ወጣቶች ሆይ፣ ምርጫችሁ ይሖዋን ማገልገል ይሁን
ወጣቶች ሆይ፣ ምርጫችሁ ይሖዋን ማገልገል ይሁን
“የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ።”—ኢያሱ 24:15
1, 2. በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ምን የተሳሳተ ጥምቀት ሲከናወን ቆይቷል?
በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ መገባደጃ ገደማ ላይ ተርቱሊያን የተባለ ጸሐፊ “[ልጆች] ክርስቶስን ማወቅ በሚችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ክርስቲያን ይሁኑ” በማለት ጽፏል። ይህ ሰው በዘመኑ ከሀዲ በነበረችው ክርስትና ውስጥ በጣም የተለመደውን ሕፃናትን የማጥመቅ ልማድ ይቃወም ነበር። ኦገስቲን የተባሉ የቤተ ክርስቲያን አባት ግን ከተርቱሊያንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በተቃራኒ ጥምቀት፣ የወረስነው ኃጢአት ያስከተለውን ጉድለት እንደሚያስወግድ እንዲሁም ሳይጠመቁ የሞቱ ሕፃናት እንደሚኮነኑ ያስተምሩ ነበር። ይህ እምነት ሕፃናትን አራስ እያሉ በተቻለ ፍጥነት የማጥመቅ ልማድ እንዲስፋፋ አደረገ።
2 አሁንም ቢሆን የሕዝበ ክርስትና ዋና ዋና ሃይማኖቶች ሕፃናትን በአራስነታቸው ያጠምቃሉ። ከዚህም በላይ ክርስቲያን በሚባሉ አገሮች ያሉ ገዢዎችና የሃይማኖት መሪዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ፣ ድል ያደረጓቸውን “አረማውያን” በግድ ሲያጠምቁ ቆይተዋል። ነገር ግን ሕፃናትን ማጥመቅም ሆነ አዋቂዎችን በግዳጅ ማጥመቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም።
በግለሰብ ደረጃ ራስን መወሰን ያስፈልጋል
3, 4. ሕይወታቸውን ለአምላክ የወሰኑ ወላጆች ያሏቸው ልጆች በፈቃደኝነት ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
3 አምላክ፣ አንዱ ወላጃቸው ብቻ እንኳን ታማኝ ክርስቲያን ቢሆን ሕፃናትን ቅዱስ አድርጎ እንደሚመለከታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (1 ቆሮንቶስ 7:14) ነገር ግን ይህ ሁኔታ ልጆቹ ለይሖዋ የተወሰኑ አገልጋዮች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል? በጭራሽ። ሆኖም ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ወላጆች ያሳደጓቸው ልጆች በፈቃደኝነት ለአምላክ ራሳቸውን እንዲወስኑ የሚረዳቸውን ሥልጠና ያገኛሉ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ትእዛዝ አክብር፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው። . . . በምትሄድበት ሁሉ ይመሩሃል፤ በምትተኛበት ጊዜ ይጠብቁሃል፤ በምትነቃበት ጊዜም ያነጋግሩሃል። እነዚህ ትእዛዞች መብራት ናቸውና፤ ይህችም ትምህርት ብርሃን፣ የተግሣጽ ዕርምትም የሕይወት መንገድ ናት።”—ምሳሌ 6:20-23
4 ወጣቶች፣ ክርስቲያን ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን መመሪያ ለመከተል ፈቃደኛ ከሆኑ ጥበቃ ማግኘት ይችላሉ። ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ተላላ ልጅ ግን ለእናቱ ሐዘንን ያተርፋል።” “ልጄ ሆይ አድምጥ፤ ጠቢብም ሁን፤ ልብህም ከትክክለኛው መንገድ አይውጣ።” (ምሳሌ 10:1፤ 23:19) አዎን፣ ወጣቶች ከወላጆቻችሁ ከምታገኙት ሥልጠና መጠቀም ከፈለጋችሁ እነርሱ የሚሰጧችሁን አስተያየት፣ ምክርና ተግሣጽ በፈቃደኝነት ተቀበሉ። ጥበበኛ ሆናችሁ አልተወለዳችሁም፤ ሆኖም ‘ጠቢብ ልትሆኑና’ በራሳችሁ ፈቃድ ‘የሕይወትን መንገድ’ ልትከተሉ ትችላላችሁ።
ተግሣጽ ምንድን ነው?
