አምላክ የመረጠው ብሔር አባል ሆኖ መወለድ
አምላክ የመረጠው ብሔር አባል ሆኖ መወለድ
‘አምላክህ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ እንድትሆንለት መረጠህ።’—ዘዳግም 7:6
1, 2. ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል ምን ታላላቅ ሥራዎችን አከናውኗል? እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር ምን ዓይነት ወዳጅነት መሥርተው ነበር?
ይሖዋ በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት በምድር ላይ የነበሩት አገልጋዮቹ ከእርሱ ጋር አዲስ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ አደረገ። በዚያው ዓመት የዘመኑን የዓለም ኃያል መንግሥት አዋርዶ እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ አወጣቸው። እንዲህ በማድረጉ አዳኛቸው ሆነ፤ እነርሱም ንብረቱ ሆኑ። አምላክ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ለሙሴ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያን ቀንበር አወጣችኋለሁ። ለእነርሱ ባሪያ ከመሆን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድና በታላቅ ፍርድ እቤዣችኋለሁ። የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።”—ዘፀአት 6:6, 7፤ 15:1-7, 11
2 እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከአምላካቸው ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ቃል ኪዳን ገቡ። ይሖዋ ከዚያ በኋላ ከግለሰቦች፣ ከቤተሰቦች ወይም ከጎሳዎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ፈንታ በምድር ላይ የተደራጀ አንድ ብሔር ይኖረዋል ማለት ነው። (ዘፀአት 19:5, 6፤ 24:7) የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን የሚመሩበት በተለይ ደግሞ አምልኮታቸውን የሚያካሂዱበት ሕግ ለሕዝቡ ሰጥቶ ነበር። ሙሴ እንዲህ ብሏቸዋል:- “በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው? ዛሬ እኔ በፊታችሁ እንዳስቀመጥሁት ሕግ ያለ ጽድቅ የሆነ ሥርዐትና ሕግ ያሉት ሌላ ታላቅ ሕዝብስ ማነው?”—ዘዳግም 4:7, 8
የይሖዋ ምሥክር በሆነ ብሔር ውስጥ መወለድ
3, 4. እስራኤላውያን በብሔር የተደራጁበት ዋነኛው ምክንያት ምን ነበር?
3 ይህ ከሆነ በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በብሔር መደራጀታቸው አስፈላጊ የሆነበትን ዋነኛ ምክንያት በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ በማለት ነግሯቸዋል:- “ያዕቆብ ሆይ! የፈጠረህ፤ እስራኤል ሆይ! የሠራህ፣ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንዲህ ይላል፤ ‘ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የእስራኤልም ቅዱስ መድኀኒትህ ነኝና፤ . . . ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ። ‘እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ’ ይላል እግዚአብሔር። . . . ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን ያውጅ ዘንድ ይህን አደርጋለሁ።’”—ኢሳይያስ 43:1, 3, 6, 7, 10, 21
4 እስራኤላውያን በይሖዋ ስም የተጠሩ ሕዝቦች እንደመሆናቸው መጠን በአሕዛብ ፊት ስለ እርሱ ሉዓላዊነት ምሥክር ሆነው ማገልገል ነበረባቸው። ‘ለይሖዋ ክብር የተፈጠሩ’ ሕዝብ መሆን ይገባቸዋል። ‘የይሖዋን ምስጋና በማወጅና’ እነርሱን ነፃ ለማውጣት ሲል ያከናወናቸውን ድንቅ ተግባሮች ለሌሎች በመናገር ቅዱስ ስሙን ከፍ ከፍ ማድረግ አለባቸው። በአጭር አነጋገር ብሔሩ ለይሖዋ ምሥክር መሆን ይገባው ነበር።
5. የእስራኤል ሕዝብ ለይሖዋ የተወሰነ ብሔር የነበረው በምን መንገድ ነው?
