሰዎቹን ካነጋገረ በኋላ “አሁን የአንተ ተራ ነው” አለኝ። በጣም የፈራሁ ቢሆንም የአንድ ቤተሰብ አባላት በጥሞና አዳምጠውኝ ያበረከትኩላቸውን ሁለት መጻሕፍት በመውሰዳቸው ተደሰትኩ። ዛሬም ቢሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት የሚያሳይ ሰው ሳገኝ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል።
በሚያዝያ 19, 1943 የክርስቶስ የሞቱ መታሰቢያ በተከበረበት ዕለት በሳልቫዶር አቅራቢያ በሚገኘው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ተጠመቅሁ። በወቅቱ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያን ወንድሞች ባለመኖራቸው የሳልቫዶርን ከተማ ሁለት ክፍሎች ከሚያገናኙት ጠባብ መንገዶች አንደኛው ላይ ባለው የወንድም አንድራዲ ቤት የሚሰበሰበውን ቡድን እንድረዳ ተመደብኩ።
ተቃውሞ ገጠመን
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት (1939-1945) ክርስቲያናዊ ሥራችን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። ብዙዎቹ ጽሑፎቻችን ከዩናይትድ ስቴትስ ይመጡ ስለነበር አንዳንድ ባለ ሥልጣናት የአሜሪካ ሰላዮች አድርገው ያስቡን ነበር። በዚህም ምክንያት መታሰርና ለምርመራ መቅረብ የተለመደ ነበር። አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ መስክ አገልግሎት ወጥቶ ካልተመለሰ በፖሊስ እንደተያዘ ስለሚገባን እርሱን ለማስለቀቅ ፖሊስ ጣቢያ እንሄዳለን።
በነሐሴ ወር 1943 አዶልፍ ሚስመር የተባለ ጀርመናዊ ወንድም በከተማችን የመጀመሪያውን ትልቅ ስብሰባ ለማዘጋጀት ወደ ሳልቫዶር መጣ። ስብሰባውን ለማካሄድ ከባለ ሥልጣናት ፈቃድ ካገኘን በኋላ “በአዲሱ ዓለም የሚገኘው ነጻነት” የሚል ጭብጥ ያለውን የሕዝብ ንግግር ርዕስ በአካባቢው በሚታተመው ጋዜጣ ላይ በማውጣት እንዲሁም በሱቆች መስኮትና በሕዝብ ማመላለሻዎች ላይ በመለጠፍ ማስተዋወቅ ጀመርን። ነገር ግን በስብሰባው ሁለተኛ ቀን ላይ አንድ ፖሊስ የስብሰባ ፈቃዳችን መሰረዙን ነገረን። የፖሊስ አዛዡ ስብሰባውን እንዲያስቆም የሳልቫዶር ጳጳስ ግፊት አድርገውበት ነበር። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ዓመት በሚያዝያ ወር ላይ ይህ የሕዝብ ንግግር እንዲቀርብ ፈቃድ ማግኘት ችለናል።
ግቤ ላይ መድረስ
በ1946፣ በሳኦ ፓውሎ በሚደረገው ደስተኛ ሕዝቦች በተባለው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ።
በሳልቫዶር ያለ አንድ የዕቃ መጫኛ መርከብ ካፒቴን፣ በመርከቧ የላይኛው ወለል ላይ ተኝተን መጓዝ ከቻልን እንደሚወስደን ነገረን። በጉዞ ላይ ማዕበል ስላጋጠመን ሁላችንም ብንታመምም ከአራት ቀናት በኋላ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ደረስን። በሪዮ ዴ ጄኔሮ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቀጣዩን የባቡር ጉዟችንን ከመጀመራችን በፊት ለበርካታ ቀናት በቤታቸው በእንግድነት ተቀብለው አስተናገዱን። የተሳፈርንበት ባቡር ሳኦ ፓውሎ ሲደርስ “የይሖዋ ምሥክሮች እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚል ጽሑፍ ያለበት ሰሌዳ የያዙ ወንድሞች ተቀበሉን።