በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባለው መልካም ነገር ላይ አተኩሩ

በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባለው መልካም ነገር ላይ አተኩሩ

በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባለው መልካም ነገር ላይ አተኩሩ

“እኛም ከቤትህ በሚገኘው መልካም ነገር . . . እንረካለን።”—መዝሙር 65:4 የ1980 ትርጉም

1, 2. (ሀ) ከቤተ መቅደሱ ጋር በተያያዘ የተደረጉት ዝግጅቶች በአምላክ ሕዝብ ላይ ምን ውጤት ነበራቸው? (ለ) ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ ምን ድጋፍ አድርጓል?

 በጥንቷ እስራኤል ይኖር የነበረው ዳዊት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከተጠቀሱት ግሩም ሰዎች መካከል አንዱ ነው። እረኛ፣ ሙዚቀኛ፣ ነቢይና ንጉሥ የነበረው ይህ ሰው በይሖዋ አምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ ይታመን ነበር። ዳዊት ከይሖዋ ጋር የነበረው የቅርብ ወዳጅነት ለአምላክ ቤት የመሥራት ፍላጎት አሳድሮበታል። እንዲህ ያለው ቤት ወይም ቤተ መቅደስ በእስራኤል የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። ዳዊት ቤተ መቅደሱም ሆነ በውስጡ የሚከናወኑት ተግባሮች ለአምላክ ሕዝብ ደስታና በረከት እንደሚያመጡ ያውቅ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “አንተ [ይሖዋ] የመረጥሃቸውና በተቀደሰ አደባባይህ እንዲኖሩ ወደ ራስህ ያቀረብሃቸው፥ ደስ ይበላቸው፤ እኛም ከቤትህ በሚገኘው መልካም ነገርና ከመቅደስህ በሚገኘው በረከት እንረካለን።”መዝሙር 65:4 የ1980 ትርጉም

2 ቢሆንም ዳዊት የይሖዋን ቤት እንዲያስገነባ አልተፈቀደለትም። ከዚህ ይልቅ ይህንን መብት ለመስጠት የታሰበው ለልጁ ለሰሎሞን ነበር። ዳዊት አጥብቆ ይመኘው የነበረው መብት ለሌላ ሰው በመሰጠቱ አላጉረመረመም። በዋነኝነት ያሳስበው የነበረው ነገር የቤተ መቅደሱ መገንባት ነው። ከይሖዋ የተቀበለውን የቤተ መቅደስ ንድፍ ለሰሎሞን በመስጠት ግንባታውን በሙሉ ልቡ ደግፏል። ከዚህም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌዋውያን በተለያየ ምድብ ተከፋፍለው ለይሖዋ አገልግሎት እንዲያቀርቡ አደራጅቷል፤ እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅና ብር በስጦታ አበርክቷል።1 ዜና መዋዕል 17:1, 4, 11, 12፤ 23:3-6፤ 28:11, 12፤ 29:1-5

3. የአምላክ አገልጋዮች ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ ለተደረጉት ዝግጅቶች ምን አመለካከት አላቸው?

3 ታማኝ እስራኤላውያንም በአምላክ ቤት ውስጥ ለሚከናወነው እውነተኛ አምልኮ የተደረጉትን ዝግጅቶች ደግፈዋል። እኛም በተመሳሳይ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ እየተከናወነ ላለው አምልኮ የሚደረጉትን ዝግጅቶች እንደግፋለን። በዚህ መንገድ የዳዊት ዓይነት አስተሳሰብ እንዳለን እናሳያለን። እንዲሁም የቅሬታ መንፈስ የለንም። በተቃራኒው በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባሉት መልካም ነገሮች ላይ እናተኩራለን። ከልብ አመስጋኝ ልንሆንባቸው ስለምንችላቸው ብዙ መልካም ነገሮች አስበህ ታውቃለህ? እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

በአመራር ላይ ስላሉት ወንድሞች አመስጋኝ መሆን

4, 5. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተግባሩን እያከናወነ ያለው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች እየቀረበላቸው ስላለው መንፈሳዊ ምግብ ምን ይሰማቸዋል?