5. ጳውሎስ ለልጆችና ለአባቶች ምን ምክር ሰጥቷል?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ ‘መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም’ የሚል ነው። አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።”—ኤፌሶን 6:1-4
6, 7. ልጆችን ‘በጌታ ተግሣጽ ማሳደግ’ ምንን ይጨምራል? ወላጆች እንዲህ ማድረጋቸው በልጆቻቸው ላይ አላግባብ ተጽዕኖ ማሳደራቸው እንደሆነ ተደርጎ መታየት የሌለበት ለምንድን ነው?
6 ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ያሳድጋሉ ሲባል ያላግባብ ይጫኗቸዋል ማለት ነው? በጭራሽ። ወላጆች ትክክልና በሥነ ምግባር ረገድ ጠቃሚ ነው ብለው የሚያምኑበትን ነገር ለልጆቻቸው ቢያስተምሩ መወቀስ አለባቸው? በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች አምላክ የለም ብለው ልጆቻቸውን ቢያስተምሩ ማንም አይነቅፋቸውም። የሮም ካቶሊክና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ልጆቻቸውን በእነርሱ እምነት መሠረት የማሳደግ ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል፤ እንዲህ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉ ብዙም የሚወቅሳቸው የለም። በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው ስለ መሠረታዊ እውነቶችና ስለ ሥነ ምግባር መመሪያዎች ይሖዋ ያለውን አመለካከት እንዲቀበሉ አድርገው ቢያሳድጓቸው አእምሯቸውን እንደተቆጣጠሩ ተደርገው ሊወነጀሉ አይገባም።
7 ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንደሚገልጸው ኤፌሶን 6:4 ላይ “ተግሣጽ” ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያው የግሪክኛ ቃል “የተሳሳተ አስተሳሰብን ለማስተካከል፣ መንፈሳዊ አመለካከትን ለማሻሻል በመፈለግ” የሚከናወንን ሂደት ያመለክታል። አንድ ወጣት ብዙኃኑን ለመምሰል ሲል በእኩዮቹ ተጽዕኖ ተሸንፎ ወላጆቹ የሚሰጡትን ማሠልጠኛ ባይቀበልስ? በልጁ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳደሩት ወላጆቹ ናቸው ወይስ ጓደኞቹ? እኩዮቹ ዕፅ እንዲወስድ፣ መጠጥ ከልክ በላይ እንዲጠጣ ወይም ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ነገር እንዲያደርግ የሚገፋፉት ከሆነ ወላጆቹ የልጃቸውን አስተሳሰብ ለማስተካከልና እንዲህ ያሉት መጥፎ ባሕርያት የሚያስከትሉትን ውጤት እንዲገነዘብ ለመርዳት ቢሞክሩ ሊወቀሱ ይገባል?
8. ጢሞቴዎስን ለማሳመን እናቱና አያቱ ምን ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር?
8 ሐዋርያው ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፎለት ነበር:- “በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና፤ ይህን ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዐውቀሃል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) የጢሞቴዎስ እናትና አያት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን እውቀት በመጠቀም ከሕፃንነቱ ጀምሮ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብር ረድተውታል። (የሐዋርያት ሥራ 16:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:5) በኋላም ክርስቲያን ሲሆኑ ጢሞቴዎስ እንዲያምን ግድ አላሉትም፤ ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጠቀም አሳማኝ ምክንያቶችን እያቀረቡ ‘ያስረዱት’ ነበር።
ይሖዋ የፈለግኸውን እንድትመርጥ ጋብዞሃል
9. (ሀ) ይሖዋ ፍጥረታቱን ያከበረው እንዴት ነው? ይህ የሆነበት ምክንያትስ ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ አንድያ ልጅ የመምረጥ ነፃነቱን የተጠቀመበት እንዴት ነው?
9 ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ የእርሱን ፈቃድ ብቻ እንጂ የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ የማይችሉ ሮቦቶች አድርጎ ሊሠራቸው ይችል ነበር። ሆኖም የራሳቸውን ምርጫ እንዲያደርጉ በመፍቀድ አክብሯቸዋል። አምላካችን የሚፈልገው ፈቃደኛ ተገዢዎችን ነው። በዕድሜ የገፋንም እንሁን ወጣቶች፣ ሁላችንም ለእርሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ስናገለግለው መመልከት ደስ ይለዋል። ለአምላክ ፈቃድ በፍቅር በመገዛት ረገድ ትልቅ ምሳሌ የሚሆነን “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ይሖዋ ራሱ የተናገረለት አንድያ ልጁ ነው። (ማቴዎስ 3:17) ይህ የበኩር ልጅ ለአባቱ “አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ” ብሏል።—መዝሙር 40:8፤ ዕብራውያን 10:9, 10
10. ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማገልገል መሠረቱ ምንድን ነው?
