በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ይደሰታሉ

የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ይደሰታሉ

የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ይደሰታሉ

ኢየሱስ “የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” ብሎ ለአባቱ ጸሎት ባቀረበበት ወቅት ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሆን ምሳሌ ትቷል። (ሉቃስ 22:42) እንዲህ ዓይነቱ ለይሖዋ ፈቃድ የመገዛት መንፈስ በዛሬው ጊዜ በሚገኙ በሚሊዮን በሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮችም ላይ ይንጸባረቃል። ከእነዚህ መካከል የ120ኛው ክፍል የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 52 ተማሪዎች ይገኙበታል። መጋቢት 11, 2006 ላይ የተመረቁት ሁሉም ተማሪዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉም እንኳ ወደተለያዩ አገሮች ሄደው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ዝግጁ በመሆናቸው ተደስተዋል።

እነዚህ ተመራቂዎች ሕይወታቸውን በይሖዋ ፈቃድ ለመምራት ያነሳሳቸው ነገር ምንድን ነው? በቦሊቪያ ሚስዮናውያን ሆነው እንዲያገለግሉ የተመደቡት ክሪስና ሌስሊ የተባሉ ባልና ሚስት ይህን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸውን ምክንያት እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ራሳችንን ስለካድን ከይሖዋ ድርጅት ጋር በተያያዘ የሚሰጠንን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ምንጊዜም ዝግጁ ለመሆን እንፈልጋለን።” (ማርቆስ 8:34) በአልባኒያ የተመደቡት ጄሰንና ሸሪ ደግሞ “ከይሖዋ ድርጅት የምንቀበለው የትኛውም ኃላፊነት የራሱ የሆነ ተፈታታኝ ነገር ይኖረዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ልንታመንበት የሚገባ አምላክ መሆኑን ተገንዝበናል” በማለት አክለው ተናግረዋል።

የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የተሰጠ ማበረታቻ

የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነውና በአርት ዲፓርትመንት የሚያገለግለው ወንድም ጆርጅ ስሚዝ ፕሮግራሙን በጸሎት ከፍቷል። በመቀጠልም የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነውና የምረቃው ሥነ ሥርዓት ሊቀ መንበር የነበረው ወንድም ስቲቨን ሌት ለተሰብሳቢዎቹ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገላቸው። ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል በተደረገው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ከ23 አገሮች የመጡ እንግዶች ተገኝተዋል። ወንድም ሌት ለተመራቂዎቹ ከፊታቸው “ከፍተኛ ኃይል” የሚጠይቅ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ተናገረ። ከዚያም አዲሶቹ ሚስዮናውያን የመጽሐፍ ቅዱስን ኃይል በመጠቀም የሐሰት ትምህርቶችን የመሳሰሉ ‘በምሽግ’ የተመሰሉ ነገሮችን እንዲደመስሱ አበረታቷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) “በተመደባችሁባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ቅን ሰዎች ልብ ውስጥ የተመሸገውን ሐሳብ አውጥታችሁ እንድትጥሉ ይሖዋ በእናንተ መጠቀሙ ከፍተኛ ደስታ ያስገኝላችኋል!” በማለት ንግግሩን ደምድሟል።

የዋናው መሥሪያ ቤት አባል የሆነው ወንድም ሃሮልድ ጃክሰን “ልታስታውሷቸው የሚገቡ ጥቂት ነገሮች” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። ለአዲሶቹ ሚስዮናውያን የአምላክን “መንግሥትና ጽድቁን” ማስቀደማቸውን ፈጽሞ መርሳት እንደሌለባቸው አሳሰባቸው። (ማቴዎስ 6:33) ‘ፍቅር እንደሚያንጽና’ ለውጤታማነትም ቁልፍ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 8:1) አክሎም “ከሌሎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት በፍቅር የምትመሩ ሁኑ” ብሏል።

ቀጥሎም የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነውና ከ1979 እስከ 2003 ድረስ በሚስዮናዊነት ያገለገለው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ለተመራቂዎቹ “የእናንተ ኃላፊነት ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ለራሳቸውም ሆነ ለአገልግሎታቸው ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ እንደሚገባቸው ጠንከር አድርጎ ተናገረ። ክርስቲያኖች የእውነትን ዘር በመዝራትና ውኃ በማጠጣት ረገድ ጠንክረው የመሥራት ኃላፊነት አለባቸው። ይሁን እንጂ ‘የሚያሳድገው እግዚአብሔር’ እንደመሆኑ መጠን ግለሰቦቹ በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸው የተተወው ለይሖዋ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:6-9) አክሎም ወንድም ጃክሰን እንዲህ ብሏል:- “ይሖዋ ከእናንተ የሚጠብቀው በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆናችሁ እንድትገኙ ነው። ይሁንና ከሁሉም በላይ የሚጠበቅባችሁ ነገር ምንድን ነው? ይሖዋንም ሆነ ተመድባችሁ በምትሄዱበት ቦታ ያሉትን ሰዎች እንድትወዱ ነው።”

የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ሎውረንስ ቦወን “እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ እወቁ” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። ወንድም ቦወን፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ በተአምራዊ ሁኔታ እንዴት እንደመራቸው ብሎም እንደጠበቃቸው ተማሪዎቹ እንዲያስታውሱ አደረገ። (ዘፀአት 13:21, 22) ዛሬም እኛን ከሚጠብቅበትና ከሚመራበት መንገዶች መካከል አንደኛው “የእውነት ዐምድና መሠረት” የሆነው የቅቡዓን ጉባኤ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) አዲሶቹ ሚስዮናውያን፣ ይሖዋ ለትሑታን መመሪያ የሚሰጥበትንና ጥበቃ የሚያደርግበትን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መያዝ ይኖርባቸዋል።

ሌላኛው የጊልያድ አስተማሪ ወንድም ዋላስ ሊቨራንስ ‘ከኋላቸው’ ሆኖ ድምፅ የሚያሰማውን የአምላክን ቃል እንዳይረሱት አሳሰባቸው። የአምላክ ቃል በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፈ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ከኋላችን የምንሰማው ያህል ነው። ከኋላ እየተከተለ በጎቹን እንደሚመራ እረኛ ይሖዋም ሕዝቦቹ የሚጓዙበትን ትክክለኛ አቅጣጫ ለማሳየት ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በመጠቀም ከኋላቸው ሆኖ መመሪያ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 30:21፤ ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) የጊልያድ ትምህርት ቤት፣ ተማሪዎቹ ለባሪያው ክፍል ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር አድርጓል። ሌላው ቀርቶ ‘ባሪያው’ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምን አዘጋጅቷል። ተናጋሪው ተመራቂዎቹን እንዲህ በማለት አበረታቷቸዋል:- “በዚህ በከበረ ሀብት ውስጥ ያለውን እውቀት ተጠቅማችሁ ሌሎችን አስተምሩ።”—ማቴዎስ 13:52

በመስክ አገልግሎት የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ

የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር “ወንጌልን ለመስበክ ጉጉት ይኑራችሁ” በሚል ጭብጥ ባቀረበው ንግግር ላይ ተመራቂዎቹ በትምህርት ቤቱ ቆይታቸው ወቅት በመስክ አገልግሎት ያገኟቸውን አንዳንድ ተሞክሮዎች ተናግሮ ነበር። (ሮሜ 1:15) ተማሪዎቹ በተደረገላቸው ቃለ ምልልስ በማንኛውም አጋጣሚ ለመስበክ ጉጉት እንዳላቸው ታይቷል።

ወንድም ኬነዝ ፍሎዲን በዩናይትድ ስቴትስ በማገልገል ላይ ለሚገኙ ሦስት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ያደረገው ቃለ ምልልስ ለተመራቂዎቹ ተጨማሪ ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል። ሪቻርድ ኬለር በደቡብ አሜሪካ አሌሃንድሮ ላኪዮ ደግሞ በመካከለኛው አሜሪካ ሚስዮናዊ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት የተለያዩ ችግሮችን እንዴት እንደተወጡ እንዲሁም ሚስዮናዊ ሆነው በማገልገላቸው ያገኟቸውን በረከቶች ተናግረዋል። ሞሴር ፌሊስቢኑ ባደገበት አካባቢ በብራዚል ተመድበው ከሚያገለግሉ ሚስዮናውያን ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ ሥልጠና እንደሰጠው ተናግሯል።

ወንድም ዴቪድ ሻፈር ተሞክሮ ካካበቱ ሦስት ሚስዮናውያን ማለትም ከሮበርት ጆንስ፣ ከዉድዎርዝ ሚልዝ እና ከክሪስተፈር ስሌ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። እነዚህ ሦስት ወንድሞች ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ እንዴት በይሖዋ ላይ እንደታመኑ ገልጸዋል። ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ በተመደቡበት ቦታ ችግር ሲገጥማቸው እንዲጸኑ የረዳቸው ይሖዋ በድርጅቱ በኩል የሰጣቸው ሥልጠና እንደሆነም ተናግረዋል። ወንድም ሚልዝ ሐሳቡን ያጠቃለለው እንዲህ በማለት ነበር:- “እኔን ይበልጥ የጠቀመኝ በጊልያድ ያገኘሁት እውቀት ሳይሆን ትምህርት ቤቱ ስለ ትሕትናና ስለ ፍቅር ያስተማረኝ ነገር ነው።”