5 ንጉሥ ሰሎሞን በ11ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ይሖዋ እስራኤላውያንን ከሌሎች የተለዩ ብሔር እንዳደረጋቸው ተናግሯል። “ርስትህ ይሆኑ ዘንድ ከምድር ሕዝቦች ሁሉ ለይተሃቸዋል” ብሎ ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (1 ነገሥት 8:53) እስራኤላውያን በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ከይሖዋ ጋር ልዩ ወዳጅነት ነበራቸው። ቀደም ሲል ሙሴ “እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ . . . ምክንያቱም አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ነህ” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 14:1, 2) ስለዚህ ወጣት እስራኤላውያን ለአምላክ ከተወሰነ ብሔር ስለሚወለዱ ሕይወታቸውን ለይሖዋ መወሰን አያስፈልጋቸውም ነበር። (መዝሙር 79:13፤ 95:7) እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ የይሖዋን ሕግጋት የሚማር ሲሆን የእስራኤልን ብሔር ከይሖዋ ጋር ባስተሳሰረው ቃል ኪዳን ምክንያት የተማረውን ሕግ የመጠበቅ ግዴታ ነበረበት።—ዘዳግም 11:18, 19
የመምረጥ ነፃነት ነበራቸው
6. እስራኤላውያን በግለሰብ ደረጃ ምን ምርጫ ማድረግ ነበረባቸው?
6 እስራኤላውያን ለአምላክ ከተወሰነ ብሔር የተወለዱ ቢሆኑም እንኳን እያንዳንዱ ግለሰብ አምላክን ለማገልገል የራሱን ምርጫ ማድረግ ነበረበት። ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከእርሱ ጋር እንድትጣበቅ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወትህ ነው፣ ለአባቶችህ፣ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሊሰጣቸው በማለላቸው ምድር ረጅም ዕድሜ ይሰጥሃል።” (ዘዳግም 30:19, 20) ስለዚህ እስራኤላውያን ይሖዋን ለመውደድ፣ ቃሉን ለማዳመጥና ከእርሱ ጋር ለመጣበቅ በግለሰብ ደረጃ ምርጫ ማድረግ ነበረባቸው። እስራኤላውያን የመምረጥ ነፃነት ቢኖራቸውም የሚያደርጉት ምርጫ የሚያስከትልባቸውን ውጤት መቀበል ይገባቸዋል።—ዘዳግም 30:16-18
7. በኢያሱ ዘመን ከነበረው ትውልድ በኋላ ምን ተከሰተ?
7 ታማኝ መሆንና አለመሆን ምን ውጤት እንደሚያስከትል የመሳፍንት ዘመን ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። የመሳፍንት ዘመን ከመጀመሩ በፊት እስራኤላውያን የኢያሱን መልካም ምሳሌነት የተከተሉ ሲሆን ይህንን በማድረጋቸውም ተባርከዋል። “ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከእርሱ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ።” ነገር ግን ኢያሱ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። ከዚያም እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ።” (መሳፍንት 2:7, 10, 11) በወቅቱ የነበረው ተሞክሮ የሚያንሰው ወጣት ትውልድ ቀደም ባሉት ዘመናት ታላላቅ ተግባሮችን ላከናወነው ለአምላኩ ለይሖዋ የተወሰነ ብሔር አባል ሆኖ የመወለድ መብቱን አቅልሎ ሳይመለከት አልቀረም።—መዝሙር 78:3-7, 10, 11
ለአምላክ መወሰናቸው የሚያስከትልባቸውን ግዴታ መወጣት
8, 9. (ሀ) እስራኤላውያን ለይሖዋ የተወሰኑ መሆናቸውን ማሳየት ያስችላቸው የነበረው የትኛው ዝግጅት ነው? (ለ) መሥዋዕቶችን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ሰዎች ምን ያገኙ ነበር?
