በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛ እውቀት ማግኘት

ትክክለኛ እውቀት ማግኘት

ትክክለኛ እውቀት ማግኘት

ታኅሣሥ 18, 1810 አመሻሹ ላይ ነበር። ማዕበል በሚያናውጠው ባሕር ላይ የምትጓዘው ፓለስ የተባለችው የብሪታንያ ነገሥታት የባሕር ኃይል መርከብ፣ ከደቡባዊ ምሥራቅ የስኮትላንድ ወደብ ርቃ በመሄድ አቅጣጫዋን ሳተች። ምሽቱ እየገፋ መሄዱና የበረዶ ውሽንፍር መኖሩ የመርከቧ ሠራተኞች በሰላም ወደ ወደብ እንዲደርሱ የሚመራቸውን የወደብ መብራት እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። መጨረሻ ላይ ብርሃን ሲመለከቱና በዚያ አቅጣጫ መጓዝ ሲጀምሩ የተሰማቸውን እፎይታ መገመት ትችላለህ! የሚያሳዝነው ግን ያዩት ብርሃን እንዲመራቸው የሚፈልጉት የወደብ መብራት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በወደቡ አካባቢ የሚሠሩ የቀን ሠራተኞች ያነደዱት እሳት ነበር። ፓለስ ከዓለት ጋር በመላተሟ ሙሉ በሙሉ ተንኮታኮተች። አሥራ አንድ መርከበኞችም ሰጠሙ። እንዴት ያለ አሳዛኝ ገጠመኝ ነው!

ከፓለስ ሁኔታ መመልከት እንደምንችለው ሰዎቹን ለአደጋ የዳረጋቸው መሳሳታቸው ነው። እንዲያውም በሌሎች ጊዜያት መርከበኞች፣ ሆን ተብለው የተቀመጡ ሐሰተኛ የወደብ መብራቶች ሊገጥሟቸውና የባሰ አደጋ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ። ሬክስ፣ ሬከርስ ኤንድ ሬስኪዩወርስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው እንደነዚህ ያሉት መብራቶች የሚቀመጡት መርከቦችን ወደ ዓለታማ የባሕር ዳርቻዎች በመምራት በሚጋጩበት ጊዜ ለመዝረፍ ታስቦ ነው።

‘መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡን የሚችሉት ቅዱሳት መጻሕፍት’

እውቀት ለማግኘት ጥረት በምታደርግበት ጊዜ እነዚያ መርከበኞች የደረሱባቸው ዓይነት አደጋዎች ይጋረጡብሃል። የተሳሳተ መረጃ ልትከተል ወይም ሆን ተብሎ በሚደረግ የማታለያ ዘዴ ልትታለል ትችላለህ። ሁለቱም እርምጃዎች አሳዛኝ ወደሆነ ገጠመኝ ሊመሩ ይችላሉ። ታዲያ ራስህን ለመጠበቅ ምን ማድረግ አለብህ? የምትጠቀምበት የእውቀት ምንጭ ትክክለኛና ተአማኒ መሆኑን አረጋግጥ። ይህ መጽሔት፣ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም የበለጠ አስተማማኝ የእውቀት ምንጭ መሆኑን ከ125 ዓመታት በላይ ሲያውጅ ቆይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የበለጠ አስተማማኝ የእውቀት ምንጭ የተባለው ‘መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡን የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍት’ ስለያዘ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:15-17

እርግጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚፈነጥቀው ብርሃን አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ትክክለኛነቱን መመርመርህ ተገቢ ነው። (መዝሙር 119:105፤ ምሳሌ 14:15) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እውነትም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት መጻፉን እርግጠኞች እንዲሆኑ ያደረጋቸውን መረጃ ማግኘት ከፈለግህ የዚህን መጽሔት አዘጋጆች ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ለምሳሌ ያህል፣ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር አንብብ። a ይህ ብሮሹር መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ፣ እምነት የሚጣልበት እንዲሁም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎችን ይዟል።

መሠረታዊ የሆኑ እውነቶች

ታዲያ እነዚህ “ቅዱሳት መጻሕፍት” የያዟቸው አንዳንድ መሠረታዊ እውነቶች ምንድን ናቸው? እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት:-

ሁሉንም ነገር የፈጠረና ሁሉን ቻይ የሆነ አንድ አምላክ አለ። (ዘፍጥረት 1:1) ሕልውና ማግኘት የቻልነው ‘አምላክ ሁሉን በመፍጠሩና’ ለእኛም ሕይወት በመስጠቱ ነው። (ራእይ 4:11) አምልኮ ለእርሱ ብቻ መቅረብ ያለበት በዚህ ምክንያት ነው። ፈጣሪ የእውቀት ሁሉ ዋና ምንጭ ነው። (መዝሙር 36:9፤ ኢሳይያስ 30:20, 21፤ 48:17, 18) እኛ እንድንጠቀምበት የሚፈልገው የግል ስም አለው። (ዘፀአት 3:15) ይህን ስም የሚወክሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት (በአማርኛው የሐወሐ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛሉ። በአማርኛ ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት የተሠራበት የተለመደው አጠራር “ይሖዋ” የሚለው ነው።—መዝሙር 83:18 NW፤ ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም

ይሖዋ ሰዎችን የፈጠረው በዚህች ምድር ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። ይሖዋ ለሰው ልጆች የእርሱን ማንነት የሚያንጸባርቁ መንፈሳዊ ባሕርያትን ለግሷቸዋል። በተፈጥሮ የሰጣቸው ችሎታም በምድር ላይ ለዘላለም የሚመሩት ሕይወት አስደሳችና እርካታ የሞላበት እንዲሆን ይረዳቸዋል። (ዘፍጥረት 1:26-28) ብዙዎች፣ የሰው ልጆች ወደ ሰማይ ካልሄዱ በቀር ከአምላክ ጋር ዝምድና መፍጠር እንደማይችሉ ይሰማቸዋል፤ በመሆኑም አምላክ ምድርን የፈጠረው ሰዎች በሰማይ ለሚያገኙት መንፈሳዊ ሕይወት የሚዘጋጁባት የፈተና ቦታ እንድትሆን ነው የሚል እምነት አላቸው። የአምላክ ዓላማ ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው።

በአምላክ ሰብዓዊ ፍጥረት ውስጥ ምንም ክፋት አልነበረም። ክፋት የሚባል ነገር የመጣው አንዳንድ ሰብዓዊና መንፈሳዊ የአምላክ ፍጥረታት የተሰጣቸውን የመምረጥ ነጻነት ያላግባብ ተጠቅመው በአምላክ ላይ ባመጹበት ጊዜ ነው። (ዘዳግም 32:5) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለራሳቸው የመወሰን መብት እንዳላቸው ተሰምቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-5) ይህ ደግሞ በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ሞት አስከትሏል። (ዘፍጥረት 3:19፤ ሮሜ 5:12) ይሖዋ በዚህ ዓመጽ አማካኝነት ለተነሱት አከራካሪ ጉዳዮች እልባት ለማስገኘት ሲል ክፋት ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል ወሰነ። ይሁን እንጂ ለምድርም ሆነ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ያለው ዓላማ ፈጽሞ አልተለወጠም። (ኢሳይያስ 45:18) በመሆኑም ወደፊት የሰው ልጆች በጸዳች ምድር ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖራቸው አይቀርም።—ማቴዎስ 6:10፤ ራእይ 21:1-5

ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ እንጂ ሁሉን ቻይ አምላክ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል እንደሆነ ተናግሮ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ ‘አብ ከእኔ ይበልጣል’ ብሏል።—ዮሐንስ 14:28

ኢየሱስ የአምላክ ዓላማ ግቡን እንዲመታ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። አምላክ ‘[በኢየሱስ] የሚያምን በጨለማ እንዳይኖር ለዓለም ብርሃን እንዲሆን’ ልኮታል። (ዮሐንስ 12:46) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረው “ድነት በሌላ በማንም አይገኝም።” (የሐዋርያት ሥራ 4:12) መዳናችን የተመካው በክርስቶስ ውድ ደም ላይ በመሆኑ ይህ አባባል ትክክለኛ ነው። (1 ጴጥሮስ 1:18, 19) ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ካመጡት ኃጢአት የሰው ልጆችን ለማዳን ሲል ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:6) ከዚህም በላይ የአምላክን ፈቃድና ዓላማ ግልጽ አድርጓል።—ዮሐንስ 8:12, 32, 46, 47፤ 14:6፤ የሐዋርያት ሥራ 26:23

አምላክ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እና ከሰው ልጆች መካከል በተመረጡ ሰዎች የሚተዳደር መንግሥት ወይም አገዛዝ በሰማይ አቋቁሟል። ይህ መልእክት በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። አምላክ ዓላማው በሰማይ እንደተፈጸመ ሁሉ በምድር ላይም እንዲፈጸም የማድረጉን ኃላፊነት የሰጠው ለዚህ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:10) አምላክ መጀመሪያ ላይ ከሰው ዘር መካከል ማንም ሰው ወደ ሰማይ እንዲሄድ ዓላማው አልነበረም። የሰው ልጆች በምድር ላይ እንዲኖሩ አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በኃጢአት አዘቅት ውስጥ በወደቀ ጊዜ አምላክ አዲስ ነገር አዘጋጀ። በሰማይ ባለው መንግሥት ከክርስቶስ ጋር ‘የሚነግሡ’ ሰዎች “ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ” የሚመረጡበትን ዝግጅት አደረገ። (ራእይ 5:9, 10) ይህ መንግሥት በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ብዙ መከራና ሥቃይ ያደረሱትን ሁሉንም ዓይነት ሰብዓዊ አገዛዞች “ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል።”—ዳንኤል 2:44