4 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ባሉት ንብረቶቹ ላይ የሾመውን “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንድናመሰግን የሚያደርጉን በቂ ምክንያቶች አሉ። በመንፈስ በተቀቡ ክርስቲያኖች የተዋቀረው ታማኝና ልባም ባሪያ ምሥራቹን በመስበኩ፣ አምልኮ የሚከናወንባቸውን ስብሰባዎች በማደራጀቱና ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማተሙ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይካፈላል። በመላው ምድር የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘በጊዜው የሚሰጣቸውን’ መንፈሳዊ ‘ምግብ’ በአመስጋኝነት ይመገባሉ። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) በዚህ ረገድ የሚያጉረመርሙበት ምንም ምክንያት የለም።

5 ኤልፊ የተባሉ በዕድሜ የገፉ የይሖዋ ምሥክር ታማኝና ልባም ባሪያ ባሳተማቸው ጽሑፎች ላይ የሚገኙትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች በሥራ ላይ በማዋል ለበርካታ ዓመታት ማበረታቻና ድጋፍ ሲያገኙ ቆይተዋል። ኤልፊ በከፍተኛ አድናቆት በመነሳሳት “የይሖዋ ድርጅት ባይኖር ኖሮ ምን እሆን ነበር?” ብለዋል። ፔተ እና ኧርምጋርት ደግሞ ለበርካታ ዓመታት አምላክን ሲያገለግሉ የቆዩ ባልና ሚስት ናቸው። ኧርምጋርት “አፍቃሪና አሳቢ የሆነው የይሖዋ ድርጅት” ላደረጋቸው ዝግጅቶች ሁሉ ምስጋናዋን አቅርባለች። ከሚታተሙት ጽሑፎች መካከል ማየትና መስማት ለማይችሉ እንዲሁም የተለየ ችግር ላለባቸው ግለሰቦች የሚዘጋጁትም ይገኙባቸዋል።

6, 7. (ሀ) በመላው ምድር የሚገኙ ጉባኤዎች የሚመሩት እንዴት ነው? (ለ) አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ምን አስተያየት ሰጥተዋል?

6 ‘ታማኙ ባሪያ’ በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ይወከላል፤ ይህ የበላይ አካል በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ጥቂት ወንዶችን ያቀፈ ቡድን ሲሆን በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ሆኖ ያገለግላል። የበላይ አካሉ ተሞክሮ ያላቸውን የይሖዋ አገልጋዮች በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ እንዲያገለግሉ ይሾማል፤ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በምድር ዙሪያ የሚገኙት ከ98,000 የሚበልጡ ጉባኤዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በበላይነት ይመራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ብቃቶች የሚያሟሉ ወንዶች በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ሽማግሌና አገልጋይ ሆነው ይሾማሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-9, 12, 13) የጉባኤ ሽማግሌዎች በእነርሱ ኃላፊነት ሥር ያለውን የአምላክ መንጋ ይመራሉ፤ እንዲሁም በፍቅር ይጠብቃሉ። የዚህ መንጋ አባል ሆኖ ‘በመላው የወንድማማች ማኅበር’ መካከል ያለውን ፍቅርና አንድነት መቅመስ እንዴት ያለ በረከት ነው!1 ጴጥሮስ 2:17 NW፤ 5:2, 3

7 ግለሰቦች ከሽማግሌዎች የሚያገኙትን ፍቅራዊ የሆነ መንፈሳዊ መመሪያ በአብዛኛው ሲያደንቁ እንጂ ሲያማርሩ አይሰሙም። ለምሳሌ ያህል፣ በሠላሳዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘውን ቢርጊት የተባለች ክርስቲያን ሚስት እንመልከት። በጉርምስና ዕድሜ ላይ እያለች ጥሩ ባሕርይ ከሌላቸው ጓደኞች ጋር በመግጠሟ መጥፎ ድርጊቶችን ለመፈጸም ተቃርባ ነበር። ነገር ግን የጉባኤ ሽማግሌዎች የሰጧት ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክርና የእምነት ባልንጀሮቿ ያደረጉላት ድጋፍ ሊያጋጥማት ከነበረው ጎጂ ሁኔታ እንድትድን ረድቷታል። አሁን ቢርጊት ምን ይሰማታል? “እስከ አሁን ድረስ ድንቅ በሆነው የይሖዋ ድርጅት ውስጥ በመገኘቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ” ብላለች። የ17 ዓመቱ አንድሬአስ ደግሞ “በዓለም ላይ ከሚገኙት ድርጅቶች ሁሉ በእርግጥ ምርጥ የሆነው የይሖዋ ድርጅት ነው” ብሏል። በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ ላሉት መልካም ነገሮች አመስጋኝ መሆን አይገባንም?

አመራር ላይ ያሉት ፍጹማን አይደሉም

8, 9. በዳዊት ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ምን አድርገዋል? ሆኖም ዳዊት በእነዚህ ሰዎች ምክንያት ምን አላደረገም?