10 ይሖዋ፣ በኢየሱስ አመራር ሥር ሆነው የሚያገለግሉትን ሰዎች ልክ እንደ ልጁ በፈቃደኝነት እንዲታዘዙት ይፈልጋል። መዝሙራዊው የሚከተለውን ትንቢታዊ መዝሙር ዘምሯል:- “ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤ ከንጋት ማሕፀን፣ በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣ የጐልማሳነትህን ልምላሜ እንደ ጠል ትቀበላለህ [“ጐልማሶችህ እንደ ንጋት ወዳንተ ይመጣሉ፣” የግርጌ ማስታወሻ]።” (መዝሙር 110:3) ጠቅላላው የይሖዋ ድርጅት ማለትም በሰማይና በምድር የሚገኙት የድርጅቱ ክፍሎች የሚሠሩት ለአምላክ ፈቃድ በፍቅር በመታዘዝ ነው።
11. ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ወላጆች ያሳደጓቸው ልጆች ምን ምርጫ አላቸው?
11 ስለዚህ ወጣቶች፣ ወላጆቻችሁም ሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንድትጠመቁ ሊያስገድዷችሁ እንደማይችሉ መገንዘብ አለባችሁ። ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት መመንጨት ያለበት ከራሳችሁ ነው። በጥንት ዘመን የነበረው ኢያሱ ለእስራኤላውያን “በፍጹም ታማኝነትም [ለይሖዋ] ተገዙለት። . . . የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ” ብሏቸዋል። (ኢያሱ 24:14-22) በተመሳሳይ እናንተም ራሳችሁን ለይሖዋ የምትወስኑትም ሆነ ለእሱ ፈቃድ ያደራችሁ ሆናችሁ የምትኖሩት በራሳችሁ ምርጫ መሆን አለበት።
ኃላፊነትህን መቀበል
12. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸውን ማሠልጠን ቢችሉም ምን ሊያደርጉላቸው አይችሉም? (ለ) አንድ ወጣት ለሚያደጋቸው ምርጫዎች በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ የሚሆነው መቼ ነው?
12 ወጣቶች ሆይ፣ ወላጆቻችሁ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ በመሆናቸው ምክንያት የምታገኙት ጥበቃ የሚያበቃበት ወቅት አለ። (1 ቆሮንቶስ 7:14) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኀጢአት ያደርጋል” ብሎ ጽፏል። (ያዕቆብ 4:17) ወላጆች ለልጆቻቸው ሲሉ አምላክን ማገልገል አይችሉም፤ ልጆችም እንዲሁ ለወላጆቻቸው ሲሉ አምላክን ሊያገለግሉ አይችሉም። (ሕዝቅኤል 18:20) ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ትምህርት ቀስማችኋል? የተማራችሁትን ነገር መረዳትና ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት በምትችሉበት ዕድሜ ላይ ደርሳችኋል? እንዲህ ከሆነ አምላክ እርሱን ለማገልገል መወሰን እንደምትችሉ አድርጎ እንደሚመለከታችሁ ማሰቡ ምክንያታዊ አይደለም?
13. በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ገና ያልተጠመቁ ወጣቶች ራሳቸውን ምን ብለው መጠየቅ አለባቸው?
13 አንተስ አምላክን የሚያመልኩ ወላጆች ያሳደጉህ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምትገኝና አልፎ ተርፎም የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ የምትካፈል ያልተጠመቅህ ወጣት ነህ? ከሆነ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በሐቀኝነት ራስህን ጠይቅ:- ‘እነዚህን እንቅስቃሴዎች የማደርገው ለምንድን ነው? በስብሰባዎች ላይ የምገኘውና በስብከቱ ሥራ የምካፈለው ወላጆቼ እንዲህ እንዳደርግ ስለሚጠብቁብኝ ነው ወይስ ይሖዋን ማስደሰት ስለምፈልግ?’ “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ” ፈትነህ አውቀኸዋል?—ሮሜ 12:2
ከመጠመቅ ወደኋላ የምትለው ለምንድን ነው?