8 ይሖዋ፣ ሕዝቡ በብሔር ደረጃ ካደረገው ውሳኔ ጋር በሚስማማ መንገድ መጓዝ የሚችልበትን አጋጣሚ ሰጥቶት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሕጉ መሥዋዕቶች የሚቀርቡበትን ሥርዓት ይዟል፤ ከመሥዋዕቶቹ መካከል አንዳንዶቹ ግዴታ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግም በገዛ ፈቃድ የሚቀርቡ ናቸው። (ዕብራውያን 8:3) እንዲህ ያሉት መሥዋዕቶች የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን እንዲሁም የእህልንና የኅብረት መሥዋዕቶችን የሚያጠቃልሉ ሲሆን እነዚህም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘትና እርሱን ለማመስገን በፈቃደኝነት የሚቀርቡ ስጦታዎች ናቸው።—ዘሌዋውያን 7:11-13
9 እነዚህ በራስ ፍላጎት የሚቀርቡ ስጦታዎች ይሖዋን ያስደስቱት ነበር። የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቁርባን ‘ሽታቸው ይሖዋን ደስ ያሰኛል’ ተብሏል። (ዘሌዋውያን 1:9፤ 2:2) በኅብረት መሥዋዕት ወቅት የእንስሳው ደምና ስብ ለይሖዋ ይቀርቡ ነበር፤ የተወሰነውን ሥጋ ደግሞ ካህናትና መሥዋዕቱን ያቀረበው ግለሰብ ይመገቡታል። በመሆኑም ይህ ምሳሌያዊ ማዕድ ከይሖዋ ጋር የተመሠረተውን ሰላማዊ ግንኙነት ያመለክታል። ሕጉ እንዲህ ይላል:- “የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ።” (ዘሌዋውያን 19:5) ሁሉም እስራኤላውያን ሲወለዱ ለአምላክ የተወሰኑ ቢሆኑም በፈቃደኝነት መሥዋዕቶችን በማቅረብ ከልባቸው ይሖዋን አምላካቸው ለማድረግ እንደሚፈልጉ ባሳዩ ጊዜ ‘ተቀባይነት ያገኙና’ የተትረፈረፈ በረከት ይፈስላቸው ነበር።—ሚልክያስ 3:10
10. ይሖዋ በኢሳይያስና በሚልክያስ ዘመን የተሰማውን ቅሬታ የገለጸው እንዴት ነበር?
10 ነገር ግን ለአምላክ የተወሰነው የእስራኤል ብሔር ለይሖዋ ታማኝ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎች አላመጣህልኝም፤ በመሥዋዕትህም አላከበርኸኝም። በእህል ቍርባን አላስቸገርሁህም” ብሏቸው ነበር። (ኢሳይያስ 43:23) በተጨማሪም መሥዋዕቶቹ በፈቃደኝነትና ከፍቅር በመነሳሳት የቀረቡ ካልሆኑ በይሖዋ ፊት ዋጋ አይኖራቸውም ነበር። ለአብነት ያህል፣ ኢሳይያስ ከኖረ ከሦስት ምዕተ ዓመታት በኋላ በነቢዩ ሚልክያስ ዘመን እስራኤላውያን እንከን ያለባቸውን መሥዋዕቶች ያቀርቡ ነበር። በመሆኑም ሚልክያስ እንዲህ ብሏቸዋል:- “‘እኔ በእናንተ ደስ አይለኝም፤ ከእጃችሁም ምንም ዐይነት ቍርባን አልቀበልም’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። . . . ‘በቅሚያ የመጣውን፣ አንካሳውን የታመመውን እንስሳ ቍርባን አድርጋችሁ ስታቀርቡ ከእጃችሁ መቀበል ይገባኛልን?’ ይላል እግዚአብሔር።”—ሚልክያስ 1:10, 13፤ አሞጽ 5:22
ብሔሩ ለአምላክ የተወሰነ መሆኑ ቀረ
11. እስራኤላውያን ምን አጋጣሚ ተሰጥቷቸው ነበር?