ወደ ሳልቫዶር እንደተመለስኩ ብዙም ሳልቆይ አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የመሆን ፍላጎት እንዳለኝ ከዩናይትድ ስቴትስ ለመጣው ሃሪ ብላክ ለተባለ ሚስዮናዊ ወንድም ነገርኩት። ሃሪም የቤተሰብ ኃላፊነት እንዳለብኝ ካስታወሰኝ በኋላ በትዕግሥት እንድጠብቅ መከረኝ። በመጨረሻም ወንድሞቼና እህቶቼ ራሳቸውን በመቻላቸው፣ ሰኔ 1952 ከሳልቫዶር በስተደቡብ 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በኤልያዉስ ባለ አንድ ትንሽ ጉባኤ ውስጥ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ።
የተትረፈረፈ በረከት
በሚቀጥለው ዓመት አንድም የይሖዋ ምሥክር በሌለባት ዜክያ በምትባል ትልቅ ከተማ ተመደብኩ። እዚያም በመጀመሪያ ያነጋገርኩት ሰው የከተማዋ ቄስ ነበር። እርሱም ከተማዋ የእርሱ ክልል እንደሆነችና በዚያም መስበክ እንደማልችል ነገረኝ። የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላትም “የሐሰት ነቢይ” እንደመጣ በማስተማር ካስጠነቀቃቸው በኋላ ሥራዬን እየተከታተሉ የሚነግሩት ሰዎች መደበ። የሆኖ ሆኖ በዚያን ቀን ከ90 በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከማበርከቴም በላይ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀምሬ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ በዜክያ 36 ሰዎች የይሖዋ ምሥክር ሲሆኑ የመንግሥት አዳራሽም መገንባት ተችሏል! በአሁኑ ወቅት በከተማዋ 700 የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፉ ስምንት ጉባኤዎች አሉ።
በዜክያ ባሳለፍኳቸው የመጀመሪያዎቹ ወራት እኖር የነበረው ከከተማዋ ወጣ ያለ ቦታ ላይ አነስተኛ ቤት ተከራይቼ ነበር። በከተማዋ ከሚገኙት ሆቴሎች መካከል በጣም ጥሩ የሚባለው ሆቴል ሱዴስታ ሲሆን አንድ ቀን የዚህ ሆቴል ባለቤት የሆነውን ሜጌል ቫዝ ዴ ኦሊቬራን አነጋገርኩት። ብዙም ሳይቆይ ሜጌል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጀመረ ከመሆኑም በላይ በሆቴሉ ውስጥ ባለው አንድ ክፍል እንድኖር አጥብቆ ጠየቀኝ። በኋላም ሜጌል እና ባለቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።
በዜክያ ያጋጠመኝ ሌላው የማልረሳው ነገር ሊዊዝ ኮትሪን ከተባለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ ነው። ሊዊዝን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናው የነበረ ሲሆን እርሱም የፓርቹጋል ቋንቋና የሒሳብ ችሎታዬን ማሻሻል እንድችል ሊያስተምረኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። እኔም ከአንደኛ ደረጃ ያለፈ ትምህርት ስላልነበረኝ ግብዣውን ሳላመነታ ተቀበልኩ። በየሳምንቱ ሉዊዝን መጽሐፍ ቅዱስ ካስጠናሁት በኋላ ይሰጠኝ የነበረው ትምህርት ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ድርጅት ላገኘሁት ልዩ መብት አዘጋጅቶኛል።
ተፈታታኝ የሆነ አዲስ ምድብ