14. አንድ ሰው በቂ ምክንያት ሳይኖረው ሳይጠመቅ መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?
14 “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን እንዳወቀ ለወንጌላዊው ለፊልጶስ ይህንን ጥያቄ ያቀረበው አንድ ኢትዮጵያዊ ነበር። ይህ ኢትዮጵያዊ በቂ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት ነበረው። እውቀቱም ጊዜ ሳያጠፋ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ሆኖ ይሖዋን ማገልገል እንደሚገባው በይፋ ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝቦታል፤ ይህም በጣም አስደስቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 8:26-39) ልድያ የተባለች ሴትም እንዲሁ “ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ” ልቧ ክፍት ነበር፤ ወዲያውኑ እርሷና ቤተሰቦቿ “ተጠመቁ።” (የሐዋርያት ሥራ 16:14, 15) በተመሳሳይም በፊልጵስዩስ ከተማ የነበረ የወህኒ ቤት ጠባቂ ጳውሎስና ሲላስ ‘የጌታን ቃል ሲናገሩ’ አዳመጠ፤ “ወዲያውም እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ ተጠመቁ።” (የሐዋርያት ሥራ 16:25-34) ታዲያ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ መሠረታዊ እውቀት ካለህ፣ ፈቃዱን ለመፈጸም ከልብህ የምትፈልግ ከሆነ፣ በጉባኤ ውስጥ መልካም ስም ካተረፍክ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎችና የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ አዘውታሪ ከሆንክ ከመጠመቅ ወደኋላ የምትለው ለምንድን ነው?—ማቴዎስ 28:19, 20
15, 16. (ሀ) አንዳንድ ወጣቶች እንዳይጠመቁ የሚከለክላቸው የትኛው የተሳሳተ ምክንያት ነው? (ለ) ራስን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ ለወጣቶች ጥበቃ የሚሆንላቸው እንዴት ነው?
15 ይህንን አስፈላጊ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ የምትለው ምናልባት መጥፎ ነገር ብፈጽም ተጠያቂ እሆናለሁ ከሚል ፍርሃት ይሆን? ከሆነ የሚከተለውን ምሳሌ አስብበት:- ከዕለታት አንድ ቀን አደጋ ያጋጥመኝ ይሆናል በሚል ፍርሃት መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ከማመልከት ትታቀባለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! በተመሳሳይም ለመጠመቅ ብቃቱ ካለህ ወደኋላ ማለት የለብህም። ሕይወትህን ለአምላክ ከወሰንክና ፈቃዱን ለመፈጸም ከተስማማህ መጥፎ ነገር ላለመፈጸም አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ እንደምታደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። (ፊልጵስዩስ 4:13) ወጣቶች ሆይ፣ ስላልተጠመቃችሁ ብቻ ከተጠያቂነት ማምለጥ እንደምትችሉ ሆኖ አይሰማችሁ። ተጠመቃችሁም አልተጠመቃችሁም በኃላፊነት መጠየቅ በምትችሉበት ዕድሜ ላይ ስትደርሱ ስለ ድርጊታችሁ ለይሖዋ መልስ መስጠት ይጠበቅባችኋል።—ሮሜ 14:11, 12
16 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ወጣት እያሉ ለመጠመቅ መወሰናቸው በእጅጉ እንደጠቀማቸው ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በምዕራብ አውሮፓ ስለሚገኝ አንድ የ23 ዓመት ወጣት ሁኔታ እንመልከት። በ13 ዓመቱ መጠመቁ ‘በወጣትነት ክፉ ምኞት’ ላለመሸነፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ለማድረግ እንደረዳው ያስታውሳል። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ገና ልጅ እያለ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን ወሰነ። በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በደስታ እያገለገለ ይገኛል። አንተን ጨምሮ ይሖዋን ለማገልገል የመረጡ ወጣቶች የተትረፈረፈ በረከት ያገኛሉ።
17. “የጌታ ፈቃድ” ምን እንደ ሆነ ማስተዋል አስፈላጊ የሆነው በየትኞቹ ዘርፎች ነው?