11 የእስራኤል ብሔር ለአምላክ በተወሰነበት ወቅት ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶ ነበር:- “በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣ እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ።” (ዘፀአት 19:5, 6) እንደሚመጣ ቃል የተገባው መሲሕ በእስራኤላውያን መካከል ይገለጥና የአምላክ መንግሥት መስተዳድር አባላት የመሆን መብት በአንደኛ ደረጃ ለእነርሱ ይከፍትላቸዋል። (ዘፍጥረት 22:17, 18፤ 49:10፤ 2 ሳሙኤል 7:12, 16፤ ሉቃስ 1:31-33፤ ሮሜ 9:4, 5) ነገር ግን አብዛኞቹ የእስራኤል ብሔር አባላት ለአምላክ እንደተወሰኑ በሚያሳይ መንገድ አልተመላለሱም። (ማቴዎስ 22:14) መሲሑን ካለመቀበላቸውም በላይ በስተመጨረሻም ገድለውታል።—የሐዋርያት ሥራ 7:51-53
12. የእስራኤል ብሔር ለይሖዋ የተወሰነ መሆኑ እንደቀረ የሚያሳዩት የትኞቹ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ናቸው?
12 ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ለአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እንዲህ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን? . . . ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማእዘን ራስ ሆነ፤ እግዚአብሔር ይህን አድርጎአል፤ ሥራውም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’ ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች።” (ማቴዎስ 21:42, 43) ይሖዋ እስራኤላውያንን ለእርሱ የተወሰነ ብሔር አድርጎ መቀበሉን እንዳቆመ ለማሳየት ኢየሱስ የሚከተለውን ምሳሌ ተጠቅሟል:- “አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ አንቺ ኢየሩሳሌም! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን ፈቃደኛ አልሆናችሁም፤ እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል!”—ማቴዎስ 23:37, 38
ለአምላክ የተወሰነ አዲስ ብሔር
13. ይሖዋ በኤርምያስ ዘመን ምን ትንቢታዊ ቃል ተናግሮ ነበር?
13 ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር በተያያዘ የሚያከናውነውን አንድ አዲስ ነገር በነቢዩ ኤርምያስ ዘመን በትንቢት አስታውቋል። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “‘ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋር’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል። ከግብፅ አወጣቸው ዘንድ፣ እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ የእነርሱ ባል ሆኜ ሳለሁ፣ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና።’ ይላል እግዚአብሔር። ‘ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።’”—ኤርምያስ 31:31-33
14. ለይሖዋ የተወሰነው አዲሱ ብሔር ወደ ሕልውና የመጣው መቼ ነው? መሠረቱስ ምንድን ነው? አዲሱ ብሔር ማን እንደሆነ ግለጽ።
14 የዚህ አዲስ ቃል ኪዳን መሠረት የተጣለው ኢየሱስ በሞተበትና በኋላም የፈሰሰውን ደሙን ዋጋ ለአባቱ ባቀረበበት ጊዜ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። (ሉቃስ 22:20፤ ዕብራውያን 9:15, 24-26) በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱና ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ የተባለው አዲሱ ብሔር መወለዱ አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን እንደጀመረ የሚያሳዩ ክስተቶች ናቸው። (ገላትያ 6:16፤ ሮሜ 2:28, 29፤ 9:6፤ 11:25, 26) ሐዋርያው ጴጥሮስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ . . . ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ። ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል።” (1 ጴጥሮስ 2:9, 10) በይሖዋና በሥጋዊ እስራኤላውያን መካከል የተመሠረተው ልዩ ወዳጅነት አክትሞ ነበር። ይሖዋ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በረከቱን ከሥጋዊ እስራኤላውያን በመውሰድ የመሲሐዊውን መንግሥት ‘ፍሬ ለሚያፈራው’ መንፈሳዊ እስራኤል ወይም ለክርስቲያን ጉባኤ ሰጠ።—ማቴዎስ 21:43
በግለሰብ ደረጃ ራስን መወሰን
15. ጴጥሮስ፣ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት አድማጮቹ ምን ዓይነት ጥምቀት እንዲጠመቁ ነግሯቸው ነበር?