ነፍስ ትሞታለች። መሠረታዊ የሆነው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስለ ሰው ማንነትም ይሁን ስለ ወደፊት ሕይወቱ በጣም ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ይሰጣል። ከዚህም በላይ ሰዎች፣ ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ግራ እንዲጋቡ ያደረጓቸውን የተሳሳቱ መረጃዎች ያስወግዳል።

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍጥረት 2:7) ይህ ጥቅስ ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቶሃል? ነፍስ ማለት በሰው አካል ውስጥ የምትገኝ የማትታይ ነገር አይደለችም። የሰው ልጅ ነፍስ የለውም። ከዚህ ይልቅ እርሱ ራሱ ነፍስ ነው። በሌላ አባባል ነፍስ ሲባል “ከምድር ዐፈር” የተገኙ ንጥረ ነገሮችና ከአምላክ የሚወጣው የሕይወት ኃይል ጥምረት ማለት ነው። ነፍስ የማይሞት ነገር አይደለም። አንድ ሰው ሞተ ሲባል ነፍስ ሞተ ማለት ነው።—ዘፍጥረት 3:19፤ መክብብ 9:5, 10

የሞቱ ሰዎች በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና ሕይወት ማግኘት ይችላሉ። አምላክ ክፋት እንዲቆይ የፈቀደበት ጊዜ ሲጠናቀቅ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ [የኢየሱስን ድምፅ] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።” (ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች፣ አምላክ መጀመሪያ ላይ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ሊሰጥ ባሰበው መሠረት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር ይችላሉ።

ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መርምር

እንደነዚህ ያሉትን መሠረታዊ እውነቶች ማወቅህ እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል ተመለከትክ? አስጨናቂና በጣም አስቸጋሪ በሆነው በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህን ዓይነት እውቀት ማግኘትህ ሰይጣን ዲያብሎስ ከሚያሰራጨው ‘የውሸት ዕውቀት’ ይጠብቅሃል። ሰይጣን “የብርሃን መልአክ” ሆኖ ለመታየት የሚጥር ሲሆን መልእክተኞቹ ደግሞ “የጽድቅ አገልጋዮች” ለመምሰል ራሳቸውን ይለውጣሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:20፤ 2 ቆሮንቶስ 11:13-15) ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ‘የእግዚአብሔርን ቃል በሚቃወሙ’ የዓለም ‘ጥበበኞችና ዐዋቂዎች’ ፍልስፍና ላይ ከተመሠረተው የውሸት እውቀት ይጠብቅሃል።—ማቴዎስ 11:25፤ ኤርምያስ 8:9

ሐዋርያው ዮሐንስ፣ በዘመኑ ብዙ አሳሳች ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች ስለነበሩ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “መንፈስን ሁሉ አትመኑ” የሚል ማስጠንቀቂያ ጽፎላቸዋል። አክሎም “መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ” ብሏቸዋል። (1 ዮሐንስ 4:1) እስቲ ይህን ምሳሌ ተመልከት። ሕይወትህን በእጅጉ ሊነካ የሚችል አንድ መልእክት ቢደርስህ ከጥሩ ምንጭ የመጣ ስለ መሰለህ ብቻ ትክክለኛነቱን ሳታረጋግጥ የሚነግርህን ሁሉ አምነህ ትቀበላለህ? እንዲህ እንደማታደርግ እሙን ነው። መልእክቱን ተቀብለህ እርምጃ ከመውሰድህ በፊት ምንጩን ማረጋገጥህና የመልእክቱን ይዘት መመርመርህ አይቀርም።

አምላክ፣ መሠረታዊ እውነቶችን ያቀፈና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ አዘጋጅቶልሃል፤ ይህ መጽሐፍ ደግሞ እየተከተልከው ያለኸው የመንገድ ብርሃን ወይም የወደብ መብራት ትክክለኛ መሆኑን ‘ፈትነህ’ እንድታውቅ ያስችልሃል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አስተዋይ ሰዎች የተማሩት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ሲሉ ‘መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመራቸው’ አድናቆት አትርፎላቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) አንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በጨለማ ስፍራ እንደሚበራ መብራት’ አስተማማኝ ወደ ሆነ ቦታ እንዲመራህ ፍቀድለት። (2 ጴጥሮስ 1:19-21) እንዲህ ማድረግህ ደግሞ ወደ ትክክለኛ እውቀት የሚመራህን ‘የአምላክን እውቀት እንድታገኝ’ ይረዳሃል።—ምሳሌ 2:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ ላይ የሚገኝ ሥዕል4]

የአምላክ ቃል እንደ መብራት ነው

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ስም ማን ነው?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው ዘር የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙታን የሚገኙት የት ነው?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትንሣኤ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው መሠረታዊ እውነቶች መካከል አንዱ ነው