በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውቀትን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

እውቀትን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

እውቀትን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

የእውቁ የፊዚክስ ሊቅ የኤንሪኮ ፈርሚ ባለቤት የሆኑት ላውራ ፈርሚ “እውቀት ምንጊዜም ቢሆን ካለማወቅ ይሻላል” ብለው ነበር። አንዳንዶች የማታውቀው ነገር ፈጽሞ ሊጎዳህ አይችልም በማለት ይከራከሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙዎች ይህን አስተያየት በሳይንሳዊ ምርምር መስክ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኑሮ ዘርፎችም እውነት ሆኖ አግኝተውታል። አለማወቅ ከሚያካትታቸው ነገሮች አንዱ ስለ እውነት ግንዛቤ ማጣት ነው። ይህ ደግሞ ብዙ ሰዎች በእውቀት፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ለዘመናት እንዲዳክሩ አድርጓቸዋል።—ኤፌሶን 4:18

አስተዋይ የሆኑ ሰዎች እውቀት ለማግኘት ፍለጋ ያደረጉበት ምክንያትም ይኸው ነው። እነዚህ ሰዎች የመኖራችን ዓላማ ምን እንደሆነና ለወደፊቱም ቢሆን ምን ሊገጥመን እንደሚችል ማወቅ ይፈልጋሉ። በመሆኑም በተለያዩ መንገዶች እውቀት ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። እስቲ ከእነዚህ መንገዶች መካከል አንዳንዶቹን በአጭሩ እንመልከት።

በሃይማኖት መስክ እውቀት ማግኘት ይቻላል?

በቡድሂስቶች ወግ መሠረት የቡድሂዝም እምነት መሥራች የሆኑት ሲድሃርታ ጋውታማ በሰው ልጆች ላይ በሚደርሰው ሥቃይና ሞት በጣም ይረበሹ ነበር። እኚህ ሰው “የእውነትን መንገድ” ለማግኘት የሂንዱ እምነት አስተማሪዎችን እርዳታ ጠይቀው ነበር። ከአስተማሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ የዮጋ እንቅስቃሴ ማድረግና ከመጠን በላይ ራስን መጨቆን እውነትን ለማግኘት እንደሚረዱ ሐሳብ ሰጧቸው። በመጨረሻም ጋውታማ በተመስጦ የማሰላሰል ሂደት ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ነው ወደሚል መደምደሚያ ደረሱ።

ሌሎች ደግሞ እውቀት ለማግኘት ሲሉ በምናብ የሚፈጠሩ የቅዥት ሐሳቦችን እንዲያውጠነጥኑ የሚያደርጓቸውን ዕፆች ይወስዳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዘመናችን ኔቲቭ አሜሪካን ቸርች የተባለው ሃይማኖት አባላት ወደ ቅዠት ዓለም የሚያስገባ ንጥረ ነገር የያዘው ፔዮቲ የተባለው የቁልቋል ዝርያ ተክል “የተደበቀ እውቀት ገላጭ” እንደሆነ ይናገራሉ።

የአሥራ ስምንተኛው ምዕተ ዓመት ፈላስፋ ፈረንሳዊው ዣን-ዣክ ሩሶ፣ አምላክ በቅንነት እርሱን ለሚጠይቅ ለማንኛውም ሰው በግሉ መንፈሳዊ ራእይ እንደሚያሳየው ያምን ነበር። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ግለሰቡ “አምላክ ለልቡ የሚነግረውን” ሲያዳምጥ ነው። ስለዚህ እንደ ሩሶ አባባል ስለ ሁኔታዎች የሚሰማህ ነገር ማለትም ስሜትህና ሕሊናህ የሚያስተላልፉልህ መልእክት፣ “የተወሳሰቡ ሰብዓዊ አመለካከቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ አስተማማኝ መመሪያ” ሊሆንህ ይችላል።—ሂስትሪ ኦቭ ዌስተርን ፊሎሶፊ

የማመዛዘን ችሎታን በመጠቀምስ እውቀት ማግኘት ይቻላል?

በሩሶ ዘመን የነበሩ ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ሃይማኖታዊ አቀራረብ አጥብቀው ይቃወሙት ነበር። ለምሳሌ ሌላኛው ፈረንሳዊ ጸሐፊ ቮልቴር፣ ሃይማኖት ሰዎች እውቀት እንዲኖራቸው ከመርዳት ይልቅ አውሮፓ በድንቁርና ብሎም በአጉል እምነት ለበርካታ ዘመናት እንድትተበተብ እንዳደረጋትና አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች የጨለማ ዘመን ብለው በሚጠሩት ጊዜ ውስጥ ለነበረው አለመቻቻልም ምክንያት እንደሆነ ይሰማው ነበር።

ቮልቴር፣ ኢንላይትመንት በመባል በሚታወቀው የአውሮፓውያን ንቅናቄ ውስጥ መካፈል የጀመረ ሲሆን ይህ ንቅናቄ አንድ ንድፈ ሐሳብ በእምነት ሳይሆን በምክንያት ላይ መመሥረት እንዳለበት ይገልጽ ነበር። የዚህ ንቅናቄ አባላት፣ የማመዛዘን ችሎታና ሳይንሳዊ ምርምር ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት የሚረዱ ቁልፍ ነገሮች እንደሆኑ ያምኑ የነበሩትን የጥንት ግሪኮች አመለካከት ተቀብለዋል። ሌላው የዚህ ንቅናቄ አባል በርናርድ ዴ ፎንትኔል ሰዎች የማመዛዘን ችሎታቸውን ይበልጥ በተጠቀሙበት መጠን የሰው ዘር “ያለፉትን ዘመናት ሁሉ በድንቁርና እንዳሳለፋቸው የሚያሳይ ከፍተኛ የእውቀት ደረጃ ላይ የሚደርስበት ዘመን” እንደሚመጣ ይሰማው ነበር።—ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ

ሰዎች እውቀት ለማግኘት ከተጠቀሙባቸው እርስ በርስ የሚጋጩ በርካታ አመለካከቶች መካከል ከላይ የተጠቀሱት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ታዲያ እውቀት ለማግኘት “አስተማማኝ መመሪያ” ሊሆንልን የሚችል ነገር ይኖራል? እውቀት ለማግኘት የሚረዳውን አስተማማኝ የሆነ ምንጭ በተመለከተ የሚቀጥለው ርዕስ የሚያቀርበውን ሐሳብ ተመልከት።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጋውታማ (ቡድሃ)፣ ሩሶ እና ቮልቴር እውቀትን ለማግኘት በተለያዩ መንገዶች ተጉዘዋል