8 በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ አመራር እንዲሰጡ የተሾሙት ሰዎች ፍጹማን እንዳልሆኑ እሙን ነው። ሁሉም ስህተት ይፈጽማሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለማሸነፍ ጠንክረው የሚታገሉት ዘላቂ የሆነ አንድ ዓይነት ድክመት አለባቸው። ይህ ሊያበሳጨን ይገባል? በፍጹም። በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው ግለሰቦች እንኳን ከባድ ስህተቶችን ፈጽመዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት ገና ወጣት ሳለ መንፈሱ ይጨነቅበት የነበረውን ንጉሥ ሳኦልን ለማረጋጋት ሙዚቀኛ እንዲሆን ተጠይቆ ነበር። በኋላ ላይ ግን ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ሙከራ አደረገ፤ ውሎ አድሮም ዳዊት ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ።1 ሳሙኤል 16:14-23፤ 18:10-12፤ 19:18፤ 20:32, 33፤ 22:1-5

9 ሌሎች እስራኤላውያንም ከዳተኞች ሆነው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የዳዊት ጦር መሪ የነበረው ኢዮአብ የሳኦልን ዘመድ አበኔርን ገድሏል። አቤሴሎም የአባቱን የዳዊትን ንግሥና በመቀናቀን አሲሯል። እንዲሁም ዳዊትን ታማኝ አማካሪው የነበረው አኪጦፌል ከድቶታል። (2 ሳሙኤል 3:22-30፤ 15:1-17, 31፤ 16:15, 21) ዳዊት ግን በጣም አልተማረረም፤ ለእውነተኛው አምልኮም ጀርባውን አልሰጠም። እንዲያውም ዳዊት ያደረገው ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ነበር። የደረሰበት መከራ ይበልጥ ከይሖዋ ጋር እንዲወዳጅ አድርጎታል፤ በሳኦል ድርጊት ምክንያት በተሰደደበት ወቅት የነበረውን በጎ አመለካከት እንደያዘ ቀጥሏል። በዚያን ጊዜ ዳዊት እንደሚከተለው ብሎ ዘምሮ ነበር:- “ማረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረኝ፤ ነፍሴ አንተን መጠጊያ አድርጋለችና፤ በክንፎችህ ሥር እጠለላለሁ።”መዝሙር 57:1

10, 11. ጌርትሩት የተባሉ ክርስቲያን በወጣትነታቸው ምን አጋጥሟቸው ነበር? የእምነት ባልንጀሮቻቸው ስለሚፈጽሙት ስህተትስ ምን ብለዋል?

10 በዛሬው ጊዜ በአምላክ ድርጅት ውስጥ በምናየው የክህደት ድርጊት የምናማርርበት ምክንያት የለም። ይሖዋም ሆነ መላእክቱ እንዲሁም መንፈሳዊ እረኞች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ክፉ ከዳተኞችን አይታገሱም። የሆነ ሆኖ ሁላችንም ከራሳችንና ከሌሎች የአምላክ አገልጋዮች የፍጽምና ጉድለት ጋር እንታገላለን።

11 ለረጅም ዓመታት ይሖዋን ሲያገለግሉ የቆዩ ጌርትሩት የተባሉ አንዲት እህት ወጣት ሳሉ አጭበርባሪ እንደሆኑና የመንግሥቱ ምሥራች የሙሉ ጊዜ አዋጅ ነጋሪ እንዳልሆኑ ተደርገው በሐሰት ተከስሰው ነበር። እህት ጌርትሩት በዚህ ጊዜ ምን አደረጉ? በሁኔታው አጉረመረሙ? በጭራሽ። በ91 ዓመታቸው በ2003 ከመሞታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ያሳለፉትን ሕይወት መለስ ብለው በማስታወስ እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህና በኋላ ላይ ያጋጠሙኝ ሌሎች ሁኔታዎች፣ ግለሰቦች ስህተት ቢሠሩም እንኳን ይሖዋ በእኛ ፍጹማን ባልሆንን የሰው ልጆች የሚያሠራውን ታላቁን ሥራውን እንደሚመራ አስተምረውኛል።” እህት ጌርትሩት በሌሎች የአምላክ አገልጋዮች የፍጽምና ጉድለት የተነሳ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት ያቀርቡ ነበር።

12. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን መጥፎ ምሳሌ ትተዋል? (ለ) አእምሯችን በምን ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ አለብን?