በ1956 ሪዮ ዴ ጄኔሮ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሯችን በመሄድ የወረዳ የበላይ ተመልካች (ተጓዥ አገልጋይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆኜ እንዳገለግል የሚያስችለኝን ኮርስ እንድወስድ የሚጋብዝ ደብዳቤ ደረሰኝ። ከአንድ ወር በላይ በቆየው በዚህ ኮርስ ላይ ስምንት ወንድሞች አብረውኝ ተካፍለዋል። ኮርሱ እንዳለቀ በሳኦ ፓውሎ የተመደብኩ ሲሆን ይህም ፍርሃት እንዲሰማኝ አደረገኝ። ራሴን እንዲህ እያልኩ መጠየቅ ጀመርኩ:- ‘እኔ ጥቁር ሆኜ ሳለሁ በእነዚህ ሁሉ ጣሊያኖች መካከል ተመድቤ ምን ልሠራ ነው? ደግሞስ ይቀበሉኝ ይሆን?’ b
በሳንቶ አማሩ ወረዳ የመጀመሪያውን ጉባኤ ስጎበኝ የመንግሥት አዳራሹ በወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ፍላጎት ባላቸው ሌሎች ሰዎች ግጥም ብሎ በማየቴ ተበረታታሁ። በዚያ ሳምንት በጉባኤው ውስጥ ያሉት 97 አስፋፊዎች በሙሉ አብረውኝ ለማገልገል በስምሪት ስብሰባ ላይ ሲገኙ፣ የፈራሁት ያለ ምክንያት እንደነበር ተገነዘብኩ። ‘እውነትም ወንድሞቼ ናቸው’ ብዬ አሰብኩ። የእነዚያ ውድ ወንድሞችና እህቶች ፍቅር የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንድቀጥል ብርታት ሆኖኛል።
አህያ፣ ፈረስና አዋልድጌሳ
በእነዚያ ዓመታት ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ተፈታታኝ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ፣ ከከተማዎች በጣም ርቀው በገጠራማ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ጉባኤዎችንና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮችን የያዙ ቡድኖችን መጎብኘት ነበር። በእነዚህ ቦታዎች ላይ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት መጠቀም የማያስተማምን ከመሆኑም በላይ መኪና ፈጽሞ የማይገኝባቸው አካባቢዎችም ነበሩ። በተጨማሪም ብዙዎቹ መንገዶች ጠባብና ኮረኮንች ነበሩ።
አንዳንድ ወረዳዎች ይህን መሰሉን ችግር ለማቃለል የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እንዲጠቀሙበት አህያ ወይም ፈረስ ይገዙ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሰኞ ሰኞ፣ በአህያ ወይም በፈረስ ላይ ኮርቻዬን ከጫንኩ በኋላ ጓዜን በኮርቻው ላይ አስሬ ወደሚቀጥለው ጉባኤ ለመድረስ 12 ሰዓት ያህል በፈረስ ወይም በአህያ እጓዛለሁ። በሳንታ ፌ ዱ ሱል ከተማ የሚገኘው ጉባኤ ዶራዶ (ጎልዲ) የሚባል አህያ ነበረው። ዶራዶ ገጠራማ አካባቢ ወደሚገኙ ቡድኖች የሚወስደውን መንገድ ጠንቅቆ ከማወቁም ሌላ ወንድሞች ቤት ስንደርስ ይቆምና በሩን እስክከፍተው ድረስ በትዕግሥት ይጠብቃል። ከዚያም ከጉብኝቱ በኋላ እኔና ዱራዶ ወደሚቀጥለው ቡድን እንጓዛለን።
አስተማማኝ የሆነ የመልእክት መለዋወጫ መንገድ አለመኖሩም የወረዳ የበላይ ተመልካችነትን ሥራ ተፈታታኝ ያደርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በማቶ ግሮሶ ግዛት ባለ አንድ የእርሻ ቦታ የሚሰበሰቡ ወንድሞችን ለመጎብኘት አራጉዋያ የሚባለውን ወንዝ በጀልባ ከተሻገርኩ በኋላ 25 ኪሎ ሜትር ደግሞ በፈረስ ወይም በአህያ በጫካ ውስጥ መጓዝ ይኖርብኛል። በአንድ ወቅት ላይ ይህን ቡድን እንደምጎበኝ ደብዳቤ ጽፌ የነበረ ቢሆንም ደብዳቤው ስላልደረሳቸው ወንዙን ከተሻገርኩ በኋላ የተቀበለኝ ሰው አልነበረም። እዚያ ቦታ የደረስኩት አመሻሹ ላይ ስለነበር በአካባቢው ለሚገኝ የአንድ ትንሽ ቡና ቤት ባለቤት ሻንጣዬን አደራ ሰጠሁና ቦርሳዬን ብቻ ይዤ በእግሬ መጓዝ ጀመርኩ።