17 ራሳችንን ስንወስንና ስንጠመቅ በምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ የይሖዋን ፈቃድ ከግምት ውስጥ ማስገባት እንጀምራለን። ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል መፈጸም ‘ዘመኑን መዋጀትንም’ ይጨምራል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቀደም ሲል ፍሬ ቢስ ነገሮችን በማከናወን እናጠፋ የነበረውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ለማጥናት፣ በስብሰባዎች አዘውትሮ ለመገኘትና አቅማችን በፈቀደ መጠን ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በመስበኩ ሥራ ለመካፈል በማዋል ነው። (ኤፌሶን 5:15, 16፤ ማቴዎስ 24:14) ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንና የእርሱን ፈቃድ ለማድረግ ያለን ምኞት በሁሉም የሕይወታችን ዘርፍ ላይ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል፤ ይህም የመዝናኛ፣ የመብልና የመጠጥ ልማዳችንን እንዲሁም የሙዚቃ ምርጫችንን ይጨምራል። ለዘላለም እንድትደሰት የሚያስችልህን የመዝናኛ ዓይነት ለምን አትመርጥም? በሺዎች የሚቆጠሩ ደስተኛ የሆኑ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከጌታ ፈቃድ’ መውጣት ሳያስፈልግ ጠቃሚ በሆኑ በርካታ መዝናኛዎች መደሰት እንደሚቻል ሊነግሩህ ይችላሉ።—ኤፌሶን 5:17-19
“አብረን እንሂድ”
18. ወጣቶች ራሳቸውን ምን እያሉ መጠየቅ አለባቸው?
18 ከ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ድረስ ይሖዋ እርሱን እንዲያገለግልና ምሥክሩ እንዲሆን ያደራጀው ሕዝብ በምድር ላይ ነበረው። (ኢሳይያስ 43:12) ወጣት እስራኤላውያን የሚወለዱት ይሖዋ ካደራጀው ከዚህ ሕዝብ ነበር። ከጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ ግን ‘ለእርሱ የሚሆኑ’ የተባሉት መንፈሳዊ እስራኤላውያን በምድር ላይ ያሉ የይሖዋ አዲስ “ሕዝብ” ሆነዋል። (1 ጴጥሮስ 2:9, 10፤ የሐዋርያት ሥራ 15:14፤ ገላትያ 6:16) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቶስ “መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚተጋውን የእርሱ የሆነውን ሕዝብ” እንዳነፃ ተናግሯል። (ቲቶ 2:14) ወጣቶች ሆይ፣ ይህ ሕዝብ የትኛው እንደሆነ ራሳችሁ ፈልጋችሁ የማወቅ ነፃነት አላችሁ። በዛሬው ጊዜ “በእምነቱ የጸና ጻድቅ የሆነ ሕዝብ” እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ የሚኖር፣ ለይሖዋ ታማኝ ምሥክር ሆኖ የሚሠራና ለሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የይሖዋ መንግሥት እንደሆነ የሚያውጅ ሕዝብ የቱ ነው? (ኢሳይያስ 26:2-4) እስቲ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች ሃይማኖቶች የሚያደርጉትን ተመልከቱ፤ ከዚያም ድርጊታቸውን ከእውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ምን እንደሚጠበቅ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ሐሳብ ጋር አወዳድሩ።
19. በመላው ምድር የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኛ ሆነዋል?
19 በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ‘ጻድቅ ሕዝብ’ ሆነው የተቋቋሙት የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎች እንደሆኑ እርግጠኛ ሆነዋል። እነዚህን መንፈሳዊ እስራኤላውያንም “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ” ይሏቸዋል። (ዘካርያስ 8:23) ወጣቶች ሆይ፣ በአምላክ ሕዝብ መካከል በመሆን ‘ሕይወትን እንደምትመርጡ’ ወይም ይሖዋ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ላይ ለዘላለም ለመኖር እንደምትወስኑ ከልባችን ተስፋ እናደርጋለን፤ በጸሎታችንም እናስባችኋለን።—ዘዳግም 30:15-20፤ 2 ጴጥሮስ 3:11-13
ለክለሳ ያህል
• ተግሣጽ ምንን ይጨምራል?
• በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምን ዓይነት አገልግሎት ነው?
• ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ወላጆች ያሳደጓቸው ልጆች ሁሉ ምን ምርጫ ቀርቦላቸዋል?
• ሳይጠመቁ ብዙ መቆየት ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምታዳምጡት ማንን ነው?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ራስን መወሰንና መጠመቅ ጥበቃ ሊሆንልህ የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንዳትጠመቅ የሚከለክልህ ምንድን ነው?