12 እጅግ ታማኝና አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያኖች እንኳን ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት፣ የተሾሙ አገልጋዮች ስህተት ሲሠሩ ‘ማንኛውንም ነገር ሳናጒረመርም’ ማድረጋችንን እንቀጥል። (ፊልጵስዩስ 2:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩትን የአንዳንዶችን መጥፎ ምሳሌ ብንከተል ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል! ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ እንደገለጸው በዚያን ዘመን የነበሩ ሐሰተኛ አስተማሪዎች “ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ።” በተጨማሪም እነዚህ መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች “የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጉረመርሙ” ነበሩ። (ይሁዳ 8, 16 የ1954 ትርጉም) የሚያጉረመርሙ ሰዎችን ጎዳና አንከተል፤ አእምሯችን ‘በታማኙ ባሪያ’ በኩል በምናገኛቸው በጎ ነገሮች ላይ ያተኩር። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉትን መልካም ነገሮች ከፍ አድርገን እንመልከታቸው፤ ‘ማንኛውንም ነገር ሳናጒረመርም እናድርግ።’

ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው”

13. ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንድ ትምህርቶችን ሲያስተምር ጥቂት ሰዎች ምን አደረጉ?

13 በአንደኛው መቶ ዘመን በተሾሙ አገልጋዮች ላይ ከሚያጉረመርሙት ሰዎች በተጨማሪ በኢየሱስ ትምህርቶች ላይ ያጉረመረሙም ነበሩ። በዮሐንስ 6:48-69 ላይ ተዘግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ “ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” ብሎ ነበር። እነዚህን ቃላት ሲሰሙ “ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች . . . ‘ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?’ አሉ።” ኢየሱስ ‘ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ነገር ማጒረምረማቸውን’ አውቆ ነበር። በተጨማሪም “ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያም ወዲያ አልተከተሉትም።” ያጉረመረሙት ግን ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ አልነበሩም። ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ የሆነውን ልብ በል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆንህ አምነናል፤ ዐውቀናልም።”

14, 15. (ሀ) ጥቂቶች በአንዳንድ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ቅር የሚሰኙት ለምንድን ነው? (ለ) ኤማኑዌል የሚባል ሰው ካጋጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 በዘመናችንም ከአምላክ ሕዝቦች መካከል ጥቂቶቹ በአንዳንድ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ቅር ተሰኝተዋል፤ በመሆኑም በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ላይ አጉረምርመዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለ ማጉረምረም የሚከሰተው አምላክ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ካለመረዳት ነው። ፈጣሪ ለሕዝቡ እውነትን የሚገልጸው ደረጃ በደረጃ ነው። ስለዚህ ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያለን ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠራ ይሄዳል። አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ ባለው ማሻሻያ ይደሰታሉ። ጥቂቶች ደግሞ “እጅግ ጻድቅ” ይሆኑና ለውጦቹን መቀበል ይከብዳቸዋል። (መክብብ 7:16) ለዚህ ምክንያቱ ኩራት ሊሆን የሚችል ሲሆን ይህም አንዳንዶች በራስ አስተሳሰብ በመመራት ወጥመድ እንዲያዙ አድርጓቸዋል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንዲህ የመሰለው ማጉረምረም ወደ ዓለምና ወደ መንገዶቹ ሊመልሰን ስለሚችል አደገኛ ነው።

15 ለምሳሌ ያህል፣ ኤማኑዌል “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ ስህተት መለቃቀም የሚቀናው የይሖዋ ምሥክር ነበር። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን ማንበብ ካቆመ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በጉባኤው ለሚገኙ ሽማግሌዎች ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደማይፈልግ ነገራቸው። ይሁንና ኤማኑዌል በአጭር ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ድርጅት የሚያስተምራቸው ትምህርቶች በእርግጥ ትክክል መሆናቸውን ተገነዘበ። በመሆኑም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘና ስህተቱን አምኖ በመቀበል እንደገና የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በዚህም ምክንያት ኤማኑዌል ቀደም ሲል የነበረውን ደስታ መልሶ ማግኘት ቻለ።

16. ስለ አንዳንድ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ያለንን ጥርጣሬ ለማስወገድ ምን ሊረዳን ይችላል?

16 የይሖዋ ድርጅት ስለሚያስተምራቸው አንዳንድ ትምህርቶች ጥርጣሬ ገብቶን ለማጉረምረም ብንፈተንስ? እንዲህ ከሆነ አንቸኩል። ምክንያቱም ውሎ አድሮ ‘ታማኙ ባሪያ’ ለጥያቄዎቻችን መልስ የሚሰጥ ጽሑፍ በማዘጋጀት ጥርጣሬያችንን ሊያስወግድልን ይችላል። የክርስቲያን ሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅም ጥሩ ነው። (ይሁዳ 22, 23) በተጨማሪም መጸለይ፣ የግል ጥናት ማድረግና መንፈሳዊ አስተሳሰብ ካላቸው የእምነት ባልንጀሮች ጋር መወዳጀት ጥርጣሬን ለማስወገድ ይረዳናል፤ እንዲሁም ይሖዋ በሚጠቀምበት መገናኛ መስመር በኩል ለተማርናቸው እምነት የሚያጠነክሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለን አድናቆት እንዲያድግ ያስችለናል።

አዎንታዊ አመለካከት ያዙ

17, 18. ከማጉረምረም ይልቅ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?

