በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አምላካችን ሊያድነን ይችላል’

‘አምላካችን ሊያድነን ይችላል’

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!”

‘አምላካችን ሊያድነን ይችላል’

ዝግጅቱ ብዙዎችን እንዲያስደንቅ የታሰበ ነበር። ከወርቅ የተሠራ ግዙፍ ምስል በባቢሎን ከተማ አቅራቢያ እንደሚገኝ በሚገመተው በዱራ ሜዳ ላይ ቆሟል። ይህን ምስል ለመመረቅ በተዘጋጀው ልዩ ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት የተገኙ ሲሆን እነዚህ ሰዎች የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ድምጽ በሚሰሙበት ጊዜ በምስሉ ፊት ወድቀው እንዲሰግዱ ይጠበቅባቸው ነበር። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ ምስሉን ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በሚንቀለቀለው እቶን እሳት ውስጥ ተጥሎ እንዲሞት ትእዛዝ አውጥቷል። ይህን ትእዛዝ ለመጣስ የሚደፍር ማን ይኖራል?

ነገሩ የተሰበሰበውን ሕዝብ በጣም ያስገረመ ቢሆንም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ ይሖዋን የሚፈሩና የሚያመልኩ ሦስት ወጣቶች ለምስሉ አልሰገዱም። ለምስሉ መስገድ ማለት ይሖዋ አምላክን ብቻ እንዲያመልኩ የተሰጣቸውን ሕግ መጣስ እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ዘዳግም 5:8-10) ናቡከደነፆር ስለ አቋማቸው እንዲያስረዱ በጠየቃቸው ጊዜ በድፍረት እንዲህ ብለው መለሱለት:- “ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።”—ዳንኤል 3:17, 18

ሦስቱ ዕብራውያን ወጣቶች በሚንቀለቀለው እቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ፤ ከዚህ ሁኔታ በሕይወት ሊተርፉ የሚችሉት ተአምር ከተፈጸመ ብቻ ነው። አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዲጠብቃቸው መልአክ ላከ። ያም ባይሆን ግን ሦስቱ ወጣቶች ይሖዋን ሳይታዘዙት ከሚቀሩ ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው ለመስጠት መርጠው ነበር። a እነዚህ ወጣቶች የወሰዱት አቋም ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኖሩት የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ካሳዩት ጽናት ጋር ተመሳሳይ ነበር። ሐዋርያቱ በአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት በቀረቡበት ወቅት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” በማለት ተናግረዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:29

ለእኛ የሚሆን ጠቃሚ ትምህርት

ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በእምነታቸው፣ በታዛዥነታቸው እንዲሁም ባሳዩት ታማኝነት ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። ሦስቱ ዕብራውያን በይሖዋ ላይ እምነት ነበራቸው። ሕሊናቸው በቅዱሳን ጽሑፎች ስለሠለጠነ በማንኛውም ዓይነት የሐሰት አምልኮ ወይም ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት ድርጊት ለመካፈል ፈቃደኛ አልሆኑም። በተመሳሳይም በዘመናችን የሚገኙ ክርስቲያኖች በእውነተኛው አምላክ ሙሉ በሙሉ ይታመናሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነው ሕሊናቸው ስለሚመሩ በሐሰት አምልኮ ወይም የአምላክን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚያስጥሱ ዝግጅቶች አይካፈሉም።

ሦስቱ ታማኝ ዕብራውያን በይሖዋ ከመታመናቸውም በላይ ከባቢሎን መንግሥት እውቅና፣ ሥልጣን ወይም ክብር ለማግኘት ሲሉ ታዛዥነታቸውን ለማጉደል ፈቃደኞች አልነበሩም። እነዚህ ወጣቶች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከማበላሸት ይልቅ የሚደርስባቸውን ሥቃይም ሆነ ሞት ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። ከእነርሱ በፊት የነበረው ሙሴ “የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቊጠር በሐሳቡ [እንደ] ጸና” ሁሉ እነርሱም በአቋማቸው ጸንተዋል። (ዕብራውያን 11:27) ሦስቱ ወጣቶች ይሖዋ ከሞት ቢያድናቸውም ባያድናቸውም ሕይወታቸውን ለማትረፍ ብለው አቋማቸውን ከማላላት ይልቅ ታማኝነታቸውን ለመጠበቅ ቆርጠው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የእሳትን ኀይል ስላጠፉ’ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የተናገረው የእነዚህን ወጣቶች ምሳሌነት ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም። (ዕብራውያን 11:34) በዘመናችንም የይሖዋ አገልጋዮች የታማኝነት ፈተና በሚደርስባቸው ጊዜ እንዲህ ያለ እምነት እና ታዛዥነት አሳይተዋል።

ከሲድራቅ፣ ከሚሳቅና ከአብደናጎ ተሞክሮ ማየት እንደሚቻለው አምላክ ለእርሱ ታማኝ የሚሆኑትን ይክሳቸዋል። መዝሙራዊው ‘እግዚአብሔር ታማኞቹን አይጥልም’ በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 37:28) አምላክ ለሦስቱ ዕብራውያን እንዳደረገው በዛሬው ጊዜም በተአምራዊ ሁኔታ ያድነናል ብለን አንጠብቅም። ሆኖም ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስብን በሰማይ ያለው አባታችን እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ ችግሩን ሊያስወግደው፣ ለመጽናት የሚያስችለንን ኃይል ሊሰጠን ወይም ደግሞ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ከሆንን በትንሣኤ ሊያስበን ይችላል። (መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ከሰው ይልቅ ለአምላክ ለመታዘዝ ከመረጥን ምንጊዜም ቢሆን እምነት፣ ታዛዥነትና ታማኝነት ድል ያደርጋሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ሐምሌ/ነሐሴ የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ሦስቱ ዕብራውያን ይህ ዓይነቱ የታማኝነት ፈተና ሲገጥማቸው በ20ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ ነበሩ።

የእቶኑ እሳት በተቻለ መጠን በኃይል እንዲነድ ተደርጎ ነበር።—ዳንኤል 3:19