15 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ጀምሮ አይሁዳዊም ይሁን የአሕዛብ ወገን እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን ለአምላክ መወሰንና “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ነበረበት። a (ማቴዎስ 28:19) ሐዋርያው ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት ለተሰበሰቡት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተቀየሩ ሰዎች እንዲህ አላቸው:- “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።” (የሐዋርያት ሥራ 2:38) እነዚህ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተቀየሩ ሰዎች በጥምቀታቸው የሚገልጹት ሕይወታቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ብቻ ሳይሆን ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር የሚላቸው በኢየሱስ በኩል መሆኑን አምነው መቀበላቸውን ጭምር ነው። ኢየሱስ በይሖዋ የተሾመ ሊቀ ካህንና መሪያቸው ማለትም የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደሆነ ማመን ነበረባቸው።—ቈላስይስ 1:13, 14, 18
16. በጳውሎስ ዘመን ቀና አመለካከት የነበራቸው አይሁዳውያንና አሕዛብ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት የሆኑት እንዴት ነው?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እንደሚከተለው ብሏል:- “በመጀመሪያ በደማስቆ ለሚኖሩ፣ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላሉት ሁሉ፣ ከዚያም ለአሕዛብ፣ ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ።” (የሐዋርያት ሥራ 26:20) ጳውሎስ አይሁዳውያንንና አሕዛብን ኢየሱስ መሲሕ ወይም ክርስቶስ እንደሆነ ካሳመናቸው በኋላ ራሳቸውን ለአምላክ እንዲወስኑና እንዲጠመቁ ረድቷቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:14, 15, 31-33፤ 17:3, 4፤ 18:8) እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ወደ አምላክ በመመለስ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ሆኑ።
17. የትኛው የማተም ሥራ ወደ ማብቂያው እየተቃረበ ነው? ምን ሌላ ሥራስ በፍጥነት እየተከናወነ ነው?
17 በዛሬው ጊዜ የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎችን የማተሙ ሥራ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ነው። ይህ ሥራ ሲጠናቀቅ “አራት መላእክት” እንዳይነፍሱ የያዟቸውን ‘በታላቁ መከራ’ የሚያጠፉ ነፋሶችን እንዲለቅቁ ይፈቀድላቸዋል። ከዚያ በፊት ግን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የመሰብሰቡ ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ ነው። እነዚህ “ሌሎች በጎች” በገዛ ፈቃዳቸው “በበጉ ደም” ለማመን መርጠዋል፤ እንዲሁም ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት አሳይተዋል። (ራእይ 7:1-4, 9-15፤ 22:17፤ ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 28:19, 20) ከእነዚህም መካከል ክርስቲያን ወላጆች ያሏቸው በርካታ ወጣቶች ይገኙበታል። አንተም ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ ከሆንክ የሚቀጥለውን ርዕስ ማንበብ ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የግንቦት 15, 2003 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30 እና 31ን ተመልከት።
ለክለሳ ያህል
• እስራኤላውያን በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን ለአምላክ መወሰን የማያስፈልጋቸው ለምን ነበር?
• እስራኤላውያን ለአምላክ የተወሰኑ ከመሆናቸው ጋር በሚስማማ መንገድ እንደሚኖሩ እንዴት ማሳየት ይችሉ ነበር?
• ይሖዋ እስራኤላውያንን ለእርሱ የተወሰኑ ሕዝቦች አድርጎ መቀበሉን ያቆመው ለምንድን ነው? በሌላ የተተኩትስ እንዴት ነው?
• በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ጀምሮ አይሁዳውያንም ሆኑ አሕዛብ የመንፈሳዊ እስራኤል አባል ለመሆን ምን ማድረግ ነበረባቸው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን ሲወለዱ አምላክ የመረጠው ብሔር አባላት ይሆኑ ነበር
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እያንዳንዱ እስራኤላዊ አምላክን በማገልገል ረገድ የራሱን ምርጫ ማድረግ ነበረበት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በገዛ ፈቃድ የሚቀርቡ መሥዋዕቶች እስራኤላውያን ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹበት አጋጣሚ ይሰጧቸው ነበር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ወዲህ የክርስቶስ ተከታዮች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰንና ይህንንም በጥምቀት ማሳየት ነበረባቸው