17 ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆች ኃጢአት የመፈጸምን ዝንባሌ መውረሳቸው እሙን ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ መሠረተ ቢስ ቅሬታ የማሰማት ከፍተኛ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሮሜ 5:12) ነገር ግን ልማደኛ አጉረምራሚዎች ከሆንን ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት አደጋ ላይ እንጥላለን። ስለዚህ ማንኛውንም ዓይነት የማጉረምረም ዝንባሌ መቆጣጠር አለብን።

18 በጉባኤ ውስጥ ስላሉት ነገሮች ከማጉረምረም ይልቅ አዎንታዊ አመለካከት ብንይዝ የተሻለ ይሆናል፤ እንዲሁም በሥራ የተጠመድን፣ ደስተኞች፣ ሰው አክባሪዎች፣ ሚዛናችንን የምንጠብቅና በእምነት ጤናማ እንድንሆን የሚያደርገንን ልማድ ብንከተል መልካም ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ቲቶ 2:1-5) ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ የሚከናወነውን ነገር ሁሉ ይቆጣጠራል፤ ኢየሱስም ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ ያሉትን ክስተቶች ያውቃል። (ራእይ 1:10, 11) ስለዚህ አምላክና የጉባኤው ራስ የሆነው ክርስቶስ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ ተስፋ አድርግ። መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች ለማስተካከል ኃላፊነት ላይ ያሉ እረኞችን ይጠቀሙ ይሆናል።መዝሙር 43:5፤ ቈላስይስ 1:18፤ ቲቶ 1:5

19. የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆችን ጉዳዮች ሙሉ በመሉ እስኪቆጣጠር ድረስ በምን ነገር ላይ ማተኮር አለብን?

19 በቅርቡ መሲሐዊው መንግሥት የሰው ልጆችን ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ይህ ክፉ ሥርዓት ይወገዳል። እስከዚያ ድረስ እያንዳንዳችን አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! እንዲህ ማድረጋችን በእምነት ባልንጀሮቻችን ስህተት ላይ ከማተኮር ይልቅ በጎ ጎናቸውን እንድናይ ይረዳናል። በመልካም ባሕርያቸው ላይ ማተኮራችን ደግሞ ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። ስለዚህ በማጉረምረም ስሜታችንን ከመጉዳት ይልቅ በመንፈሳዊ መበረታታትና መጠናከር እንችላለን።

20. አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ምን በረከቶችን እንድናገኝ ያስችለናል?

20 አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን፣ የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል አባል በመሆናችን ምክንያት ያገኘናቸውን ብዙ በረከቶች እንዳንዘነጋም ጭምር ይረዳናል። በምድር ላይ ለጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ታማኝ የሆነው ይህ ድርጅት ብቻ ነው። ስለዚህ ሐቅ እንዲሁም ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ በሚቀርበው አምልኮ ለመካፈል ስላገኘኸው መብት ምን ይሰማሃል? የአንተም አስተሳሰብ እንደሚከተለው በማለት እንደዘመረው እንደ ዳዊት ይሁን:- “አንተ የሰዎችን ጸሎት ስለምትሰማ ሰዎች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ። አንተ የመረጥሃቸውና በተቀደሰ አደባባይህ እንዲኖሩ ወደ ራስህ ያቀረብሃቸው፥ ደስ ይበላቸው፤ እኛም ከቤትህ በሚገኘው መልካም ነገር . . . እንረካለን።”መዝሙር 65:2, 4 የ1980 ትርጉም

ታስታውሳለህ?

• በጉባኤ ውስጥ በአመራር ላይ ስለሚገኙት ሰዎች አመስጋኝ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

• በኃላፊነት ላይ የሚገኙ ወንድሞች በሚሳሳቱበት ጊዜ ምን ዓይነት ስሜት ሊኖረን ይገባል?

• ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ሲደረግ ምን ሊሰማን ይገባል?

• ክርስቲያኖች ጥርጣሬን እንዲያስወግዱ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት ለሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ንድፍ ከመስጠቱም በላይ እውነተኛውን አምልኮ በሙሉ ልቡ ደግፏል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጉባኤ ሽማግሌዎች በደስታ መንፈሳዊ እርዳታ ይሰጣሉ