ብዙም ሳይቆይ በጉዞ ላይ እያለሁ ጨለመ። በጨለማ ውስጥ እየተደናበርኩ ስሄድ የአዋልድጌሳ ዝርያ የሆነ ጉንዳንና ምስጥ በል እንስሳ ጩኸት ሰማሁ። ይህ እንስሳ ጠንካራ በሆኑት የፊት እግሮቹ ሰውን በመምታት ይገድላል የሚል ወሬ ሰምቼ ስለነበር ከጥሻው ውስጥ ትንሽ ኮሽታ በሰማሁ ቁጥር ቦርሳዬን ለመከላከያነት እንዲያመቸኝ ከፊት ለፊቴ በመያዝ በጥንቃቄ እራመድ ነበር። ከሰዓታት ጉዞ በኋላ አንድ አነስተኛ ወንዝ አጠገብ ደረስሁ። ጨለማ ስለነበረ ከወንዙ ባሻገር በእሾሃማ ሽቦ የተሠራ አጥር መኖሩን መመልከት ባለመቻሌ ወንዙን ለመሻገር በምዘልበት ጊዜ ከአጥሩ ጋር በመጋጨቴ ሽቦው ቆረጠኝ።
በመጨረሻም ወደ ወንድሞች ቤት ስደርስ ውሾች
እየጮሁ መጡብኝ። በአካባቢው የበግ ሌቦች ሌሊት ላይ መስረቃቸው የተለመደ ነገር ነበር። በመሆኑም ልክ በሩ ሲከፈት ማንነቴን ቶሎ ተናገርኩ። የተቀደደና በደም የተበከለ ልብስ ለብሼ ለተመለከተኝ ባሳዝንም ወንድሞች እኔን በማየታቸው በጣም ተደስተው ነበር።እነዚያ ጊዜያት እንዲህ ያሉ ችግሮች ቢኖርባቸውም እንዴት ደስ የሚሉ ነበሩ! አልፎ አልፎ በዛፍ ጥላ ሥር አረፍ እያልኩና የወፎችን ዝማሬ እያዳመጥኩ በፈረስ ወይም በእግር የማደርጋቸው ረጃጅም ጉዞዎች ያስደስቱኝ ነበር፤ በእነዚያ ጭር ባሉ መንገዶች ቀበሮዎችም ያጋጥሙኝ ነበር። ሌላው የደስታዬ ምንጭ ደግሞ የማደርገው ጉብኝት ሌሎችን የሚረዳ መሆኑን ማወቄ ነው። ብዙዎች የምስጋና ደብዳቤ ይጽፉልኛል። አንዳንዶች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገናኝ በአካል መጥተው ያመሰግኑኛል። ሰዎች ያሉባቸውን ችግሮች ተቋቁመው መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ ማየት እንዴት ያስደስታል!
በመጨረሻ ረዳት አገኘሁ
በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ካገለገልኩባቸው ከእነዚያ ዓመታት ብዙውን ጊዜ ያሳለፍኩት በነጠላነት ሲሆን ይህም ይሖዋን ‘ዐለቴና መጠጊያዬ’ ማድረግን አስተምሮኛል። (መዝሙር 18:2) በተጨማሪም ያላገባሁ መሆኔ ትኩረቴ ሳይከፋፈል ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዳከናውን አድርጎኛል።
በ1978 ዡሊያ ታካሺ ከተባለች አቅኚ እህት ጋር ተዋወቅን። ዡሊያ በሳኦ ፓውሎ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሆስፒታል ውስጥ በነርስነት ታገለግል የነበረ ቢሆንም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ሄዳ ለመስበክ ስትል ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝላትን ይህን ሥራ ለቅቃለች። የሚያውቋት የጉባኤ ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ ባሕርያቶቿና በአቅኚነት ባላት ችሎታ ያደንቋታል። ለዓመታት በነጠላነት ቆይቼ ትዳር መመሥረቴ አንዳንዶችን ምን ያህል እንዳስደነቃቸው መገመት ትችላላችሁ። አንድ ጥሩ ወዳጄ እንደማገባ ስነግረው ለማመን ስለከበደው ማግባቴ እውነት ከሆነ 270 ኪሎ ግራም የሚመዝን በሬ እንደሚሰጠኝ ቃል ገባልኝ። በሬው፣ ሐምሌ 1, 1978 ሳገባ በሠርጌ ላይ ተጠብሶ ቀረበ።
የጤንነት ችግር ቢኖርብኝም መጽናት ችያለሁ