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጋይ ፒርስ “ይሖዋ ያሰበው ሳይፈጸም አይቀርም” በሚል ጭብጥ የፕሮግራሙን ዋነኛ ንግግር አቀረበ። አዳም ኃጢአት ሠራ። ይህ ታዲያ አምላክ ያሰበውን መፈጸም እንዳቃተው ማስረጃ ይሆናል? አንዳንዶች እንደሚሉት አምላክ አዳምን ፍጹም አድርጎ ለመፍጠር ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም ማለት ነው? በፍጹም አይደለም፤ ‘እግዚአብሔር ሰውን [የፈጠረው] ቅን’ ወይም ቀና አድርጎ ነው። (መክብብ 7:29) ተናጋሪው ኢየሱስ ምድር በነበረበት ወቅት ከባድ ችግር እየደረሰበት እንኳ አቋሙን መጠበቅ መቻሉ “አዳም የተሳሳተ ነገር እንዲያደርግ የሚያስገድድ አንዳችም ምክንያት እንዳልነበረው ያሳያል” በማለት ገልጿል። አዳም በዔደን ገነት የገጠመው የታዛዥነት ፈተና ኢየሱስ በተሳካ ሁኔታ ከተወጣው ፈተና ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ይሁን እንጂ አዳም በፈተናው ወድቋል። የሆነ ሆኖ ይሖዋ ያሰበው ሳይሳካ አይቀርም። ዓላማው ከፍጻሜው ይደርሳል። (ኢሳይያስ 55:11) ወንድም ፒርስ ለአዲሶቹ ሚስዮናውያን እንዲህ አላቸው:- “እናንተ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ይሖዋን የማክበር ልዩ መብት አግኝታችኋል። ሚስዮናዊ ሆናችሁ እርሱን የምታገለግሉት የትም ይሁን የት ይሖዋ ከእያንዳንዳችሁ ጋር ይሁን።”

ከተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የተላኩ ሰላምታዎች ከቀረቡ በኋላ የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የሆነው ወንድም ሌት ለተመራቂዎቹ ዲፕሎማቸውንና የተመደቡበትን ቦታ የሚገልጸውን ደብዳቤ ሰጣቸው። ከዚያም ለረጅም ጊዜ በቤቴል ያገለገለው ወንድም ቨርነን ዋይዝጋርቨር የመደምደሚያውን ጸሎት አቀረበ።

በዚያ የተገኙት 6,872 ሰዎች ፕሮግራሙ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቅንዓታቸውን ይበልጥ እንዳነሳሳላቸው ተሰምቷቸዋል። (መዝሙር 40:8) ከተመራቂዎቹ መካከል አንድሪውና አን እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ሕይወታችንን ለይሖዋ ወስነናል። ይሖዋ አድርጉ ያለንን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተናል። አሁን ይሖዋ ወደ አፍሪካዊቷ አገር ወደ ካሜሩን እንድንሄድ ይፈልጋል።” እነርሱም ሆኑ ሌሎቹ ተመራቂዎች ውጤት ያለውንና እርካታ የሚያስገኝላቸውን የዕድሜ ልክ ሥራ ለመጀመር ጓጉተዋል። በእውነትም እነዚህ ሚስዮናውያን የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ይደሰታሉ።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

ተማሪዎቹ የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 6

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 20

የተማሪዎቹ ብዛት:- 52

አማካይ ዕድሜ:- 35.7

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 18.3

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 14.5

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 120ኛ ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ሱዛን ራይት፣ ቢአ ስዋረስ፣ ቢቲያ ክራይሰንት፣ ሎይዳ ዴቨንፖርት፤ (2) አን ጆንሰን፣ ሸሪ አሊ፣ ኪሚዬ ኬዲ፣ ፒላር ጉሬሮ፣ አንሄሊታ አሴስ፤ (3) ሉሲ ኦርቲዝ፣ ኪም ሊል፣ ማርያ ኡዜታ፣ ሬቼል ፔሬዝ፣ ካሪስ ባክስ፣ ክላውዲያ ካተሪና፤ (4) ብሪጂት ፓልመር፣ ዴቢ ላቪንግ፣ ጄሲካ ማክዶናው፣ ዳያን ቦስቶክ፣ ሌስሊ ቤኔታቶስ፤ (5) ማሊ ጃስኪ፣ ኤልሳቤት ሳራፊያኖስ፣ ኮሪና ስቴልተር፣ ሮቤርታ ቫይራ፣ ጀኒን ዉን፣ ካረን ፕሬንተስ፤ (6) ሀንክ ዴቨንፖርት፣ ሁጎ ክራይሰንት፣ ሞይስስ ፔሬዝ፣ ኤንዞ ቫይራ፣ ኤንሄል ስዋረስ፣ ኢታሎ ካተሪና፣ ኮሪ ራይት፤ (7) ኬን ኬዲ፣ ጄሲ ማክዶናው፣ ማርክ ኦርቲዝ፣ ጄሰን ዉን፣ ጄሰን አሊ፣ ሚጌል አሴስ፤ (8) ዮርጅስ ሳራፊያኖስ፣ ዴኒስ ሊል፣ ካርሎስ ኡዜታ፣ ፖል ስቴልተር፣ ግሬግ ፕሬንተስ፣ አንድሪው ጆንሰን፣ ክሪስ ቤኔታቶስ፤ (9) ጄረሚ ፓልመር፣ ዌድ ጃስኪ፣ ጄረሚ ባክስ፣ ስቴፈን ቦስቶክ፣ ሆሴ ሚጌል ጉሬሮ፣ ስቲቭ ላቪንግ።