በቀጣዮቹ ስምንት ዓመታት በደቡብና በደቡባዊ ምሥራቅ ብራዚል የሚገኙ ጉባኤዎችን ስጎበኝ ዡሊያ አብራኝ አገልግላለች። የልብ ችግር የጀመረኝ በዚያ ጊዜ ነበር። ከቤት ወደ ቤት እያገለገልኩ ሳለሁ ሁለት ጊዜ ራሴን ስቼ ወደቅሁ። ከዚያም የጤናዬ ሁኔታ እየከፋ በመምጣቱ በሳኦ ፓውሎ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ቢሪግዌ ልዩ አቅኚ ሆነን እንድናገለግል ተመደብን።
በዚህ ጊዜ በቢሪግዌ የሚገኙ ወንድሞች ለሕክምና 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ጎያኒ በመኪና ይዘውኝ ሄዱ። ጤንነቴ ሲሻሻል የልብ ምቴን የሚያግዝ መሣሪያ በቀዶ ሕክምና አማካኝነት አስገቡልኝ። ይህ የሆነው ከ20 ዓመታት በፊት ነበር። ከዚያ ወዲህ ሁለት ተጨማሪ የልብ ቀዶ ሕክምናዎች ቢደረጉልኝም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አሁንም በመካፈል ላይ እገኛለሁ። ዡሊያ፣ ልክ እንደ ሌሎቹ ታማኝ ክርስቲያን ሚስቶች ሁሉ የጥንካሬና የብርታት ምንጭ ሆናልኛለች።
በጤና ችግር ምክንያት እንቅስቃሴዬ ውስን ከመሆኑም በላይ አንዳንዴ ተስፋ የምቆርጥበት ጊዜ ቢኖርም እንኳ እስካሁን ድረስ አቅኚ ሆኜ ማገልገሌን አላቋረጥኩም። ይሖዋ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ አልጋ በአልጋ የሆነ ሕይወት ይኖራችኋል ብሎ ቃል እንዳልገባልን ለማስታወስ ጥረት አደርጋለሁ። ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ሌሎች ታማኝ የጥንት ክርስቲያኖች በተለያዩ ችግሮች መጽናት ካስፈለጋቸው እኛስ ከዚህ ውጭ ምን እንጠብቃለን?—የሐዋርያት ሥራ 14:22
በቅርቡ በ1930ዎቹ እጠቀምበት የነበረውን የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱሴን አገኘሁት። በሽፋኑ ውስጠኛ ክፍል ላይ በ1943 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ስጀምር በብራዚል የነበሩት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር 350 መሆኑን ጽፌበት ነበር። በአሁኑ ጊዜ ከ600,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች በብራዚል መኖራቸው ለማመን ያዳግታል። ለዚህ እድገት ትንሽ አስተዋጽኦ ማበርከቴ እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው! በእርግጥም ይሖዋ በመጽናቴ ክሶኛል። እንደ መዝሙራዊው እኔም “እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገልን፤ እኛም ደስ አለን” እላለሁ።—መዝሙር 126:3
[የግርጌ ማስታወሻዎች
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን መታተም አቁሟል።
b በ1870 እና በ1920 መካከል ባሉት ዓመታት ወደ 1,000,000 የሚጠጉ ጣሊያናውያን ስደተኞች በሳኦ ፓውሎ ሰፍረው ነበር።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንድሞች በሳልቫዶር ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የሚቀርበውን የሕዝብ ንግግር ሲያስተዋውቁ፣ 1943
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ደስተኛ ሕዝቦች በተባለው ስብሰባ ላይ ለመገኘት የይሖዋ ምሥክሮች ሳኦ ፓውሎ ሲገቡ፣ 1946
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1950ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከዡሊያ ጋር